“በመትከል ማንሰራራት!”

የኢትዮጵያ ማንሰራራት ማሳያ በሆነው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል እንዲሳተፍ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥሪ አቀረቡ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰሞኑን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ የዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር “በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ ቃል ይካሄዳል። የአረንጓዴ ዐሻራ እጅግ ዘርፈ ብዙ ትሩፋቶችን ያስገኘ ሥራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህ ዓመት ከሚተከለው ችግኝ ጋር ወደ 47 ነጥብ 5 ቢሊዮን ገደማ ይደርሳል፡፡

በዚህም በሚቀጥለው ዓመት ከሚተከለው ጋር ሲደመር 54 ቢሊዮን ሊደርስ እንደሚችል ጠቁመው፤ በዚህ መርሐ ግብር ያመናችሁ፣ የተሳተፋችሁ እጆቻችሁ ጭቃ የነካ፤ የተከላችሁ፤ የተንከባከባችሁ ኢትዮጵያውያን፣ በኢትዮጵያ የምትገኙ ዲፕሎማቶች፣ ይህንን ሕልም የደገፋችሁ የየትኛውም ሀገር ዜጎች በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ እንኳን ደስ ያለን ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በየዕለቱ የኢትዮጵያ ማንሰራራት ማሳያ በሆነው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍልና የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ እንዲሳተፍ ጥሪዬን አቀርባለሁ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉለሌ የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክት የችግኝ መትከል መርሐ ግብር ያካሄዱ ሲሆን፤ “በመትከል ማንሰራራት” በሚል ሃሳብ የሚካሄደው የዘንድሮ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር አካል በሆነው በዚህ የችግኝ ተከላ ሥነ ሥርዓት ላይ የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዚዳንት ካሺም ሼቲማ ተሳትፈዋል። በተጨማሪም የፌዴራል እና ክልል ከፍተኛ አመራሮች በችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ መሳተፋቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መረጃ አመልክቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዚዳንት ካሺም ሼቲማ፣ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ልማት የችግኝ የተከላ መርሐ ግብር መካሄዱ ይታወቃል። በመርሐ ግብሩ ላይ የተሳተፉ ሚኒስትሮች እንደገለጹት፥ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ኢኮኖሚው እንዲያንሰራራ የተያዙ ግቦችን ለማሳካት ጉልህ አስተዋፅዖ እያበረከተ ነው። የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ለቀጣዩ ትውልድ የተበረከተ ስጦታ መሆኑን ጠቁመው መርሐ ግብሩ ተጨባጭ ውጤቶች እየተገኙበት መሆኑንም አንስተዋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ባለፉት 6 ዓመታት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከ40 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን፤ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ለኢኮኖሚው ፈጣን ዕድገት መመዝገብ ጉልህ አስተዋፅዖ እያበረከተ መሆኑን በአብነት ጠቅሰው፤ በመርሐ ግብሩ በርካታ የቡና ችግኞች መተከላቸውን ገልጸው ይህም ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ ከቡና የምታገኘው የወጪ ንግድ ገቢ እየጨመረ እንዲመጣ ማስቻሉን፤ አቮካዶን ጨምሮ የተለያዩ የፍራፍሬ ምርቶች ወደ ውጭ በመላክ ገቢ እየተገኘ መሆኑን ጠቅሰው፥ የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ግቡን እንዲመታ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ጉልህ ሚና አለው። በመርሐ ግብሩ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ በሚደረገው ሀገራዊ ጥረት ውስጥ የማይተካ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።

የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ በበኩላቸው አረንጓዴ ዐሻራ ለትውልድ የሚበረከት ስጦታ ነው። የአረንጓዴ ዐሻራ ትሩፋቱ እየታየ መሆኑን ጠቅሰው፥ ኢኮኖሚው እንዲሳለጥ ከማገዝ ባለፈ ለኑሮ ምቹ ከባቢን የእየፈጠረ እንደሚገኝ ገልጸዋል። የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) በሌላ በኩል፤ አረንጓዴ ዐሻራ የከርሰ ምድርና ገጸ-ምድር ውሃ እንዲጨምር እያደረገ መሆኑን፤ መርሐ ግብሩ ምንጮች እንዲጎለበቱ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው ደርቆ የነበረው የሀሮማያ ሐይቅ ማገገምና ማንሰራራት የአረንጓዴ ዐሻራ ውጤት መሆኑን፤ አፈር እንዳይሸረሸርና ግድቦች በደለል እንዳይሞሉም መርሐ ግብሩ ትልቅ ሚና እንዳለው አመልክተዋል።

