ሊዲያ ተስፋዬ፤ ሀና ጥላሁን፤ ሚዳ ገባሳ፤ መስታወት ቦጋለ እና ከድጃ አሊ ይባላሉ። የጂማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ናቸው። ምስጋና ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ይሁንና የሀገራችን እንስቶች፤ እናቶችን በወሊድ ጊዜ ለሞት ሊዳርጉ የሚችሉ ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችል ዲጅታል መሳሪያ ሰርተዋል:: እነዚህ ወጣቶች የእናቶቻቸውን ችግር ለመቅረፍ በማሰብ ባደረጉት ጥናትና ምርምር ያገኙት ውጤት አበረታችና ይበል የሚያስኝ ነው፡፡
ዛሬ በሳይንስ አምዳችን በህክምናው ዘርፍ ብቅ ያሉትን ታታሪ እንስቶች አነጋግረን ስለ ፈጠራቸውና የምርምር ስራቸው ያዘጋጀነውን ይዘን ቀርበናል። መልካም ንባብ፤
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ሜዲካል ኢንጂነሪንግ ተማሪ የነበሩት እነዚህ አምስት እንስቶች በሀገራችን የህክምና ተቋማት ነፍሰ ጡር እናቶች የመውለጃ ጊዜያቸው ሲያልፍና ምጣቸው ሳይመጣ፤ ወይም በቂ የመግፋት አቅም ሳይኖራቸው ሲቀር በእጅ ወይም በማንዋል ይሰጣቸው የነበረውን ህክምና፤ ዘመናዊ በማድረግ በቀላሉ ህክምናው የሚሰጥበትን መላ መዘየድ ችለዋል፡፡
የሀሳቡ አመንጪ የሆነችው ሊዲያ ተስፋዬ የመመረቂያ ፅሁፍቸውን ለመስራት በሚያስቡበት ጊዜ “አባቴ ሃኪም በመሆኑ የሚያጋጥመውን የእለት ተእለት ክስተት ስለሚነገረኝ በውስጤ ያደረውን ፍላጎት ለጓደኛቼ ነገርኳቸው” በማለት ጓደኞቿ በሀሳቧ ተስማምተው ወደ ፈጠራ ስራ እንደገቡ ትናገራለች፡፡
ሊዲያ፤ ጓደኞቿ ሁሉም ሴቶች በመሆናቸውና ችግሩ ከእናቶቻቸው ጀምሮ በቅርብ የሚያወቋቸው ሴቶች ላይ የሚያጋጥም በመሆኑ፤ ለጉዳዩ ቅርበት ስላላቸው በፈጠራ ስራው ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ እንዳገዛቸው ትገልጻለች፡፡
የፈጠራ ስራዎች
የእንስቶቹ የምርምርና የፈጠራ ስራ የእናቶች የምጥ መቆጣጠሪያ/Augmentation and induction monitoring device/ ሲሆን፤ በባለሙያዎቹ የተሰጠው “የኛ” የሚል ስያሜ ያለው ዲጅታል መሳሪያ ነው፡፡
የፈጠራ ስራውን ለየት የሚያደርገው
እናቶች በወሊድ ጊዜ የመውለጃ ጊዜያቸው ሲያልፍ፤ ምጣቸው ሲዘገይ ወይም በቂ የመግፋት አቅም ሳይኖራቸው ሲቀር በአብዛኛው በሀገራችን የሚገኙ የህክምና ተቋማት የሚሰጣቸው የምጥ ማምጫ መድኃኒት አለ፡፡ መድኃኒቱን ከወሰዱ በኋላም ምጥ መምጣት ያለመምጣቱን፤ የምጡ ግፊት ምን ያህል መጠን ላይ እንደደረሰ የሚያረጋግጡት በእጃቸው በመለካትና የመድኃኒቱን ጠበታ በመቁጠር ጭምር ነበር፡፡ እነዚህ ወጣቶች ደግሞ ይህንን አሰራር በማስቀረት ዲጅታል መሳሪያ ሰርተዋል፡፡
አዲሱ የእናቶች የምጥ መቆጣጠሪያ ወይም “የኛ” በሀገር ውስጥ የሌለ አዲስ መሳሪያ ሲሆን፤ ከውጭ ሀገር የሚመጣውም መሳሪያ የሚታሰር ቀበቶ ብቻ ያለው ነው፡፡ የኛን ለየት የሚያደርገው ግን የመድኃኒቱን ጠብታ እና የምጡን ግፊት አንድ ላይ እንዲቆጣጠር ተደርጎ የተሰራ መሆኑ ነው፡፡
የፈጠራ ስራው ጠቀሜታ
ዲጅታሉ የምጥ መቆጣጠሪያ መሳሪያ ሆድ ላይ የሚታሰር ቀበቶ ሲሆን፤ ሁለት ምልክት መስጫ ወይም ሴንሰሮችን አሉት፡፡ የመድኃኒቱ ጠብታ በ15 ሴኮንድ ምን ያህል ይወርዳል የሚለውን በመከታተልና ወደ ደቂቃ በመቀየር ስሌት ይሰራበታል። በእጅ ወይም በማኑዋል የሚደረገው ክትትል ህክምና ባለሙያው ቢሳሳት ወይም ከቁጥጥር ውጪ ቢሆን በእናትዬዋ ጤና ላይ ጉዳት ያስከትላል። ጉዳቱ ከከፋም ለማህፀን መሰንጠቅ ሊዳርጋት ይችላል፡፡
