የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በማኔጅመንት ሰርተዋል፤ በጋዜጠኝነት የፖስት ግራጅዌት ሰርተፍኬት አላቸው፤ ከሊደርሺፕ ዩኒቨርሲቲ የብቃት ማኔጅመንት (ኮምፒተንሲ) ላይ ማስተር ፕሮፌሽናል በሚል ማዕረግ እውቅና ተሰጥቷቸዋል። ወደ አውስትራሊያ አቅንተውም በፐብሊክ ፖሊሲ ማኔጅመንት የሁለተኛ (የማስተርስ) ዲግሪያቸውን ሰርተዋል ።
ስራን አሃዱ ብለው የጀመሩት የልማት ድርጅት በሆነው የኢትዮጵያ እህል ንግድ ድርጅት ውስጥ ነው ከዛም በኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለስልጣን የኦፕሬሽን ሀላፊ፤ የጉምሩክ አስተዳዳሪ ሆነው ሰርተዋል፤ ሪፎርምና የለውጥ ስራዎች ላይም የበኩላቸውን ሚና ተጫውተዋል።
በቀድሞ ማስታወቂያ ሚኒስቴር የሚኒስትሩ የሪፎርም አማካሪ። በአቅም ግንባታ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ። ተቋሙ ሲፈርስ ደግሞ ወደ አውስትራሊያ በመሄድ ትምህርታቸውን ቀጥለዋል ።
በሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር የፌዴራል ሪፎርሞች ዳይሬክተር። የስኳር ኮርፖሬሽን የሚኒስትሩ አማካሪ እንዲሁም ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ በመሆንም ሰርተዋል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው ተሹመዋል ።የዛሬ የተጠየቅ አምድ እንግዳችን ኮሚሽነር በዛብህ ገብረየስ ።ስለ ኮሚሽኑ የለውጥ ስራዎች፣ ያሉበት ፈተናዎችና ሌሎች ጉዳዮች ላይም ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበናል።
አዲስ ዘመን፦ ወደ ኮሚሽኑ ሲመጡ ምን ጠብቀው ምንስ አገኙ?
ኮሚሽነር በዛብህ ፦ ወደ ተቋሙ ከመምጣቴ በፊት አብዛኛው የስራ ልምዴ በዘርፉ ስለነበር አስብ የነበረው የአንድ መስሪያ ቤትን ገጽታና ምስል አልነበረም።ኮሚሽኑ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ገጽታ መገለጫ አድርጌ ነው ያሰብኩት፤ሆኖም የጠበቅሁት ሳይሆን መሰረታዊ ለውጥ በሚያስፈልገው ቁመና ላይ ሆኖ ነው ያገኘሁት።
አዲስ ዘመን፦ ግን በእኛ አገር ሲቪል ሰርቫንቱ የሚገባውን ክብር አግኝቷልን ?
ኮሚሽነር በዛብህ፦ እኔ ወደ ተቋሙ ስመጣ ይህ ክብር ጭራሽ የሌለበት ሁኔታ ነው ያየሁት።ሰው የመንግስት ሰራተኛ በመሆኑ የሚሸማቀቅበት፣ ድምቅ ያለ ነገር የማይታይበት፤ ጉስቁልና ያለበለትም ነው ።
አዲስ ዘመን፦ ይህ እንዲሆን ያደረገው ምንድን ነው?
ኮሚሽነር በዛብህ፦ በመጀመሪያ ሲቪል ሰርቪሱ ራሱ ነገሮችን ለራሱ ከልክሎ ነው ያለው፤ የሚገርመው ነገር ጥቅሙንም ቢሆን የሚመችንም የስራ አካባቢ በመፍጠረም በኩል መሆን ያለበትን እንኳን እየሆነ አይደለም።“ እኔ ኮሚሽነሩ እንኳን አንድ ነገር እናድርግ “ ብዬ ሀሳብ ሳነሳ “አይሆንም “ ነው የሚሉት “ለምን? “ ብዬ ስጠይቅ ህጉ አይፈቅድም ይላሉ፤
ህጉን ማነው ያወጣው”ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው?” ብዬ እጠይቃለሁ፤ ምክንያቱም በዛ ደረጃ የወጣ ከሆነ ለመንቀልም ለመትከልም አስቸጋሪ እንደሚሆን ስለሚገባኝ፤ ግን አይደለም ማነው ብለሽ በደንብ ስትጠይቂ ይህንን እያሉ ያሉት ሰዎች እራሳቸው ናቸው የጻፏቸው።የፈረሙት ደግሞ ከሚኒስቴርና ሚኒስትር ዴኤታዎች ጀምሮ እስከ ዳይሬክተር ድረስ ያሉት ናቸው።
እሺ ይህም ይሁን “አምጧቸውና እንወያይባቸው” ብዬ ስጠይቅ አይፈቅድም የተባለውን ህግ ቁጭ ያደረገልኝ ሰው አላገኘሁም።አሁን የምነግርሽ ኮሚሽኑ ውስጥ ያለውን ብቻ ነው ፤ሁሉንም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እና ሲቪል ሰርቫንቱን እንይ ብንል ችግሩ ሰፊ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ ግን በውስጡ ያለውን የመንግስት አሰራር ማሳያም ከመሆኑ አንጻር እርስዎ ከነበረበት ተነስተው ምን ለመስራት እቅዱ የቱስ ተሳካልዎት?
