የሰው ልጆች ያላቸውን ወሰን አልባ ፍላጎት ለማሟላት ሲሉ ህብረት የመፍጠራቸውን ያክል ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ አለመግባባቶችን ያስተናግዳሉ። ይሁን እንጂ ለህብረታቸውም ሆነ ለአለመግባባታቸው የየራሳቸው ህግና ስርዓትን አበጅተው ይጓዛሉ። ኢትዮጵያውያን ደግሞ ለዚህ ዓይነት ጉዳዮቻቸው እልባት መስጫ የሚውሉ ብዙ የባህል እሴቶች ያሏቸው ሲሆን፤ እነዚህ እሴቶችም አብሮነታቸው ሳይላላ ጠብቆ ዘመናትን እንዲሻገሩ አድርጓቸዋል።
እኛም ለዛሬው ሀገርኛ አምዳችን ይዘን የቀረብነው፣ ‹‹የኩናማ ብሄረሰብ ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት›› በሚል ርዕስ በሀፍታይ ገብረእግዚኣብሔር በ2004 ዓ.ም በዶክተር ፈቃደ አዘዘ አማካሪነት የቀረበ ጥናት ሲሆን፤ በዶክተር ዓለሙ ካሳዬ አርታኢነት በባህልና ቱሪዝም አሳታሚነት በመጽሐፍ ታትሞ የወጣ መረጃ ዋቢ በማድረግ ነው። የጹሑፉ ዓላማም በህዝቦች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶች ወደከፋ ቀውስ ሳያመሩ ሰላም መፍጠርና አንድነታቸውን ማጠናከሪያ እሴቶቻቸውን ማስተዋወቅ ነው።
በጽሑፉ እንደተመላከተው፤ የኩናማ ብሔረሰብ በትግራይ ክልል ሰሜንና ሰሜን ምዕራብ ክፍል የሚገኘ ሲሆን፤ በግብርና እና በእንስሳት እርባታ የሚተዳደር ቢሆንም የሰሊጥ ምርት ዋነኛው የገቢ ምንጫቸው ነው። የብሔረሰቡ አባላት መግባቢያ ቋንቋ ኩናምኛ ሲሆን፤ ከአጎራባች ህዝቦችና ክልሎች ጋር በትግርኛ እና በአማርኛ ይግባባሉ።
ይህ ብሔረሰብ እርስ በእርሱም ሆነ ከሌሎች ህዝቦች ጋር መልካም የሆነ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ያለው ቢሆንም፤ እንደማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል በመካከሉ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችና ግጭቶች መኖራቸው አይቀሬ ነው። ምንም እንኳን ግጭቶች አንድም በግልግል፤ ሁለትም በእርቅ የሚፈታ ቢሆንም የሰው ልጅ ከቤተሰቡ፣ ከጎረቤቱ፣ እንዲሁም ከጥቅም ተጋሪው ጋር ይጋጫል። በኩናማዎች እሳቤ ግጭቶች ከሀብት እጥረትና ከመልካም ሥነምግባር ጉድለት የሚመነጩ ናቸው። በሀብት እጥረት ረገድ ከሚጠቀሱ የግጭት ምክንያቶች መካከል ደግሞ፤ ድንበር መግፋት፣ የእህልና የእንስሳት ስርቆት ሲሆኑ፤ በመልካም ስነምግባር ጉድለት የሚገለጹ የግጭት ምክንያቶች ደግሞ ጎሳዊ አስተሳሰብ፣ መጠጥ፣ የሰው ሚስት መድፈር ወይም በትዳር ላይ መማገጥ፣ አሉባልታና ፀያፍ ስድብን የመሳሰሉት ናቸው።