ይህ መሳሪያ ግን የምጡ ግፊት ያለበትን ደረጃ እያንዳንዱን መረጃ ለህክምና ባለሙያው በመስጠት እገዛ ያደርጋል፡፡ መድኃኒቱ ከአቅም በላይ የሚሰጥ ከሆነም እንዲያቆሙት ምልክት ያሳያል። በማኑዋል ክትትሉ አንድ እናት እስከትወልድ ድረስ የፈጀውን ያህል ሰዓት ቢፈጅም የህክምና ባለሙያው ከአጠገቧ መራቅ የለበትም፡፡ በአዲሱ ግኝት ሦስት፤ አራት እናቶችን በአንድ የህክምና ባለሙያ መከታተል ይቻላል፡፡
በመሆኑም፤ የህክምና መሳሪያ እንደመሆኑ መጠን ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያበቃውን ማረጋገጫ ለማግኘት ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር በሂደት ላይ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡
የፈጠራ ስራው ያስገኘው እውቅና ሽልማት
እነዚህ እንስቶች በስራዎቻቸው በርካታ ሽልማቶች ከጅማ ዩኒቨርሲቲ፤ ቢስ ጂማ ግራንት (BIC Jimma Grant) ፣ ሶልቪት (Solveit 2019) ፣ አሶሴሽን ፎር ዘ ፕሮሞሽን ኦፍ ሳይንስ ኢን አፍሪካ (APSA) 2018 እና አፍሪካን ሁኒየን ቤስት ፊፍቲ (Africa Union Best 50) በመውጣት የተለያዩ ሽልማቶችን ያገኙ ሲሆን፤ ከመሀከላቸው ሁለቱ የሁለተኛ ዲግሪ የትምህርት እድል /ስኮላርሺፕ/ አግኝተዋል፡፡
በ2011 ዓ.ም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ባዘጋጀው ሀገር አቀፍ የተመራማሪዎችና የፈጠራ ባለሙያዎች ውድድርም የእውቅና ሰርተፍኬትና የወርቅ ሜዳሊያ ሽልማት አግኝተዋል፡፡ በተጨማሪም በአፍሪካ የወጣቶች ውድድር ላይ /African challenge / የመጨረሻ ዙር ከደረሱ 11 ሀገሮች አንደኛ በመውጣት የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡
የፈጠራው ስራ ያጋጠሙ ፈተና
እንደሊዲያ ገለጻ በህክምና ዘርፍ የሚደርጉ የምርምርና የፈጠራ ስራዎች በጥንቃቄ የሚሰሩ በመሆናቸው ለስራው የሚያገለግሉት ቁሳቁሶች በሀገር ውስጥ ስለማይገኙ ከባድ ፈተና ነው፡፡ ለዚህ ስራቸው የተጠቀሙባቸው ቁሳቁሶች ከውጭ አገር የመጡ የዩኒቨርሲቲው መምህራን ባደረጉላቸው እገዛ የተገኙ መሆኑን ጠቁማለች።
ወጣቶቹ ሁሉም ተማሪዎች እንደ መሆናችን መጠን ለምርምር የሚሆን አቅም የላቸውም። በመሆኑም፤ የፋይናንስ ድጋፍ የሚያደርግልን አካል ያስፈልጋቸዋል። ለወደፊትም በእናቶችና በህጻናት ዙሪያ ትኩረት በማድረግ የሚሰሩት ፕሮጀክት ያላቸው በመሆኑ የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ የሚያበረታታና ድጋፍ የሚያደርግላቸው አካል እንደሚፈልጉና ቀና ሀሳብ ያለው እንዲተባበራቸው ጥሪ አቅርበዋል።
የእነዚህ እንስቶች የዛሬ የፈጠራ ውጤት ጥቅም እንዲውል ቢደረግ ለህክምናው ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል። ነገ ለሀገር መኩሪያ የሚሆኑ ናቸውና ህልማቸው እውን እንዲሆን ሊበረታቱና ሊደገፉ ይገባል እንላለን፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 2/2012
ወርቅነሽ ደምሰው