ኮሚሽነር በዛብህ፦ የመንግስት ቢሮክራሲ ሪብራንድ መሆን አለበት የሚል ሀሳብ ይዤ ነው የመጣሁት፤ ለውጡ ከሚሄድበት ፍጥነትና ካለው ፍላጎት ጋር በሚመጣጠን መልኩ እንዲለወጥ ለማድረግ ነው ሳስብ የነበረው።በተለይም ሲቪል ሰርቪሱ ከገባበት ማጥ ሊወጣ የሚችልበትን መንገድ ወደማየት ነው የሄድኩት።
አዲስ ዘመን፦ መሰረታዊ ለውጥ የሚያስፈልገው አካባቢ ከሆነ ግን ለውጡ የት ላይስ ነው ማረፍ ያለበት ይላሉ?
ኮሚሽነር በዛብህ፦ የመጀመሪያው በሲቪል ሰርቪሱ ላይ ያለውን ድህነት የወረሰውን አስተሳሰብ መቀየር ይገባል፤ ይህ አስተሳሰብ አስከፊ የሚያደርገው ደግሞ የራሱን አካባቢ ምቹ አለማድረጉ ላይ ነው።ለምሳሌ የስራ አካባቢ ምቹ ይሁን ሲባል ይኸው አብሮ የኖረ ቢሮክራሲ ከመቀየር ይልቅ በጀት በፈቀደለት ልክ ቢሮዎችን ቀለም መቀባት ወንበርና ጠረዼዛን መቀየር ላይ ነው ትኩረቱ፤ ግን በተቀየሩት ቢሮዎች ውስጥ ተቀምጦ የሚሰራው ሀይል አሁንም ድህነት የወለደውን ሀሳብ ነው የሚያራምደው። ስለዚህ ሲቪል ሰርቫንቱ ሪብራንድ ይሁን የሚል የሪፎርም አቅጣጫዎችን የሚያመላክቱ ዝርዝር ፍልስፍናዎችን አውጥተን ለሁሉም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ፣ ለኮሚሽኖችና ኤጀንሲዎች በመበተን አመራሩ የሪፎርም ስራውን በዚህ መልኩ እንዲቃኝ እየተደረገ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ የሪፎርሙ ይዘት ምንድን ነው?
ኮሚሽነር በዛብህ፦ ይዘቱ የምንለውጠውን ነገር ሁሉ ሀሳብን ከመለወጥ ወይም ከተለወጠ ሀሳብ በሚመነጭ አዳዲስ ሀሳብ እንመስርት፤ እንደከዚህ ቀደሙ አንድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ላይ ተጽፈው አካሄዳቸው (ፕሮሲጀራቸው ) ተቀምጦ የሚፈጸሙ፣ የጊዜ ገደብ ተቀምጦላቸው የሚተገበሩ የሪፎርም ፕሮግራሞች መኖር የለባቸውም የሚል ነው።ስለዚህ የጤና ሚኒስቴር ሪፎርም ማድረግ አለበት ወይ? አዎ፤ ለምን የነበረው አካሄድ ለውጡን የሚመጥን ባለመሆኑ እናም ሪፎርሙን ከአዲስ ሀሳብ ይጀመር።
ቀጣዩ ወደ ግለሰቦች በሚወርድ ልክ መግባባትን በሀሳቡ ላይ መፍጠር፤ ምክንያቱም ይህ የሲቪል ሰርቪሱ አካሄድ በጣም የተጎሳቆለ፣ ለራሱ በሚሆን ነገር ላይ እንኳን የጻፋቸው ህጎችና ሊመራበት የሄደው ፍልስፍና ጉዳት ያለው መንግስትም ያልከለከለው ነው።መንግስት በጀት በጅቶ ያስቀመጠውን እንኳን በደንብ አያይዞ እየተጠቀመ ዜጋን የሚጠቅም ስራ መስራት ያልቻለ በመሆኑ እዚህ ላይ መግባባት ሳይቻል ስለ ለውጥ ማሰብ ከባድ ነው።በመሆኑም የለውጥ ስራ እሰራለሁ የሚል ሁሉ ሀሳብ በማምጣትና ብዙዎች ጋር በመግባባት ወደ ሰው ማውረድ ይገባል ።ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ ለውጡን ተቋማዊ የማድረግ ስራው ይቀጥላል።ተቋማቱም የለውጥ ስራቸውን በዚህ መልኩ እንዲቀጥሉ አሳይተናል።
አዲስ ዘመን፦ የእርስዎ ኮሚሽንስ በዚህ ሁኔታ ላይ ምን ማድረግ ነው ያለበት ሌሎችን በመርዳትና ራሱንም ወደለውጥ ለማስገባት?