በእነዚህ ምክንያቶች የሚፈጠሩ ግጭቶችም ከተራ አለመግባባት እስከ ነፍስ ማጥፋት የሚደርሱ ክስተቶችን ሊያስከትሉ የሚችሉ ናቸው። ሆኖም የኩናማ ብሔረሰብ አባላት ውስጣዊ ግጭቶች ሲያጋጥሟቸው እንዲሁም ልዩ ልዩ ልማዳዊ ድርጊቶቻቸውን ሲፈጽሙ የሚቀድሙላቸው ‹‹ላጋኬ›› እና ‹‹ሳንጋኔና›› የተባሉ ሁለት ባህላዊ መሪዎች አሏቸው። በዚህም መሰረት ኩናማዎች ተራ የሚሏቸውን ግጭቶች በ‹‹ላጋኬ›› ማለትም በአገር ሽማግሌዎች፤ ከባድ የሚሏቸውን ግጭቶች ደግሞ በ‹‹ሳንጋኔና›› ማለትም ‹‹በአጥንት አስታራቂ ሽማግሌዎች›› በሽምግልና ዳኝነት አማካኝነት ያረግባሉ። አለመግባባቱንም በእርቀ ሰላም ይደመድማሉ።
በእነዚህ ሁለት መንገዶች እርቅ ሲከናወን ሁለቱም የየራሳቸው ሚና እና ኃላፊነት አላቸው። ለምሳሌ፣ ‹‹ላጋኬ›› ወይም የአገር ሽማግሌና አስተዳዳሪ የሚባሉት፤ እንደ አገር ሽማግሌም እንደ አስተዳዳሪም ሆነው የሚያገለግሉ ሰዎች ናቸው። ለዚህ ዓይነቱ ኃላፊነት የሚመረጡትም ቀዳሚ የኩናማዎችን መንደሮች ቆርቁረዋል የሚባሉ ስመ ጥር ሰዎች ተወላጆች ወይም ዝርያዎች ሲሆኑ፤ ከዚህ ባለፈም ባህላቸውን ጠንቅቀው የሚያውቁና የሚያከብሩ፣ መንደራቸውንም በብቃት ለመምራትና ለማስተዳደር ችሎታ ያላቸው፣ የህዝባቸው ፍቅር ያልተጓደለባቸው መሆን አለባቸው።
እነዚህ ለመሪነት የሚመረጡት ላካኬዎች ከነፍስ ማጥፋት በመለስ ያሉ (ለምሳሌ፣ የባልና ሚስት አለመግባባትን፤ ከጋብቻ ውጪ ማስጸነስን፤ ሰውን በመድሃኒት ማብከንከንን፣ መመረዝን ወይም መበሸትን፣ ደዌተኛ ማድረግንና ለሞት መዳረግን የመሳሰሉ) ግጭቶችን በሽምግልናና ዳኝነት አይተው የሚፈቱ ናቸው። ‹‹ላጋኬ››ዎች ከግድያ መልስ ያሉ መለስተኛ ግጭቶችን ከመፍታትና ከማስማማት ባለፈ፤ በጋብቻ፣ በግርዘት፣ በተዝካር፣ በበዓላት አከባበር(በፉሽካ፣ ኮሎ ኺሻ፣ አናሳሳ፣ የካላ፣ የአናኢላ ወይም የመላጨት ሥነስርዓቶች እንዲሁም ማስካላ፣ ሻታ፣ ቱካ፣ ታፊላ፣ ሾምሩና ኮንዱራ በዓልን በመሳሰሉ) እየተገኙ የመክፈቻና የመዝጊያ ምርቃት ሰጪዎች ናቸው። ከዚህ አንጻር ሲታይ ላጋኬዎች የብሔረሰቡ ልዩ ልዩ ሥነ ስርዓቶች ተቀዳሚ መሪዎች ናቸው ማለት ይቻላል።
በሌላ በኩል፣ ‹‹ሳንጋኔና›› በመባል የሚታወቁት የኩናማ የአገር ሽማግሌዎች በተለይ የነፍስ ግድያ ግጭትን ብቻ ለመሸምገልና ደምን ለማድረቅ ወይም ‹‹የአጥንት አስታራቂ ሥርዓት›› ለመፈጸም የሚሰየሙ ናቸው። በብሔረሰቡ የደም ግጭት ጉዳይ ከ‹‹ሳንጋኔና›› ውጪ በሌላ አካል ፈጽሞ አይታይም። ምክንያቱም በብሔረሰቡ የደም ግጭት በ‹‹ሳንጋኔና›› ሽምግልና ካልተፈታ በስተቀር የሚፈጸመው እርቅ ሕጋዊነት፣ ሰላማዊነትና ዘላቂነት አይኖረውም የሚል ጠንካራ እምነት አለ። ስለዚህም በ‹‹ሳንጋኔና›› የተፈጸመ ውሳኔ ይግባኝ የለውም፤ አይሻርምም። እርቁም ጽኑ ነው።
