ጸጋዬ ትውልድና ዕድገቱ ሞረትና ጅሩ አካባቢ ነው። ጅሩና የልጅነት ህይወቱ የሚጀምረው ደግሞ በቀለም ትምህርቱ ተቃኝቶ ነው። ቤተሰቦቹ አግዘውትና ዕጣ ፈንታው ሆኖ ፊደል መቁጠር የጀመረው ገና በጠዋቱ ነበር።
ትምህርት ቤት ውሎ ሲመለስ ደብተሩን ለጥናት የሚገልጠው ጸጋዬ በጅማሬው የተለየ ተስፋን ሰንቆ ለያዘው ዓላማ ትኩረት ሰጠ። ይህን ፍላጎቱን ያስተዋሉ ወላጆቹ በሥራ እምብዛም አልተጫኑትም። የአቅሙን ያህል እያገዛቸው በጀመረው እንዲቀጥል ዕድል ሰጡት።
ጸጋዬ ቀለም ከመቁጠር ባለፈ ስለወደፊት ማንነቱ አሻግሮ ያስባል። ዛሬን በትምህርቱ ከበረታ ነገን በተሻለ እንደሚያገኘው እርግጠኛ ከሆነ ቆይቷል። እሱን መሰል ወጣቶች ከሃሳባቸው ዳር ለመድረስ ትምህርታቸው እንደረዳቸው ጠንቅቆ ያውቃል። በርካቶቹ ዛሬ ላይ ለደረሱበት ስኬት ምክንያቱ ትናንት አጥብቀው የያዙት ትምህርት ስለመሆኑ ነጋሪ አያሻውም።
የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቆ ወደ ሰባተኛ ክፍል ሲዛወር አብሮት ያደገው ጠንካራ ስሜት ከእሱ ጋር ነበር። ይህ ጊዜ የተሻለ መሰረት የሚጥልበት ወሳኝ መንገድ መሆኑ የገባው ጸጋዬ በጀመረው ጥንካሬ ቀጠለ።
ጠዋት የተማረውን ምሽቱን እያጠና የቀኑን ትምህርት በቀለም ዕውቀት ቀምሮ ራሱን ማበርታት ያዘ። በቀጣይ ዓመት ለሚወስደው የሚኒስትሪ ፈተና ትኩረት ሰጥቶም ሌት ተቀን ባተለ።
ጸጋዬ የዓመቱን ትምህርት አጠናቆ ስምንተኛ ክፍል ሲገባ ግን ነገሮች ሁሉ እንዳልነበር ሆነው ተቀየሩ። በድንገት አካባቢውን ለመልቀቅ የደረሰበት ውሳኔ የዓመታት ዕቅዱን ለውጦ ልቡን ለሩቅ መንገድ አሻገረው።
ድንገቴው የጸጋዬ ውሳኔ መድረሻው አዲስ አበባ ሆነና መገኛውን ከቅርብ ዘመዶቹ ቤት አደረገው። በከተማው ሲደርስ አካባቢውን ወደደው። ዘመዶቹ ያደረጉለት መልካም አቀባበል እንግድነቱን አራዝሞ ቤተኛ አድርጎት ከረመ።
ዋል አደር ሲል ጸጋዬ በነበረበት ለመቀጠል የተለየ ፍላጎት አደረበት። ያቋረጠውን ትምህርቱን እንደንደሚቀጥል በገባው ጊዜም የነበረበትን ታሪክ ረስቶ የቆመበትን ህይወት ብቻ ማሰብ ያዘ። ስለትምህርቱ ሲያስብ ከአገሩ ይልቅ አዲስ አበባ ያለው ምቹነት ይበልጥ እንደሚሻል ከራሱ ጋር ተማመነ።
ጸጋዬ ቀጣዩን ዓመት በአዲስ የትምህርት መንፈስ ለመቀጠል ስለመወሰኑ ለሌሎች ባስረዳ ጊዜ አብዛኞቹ ሃሳቡን ደገፉለት። በዘመዶቹ ቤት ኑሮው ምቹ የሆነለት ወጣትም ይህን ባወቀ ጊዜ ያቋረጠውን ትምህርት በተሻለ ዝግጅት እንደሚቀጥለው አምኖ ዓመቱን አገሩን በመላመድና በርካቶችን በመተዋወቅ አሳለፈው።