ኮሚሽነር በዛብህ ፦ አዎ ኮሚሽኑም ሪብራንድ መሆን አለበት የሚል እምነት አለኝ።ኮሚሽኑም ይህንን ስሌት ተከትሎ መስራት አለበት። የኮሚሽኑ ትልቁ ሀሳብ የሲቪል ሰርቪሱን አካሄድ መምራት ነው፤ይህን መነሻ የሚያደርገው ደግሞ በሰው ሃብት ላይ መሰረታዊ የሆነ ለውጥ ኖሮ ብራንድ ለማድረግ መስራት ነው።እዚህ ላይ ሲቪል ሰርቪሱን ሪብራንድ እናደርገዋለን ስንል የትኛውን ብራንዱ ነው? ለመሆኑ ብራንድ የሚባል ነገርስ አለው እንዴ? የሚሉ አሉ ግን የማይታይ የተደበቀ ብራንድ አለው።
አዲስ ዘመን፦ አንባቢዎቻችንም ይረዱን ዘንድ እርስዎ ኮሚሽኑ የተደበቀ ብራንድ አለው ካሉ ምንድነው ብራንዱ? እንዴትስ ነው ሪ-ብራንድ ማድረግ የሚቻለው?
ኮሚሽነር በዛብህ፦ አዎ የተደበቁት ብራንዶቹ ያሉት።እነሱም ነገረኛ ከልካይ ፣ ምንም ነገር የማይደግፉ ግን ደግሞ በቀጠሮ ሰውን የሚያጉላሉ ፣ ለምሳሌ በአስተዳደራዊ ሂደታቸው ሶስት ዓመት ደመወዝ ሲበላ የነበረን ሰው አሁን ደመወዙ ይቁምና ከመደቡ ተነስቶ ሌላ ቦታ ይመደብ የሚሉ ህጎች ናቸው። እንዲህ እያልን ብንገልጸው በሁሉም በኩል በችግር የተሞሉና በክልከላ የታጨቁ መፍትሔ የማያመላክቱ የማያምር ብራንድ ነው ያለን። ኮሚሽኑ ምንም የፈታው ችግር ስለሌለ ዜጋውም ሆነ ሚኒስትሮች አይወዱትም። ለምሳሌ አንድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ተልዕኮውን ለመፈጸም የሚረዳውን የስራ መደብ ለመፍጠር ፍቃድ ይጠይቀዋል፤ ፍቃድ ተጠያቂው ደግሞ ምንድነው ተልዕኮው? ለምንድን ነው እኚህ ሚኒስቴር ያልቻሉት ይህንን ለመፈጸም የሚለውን ሳያይ ወደ ክልከላ ይገባል።
አዲስ ዘመን፦ ኮሚሽኑ የሚገርም ብራንድ ነው ያለው እና እንዴት ነው የሚቀየረው?
ኮሚሽነር በዛብህ፦ ይህንን ለመቀየር የተለያዩ ዘዴዎችን ነድፈናል። የመጀመሪያው ሰው በአስተሳሰቡ ሊቀየር ይገባል፤ ኮሚሽኑ ራሱን ከፖለቲካዊ አመለካከቶች ነጻና ገለልተኛ ማድረግ ፤ ስልጣን ላይ ያለውን ብቻ ሳይሆን በየትኛውም ጊዜ የሚመጣን መንግስት ማገልገል የሚችልበትን ስርዓት እየፈጠረ መሄድና መቃኘት እንዲሁም የሚመራቸው ተቋማት ላይ ይህ ነገር መንጸ ባረቅ አለበት ነው።
ሁለተኛው በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ዜጎችን የሚያከብር በጥቅማቸው ዙሪያ በፍጹም በአሉታዊ መልኩ የማይደራደር አሰራር ሊኖረን ይገባል። ሶስተኛው ሰዎች ለሚሰሩት ስራ ብቃት ያላቸው መሆኑን ማረጋገጥ አለበት።ምክንያቱም እነዚህ ሁኔታዎች የአገሪቱን የሲቪል ሰርቪስ አሰራር እየተፈታተኑ ያሉ በመሆኑ ።
አዲስ ዘመን ፦ የስራ ምዘናና ደረጃ ምደባ (ለእኩል ስራ እኩል ክፍያ )የሚል ፕሮጀክት በሲቪል ሰርቪስ ውስጥ ተጀምሮ ነበርና አሁን ላይ ተጠናቋል? ወጤቱስ ምን አመላክቷል?
