በጥልቅ ፍተሻ ለሃይል መቋረጥ መንስኤ የሆኑ ከባድና ቀላል ችግሮች ተለይተዋል

አዲስ አበባ፦ በጂፒኤስ ቴክኖሎጂ በመታገዝ በአዲስ አበባ ያሉ 152 የመካከለኛ መሥመሮች እና እነዚህን መሥመሮች የሚሸከሙ 59 ሺህ 48 ምሰሶዎች ላይ በተደረገ ጥልቅ ፍተሻ 25 ሺህ 973 ከባድና ቀላል የኃይል መቋረጥ መንስኤ የሆኑ የግኝት ነጥቦችን መለየቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኔትወርክና ኢንፍራስትራክቸር ዳይሬክተር አቶ ፈሪድ አብዱሰላም መሥሪያ ቤቱ የኃይል መቆራረጥን ለመቀነስ በክረምት የተደረጉ የዝግጅት ሥራዎች ዙሪያ አስመልክተው እንደተናገሩት፤ ባለፉት 100 ቀናት ለክረምት ወራት የኃይል መቆራረጥ ችግር እንዳይኖር አገልግሎቱ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል። በዚህም በጂፒኤስ ቴክኖሎጂ በመታገዝ በአዲስ አበባ ያሉ 152 የመካከለኛ መሥመሮች እና እነዚህን መሥመሮች የሚሸከሙ 59 ሺህ 48 ምሰሶዎች ላይ ጥልቅ ፍተሻ ተደርጓል። በፍተሻውም 25 ሺህ 973 ከባድና ቀላል የኃይል መቋረጥ መንስኤ የሆኑ የግኝት ነጥቦች ተለይተዋል።

ይህንንም የመለየት ሥራ የሠራው 144 የፍተሻ ቡድን ሲሆን የምርመራ ቡድኑ 1ሺህ 767 ኪሎ.ሜ ትር ያህል በእግር ተጉዟል ብለዋል።

ከ25ሺህ በላይ ከሆኑት ግኝቶች ውስጥ 7ሺህ 277 ቦታዎች የዛፎች ንክኪ ያለባቸው 6ሺህ 367 መቀየር የሚያስፈልጋቸው ምሰሶዎች፤ 2ሺህ 425 ከግንባታዎችና እርስ በእርሳቸው የተቀራረቡ መሥመሮች 16 ሺህ 298 የረገቡ እና የተለያዩ የመስመር ችግር ያለባቸው መሆናቸውንም አብራርተዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ከተገኙ ግኝቶች መካከል እስከ አሁን ለ14ሺህ 64 (56 በመቶ) አስፈላጊው ማስተካከያ መደረጉንም ጠቁመዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ወደ መሠረተ ልማት የተጠጉ 55 ሺህ 325 ዛፎች የተገኙ ሲሆን፤ 3ሺህ 734 የሚሆኑትን ማፅዳት ተችሏል፤ እንዲሁም አዲስ አበባ ላይ 7ሺህ 277 የሚሆኑ ዛፎች ወደ መሠረተ ልማቱ ተጠግተው የተገኙ ሲሆን፤ 5ሺህ 585 የሚሆኑትን ማፅዳት መቻሉንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

አቶ ፈሪድ ህብረተሰቡ መከተል የሚገባቸውን የጥንቃቄ መንገዶች ሲያብራሩ፤ ክረምቱን ተከትሎ የሚመጣ ኃይለኛ ነፋስ በሚነፍስበት ወቅት ከኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ርቀት በመጠበቅ እንዲንቀሳቀሱ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሚዩኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ አቶ አንዋር አብራር በበኩላቸው በጥናቱ መሠረት ለኃይል መቆራረጥ መንስኤ ከሆኑ ዋና ዋና ምክንያቶች 47 በመቶ የሚሸፍነው የዛፎች ንክኪ ሆኖ መገኘቱን ገልፀዋል።

በመሆኑም የተቀመጠውን ስታንዳርድ በማለፍ በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት በሶስት ሜትር ርቀት ውስጥ የነበሩ ዛፎችን በሀገር አቀፍ ደረጃ ቆረጣ መከናወኑን ተናግረዋል። ዛፎች በመቆረጣቸው እንደ አጠቃላይ በበጀት ዓመቱ ሊከሰት የሚችለውን የኃይል መቆራረጥ ድግግሞሽ በአዲስ አበባ በ15 በመቶ መቀነስ መቻሉንም ጠቁመዋል።

ተቋሙ ለኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ሲባል የተቆረጡ ዛፎችን መልሶ ለመተካት በክረምቱ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር 100 ሺህ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅቱን ማጠናቀቁንም አቶ አንዋር አስታውቀዋል። 100 ሺህ ችግኞችን ለመትከል የአንድ ችግኝ ዋጋ እና የአንድ ጉድጓድ ማስቆፈሪያ ግምታዊ ዋጋ 200 ብር በማውጣት በጥቅሉ 20 ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጉንም ተናግረዋል።

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You