ጥር 6 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የሠራተኞቹን ቅሬታና የአስተዳደር አካላት ምላሽ የያዘ ዜና እንዲሁም ‹‹ከአየር መንገዱ ዝና በስተጀርባ›› በሚል ርዕስ ደግሞ በፍረዱኝ ገጽ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ላይ ሰፊ ዘገባ መሥራታችን ይታወቃል፡፡ በዘገባው የቅሬታ አቅራቢዎቹ የመሠረታዊ ሠራተኛ ማህበሩ አቤቱታ፣ ቀዳማዊ መሠረታዊ ሠራተኛ ማህበር፣ ሰነዶች፣ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበር ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ)፣ ሕገ መንግሥቱ ምን ይላል? በሚል የተዳሰሰ ሲሆን፤ የአየር መንገዱ የሠው ሀብት ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት እንዲሁም ዋና ሥራ አስፈፃሚው አቶ ተወልደ ገብረማርያም በሠራተኞች ላይ ይደርሳሉ ተብለው የቀረቡ መብት ጥሰቶችና የተለያዩ ቅሬታዎችን የፈጠሩ የሕግ ማዕቀፎች ብሎም አሠራሮች ላይ የሰጡትን ምላሽ በማካተት ተስተናግዶ እንደነበር ይታወሳል፡፡
በዘገባው ላይ የተካተተው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ሃሳብ ቅሬታን እንደፈጠረበት የኢትዮጵያ አቪየሽን ቴክኒሽያኖች ማህበር በቁጥር Ref.No. EATA/10/02-03 ወጪ በሆነ ደብዳቤ ለተቋማችን ይህንን መግለጫ ልኳል፡፡
ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት
አዲስ ዘመን ጋዜጣ
አዲስ አበባ
በድርጅቱ ለንባብ የበቃውን ዘገባ ተንተርሶ ከማህበሩ የተሰጠ መግለጫ
እንደሚታወቀው አዲስ ዘመን ጋዜጣ፤ በጥር 6 ቀን 2012 ዓ.ም ዘገባው የሚከተለውን ለሕዝብ ማስነበቡ ይታወሳል፡፡ “የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም፤ ከሰሞኑ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለቀረበላቸው አስተያየትና ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፤ አየር መንገዱ ለስኬታማነቱ ትልቁ ምስጢሩ ሥነ-ምግባር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን በአገሪቱ ካለው የሥራ ባሕል አንፃር ይህ የማይዋጥላቸውና ምቾት የሚነሳቸው ሠራተኞች አይጠፉም፡፡
አራት መቶ መንገደኞችን ይዞ ከባህር ወለል 40 ሺህ ጫማ ከፍታ ላይ የሚበር አውሮፕላን የሚጠግን ቴክኒሽያን ትንሿ ስህተት ሕይወት ልታስከፍል ስለምትችል ከፍተኛ ጥንቃቄ ይጠበቅበታል፡፡ በዚህ ደረጃ ሕጉን ለማስፈፀም ጠንከር ያሉ ዕርምጃዎች ሲወሰዱ ደግሞ ቅሬታዎች ይበዛሉ፡፡”
በዚህም መሠረት ይህንን ግልጽ የሆነ መግለጫ ማውጣት አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡
እኛ የኢትዮጵያ አቪየሽን ቴክኒሽያኖች በየትኛውም ዓለም የአቪዬሽንን የደህንነት መርሆዎች በመጠበቅ እና በማስጠበቅ ውስብስብ የሆኑ ችግሮችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመፍታት ብቁ የሆንን እንዲሁም ለዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ደህንነት መርሆዎች ትኩረት በመስጠት የዓለም አቀፉን ተጓዥ ደህንነት በሚገባ እያስጠበቅን ያለን ባለሞያዎች ስንሆን፤ በዋናነትም ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ዘርፍ አሁን ላለችበት ደረጃ የጀርባ አጥንት ሆነን የዘለቅን እና ለሀገራችን አቪዬሽን ዘርፍ ሰፊ ራእይ ሰንቀን ይህንን የምንቀጥል ዜጎች ነን፡፡