ኮሚሽነር በዛብህ ፦ አዎ አልቋል ማለት የመንግስት መስሪያ ቤቶች ደረጃዎች አንድ እንዲሆኑ ሆኗል፤ በዚህም ከ150 ስኬል ወደ አንድ ስኬል ማምጣት ተችሏል።ይህ ስኬት ከአፍሪካም የተደነቀ ነው። ግን ይህ ብቻ በቂ ስላልሆነ ብቃት ያላቸው ሰዎች በስራ መደቦቹ ላይም መመደብ መቻልን ይጠይቃል። የብቃትን ነገር ለማሟላት ደግሞ ብቃት ማረጋገጫ ፕሮጀክት ተብሎ በመንግስት በኩል የተቀረጸ አለ፤ ከፊታችን ሚያዚያ ወር 2012 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ተግባር በማስገባት ማንም ሰው ወደ ሲቪል ሰርቪሱ ፈተና ሳይፈተንና ብቃቱ ሳይረጋገጥ እንዳይገባ ይደረጋል።
አዲስ ዘመን፦ አዲስ የሚቀጠሩትስ ተፈትነው አልፈው ብቃታቸው ተረጋግጦ ገቡ፤ ነባሮቹስ ምንድን ነው የሚደረጉት? እንዴትስ ተወዳዳሪ መሆን ይችላሉ ?
ኮሚሽነር በዛብህ፦ ፕሮጀክቱ ለአንድ የስራ መደብ የሚያስፈልገውን ብቃት ያስቀምጣል ፤ይህም ሲባል ስራን የመቻልን ጥያቄ ነው የሚያቀርበው፤ በዚህ
ውስጥ ደግሞ አንድ ሰራተኛ ለስራ መደቡ ሲታጭ እንግሊዝኛ ፈረንሳይኛ ወይም ሌሎች ቋንቋዎችን መቻል አለበት ፣ የሚል ማስታወቂያ ከወጣ ይችላል ወይ ብሎ መፈተን ሳይሆን ማስቻልን መሰረት አድርጎ ነው የሚሰራው ብቃት ማለትም ይህ ስለሆነ፤ ይህ የማስልጠኛ ወይም የመማሪያ ጊዜ ወደ ስራ ከተገባ በኋላ ግን ችሎ የገባ ሰው ብቻ አሸንፎ የሚወጣበት ሜዳ ነው የሚሆነው።
አዲስ ዘመን፦ ይህንን የብቃት ማረጋገጫ ስልጠናም ይሁን ፈተና ተቋማት ራሳቸው ናቸው የሚያደርጉት ወይስ ኮሚሽኑ ነው?
ኮሚሽነር በዛብህ፦ ለስልጠናውም ሆነ ፈተናው ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ተመርጧል፤ ስለዚህ የፌዴራል የብቃት ማዕከል ይሆናል ማለት ነው።በሌላም በኩል እሱን የሚመጥኑና በእሱ ደረጃ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎችም በሂደት ወደ ስራው የሚገቡበት ሁኔታ ይመቻቻል።በዚህ ሁኔታ በመንግስት ስራ ላይ ያሉትን ሁሉ ብቃታቸውን እያረጋገጠና ሰርተፍኬት እየሰጠን ወደ ስራ እንመልሳቸዋለን።ይህ ሲሆን ደግሞ የአቅም ግንባታ እቅዳችን በተጨባጭ ነገር ላይ የተመሰረተ ይሆናል።
አዲስ ዘመን ፦ እዚህ ላይ ግን ሁሉም ሰው ስልጠናውን ወስዶ የሚቀጠር ከሆነ ወደፊት በመንግስት መስሪያ ቤት ለመቀጠር የስራ ልምድ አያስፈልግም ማለት ነው ?
ኮሚሽነር በዛብህ፦ የመጀመሪያ ዲግሪና ስምንት ዓመት የስራ ልምድ የሚለው ጨዋታ ያበቃል ፤ ይህ ሲባል ደግሞ ሙሉ በሙሉ የስራ ልምድ አያስፈልግም ማለት አይደለም። ግን ልምዱን ይዞ እንኳን ቢገባ ስራውን ይችላል ወይ? የሚለውን ለማየት ወደ ሲቪል ሰርቪስ ማዕከል ገብቶ ችሎ እንዲወጡ ይደረጋል።
አዲስ ዘመን፦ ሰው ስራ ተቀጥሬያለሁ ካለ በኋላ ወዲያው ወደአእምሮው የሚመጣው የደመወዝ ቀን ነውና ፤ ስልጠናውን እስከሚጨርስ ደመወዝ አይታሰብም ማለት ነው?
ኮሚሽነር በዛብህ፦ አይ አይደለም፤ አንድ ሰው ስልጠናውን ወስዶና ተፈትኖ የሚመደብበትን ስራ ችሎ እስኪወጣ ድረስ ደመወዝ ይከፈላል ።
አዲስ ዘመን፦ ምናልባት አንድ ሰው በታሰበው ጊዜ ብቁ መሆን ካልቻለ መንግስትን ለተጨማሪ ወጪና ለጊዜ ብክነት አይዳርገውም ?