በአፍሪካ ኅብረት የሥነ ምሕዳር ባለሙያ እና ከፍተኛ የፖሊሲ ኦፊሰር ሊያ ዋንምብዋ ናኢስ ዛፍ መትከል ለአፍሪካ አኅጉር የሕልውና ጉዳይ ነው ይላሉ። ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ሳታቋርጥ እየተገበረችው ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የተስተካከለ እና ዘላቂነት ያለው ሥነ ምኅዳር ለመፍጠር ወሳኝ ሚና እንዳለው፤ ሊያ ዋንምብዋ ናኢስ ሰሞኑን ለፋና ዲጂታል እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ እየተከናወነ የሚገኘው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የደን ሽፋንን ከማሳደግ ባሻገር የግብርና ምርታማነትን ለመጨመር፣ የአየር ንብረት ለውጥ ጫናን ለመቋቋም እና የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የጎላ አስተዋፅዖ ይኖረዋል። የደን ሽፋን መጨመር የአፈር መከላትን የሚከላከል፣ የዝናብ መጠንን የሚጨምር እና የብዝኃ ሕይወት ሀብት ደኅንነትን የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጸዋል።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የተስተካከለ እና ዘላቂነት ያለው ሥነ ምኅዳር መፈጠሩ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እገዛ ከማድረጉ ባሻገር የሥራ ዕድል ይፈጥራል። ይህ ደግሞ ፍልሰትን በማስቀረት ዜጎች ባሉበት አካባቢ ተረጋግተው አምራች እንዲሆኑ ያስችላቸዋል። በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ስኬት እያስመዘገበች የምትገኘው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ኅብረት ‘ግሬት ግሪን ኢኒሼቲቭ’ አማካኝነት ከፍተኛ ሥራ እየሠራች እንደሆነ፤ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በተመሳሳይ ዘላቂ በሆነ የአካባቢ ጥበቃ ላይ ትኩረት ማድረግ ይኖርባቸዋል ያሉት ባለሙያዋ፤ አንዳችን ከሌላችን በመማር የተሻለ ሥራ መሥራት

አለብን ብለዋል በአፍሪካ ኅብረት የሥነ ምኅዳር ባለሙያ እና ከፍተኛ የፖሊሲ ኦፊሰር ሊያ ዋንምብዋ ናኢስ። ደጋግሜ እንደገለጽሁት አረንጓዴ ዐሻራ ለእኔ የምንጊዜም ግዙፉ ወይም ሜጋ ፕሮጀክት ነው። ሀገራችን በታሪኳ ከፈጸመቻቸው እየፈጸመቻቸው ካሉ ግዙፋን ፕሮጀክቶች ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጨምሮ አንድ ላይ ቢደመሩ የ”አረንጓዴ ዐሻራ”ን ያህል ክብደት አልሰጣቸውም። የህዳሴውም ሆነ የሌሎች ታላላቅ ግድቦች ሕልውና የሚወሰነው ዛሬ በትጋት በምንከውነው የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ነውና።

ችግኝ ተከላ የአየር ንብረት ለውጥን፣ የዓለም ሙቀት መጨመርንና የአካባቢ ጥበቃ ችግሮቻችንም ሆነ ድህነትን ፣ የምግብ ዋስትና ጉድለትን፣ የምርታማነት ተግዳሮትን፣ ድርቅን፣ ረሃብን፣ የዝናብ መቆራረጥንና መቅረት፣ የውሃ እጥረትን፣ የኑሮ ውድነትን፣ በፈጣን የሕዝብ ቁጥር እድገትና በምርት አቅርቦት መካከል ያለውን ክፍተትን፣ ሥራ አጥነትን፣ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰትን፣ የፀጥታና የደኅንነት ችግርን፣ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን ሽግግር በማሳለጥ እና ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማለም መስፈንጠሪያ በመሆን ያገለግላል። ለዚህ ነው ችግኝ ተከላን የእንቆቅልሹ አንዱ መፍቻ ነው ያልኩት።

ከጥቂት ዓመታት በፊት ደጋ የነበሩ ወይና ደጋ፣ ወይና ሰደጋ የነበሩ ቆላ፣ ቆላ የነበሩ በርሃ፣ በርሃ የነበሩ አካባቢዎች እንደ ሰሓራ እጅግ በረሃማ እየሆኑ ነው።ዓመት እስከዓመት ይገማሸሩ የነበሩ ወንዞች፣ በየገመገሙ፣ በየጋራና በየሸንተረሩ ይንፎለፎሉ የነበሩ ምንጮች ደርቀዋል። ወደ 60 በመቶና ከዚያ በላይ የነበረው የደን ሽፋን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከሦስት በመቶ የማይበልጥ ነበር። አሁን በተደረገ ርብርብ የደን ሽፋኑ በእጅጉ ከፍ ብሏል። በአየር ንብረት ለውጡ የተነሳ በየአስር ዓመቱ ይከሰት የነበረው ድርቅ በየዓመቱ ከመመላለሱ ባሻገር በበልግና በመኸርም መከሰት ጀምሯል። ከዓመት ዓመት ይከሰት በነበረ የዝናብ እጥረት የተነሳ የከርሰና የገፅ ምድር ውሃ እጥረት ተከስቷል። እየተቆራረጠና እየተዛባ የሚጥለውን ዝናብ ቢሆንም ደኖች በመራቆታቸው የተነሳ አፈሩ ውሃ መያዝ ባለመቻሉ ጠብ ባለቁጥር ስለሚሸረሸር የአፈር መከላትን እያባባሰ ግብርናውን አደጋ ላይ ጥሎታል፡፡