አዲስ ዓመት
እነሆ ! አዲስ ዓመቱ ከባተ ጥቂት ቀናት ተቆጥረዋል። ከዓመቱ መወለድ ጋር አዲስ ስሜትን የጨበጠው ጸጋዬ ይህን ጊዜ በጉጉት ሲያስበው ቆይቷልና የተለየ ደስታ ፈጥሮበታል። አዲሱን ዘመን በአዲስ መንፈስና በተለየ ብርታት ሊጀምረው በመሆኑ በማንነቱ ላይ ታላቅ ለውጥ እንደሚኖር እርግጠኛ ነው።
አሁን አምና ያቋረጠውን የስምንተኛ ክፍል ትምህርቱን በወጉ የሚቀጥልበት ጊዜ ነው። ያለፈውን ሲያስታውስ ግን ጓደኞቹ ከእሱ አንድ ርምጃ መሄዳቸው ትውስ ይለዋል። ወዲያው ደግሞ እምብዛም እንዳልራቁት ሲረዳ ራሱን አጀግኖ ማንነቱን በጥንካሬ መገንባት ይ ጀምራል።
እንደታሰበው ሆኖ ጸጋዬና ትምህርት ዳግመኛ ተገናኙ። በተለየ ስሜት ጅምሩን የቀጠለው ወጣት ዛሬ ላይ ቆሞ ስለነገው መልካሙን አለመ። አብሮት ያደገው የትምህርት ፍቅርም እንደትናንቱ ከደብተሩ አገናኝቶ ከቀለም ሊያዋድደው ግድ አለ።
ወራት እየተገፉ ጊዜው ሲገባደድ ግን ጸጋዬና ጅምር ትምህርቱ ዳግም ፈተና ገጠማቸው። ወጣቱ ተጠግቶ ይኖርባቸው ከነበሩ ዘመዶቹ ጋር በድንገት ተጋጨ። ይህ አጋጣሚ የፈጠረው ቅራኔም እንደቀድሞው ሆኖ እንዲቀጥል ዕድል አልሰጠም። ድንገቴው መቀያየም የጸጋዬን ህይወት ሊያፋልስ ግድ አለው። ከዘመዶቹ ቤት ወጥቶ ትምህርቱን ለመቀጠል ሞከረ። የአዲስ አበባ ኑሮ እንዳሰበው ሆኖ የልቡን አልሞላም። ትምህርቱን አቋርጦ በሥራ ፍለጋ ባዘነ።
አዲስ መንገድ
ጸጋዬ ከዘመዶቹ ቤት እንደወጣ በሰው ቤት የጥበቃ ሠራተኛ ሆኖ ተቀጠረ። ይህ ጊዜ ራሱን ከማስቻል ባለፈ በቂ የሚባል ገንዘብ አስቋጠረው። ምግቡን ከቀጣሪዎቹ እየተጠቀመ ውሎ አዳሩን በሥራው ላይ አደረገ። ጥቂት ቆይቶም በተሻለ ደሞዝ ሌሎች ቤቶችን እያማረጠ የብዙዎችን ግቢ አዳረሰ።
አዲስ አበባን ሲላመድ የራሱን መኖሪያ አመቻችቶ ወግ ያለው ህይወት ጀመረ። ቤት ተከራይቶም ለሌሎች ጭምር ማረፊያ መሆን ቻለ። እንዳንዴ የቅርብ የሚላቸውና አዲስአበባ የሚኖሩ ዘመዶቹ እየመጡ ይጎበኙታል። ከእነዚህ መሀል ደግሞ አንዱ ለጸጋዬ የተለየ ምስጢረኛው ነው።
አልፎ አልፎ በተገናኙ ጊዜ የልቡን ሃሳብ ገልጦ ይነግረዋል። በጨዋታቸው መሀልም ኑሯቸውን በአንዴ መለወጥ የሚያስችላቸውን አጋጣሚ ሁሉ እያነሱ ይወያያሉ። ይህ ዘመዱ በጸጋዬ ላይ ብርቱ አመኔታን አሳድሯል። በቅርብ ጊዜ በዘጠኝ ሺህ ብር የገዛውን ኮልት ሽጉጥ ሳይቀር በአደራ እንዲያስቀምጥ ሰጥቶታል።
ጸጋዬ የዘመዱ የአደራ ሽጉጥ በእጁ ከገባ ወዲህ በሃሳብ ብዙ ቦታዎች ደርሶ ይመለሳል። ሁሌም ስላቋረጠው ትምህርቱ ባስታወሰ ጊዜም ያልመው የነበረው ሁሉ እንደመከነበት ይሰማዋል። በትምህርቱ የት ይደርስ እንደነበር ውል ሲለውም አሁን ያለበትን ደረጃ እያሰበ በቁጭት ይበግናል።