ኮሚሽነር በዛብህ፦ ረጅም ጊዜና ብዙ ገንዘብ ሊወስድ ይችላል፤ ግን የመንግስት ቀጣሪነትን እየቀነሰ የግል ባለሀብቱ አቅም እየሰፋ ሰዎች በመክፈል አቅሙ ውስን የሆነ የመንግስት አካል ከሚቀጥራቸው ባገኘው ትርፍ ልክ ወደሚቀጥራቸው እንዲሄዱ ሁኔታው ያበረታታል። ምን ማለት ነው ስልጠናውን ወስደው በራሳቸው የሚተማመኑ ባለሙያዎች በሆኑ ልክ የተፈላጊነት መጠናቸው ይጨምራል።
አዲስ ዘመን፦ አሁን ከተጀመረው የለውጥ መንገድ አንጻር ግን ሲቪል ሰርቪሱ ምን መምሰል አለበት ይላሉ?
ኮሚሽነር በዛብህ፦ የቀድሞው ኢህአዴግ አሁን ብልጽግና ፓርቲ ሆኗል ፤ ይህ ደግሞ ገና ከጅምሩ ብልጽግናን እያመላከተ መሆኑን ያሳያል። በመሆኑም ብልጽግናን ሊያመጡ የሚችሉ ዓለም ላይ ያሉ እውቀቶችን ሁሉ በስራው ውስጥ ፍልስፍና ያደረገ ሲቪል ሰርቪስ ደግሞ የግድ ነው።ስለዚህ ልማት የሚፈልግ ሲቪል ሰርቪስ ከመጀመሪያውም በጣም የተመጠነና ቆንጆ መሆን አለበት። ይህንን ከፈለግን ደግሞ እኛ የማንሰራቸውን ስራዎች ፍልስፍናው ለገባው እየተውን መውጣት አለብን።
ይህ ሲሆን የመንግስት ስራ የቢዝነስ ስራ እየሆነ ስለሚመጣና ሁኔታው የሚፈልገው እውቀት የሌለው ሰው ደግሞ ስለማይገባበት “አላዋቂ ሳሚ” ከመሆንም እንድናለን ማለት ነው።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የምንሰራበትን ሂደት (ሲስተም ) ላይ ስንመጣ ሁሉንም ማዘመን የሚለውን እንይዛለን ፤ ከዚህ ቀደም የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መጠቀም መቻል መዘመን ነበር፤ አሁን ግን ያ አይደለም እሳቤው። አንድ ሰው ጉዳይ ኖሮት ለምንድን ነው ወደ መንግስት መስሪያ ቤት እንዲመላለስ የሚሆነው? ለምን ባለበት ቦታ ጉዳዩን ማስፈጸም አይችልም? ሌላው ኮሚሽኑ ራሱ ከአሁን ቀደም ይሄድበት የነበረው የቁጥጥር አካሄድ አስተማሪ ወይም ችግር ፈቺ ከመሆን ይልቅ ከልካይ ስለነበር እሱን ማስተካል ላይ እየሰራን ነው፤ስለዚህ ኮሚሽኑ ሊፈቅድ የስራ አካባቢን ምቹ ሊያደርግ እንደመቋቋሙ ያንን ተግባሩን ይወጣ ዘንድ ማድረግ ማሳወቅ ነው የሚጠበቅበት ፤ ስለዚህ አሁን ያሰብነው እንደ ኮሚሽን የሰው ሀብቱ ላይ እንዳይጣሱ ከለላ ሊደረግላቸው የሚገቡ ህጎችን ማሳወቅና በዛ መሰረት መሄድ ፤ ከዛ ደግሞ የትኛው ነው ቁጥጥር የሚያስፈልገው የሚለውን ግልጽ ማድረግ የመቆጣጠሪያ መስፈርቶቹን ለምንቆጣጠራቸው አካላት ማሳወቅ ነው የሚጠበቅበት።
አዲስ ዘመን፦ኮሚሽኑ አሁን ከላይ በተ ቀመጠው ራስን የማዘመን መንገድ ተጠቅሞ ተቋማትን መመዘን ጀምሯል ?
ኮሚሽነር በዛብህ፦ አሁን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አካሄድ እንመዝናለን ብለን አምስት ተቋማት ላይ መረጃዎችን (ዳታዎችን) በመጫንና ከተቋሙ ቋት ጋር የማገናኘት ስራ ጀምረናል።የኮሚሽኑ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት አብዛኛው ስራው የዳኝነት ነበር፤ ይህ ከሚሆን ይልቅ ቅሬታ አቅራቢዎች በአስተዳደር ፍርድ ቤቱ እንዲታገዙና ችግሮች በተቋማት በራሳቸው እንዲፈቱ ግፊት እናደርጋለን። በሂደት ተቋማት ዘመኑ የሚጠይቀውን ይዘት ይይዛሉ ብለን እናስባለን።
አዲስ ዘመን ፦ ህዝብን እያስለቀሰ ባለው አገልግሎት አሰጣጥ ላይስ እንደው ምን ዓይነት እርምጃ መወሰድ አለበት ? ሲቪል ሰርቫንቱስ እንዴት ነው የአገልጋይነት ስሜትን ሊላበስ የሚችለው?
