“ቲፕ” የኛ ቃል አይደለም። “መጤ” ነው። በእንግሊዝኛውም ቢሆን ከየት እንደመጡ (“etymology” ያቸው) ከማይታወቁት ቃላት ስር ሲሆን ምድቡም ከ”የአራዳ ቋንቋ” ነው።
የ”ቲፕ” መነሻ ዘመኑ 17ኛው ክፍለ ዘመን ሲሆን፤ በሀገረ እንግሊዝ በ18ኛው ክፍለ ዘመን ወደ አሜሪካ፣ ጃፓን፣ እያለ እያለ አድማሱን በማስፋት ይሄው እኛ ጋር ደርሶ እያደረግነውና እየተወያየንበት እንገኛለን።
“ቲፕ” በእኛ “ጉርሻ” እምንለውን ይዘን፣ ግን ደግሞ ተለምዷልና በ”ቲፕ” ሀሳብ መለዋወጡን እንቀጥል።
ከላይ “ጉርሻ” መሆኑን ስንጠቅስ ምክንያቱንም መናገራችን ሲሆን፤ ምንነቱ በበኩሉ ለምን? ስለምን ሲባል ቲፕ ይሰጣል? አላማውስ ምንድን ነው? እና ሌሎች መሰል ጥያቄዎችን እያሰለፈ ከተፍ ይላል።
የ”ቲፕ” አላማ ግልፅ ነው፤ መልካም አገልግሎት ያፈራው እርካታን መሰረት ያደረገ፣ ተገቢ አገልግሎት ላይ የተመሰረተ ወዘተ፤ እንዲሁም ይህንንና ይህንን ብቻ ታሳቢ ያደረገ የ”ጉርሻ” አሰጣጥ ሂደት (tipping) ነው። ይህ ደግሞ ቀጥታ ከስነ-ልቦና ጋር የተያያዘ ስለሆነ ለዚህ ፅሁፍ ይሰፋልና እንለፈው።
የ”ቲፕ” አላማ ይህ ከሆነ ያልሆነውስ ምንድን ነው?
የ”ቲፕ” ዓላማ ያልሆኑት ብዙ ናቸው። የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያህል፤ “ቲፕ” የስራ ውጤት እንጂ ችሮታ አይደለም፤ ጉቦ ወይም ምልጃም አይደለም። ድጎማ ወይም ደራጎትም አይደለም። “ቲፕ” አስገዳጅነት የለበትም፤ የሰጪው ሀብት ማሳያ፤ የበታችነት ወይም በላይነት መግለጫም አይደለም። “ቲፕ” በይሉኝታ የሚከወን፣ በግልምጫና ፍጥጫ የሚዘረጋ እጅ ውጤት ነው ሲባልም ተሰምቶ አይታወቅም። “ቲፕ” ከውበትና ቁንጅና፣ ፉንጋነትና ጉራዳነት ጋር ውል የለውም። “ቲፕ” መነሻና መድረሻ ውጤቱ አንድና አንድ ነው፤ “መልካም አገልግሎትን ማግኘት” ብቻ። አንዳንዶች “ሰጥቶ መቀበል” ሲሉት ይሰማሉ።
ቲፕ እጅጉን የተለመደባቸው አገራት እንዳሉ ሁሉ አይነኬ የሆነባቸውም ሞልተዋል። (ይህ ዓለም አቀፍ አገልግሎት የሚሰጡ ወይም “ቢል” የሚጠቀሙ ተቋማትን አይጨምርም።)
ለምሳሌ በአሜሪካ የቲፕ ገፅታ መልከ-ብዙ ነው። መንግስት አያገባውም፤ ይሁን እንጂ በዜጎች መካከል ቲፕን የተመለከቱ መግባባቶች ያሉ ይመስላል።
በአገረ አሜሪካ 10 እና ከዚያ በታች ሳንቲም ቲፕ መስጠት ምሳሌነቱ ተግሳፅና ወቀሳ ሲሆን ትርጉሙም “አገልግሎትህ ከደረጃ በታችና አርኪ አይደለም፤ አሻሽል!” ማለት ሲሆን ከዛ በላይ ግን የአድናቆትና እርካታ መግለጫ ቋንቋ ነው።