ጸጋዬ አዲስ አበባ ከገባና ዘበኝነትን እንጀራ ካደረገ ጀምሮ በርካታ ቤቶችን ቀያይሯል። ማንነቱን በዚህ ቦታ ላይ እንደሚያገኘው ገምቶ ባያውቅም አሁን ባለበት ኑሮ እምብዛም አይከፋም።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከግለሰብ ቤቶች ዘበኝነት በተሻለ ያገኘው የድርጅት ጥበቃ ደግሞ ህይወቱን በተሻለ ለውጦታል። ባለው የትምህርትና የሥራ ልምድ መስፈርት ተወዳድሮ ወደዚህ የግል ድርጅት ተቀጥሮ ሲገባም ገቢና ኑሮውን በተሻለ ሁኔታ ለመቀየር አስችሎታል።
ጸጋዬ ወደዚህ የግል ድርጅት ተቀጥሮ መሥራት ከጀመረ ወዲህ የበርካቶችን ማንነት ለይቶ ተረድቷል። ጥሩ የሚባል ደሞዝ የሚከፈላቸውን ሠራተኞች ገቢ እያሰላም እነሱን ለመሆን የተመኘበት ጊዜ የበረከተ ነው።
አብዛኞቹን በሰላምታ ሰበብ እየተግባባ ስለድርጅቱ አቅምና ሁኔታ ሲረዳ ቆይቷል። የቤቱን ገንዘብ አያያዝና ጥንቃቄን ባሰበው ጊዜ ደግሞ በየጊዜው ኑሮን በአንዴ ለመለወጥ ያለው ምኞት ውል እያለ ይፈትነዋል።
በተቀጠረበት የግል ድርጅት በአጋርነት የሚሠሩ ሌሎች ጥበቃዎች አብረውት አሉ። ሁሌም ተረኛ በሆኑ ጊዜ በሰዓቱና በቦታው ተገኝተው ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ። እንደነሱ ሁሉ የእሱ ተራ በሆነ ጊዜም መዋል ማደር ባለበት ጊዜ ተተክቶ የድርሻውን ይወጣል። ይህ አውነትም ለዓመታት የድርጅቱ ደንብና ህግ ሆኖ በርካቶች ሲተዳደሩበት ቆይተዋል።
ሰሞኑን ጸጋዬ በእጁ ገንዘብ አስፈልጎታል። ይህ ፍላጎቱ ለቀናት አለፍ ካለው የደሞዝ ክፍያ ጋር ተዳምሮም ያቁነጠንጠው ይዟል። አንዳንዴ ደሞዝ ከታሰበው ጊዜ ጥቂት አለፍ ብሎ ሊከፈል ይችላል። አንዳንዴ ደግሞ በተገቢው ወቅትና ከታሰበው ጊዜ ቀደም ብሎ ጭምር ከኪስ ይደርሳል። ይህን አውነት ጸጋዬን ጨምሮ መላው የድርጅቱ ሠራተኞች ጠንቅቀው ያውቁታል።
ታኅሣሥ 4 ቀን 2006 ዓ.ም
በዚህ ቀን ጸጋዬ የለሊት ተረኛ ስለነበር ማለዳ ሥራውን ለሌላ ጥበቃ አስረክቦ ለዕረፍት ወደቤቱ ገስግሷል። አሁንም የሰሞኑ የገንዘብ ጉዳይ በሃሳቡ እየተመላለሰ ነው። ዕለቱን ክፍያ እንደሚፈጸም ቢሰማም በ ‹‹ልሂድ፣ ልቅር…›› ሙግት ከራሱ ጋር ሲታገል ቆይቷል።
ድንገቴው የእጅ ስልኩ መልዕክት ግን ለጆሮው የምስራችን አበሰረው። እሱ ከተካው ጥበቃ የመጣለት ምላሽ ሂሳብ ሠራተኛዋ ደሞዝ ለመክፈል ከግቢው መድረሷን አረጋገጠለት። ጸጋዬ የእጅ ሰዓቱን ተመለከተ። ጊዜው ሳብ እንዳለ ቢያውቅም ሰዓቱ ሳይባክን ለመድረስ በታክሲ እያሳበረ ወደመስሪያቤቱ ገሰገሰ።