ኮሚሽነር በዛብህ፦ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋለው ሁኔታ እጅግ የሚያስፈራ ነው፤ አሁን የምርጫ ጉዞ ላይ ነን። ግን የቀረቡትን አገልግሎቶች እንኳን በአግባቡ ባለመስጠት ምርጫውን ለማደናቀፍ የሚሰሩ አካላት ይኖራሉ ።ይህ ደግሞ ለአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ትልቅ ችግር ነው።በመሆኑም አገልግሎት አሰጣጥ ትኩረት ሊያገኝ ይገባል በማለት ከሰላም ሚኒስቴር ጋር አንድ የንቅናቄ መድረክ ለማድረግ ተዘጋጅተናል።
በሌላ በኩል እያንዳንዱ መስሪያ ቤት የአገልግሎት አሰጣጥ ካውንስል እንዲኖረው ያስፈልጋል ። ኮሚሽኑ እንደ ኢ-ሰርቪሲንግ ፣የአንድ መስኮት አገልግሎት ፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ባህልና ሌሎችን ስራውን ቀልጣፋ ሊያደርጉ የሚችሉ አሰራሮችን ለይቷል ። ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ላይ ያሉ ባለሙያዎችም ጥሩ አደርገው አዘጋጅተዋቸዋል በቀጣይ አገልግሎት ሰጪው ስልጠና እንዲያገኝ ይደረጋል።
አዲስ ዘመን፦ አገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን የሚሰራው ስራ በጀት ተይዞለታል? ምክንያቱም አንዳንድ ስራዎች ይታሰባሉ እንጂ ወደ ተግባር ሊገባ ሲል የገንዘብ ችግር ያጋጥማቸዋል ?
ኮሚሽነር በዛብህ ፦ ኮሚሽኑ ለመስሪያ ቤቶቹ የበጀት ድጋፍ ያደርጋል።
አዲስ ዘመን ፦ ከራሱ በጀት ቀንሶ ማለት ነው?
ኮሚሽነር በዛብህ፦ አይ አይደለም።ፕሮጀክት እንሰራለን። አሁን እንኳን በሰራነው ፕሮጀክት አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊየን ፓውንድ ተገኝቷል ።ይህንን ገንዘብ አገልግሎት ሰጪ ተቋሙ ሰራተኞቹን ወደ ስልጠና ከመላክ ባሻገር አሁን ብቁ ናቸው እኔም ስራውን እሰራለሁ ቀጣይነቱንም አረጋግጣለሁ የሚል ስምምነት ተፈራርሞ የሚሰጥ ገንዘብ ነው። በዚህ ገንዘብ ውጤት ካመጡ በኋላም በቀጣይ በጀት ያስይዛሉ ።ይህ ደግሞ ዘርፉን በደንብ ሊያሻሽለው ይችላል።
አዲስ ዘመን፦ ከላይ በተለይም የሲቪል ሰርቫንቱን መረጃ የምንይዝበትን መንገድ ማዘመን (ኢስሚስ) ተግባራዊ እያደረግን ነው ብለውኝ ነበርና ስለእሱ ትንሽ ይንገሩኝ?
ኮሚሽነር በዛብህ፦ የአንድ የመንግስት ሰራተኛ መረጃዎች ሲደራጅ በፋይሉ ውስጥ ታጭቀው ያሉ ነገሮች ሁሉ ለሰውየውም ለመስሪያ ቤቱም ምንም የሚያስፈልጉ አይደሉም።መሰረታዊ የሰራተኛ ወይም የሲቪል ሰርቪስ መረጃ የሚባለው ከሶስት ገጽ አይበልጥም ፤እነሱን ደግሞ ዲጂታላይዝድ ማድረግ ነው ኢስሚስ።
አሁን በፌዴራል ደረጃ 13 መስሪያ ቤቶች ጥሩ ደረጃ ላይ ደርሰዋል። እነዚህ ተቋማት ከዚህ በኋላ ከኮሚሽኑ ጋር በሚኖራቸው ጉዳይ ወረቀቶችን አይላላኩም ። ይህ አሰራርም ልዩ ድጋፍ ከሚሹ ክልሎች ውጪ በሁሉም ተጀምሯል። እዚህ ላይ ግን 240 የፌዴራል መስሪያ ቤቶች እያሉን 13 ብቻ ወደ ስራው መግባታቸው አፈጻጸማችን ደካማ እንደሆነ ያሳያል ። ነገር ግን ተቋማቱ በውጤቱ ላይ ያላቸው አፈጻጸም ደካማ ይሁን እንጂ አካሄዱ ላይ የተፈጠረው መግባባት ጥሩና ብሩህ ነገር የሚያሳይ ነው።
አዲስ ዘመን፦ ብዙ ተቋማት አደረጃጀታቸውን ለማሻሻል የተለያዩ ጥናቶችን አጥንተው ወደ እናንተ ኮሚሽን ሲልኩ ምላሽ ለማግኘት ብዙ ጊዜ ለመጠበቅ ይገደዳሉ ፤በእዚህስ ላይ ምን አስባችኋል?