በአሜሪካ ግለሰብ ከፌና ሬስቶራንቶች የየራሳቸው የተፃፉ ህጎች ያሏቸው መሆኑ ሌላው ነው። ከእነዚህ መካከል አንዱ ስታርባክስ ሲሆን በሱ ካፌዎች ቡና ፉት ለማለት የሚመጣ ቲፕ የመስጠት ግዴታ የለበትም፤ መስጠት አለብኝ የሚል ካለ ግን ሶስት አማራጭ ህጎች ተቀምጠውላታል። ሀ) 0.50ሳንቲም ለ) 1 ወይም ሐ) 2 ዶላር። በቃ ከሶስቱ አንዱን እንጂ ከዚህ ውጪ ከሆነ ጉዳዩ ሌላ ነው ማለት ነው።
ስታርባክስ ይህንን ህገ-ደንብ ተግባራዊ ያድርግ እንጂ የካፌ አስተናጋጆቹ የወደዱለት አይመስልም። ከአስተናጋጆቹ አንዷና ቅሬታ አቅራቢዋ ጎትስማ ስትሆን እንደሷ አስተያየት ይህ ድንጋጌ እዚህ ግባ የማይባል “ማላገጥ ነው። እንዴት ባንድ ስኒ (ካፕ) ቡና ይቺ ቲፕ እንድትሰጥ ይወሰናል? የማይረባ። ለቋሚ ደንበኞች (loyal customers) ብቻ እንኳን ቢሆን ጥሩ” ነበር።
“ቲፕ” በእንግሊዝ ከ10 እስከ 15 በመቶ ሆኖ አሰራሩ ቢልን መሰረት ያደረገ ሲሆን፤ የአገልግሎትና ቫት በጥምር በዋጋ ላይ ተደምሮ በሚመጣባት ጀርመን እንደ ተቀሩት የአውሮፓ አገራት ሁሉ የተለመደና ጠባቂዎች ያሉት ሲሆን፤ ግን ደግሞ እንደነ ደቡብ አሜሪካ እጅግ የተተጋነነ ጠባቂነት አይታይም። (በጀርመን የአንድ ካፊቴሪያ አስተናጋጅ ዓመታዊ ገቢ ቲፕን ሳይጨምር 20,000 ዩሮ ሲሆን ተገቢነት አለው ተብሎ የሚሰጠው የቲፕ መጠንም ከ10 እስከ 15 በመቶ ነው።)
የሌሎች አገራትን ልምድ ስንመለከት ደግሞ “ቲፕ” ጭራሽ ውጉዝ ከመአሪዎስ ሆኖ እናገኘዋለን፤ ቻይናንና ደቡብ ኮሪያን መጥቀስ ይቻላል። አሁን “ቲፕ የት?” ወደሚለው እንሂድ።
“ቲፕ” እዚህ ቦታ ተብሎ የተወሰነለት ቦታ የለም የሚሉ አሉ። አይደለም ማን ከካፌና ሬስቶራንት ውጣ አለው? የሚሉም አሉ። በሁሉም ቦታ፣ በሁሉም ስራና እንቅስቃሴ ውስጥ ያለና የሚኖር ነው በማለት የአጠቃላይነት ገፅታን የሚሰጡትም አሉ።
በጣሊያን በሬስቶራንት ለተገኘ አገልግሎት ምንም አይነት ቲፕ መስጠት አይጠበቅም። በአውሮፓ ከሬስቶራንት ውጭ ለሚሰጥ አገልግሎት ቲፕ የመስጠት ባህል እንደሌለ፤ በሬስቶራንትም ቢሆን ከ10 በመቶ እንደማይበልጥ ከተደረጉ ጥናቶች መረዳት የሚቻል ሲሆን አንዳንዴ እስከ 20 በመቶ ድረስ የሚሰጡ መኖራቸው እንደሚታይና እነዚህ ሰዎችም ይህን የሚያደርጉት ካለማወቅ እንደሆነና ሊያደርጉ እንደማይገባ ተመልክቶ እናገኛለን። ይህ በኳታር፣ ሳውድ አረቢያ እና አረብ ኢመሬትስ ከ15 አስከ 20 በመቶ ቲፕ መስጠት የተለመደ ጉዳይ ነው።
በጃፓን፣ ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ሆንግ ኮንግ፣ ስዊዘርላንድ፣ አውስትራሊያ፣ ቤልጂየምን በመሳሰሉ አገራት መስጠትና መቀበል ቀርቶ ማሰብም ፀያፍ ነው። በጃፓን እርስዎ ቲፕ ሊሰጡ አይደለም ጭራሽ “ተቀብለው” መሄድዎ ነው ገራሚው ነገር። ልክ ተስተናግደው ሲወጡ ከአስተናባሪዎችዎ “Gochisosama deshita” የሚል ድምፅ ይሰማሉ። በሬስቶራንቱ ተገኝተው የጣፋጭ ምግቡ ተቋዳሽ በመሆንዎ የሚያመሰግን ሀረግ።