በስፍራው ሲደርሰ ከምሽቱ አስራሁለት ሰዓት ሆኖ ነበር። በደሞዝ ከፋይዋ ፊት ጥቂት ሠራተኞች መቆማቸውን ሲያስተውል እሱም ተራ ይዞ ከኋላ ተሰለፈ። ወዲያው ደሞዙን ቆጥሮ ኪሱ እንዳስገባ ሌሎች ሠራተኞች ይመጡ እንደሁ በሚል በዓይኖቹ አማተረ። ማንም ብቅ ያለ አልነበረም።
ደሞዝ ከፋይዋ ለመጡት ሠራተኞች የሚገባቸውን ደሞዝ እያስፈረመች ከከፈለች በኋላ የሰዓቱን መግፋት ገምታና ቀሪውን ገንዘብ ከካዝናው መልሳ የነበረችበትን ክፍል ቆልፋ ወጣች። ይህን ሁሉ አንድ በአንድ ያስተዋለው ጸጋዬም ነገሮችን በስሱ እየቃኘ ከልቡ ላይ ከተበ።
ምሽቱና ጸጋዬ
የሆነውን ሁሉ በዓይኑ ያረጋገጠው ጸጋዬ አስከምሽቱ ሦስት ሰዓት ኮተቤ በሚገኘው መኖሪያው ሲቁነጠነጥ ቆየ። ጥቂት ቆይቶ ግን የዘመዱን የአደራ ኮልት ሽጉጥ ከመሰል ጥይቶቹ ጋር ቆጥሮና በወገቡ ሸጉጦ ወደመስሪያ ቤቱ ቅጥር አመራ።
ከስፍራው ደርሶ አካባቢውን ሲቃኝ ሰዓቱ ገፍቶ ነበር። መውጫ መግቢያውን የሚያውቀውን ግቢ ግንቡን ዘሎ ወደ ውስጥ መዝለቅ ሲጀምር ያየውም ሆነ የሰማው አልነበረም። ወደውስጥ ሲያጮልቅ የዕለቱ ተረኛ ዕንቅልፍ ላይ መሆኑን አወቀ።
ኮቴውን አጥፍቶ በጊዜ ወዳየውና ካዝናው ወደሚገኝበት ቢሮ አማተረ። በተለመደው ሁኔታ እንደተዘጋ ነው። ቀረብ ብሎ ቁልፉን በአንድ እጁ ፈለቀቀው። አላስቸገረውም። ገራገሩ በር ወለል ብሎ ተከፈተለት። የጨለማው ምስጢረኛ ተስገብግቦ ካዝናውን ፈለገው። ከስፍራው እንደተቀመጠ ነው።
ወዲያው ወደጓሮ ዞር አለና ወፍራም ብረት ከአንድ ዶማ ጋር ይዞ ተመለሰ። ጊዜ አላጠፋም። ኃይል ተጠቅሞ ካዝናውን መቀጥቀጥ ጀመረ። በውድቅት ጭርታውን አሳብሮ መሰማት የጀመረው ድምፅ አፍታ ሳይቆይ ከጥበቃው ጆሮዎች ደረሰ። የዕለቱ ተረኛ በድንጋጤ እየተዋከበ ወደቢሮው ሲጠጋ የበሩን መከፈት አስተዋለ።
ዘበኛው ካለበት ሆኖ በድረሱልኝ ድምፅ ጩኸቱን አቀለጠው። ድምፁ የለሊቱን አየር ሰንጥቆ ከጣራ በላይ መሰማት ሲጀምር ጸጋዬ ባልደረባው አይቶ በቀላሉ እንዳይለየው በመስጋት ሁለት ጥይቶችን አከታትሎ ወደሰማይ ተኮሰ።
አሁንም ዘበኛው የሚይዘው ጠፍቶት ወደማደሪያው ገብቶ ተሸሸገ። ይህኔ ጸጋዬ አጋጣሚውን ተጠቅሞ በመኪና መግቢያው በር በኩል ባለው አጥር ዘሎ ወድጪ ሮጠ።
ፍጥጫ
ጸጋዬ ያሰበው ባለመሳካቱ እየተቆጨና በሩጫ ጨለማውን እየጣሰ ወደፊት አመራ። የሁልጊዜው ህልሙ ያለመሳካቱ በእጅጉ አብግኖታል። ይህን ሁሉ ዋጋ ከፍሎ አንድም ይዞ ያለመውጣቱ ከልብ አበሳጭቶታል። ከራሱ ጋር እያወራ መሮጡን እንደያዘ በድንገት ከአንድ ሰው ጋር ፊት ለፊት ተፋጠጠ።