የ‹‹ሳንጋኔና›› የሽምግልና እና የዳኝነት እርቅ ፅኑነት ሌላው ምክንያት እርቅ አፍርሶ ደሙን ለመበቀል የቃጣ ወይም የሞከረ (በትር ያነሳ፣ ድንጋይ የወረወረ፣ ብረት ያቀና፣ ካራ የሳለ) ሰው ሁሉ እጁ ይሰበራል፤ ዘሩም (ትውልዱ ሁሉ) ይጠፋል ተብሎ ስለሚታመን ነው። ምክንያቱም የ‹‹ሳንጋኔና›› አባላት በብሔረሰቡ አባላት ዘንድ ታማኝ፣ የተናገሩት መሬት ጠብ የማይል ነው ተብለው የሚታመኑ የግድያ ግጭት አስታራቂዎች ናቸው። ከመታመናቸውም በተጨማሪ ሳንጋኔናዎች የረገሙት፣ ቃላቸውን ያልፈጸመ፣ በክፉ ያነሱት እና ያዩት ሁሉ በህይወት የመቆየት ዕድሉ የመነመነ ነው። ከብቶቹና ዘመድ አዝማዱ በሙሉ የመበታተንና የመጥፋት እንዲሁም የሞት አደጋ ይገጥማቸዋል የሚል ጠንካራ እምነት አለ። እናም ሳንጋኔናዎች በህብረተሰቡ ዘንድ ይከበራሉ፤ይታመናሉ፤ትዕዛዛቸውም ይፈጸማል።
ለዚህም ነው፣ በኩናማ ብሔረሰብ ውስጥ ግጭት ተከስቶ የሰው ሕይወት ከጠፋና ገዳዩም ድርጊቱን ከፈጸመ በኋላ ምን ጊዜም ከደም ተበቃዮች እየተደበቀና እየሸሸ ወደ አስታራቂው ወይም ‹‹ሳንጋኔና›› ቤት ሮጦ ይገባል እንጂ ወደ ሌላ ቤት ወይም ቦታ አይሄድም። አንዳንዴ ገዳይ ብቻም ሳይሆን ለነፍሳቸው የሰጉ የገዳይ ቤተሰቦችም ጭምር ወደ አስታራቂው ወይም ‹‹ሳንጋኔና›› ቤት ገብተው ይጠለላሉ። እናም ገዳይም ሆነ ቤተሰቦቹ ወደ ሳንጋኔናዎች መኖሪያ ከገቡ የሚተናኮላቸውና የሚገድላቸው የለም። ገዳይ ሊሞት የሚችለው ወደ ሳንጋኔናዎች ቤት ሲሄድ ከሳንጋኔናዎች ቤት ሳይደርስ በመንገድ ላይ የሟች ቤተሰቦች ካገኙት ብቻ ነው። በመሆኑም የኩናማዎች ሳንጋኔና፣ ሰው አውቆም ይሁን ሳያውቅ (በአብዛኛው ሳያውቅ) ለገደለ ሰው ጥላ፣ መጠጊያና መማጠኛ ሆኖ የሚያገለግል፤ ችግሩንም ፈትቶ በቀልን በማራቅ በእርቅ የሚጨርስ ተቋም ነው።
አንዳንድ ጊዜ ገዳይ ወደ ‹‹ሳንጋኔና›› መሄድ ፈልጎ ነገር ግን መሄጃ መንገድ አጥቶ በረሃ ገብቶ ጠፍቶ ከቀረ በብቀላ እናልቃለን ብለው የሚሰጉ የገዳይ ቤተሰቦች በሙሉ ተሰብስበው ወደ ሳንጋኔና ቤት ይጠጋሉ። ከዚህ በኋላ የሟች ቤተሰቦችና ወገኖች ወደ ሳንጋኔና ቤት የተጠጉትን የገዳይ ቤተሰቦች ደመኞቻችን ናቸው ብለው ለመበቀል አይሞክሩም። ሳንጋኔናዎቹም ሁለቱንም ቤተሰቦች ከተቀበሉ በኋላ መከታ የሰጧቸውን የገዳይ ቤተሰቦች በአንድ ቤት ወይም ስፍራ አቆይተው ከሟች ቤተሰቦች መሃል የቅርቦቹን፣ ታዋቂዎቹንና ትላልቆቹን ሰዎች መርጠው በመጥራት እነርሱንም በአንድ ቤት በማስቀመጥ መሸምገል ይጀምራሉ። ሽምግልናውም በእርቅ ይደመደማል።
ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ወደ ሳንጋኔናዎች የገባው ገዳይ እና የገዳይ ቤተሰቦች ጥቃት የማይደርስባቸው እና በሳንጋኔና አማካኝነት እርቅ የሚፈጸም ቢሆንም፤ እስከ እርቅ ስርዓቱ ድረስ ግን ለሁሉም አንድ ክፍል ተሰጥቷቸው እንዲያርፉ ይደረጋል። በዚህ መልኩ ሳምንት ከሞላቸው በኋላ የእርቅ ስነስርዓቱን ለመጀመር የግድያውን መንስኤ ለማወቅ የማጣራት ሥራ ያከናውናሉ። የማጣራት ሂደቱ የሚጀምረውም ከገዳይ ቤተሰብ ለግድያ ያደረሳቸው ጉዳይ ምን እንደሆነ በመጠየቅ ሲሆን፤ ሳንጋኔናዎቹም የግጭቱን መንስኤ ካጣሩ በኋላ ወደ ሟች ወገኖች የሚቀርቡ ሦስት መልዕክተኛ ሽማግሌዎችን ይመርጣሉ።
በሳንጋኔናዎች ለመልዕክተኛ የሚመረጡት ሽማ ግሌዎችም የንግግር ክህሎታቸው የዳበረ፤ ሰው እንዲፋቀር እንጂ እንዲጣላ ፍላጎት የሌላቸው፤ ‹‹ዋሽተው›› የሚያስታርቁ እንጂ ዋሽተው የሚያጣሉ አይደሉም፤ እንዲሁም የሄዱበትን ጉዳይ ሳይፈጽሙ ወደኋላ የማይመለሱ ዓይነት ሰዎች ናቸው። እናም በሳንጋኔናዎች የተላኩ ሽማግሌዎች ወደ ሟች ቤተሰብ በመሄድ እንዲታረቁና ሰላም እንዲያወርዱ በሳንጋኔና እየተጠየቁ መሆኑን ይገልጹላቸዋል። የሟች ቤተሰቦችም ምንም እንኳን በሳንጋኔናው ላይ ያላቸው እምነት ጠንካራ ቢሆንም በመልዕክተኞቹ ሽማግሌዎች የቀረበላቸውን የደም እርቅ ጥያቄ በአንድ ጊዜ ላለመቀበል ያንገራግራሉ።
መልዕክተኛ ሽማግሌዎቹም በተደጋጋሚ በመመላለስ ይለማመጧቸውና የሟች ቤተሰቦችን የእርቅ ይሁንታ ያገኛሉ። ከዚህ በኋላ ወደላኳቸው ሳንጋኔናዎች ተመልሰው ‹‹እነዚህ ሰዎች ወደልባቸው ተመልሰዋል፤ ሊታረቁ ፈልገዋል›› ብለው ይናገራሉ። ሳንጋኔናዎቹም የገዳይና ሟች ቤተሰቦችን አንድ ላይ አቀራርበው፣ የገዳይ ቤተሰቦችን ‹‹በሉ እናንተም ሰው ገድላችኋልና የደም ካሳችሁን ይዛችሁ ታረቁ›› በማለት ያዛሉ። የገዳይ ቤተሰቦችም የተጣለባቸውን የደም ካሳ ይዘው ለእርቅ በተቆረጠው ቀን ይቀርባሉ። የደም እርቁ በሚፈጸምበት ዕለትም ህዝቡ ሰፊ ሜዳ ላይ እንዲሰባሰብ ይደረጋል። ለደም ካሳነት የተዘጋጁት ከብቶችም ይቀርባሉ።
ሳንጋኔናዎችም የእርቅ ስርዓቱን ለመመልከት በተሰበሰበው ህዝብ መሃል በመቆም ፈጣሪያቸውን የሚማጸኑበትን ልመና ያቀርባሉ። እርቁም የተሳካ እንዲሆን መርቀው የእርቅ ስርዓቱን መጀመር ይገልጻሉ። የተሰበሰበው ህዝብና ታራቂዎችም ምርቃቱም ‹‹አሺባ›› /አሜን/ እያሉ በአንድ ድምጽ ይቀበላሉ። ለካሳ ከተዘጋጁት መሃል የገዳይ አጎት (የእናት ወንድም) ያመጣው አንድ ከብት ይታረዳል። የተቀሩት ለሟች ቤተሰብ ይሰጣሉ። በሜዳው የተሰበሰበው ህዝብም ክብ ክብ እየሠራ የታረደውን ስጋ እያበሰለ ይመገባል። በዚህ መሃል ገዳይን ጨምሮ የገዳይና የሟች ቤተሰቦች መካከል ምራቅ ዋጥ ያደረጉ አራት አራት ሰዎችን በመምረጥ ሳንጋኔናዎች ግራና ቀኝ ያሰልፏቸዋል። በተነጠፈ ሰሌን ላይም አንድ ላይ ያስቀምጧቸዋል። በተቀመጡበት አንድ ሰፌድ የበሰለ ስጋ ይሰጣቸውና አንድ ላይ ይመገባሉ።