ቲፕ በአፍሪካ የተለመደና ብዙ ጠባቂዎች ያሉት ሲሆን አስቸጋሪው ነገር ምንም አይነት ደንብና መመሪያ የሌለው መሆኑ ነው። ሂደቱ የሚከናወነው በሰጪው ውሳኔ ላይ ተመስርቶ ስለሆነ ከሰው ሰው ይለያያል። ይህ ደግሞ የራሱ ችግር አለው።
የኢትዮጵያን ሁኔታ በምን መንገድ መግለፅ እንደሚገባ ለጊዜው ባይታወቅም ቲፕ ተጠባቂ መሆኑን ግን መካድ አይቻልም። ልክ ነው አይደለም የሚል ጥናት የሚፈልግ ሆኖ እጁ እስኪቃጠል ሲያጨበጭብ የዋለው ተስተናጋጅ አሁንም አሁንም “ምን ላምጣ፤ አቤት ጠሩኝ …” እየተበላ ከተስተናገደው እኩል ቲፕ(ምናልባትም በላይ) ከፍሎ ካልወጣ የሚቀጣ የሚመስለው ቁጥሩ ብዙ ነው። በአብዛኛው የእኛ አገር ቲፕ መሰረቱ የተገልጋይ እርካታና የአገልግሎት ሰጪ ሙያዊ ስነምግባር ሳይሆን ጉራ፣ ይሉኝታ፣ ፈገግታ፣ አካላዊ ውበት፣ አዘኔታ (ደሞዛቸው ትንሽ ነው በሚል) እና የመሳሰሉት ናቸው እንጂ በእውቀትና ሙያውን በሚያሳድግ፤ አስተናጋጆችን በሚያስተምር መንገድ አይደለም።
በሙያው ሥነ ምግባር ልመራ ያለና እጁን ከቲፕ ሰብሰብ ያደረገ ተስተናጋጅ ከጠባቂዎቹም ሆነ ከደጋፊዎቻቸው የሚፈናጠረው አስተያየት “ገብጋባ፣ ቋጣሪ …” የሚል ሲሆን ከእነዚህ ሰለባዎች አንዱ አትሌት ሀይሌ ነው።
ቲፕን በተመለከተ አንድ አስገራሚ በቀጣሪዎቹ ወይም በሬስቶራንት ባለቤቶች ለየት ያለ አተያይ አላቸው። ገና ለገና አስተናጋጆች ቲፕ ያገኛሉ በሚል በ160 ብር የወር ደመወዝ መቅጠራቸው ነው። ይህ የተነገረኝና የምነግራችሁ አንድ ኬክ እስከ 80 ብር በሚሸጥበት ካፌ ውስጥ እየሆነ ያለ ነው። መቸም ይህ አይነቱ ግፍ በምድርም፤ በሰማይም ያስጠይቃልና ቢታሰብበት አይከፋም ብለን እንለፈው።
ሌላው የኛን አገር ለየት የሚያደርገው ወሳኝ በሆኑ ዘርፎች ላይ እንኳን ትንሽዬ ሀሳብ የምትሰጥ መንግስታዊ በራሪ ወረቀት ነገር አለመኖሯ ነው። ይህንን ክፍተት ለመሙላት ይሁን ወይም ሌላ ለጊዜው ባይታወቅም (እንደ ሌሎች አገራት “Tipping policy”ው ቀርቶ) አንድ አንድ አካላት ግን ድረ-ገፅ ዘርግተው የመሰላቸውን ማብራሪያ የሚሰጡ አሉ። በእንደዚህ አይነት በጥናት ላይ ያልተመሰረተ፤ አካባቢን ለይቶ ያላመለከተ መልስ ደግሞ ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመጡ አሉታዊ ተጽእኖ ይኖረዋልና ባለቤት ካለው ያስብበት እንላለን።
አዲስ ዘመን የካቲት 6/2012
ግርማ መንግሥቴ