ኮሚሽነር በዛብህ፦ አደረጃጀት የሚለው ክፍላችን በፊት የሚሰራው ስራ አንድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት አደረጃጀቴን ቀይሬያለሁ ብሎ ሲልክ ድሮ ሲሰራቸው የነበሩ ስራዎችን አውጥቶ በደፈናው አይገባህም ወይም ይገባሃል ይል ነበር። ይህ ደግም ከፍተኛ የሆነ ጭቅጭቅ ሲፈጥር ነው ቆይቷል። ይህንን አሰራር ላለመቀጠል ከሶስተኛው ሩብ ዓመት ጀምሮ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶቹን ክላስተር እናደርጋለን። አደረጃጀታቸውን ኮሚሽኑ ይሰራል፤ የስራ መደቡና ደረጃው ሲያስቀምጥ ደመወዙንም አብሮ ተክሎ ለገንዘብ ሚኒስቴር ይላካል፤ በዚህ ደረጃ (ስታንዳርድ) መሰረት በዛ ክላስተር ስር ያሉ ሁሉ በቀላሉ የተቋማቸውን አደረጃጀት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰርተው ያጠናቅቃሉ ማለት ነው።
አዲስ ዘመን ፦ግን አንድ ተቋም በምን ያህል ጊዜ ነው አደረጃጀት መስራት ያለበት? አንዳንዴ ፋሽን በሚመስል ሁኔታ ሁሉም ትኩረታቸውን አደረጃጀት መቀየር ላይ ስለሚያደርጉ ?
ኮሚሽነር በዛብህ፦ ይህ በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው። ኮሚሽኑም ሊቆጣጠር የሚገባውም ይህንን ነበር። በእርግጥ አደረጃጀት ቋሚ ሊሆን አይችልም ፤ በተፈለገ ጊዜ ሁሉ ይሰራ ብሎ የሚፈቅድ ህግ ደግሞ የለም። የመንግስት ሲሆን ደግሞ ምክንያታዊ ጊዜያት አሉ።
አዲስ ዘመን ፦ ጠቅለል አድርገን ስናየው ግን ከለውጡ በኋላ ያለው የሲቪል ሰርቪስ ተቋማት መሻሻልን እንዴት ይገልጹታል?
ኮሚሽነር በዛብህ፦ አሁን ላይ ያለው ነገር ብዙ ተጉዟል ባይባልም ጥሩ ሁኔታ ይታያል።ከ 20 ፌዴራል ተቋማት አምስት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ስራዎች ተመዘኑ ደረጃ ወጣላቸው ወደ ደመወዝ ደረጃ ሽግግር ሄዱ ግን ይህንን ስራ አጠናቀው ያልጨረሱ መስሪያ ቤቶች አሉ።ከዚህ አንጻር ኮሚሽኑም ደብዳቤ ጽፏል። ክልል ላይ ስንሄድ ከ ሶስት ክልልች በቀር ሌሎቹ ይሄነው በጀታችን ብለው ለገንዘብ ሚኒስቴር አቅርበው ተጨማሪ ገንዘብን መውሰድ ላይ እግራቸውን እየጎተቱ ነው። በዚህ ላይም ለክልል ርዕሰ መስተዳድሮች ደብዳቤ ጽፈናል። አገልግሎት አሰጣጥ ላይ በሁሉም ተቋምት ንቅናቄ ነው የምንጀምረው ስላልን ያለንበት ነገር ጥሩ አይደለም።
በጠቅላለው ስናየው የመንግስት ተቋምት ያሉበት ሁኔታ በጣም መስራት የሚጠይቅ እንጂ በጥሩ የለውጥ ሂደት ላይ ነው ለማለት ያስቸግራል።
አዲስ ዘመን፦ የነጥብ ምዘና ጄ ኢ ጂ ለአንዳ ንዶች ምቾት አልሰጠምና ይህ ለምን ሆነ ?
ኮሚሽነር በዛብህ፦ የ150 ስኬል ምስጢር የመንግስትን ውጤታማ ያለመሆን መገለጫ ነው።በነገራችን ላይ መንግስት በየትኛውም ዓለም ስኬታማ አይደለም። ግን ይህ ስኬል እንደዚህ ለመ ብዛቱ ዋናው ምክንያት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ቅርብ ከመሆንና እዛም ያለን ወሳኝ ሰው በእጅ ከማድረግ ጋር የተያያዘ ነው።በሌላ በኩል ደግሞ ልዩ ስኬል ይሉና ከውጪ ለስራው የሚመጥን ሰው እኛ በምንከፍለው ደመወዝ መሳብ አልቻልንም በሚል የሚሰሩት ነው።
አዲስ ዘመን፦ “በምንከፍለው ደመወዝ ባለሙያ መሳብ አልቻልንም” የሚለው አባባል ግን እውነታ የለውም ይላሉ? አሁን ላይስ የመንግስት ደመወዝ ሳቢ ነው ? ለማሻሻልስ የሚደረጉ ጥረቶች በምን ደረጃ ላይ ይገኛሉ?