ሰውየው በአካባቢው ከሚገኙ ድርጅቶች የአንደኛው ጥበቃ ናቸው። ጩኸትና የጥይት ድምፅ ሰምተው ከመውጣታቸው ያገኙት ሰው እሱን በመሆኑ ሌባ ስለመሆኑ አልተጠራጠሩም። ወዲያው ቁም..ቁም..ቁም.. እያሉ ከኋላው ደረሰበትና በያዙት ዱላ እግሩ ላይ ደጋግመው አሳረፉበት።
ጸጋዬ የሚወርድበትን ዱላ መቋቋም ቢያቅተው ጥበቃው እንዲተውት አጥብቆ ተማጸነ። ሌላ ሰው ደርሶ እንዳይጨምርለትም ሰጋ። ሁኔታውን የተረዱት አባት ድብደባቸውን አላቆሙም። አጥብቀው በያዙት ቆመጥ እየደጋገሙ ቀጠቀጡት። ምቱን መቋቋም የተሳነው ጸጋዬ ሽጉጡን አውጥቶ አስፈራራቸው። ዘበኛው አልተበገሩም። ወዲያው ያወጣውን ሳይመልስ አከታትሎ ሦስት ጥይት ተኮሰባቸው። ወዲያው ደም ያሰከራቸው ሰው ወደሚጠብቁት ግቢ ተመልሰው በልባቸው ድፍት አሉ።
የፖሊስ ምርመራ
ሲነጋ በተለምዶ አክሱም ሆቴል ከሚባለው አካባቢ የደረሰው ፖሊስ የአዛውንቱን አስከሬን መርምሮ አስፈላጊ የሚባሉ መረጃዎችን ሁሉ አሰባሰበ። በማለዳው እሳቸውን ሊተካ የመጣው ተረኛ በሩን ሲያንኳኳ እንዳልተከፈተለት የሰጠውን ቃል መሰረት አድርጎም አካባቢውን በጥልቀት ቃኘ። በዋና ሳጂን ግሩም ታረቀኝ የሚመራው የምርመራ ቡድን በመዝገብ ቁጥር 503/06 በተከፈተው ዶሴ ላይ በየቀኑ የሚገኙ ወሳኝ መረጃዎችን በማስፈር ተጠርጣሪውን ለመያዝ አሰሳውን ቀጠለ።
ጸጋዬ ድርጊቱን ከፈጸመ በኋላ ከዘመዱ የወሰደውን ሽጉጥ ከአንድ ቦንብ ጋር አክሎ ለባለቤቱ መለሰ። ጥይቶቹ መጉደላቸውን ያስተዋለው ዘመድ ምክንያቱን ጠየቀው። በአጋጣሚ እንደተኮሰው ተናግሮ አሳመነው። ይህ ሙከራ ግን ከፖሊሶች እይታ አላራቀውም። በጥርጣሬ ተይዞ ሲጠየቅ ድርጊቱን ስለመፈጸሙ አመነ።
ውሳኔ
ጥር 10 ቀን 2011 ዓ.ም በችሎቱ የተሰየመው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድቤት የልደታ ምድብ ችሎት በተከሳሽ ጸጋዬ አበበ ላይ የፍርድ ውሳኔውን ለመስጠት መረጃዎችን አጠናቋል። ተከሳሹ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱም እጁ ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ በሚታሰብ የ18 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ በሚል ወስኗል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 7/2012
መልካምስራ አፈወርቅ