በአንድ ሰሌን ላይ እንዲቀመጡና በአንድ ሰፌድ እንዲመገቡ መደረጉም ደግሞ የወደፊት አብሮነትና የወንድማማችነት መንፈስ እንዲሰርጽባቸው፤ እንዲረብባቸው ለማድረግ ነው። ስለሆነም ያለምንም ፊት መንሳት በሳንጋኔና ተነጥፎ በተሰጣቸው ሰሌን ላይ ተቀምጠው አድርጉ የተባሉትን ሁሉ በህብረት ያደርጋሉ። ህዝቡም በመብላትና በመጠጣት እንዲሁም በእልልታ ያጅባቸዋል። ከመብል መጠጡ ማሳረጊያ ምርቃት በኋላ አስታራቂው ሽማግሌ (ሳንጋኔና) የሟችና የገዳይ ቤተሰቦችን አቀራርበው ከታረደው ከብት አንድ ቅልጥም እየፋቁ በደንብ አጥርተው እንዲበሉ ታራቂዎቹን ያዛሉ። ታራቂዎቹም የተሰጣቸውን ቅልጥም ከስጋ የነጻ ያደርጉታል። ይሄም አጥንት ለሁለቱ ቤተሰቦች እንደ ማስታረቂያ ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን፤ ሳንጋኔናውም ይሄን ቅልጥም ህዝቡ በተሰበሰበበት ሜዳ ላይ ትንሽ ጉድጓድ ቆፈር አድርገው ያጋድሙታል። ሳንጋኔናው ትንሽ ጠጠር በማንሳት ግለ ጸሎት ጸልየውና ጠጠሩንም ባህላዊ መድሃኒት ቀብተው ቀስ አድርገው ወደ አጋደሙት አጥንት ይወረውሩታል። አጥንቱም ይሰበራል።
ቀጥሎም ‹‹በሉ እዚህ መጥታችሁ ማሉ፤ ከእናንተ መካከል ወንድሜን፣ ወገኔን ገደልክብኝ ብሎ ሰው ለመግደል ያሰበ እንደዚህ አጥንት ይሰበር›› ይላል። እነርሱም ይሄንኑ የሳንጋኔናውን ቃል ይደግማሉ። የተሰበረው አጥንት መቅንም ከሟችና ከገዳይ ቤተሰብ የተመረጡ ሰዎች ደረታቸውን እንዲቀቡት ይደረጋል። ሳንጋኔናው የተሰበረውን አጥንት መቅኔውን የተቀቡ ሰዎችም ሁለት ሁለት እየሆኑ ደረት ለደረት ይነካካሉ። በመቀጠልም ‹‹ወንድሜ ነህ ምንም አልልህም ፤ምንም አትለኝም ሁለታችን ወንድማማቾች ነን። ቂም በቀል የሚባል ነገር ይብቃ። በአንድ መዓድ በልተናል፤ ለወደፊቱም እንበላለን። በበረሃም ይሁን በመንደር አንድ ላይ ነን። ሰውነቴን ትጠብቅልኛለህ፤ ሰውነትህን እጠብቅልሃለሁ፤›› እያሉ ቃል ኪዳን ይገባባሉ። ይሄም የታራቂዎቹን የወደፊት ወንድማማችነትና ወዳጅነት ያጠናክራል ተብሎ ይታመናል። ከዚህ ስነ ስርዓት በኋላም ለቂም በቀል መፈላለግ ቀርቶ ሁለቱም እንደ ወንድምና ወዳጅ ተያይተው አብረው ይኖራሉ።
እናም የኩናማዎች ‹‹ላጋኬ›› እና ‹‹ሳንጋኔና›› የብሔረሰቡ የግጭት መፍቻ የሰላም ማዕከሎች ሲሆኑ፤ ሁለቱም በየፈርጃቸው በብሔረሰቡ ውስጥ የሚስተዋሉ አለመግባባትና ግጭቶችን ወደ ተካረረ ፀብና ብቀላ ሳያመሩ በሰላም በእርቅ እንዲፈጸም የሚያስችሉ የብሔረሰቡ የባህል ተቋማት ናቸው። በዚህም ‹‹ላጋኬ›› በብሔረሰቡ ውስጥ ከግድያ መልስ ያሉ መለስተኛ ግጭቶች በሽምግልና መፍትሔ የሚያገኙበት አሠራር ነው። ሌላው ‹‹ሳንጋኔና›› ደግሞ ሰው የገደለ ሰው ለጊዜው የሚጠለልበትና ያለተጨማሪ ደም እርቅ እንዲፈጠር የኩናማ ብሔር ያቆመው የራሱ መማጠኛ ስፍራው ወይም ተቋሙ ነው ማለት ይቻላል።
አዲስ ዘመን አርብ የካቲት 6/2012
ወንድወሰን ሽመልስ