ኮሚሽነር በዛብህ፦ በነገራችን ላይ በየትኛውም ዓለም የመንግስት ደመወዝ በመንግስት የመክፈል አቅም ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ሀብታም አገር ከሆነ ሀብታም መንግስት ይፈጠራል። ይህ ሲሆንም ጥሩ ደመወዝ ይከፈላል።ግን ጥሩ ደመወዝ በሚከፍሉ አገራት ደግሞ ሲቪል ሰርቪሱ የተመጠነና የመፈጸም ብቃቱም ላቅ ያለ ነው።
እኛ እንደ አገር አንድ ነጥብ ሰባት ሚሊየን የመንግስት ሰራተኛ አለን፤ በዚህ ውስጥ 20 ሰዎች 80 ሰዎችን የሚቀልቡ አለመሆናቸውን ማረጋገጥ በእጅጉ ይከብዳል።
አሁን ለመንግስት ቀርቦ የሚወሰንና አምስት ወይም ስድስት ነጥቦችን የያዘ የጥናት ውጤት በቅርቡ ይጠናቀቃል፤ በጥናቱም መንግስት ለዜጎች የስራ እድል እየፈጠረ መዝለቅ ይችላል ወይ? የሚለውን ይመልሳል። ምክንያቱም በጣም ሰፊ የስራ እድል በመንግስት መስሪያ ቤት ውስጥ ፈጥሮ በአንጻሩ ደግሞ የመክፈል አቅም ውስንነት እያለ ድሆችን የሚፈለፍል መንግስት መሆን ተገቢ አይደለም።
እነዚህ ደሃ የሆኑ ዜጎች ደግሞ ቅድም በምንለው አቅም በአስተሳሰብ በአገልግሎት አሰጣጥ የመንግስትን ፖሊሲ በመፈጸም በኩል ጠንካራ ካልሆኑ ሀብት ሊፈጥር የሚያነሳሳ ፖሊሲን ሊፈጥሩም አይችሉም።ስለዚህ መንግስት በተቻለ መጠን እራሱን መመጠንና ጥሩ ደመወዝ የሚከፈላቸው ጥሩ አፈጻጸም ያላቸውን ይዞ ነው መሄድ ያለበት።
አዲስ ዘመን፦ መንግስት የሰራተኛውን ቁጥር ይመጠን ሲባል ያባር ነው ወይስ ሌላ መንገድ ይኖረዋል?
ኮሚሽነር በዛብህ፦ እንደሱ ማለት አይደለም፤ አሁን ባለው ብቻ ነው የምቀጥለው ፤ ያለውንም በዚህ ደረጃ ቆንጆ መልክ አስይዤ እሰራለሁ የሚል አቅጣጫ ይዞ ራሱን ማሳነስ አለበት። መጠን ሲቀንስ ደግሞ ለብዙ ይፈስ የነበረውን በጀት ሰብሰብ አድርጎ መጠቀም ይችላል። መንግስት ነጻና ገለልተኛ የስራ አካባቢን ነው የምፈልገው ካለ ሊወስንባቸው የሚገቡ ነጥቦች አሉ።እነዚህን ከወሰነ በኋላ ሌላው ነገር ቀላል ይሆናል ።
አዲስ ዘመን ፦ እርስዎ የሚመሩት ኮሚሽን ራሱን አደራጅቶና ነጻና ገለልተኛ አድርጎ ሌላውንም በማገዝ በኩል በቀጣዮቹ ጊዜያት ምን አቀደ?
ኮሚሽነር በዛብህ፦ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ አሁን በጀመርናቸው ሀሳቦች መነሻነትና በጥናት ሁሉም ነገሮች እየተነካኩ በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ በጣም የተመጠነና ቆንጆ እንዲሁም ነጻና ገለልተኛ ይሆናል ብዬ አስባለሁ።ነጻና ገለልተኝነት ሲባል አንድ ፓርቲ ወደ መንግስትነት ከመጣ በኋላ የሚያወጣቸውን ፖሊሲዎች አይፈጽምም ማለት ሳይሆን ሙያዊ አገልግሎት ይሰጣል።ይህ ማለት ምን ማለት መሰለሽ መንግስት የሆነ ነገር ሲያደርግ “አይ ይህማ መሆን የለበትም ምክንያቱም ህገ መንግስቱ ለዜጋው የሰጠውን መብት የሚያጓድል ነው” የሚል ይሁን ነው።
ዜጎች በኑሯቸው የተመቻቸው መሆን ከፈለጉ የመንግስት ሰራተኛ መሆን የለባቸውም፤ ይህ የእኔ ምክር ነው።በቀጣይ ኢኮኖሚውም በደንብ ያድግና የግል ተቋሙም በጥሩ ደመወዝ ሰራተኛን ይቀጥራል ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
ኮሚሽነር በዛብህ፦ እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 4/2012
እፀገነት አክሊሉ