ነገር ግን በዚህ አዲስ ዘመን ባስነበበው እትም የተገለጹት ነገሮች፤ በምንም ዓይነት ሙያውንም ሆነ ባለሙያውን የማይወክሉ ናቸው ብለን እናምናለን፡፡ ይህም በዚህ ዘገባ ላይ የተገለጸው የዋና ሥራ አስፈፃሚው ንግግር፤ በድርጅቱ ውስጥ በአውሮፕላን ጥገና ላይ የተሰማራውን ሀገሩን የሚወድ ትጉህ ባለሙያን የሚንቅ እና የሚያዋርድ እንደሆነ ተረድተናል፡፡
እኛ ሁላችን ሙሉ በሙሉ የአየር መንገዱ ሠራተኞች ስንሆን፤ ቅሬታዎች እንደሚኖሩን የማይካድ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ የተጠቀሰው ንግግር፤ “የቴክኒሽያኑ ቅሬታ የሚመነጨው የደህንነት መርሆዎችን ባለመከተሉ ምክንያት በሚወስደው ዕርምጃ ብቻ ነው” የሚል አንደምታ የሚፈጥር እና “ቴክኒሽያኑ የአቪዬሽን ደህንነትን ለማስጠበቅ ሲባል የሚወጡ ህጎችን (safety procedures) የመከተል መሰረታዊ ችግር አለበት በተጨማሪ ብቁ ባለመሆኑ ብዙ ዕርምጃዎች ይወሰዳሉ” የሚል ትርጉም አለው ብለን እናምናለን፡፡
ይህ በሙያተኛው እና በሙያው ላይ የተደረገ የንቀት፣ የስም ማጥፋት እና አግባብ ያልሆነ ውንጀላ ነው ብለን ስለምናምን ተቀባይነት የለውም፡፡ አጥብቀንም እንቃወመዋለን፡፡
ያለመታከት ለሀገሩ ብልፅግና፣ ለአየር መንገዱ ልእልና ብሎም ለዓለም አቀፉ ተጓዥ ደህንነት የሚለፋውን ባለሙያ በዚህ መልኩ ለመወንጀል መሞከር እጅግ የሚያሳዝን እና በተለይም በዋና ሥራ አስፈፃሚው ሲደረግ እጅግ ሞራል የሚነካ ነው፡፡
ቴክኒሽያኑ በሙሉ ማንኛውንም ዕፀፆች የውስጥ ገመና ናቸው በሚል እሳቤ ወደ ውስጥ በመያዝ የተሻሉ ነገሮችን ለማምጣት እየተጋ ባለበት በዚህ ሰዓት በዚህ መልኩ የቴክኒሽያኑ እና የሙያው ክብር በህዝብ ፊት መዋረዱ አሳዝኖናል፡፡ የቴክኒሽያኑ በህዝብ ፊት በዚህ መልኩ መቅረብ ለአየር መንገዳችንም ቢሆን ስሙን የሚያጎድፍ ነው ብለን እናምናለን፡፡
ሙያው እጅግ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚፈልግ መሆኑን የምንረዳ፤ ይህንን ለማድረግ የሙያው ስነ-ምግባር እና ያለን በቂ እውቀት የሚያስገድደን መሆኑ፤ እንዲሁም ነገሮች ባልተሟሉበት ሁኔታ እያንዳንዱ ቴክኒሽያን ከፍተኛ በሆነ የግል ጥረቱም ጭምር የበረራ ደህንነትን አስጠብቆ፤ ከፍተኛ ገቢ እያስገኘ ያለ ለሀገሪቱ እና ለአየር መንገዳችን ዋልታ የሆነ ባለሙያ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ የበረራም ደህንነት በበቂ ሁኔታ የሚጠበቀው ጠንካራ ዕርምጃ በሚወስዱ ኃላፊዎች ብቻ ሳይሆን፤ በሙያ በበለጸጉ፣ በእውቀት እና በመልካም ስነ-ምግባር በታነፁ ቴክኒሽያኖች ነው ብለን እናምናለን፡፡
በዚህም አጋጣሚ፤ እኛ የአውሮፕላን ጥገና ባለሙያዎች በዚህ ነገር ሞራላችን ሳይነካ ለሀገራችን አቪዬሽን ዘርፍ እንዲሁም ለውዱ አየር መንገዳችን የሰነቅነውን ራእይ ከግብ ለማድረስ በትጋት መሥራት እና ለደህንነት ምክንያት መሆናችንን አጠናክረን መቀጠላችን የአማራጭ ጉዳይ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑን ለማረጋገጥ እንወዳለን፡፡
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 4/2012