በዚህ የተነሳ ከሕዝብ ብዛቷ አንጻር ተመጣጣኝ ምርት ማምረት አልቻለችም ። የግብርና ቴክኖሎጂ ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ፣ ፀረ አረምና ተባይ ኬሚካል በመጠቀም ምርትን ለማሳደግ የተደረገው ጥረት አይደለም አግሮ ኢንዱስትሪውን ዜጋውን ሙሉ በሙሉ ለመመገብ ተስፋ ያሰነቀ ቢሆንም ገና ብዙ ይቀረዋል። ሕዝቧን ለመመገብ በሌለ የውጭ ምንዛሪ ጥሪቷ ከውጭ ስንዴን ጨምሮ የምግብ ሸቀጣሸቀጦችን ለማስገባት ስትገደድ ኖራለች። ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተደረገ ርብርብ ይሄን ታሪክ ማድረግ እንደተቻለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚያ ሰሞን ይፋ አድርገዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዓለማችን እያየናቸው ያሉ የደን ቃጠሎዎች ፣ ድርቅ፣ ጎርፍ፣ ውሽፍር፣ የበረሃ መስፋፋት፣ የወቅቶች መዛነፍ፣ ወዘተረፈ የዓለም ሙቀት መጨመር እነ ትራምፕ እንደሚሉት የደባ ኀልዮት ሳይሆን የዕለት ተለት የሕይወት ገጠመኝ ከሆነ ውሎ አድሯል። የበለፀጉ ሀገራት ዛሬ ድሀ ሀገራትን ዋጋ እያስከፈለ ባለው የኢንዱስትሪ አብዮት ባካበቱት ሀብት እየተቋቋሙት ሲሆን እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት ግን በዓለም ሙቀት መጨመር ያለዕዳቸው ውድ ዋጋ እየከፈሉ ነው።

በግብርናችን ያለ መዋቅራዊና ተቋማዊ ችግር የራሱ ድርሻ ቢኖረውም የዓለም ሙቀት መጨመር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ ጋሬጣ እየሆነ ይገኛል። ግብርናችን ዛሬም ከበሬ ጫንቃ ያልወረደ፣ በተበጣጠሰ መሬት ላይ የተመሠረተ፣ የግብርና ቴክኖሎጂውም በተለይ የማዳበሪያና የምርጥ ዘሩ አቅርቦቱ የየአካባቢውን ሥነ ምኅዳርን ከግምት ያላስገባ ስለነበር ከሞላ ጎደል የገጠር ልማት ፖሊሲው የታለመለትን ያህል ውጤታማ ሊሆን ባለመቻሉ ዛሬም ከተመፅዋችነት ሊያወጣን አልቻለም። ዛሬም በቀን ሦስት ጊዜ መመገብ አልቻልንም፡፡

የዓለም ሙቀት መጨመርን ተከትሎ የመጣው የአየር ንብረት ለውጥ ለሀገራችንም ሆነ ለአፍሪካ ጥሩ ዜና የለውም። እየታረሰ የነበረው መሬት ለምነቱን በማጣቱና በመራቆቱ የተነሳ እየቀነሰና እየተራቆተ ይገኛል። ግብርና ለሀገሪቱ ጥቅል ብሔራዊ ምርት ድርሻው 47 በመቶ ቢሆንም፤ መታረስ ካለበት መሬት የተወሰነው ብቻ ነው እየታረሰ ያለው። ይህ በሌላ በኩል እርስ በርሱ የሚቃረን ይመስላል። የከፋ የምግብ እህል እጥረት፣ ድህነትና የበዛ ሥራ አጥ ባለበት ሀገር መታረስ የሚገባው አብዛኛው መሬት ጦም ያድራል። አበው የወለፈንዲ ስልቻ ጤፍ ይቋጥራል፣ ባቄላ ያፈሳል እንዲሉ።

ይሁንና በተለይ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ የበጋ ስንዴ ልማት፣ የኩታ ገጠም ግብርናን፣ በተወሰነ ደረጃ ሥነ ምኅዳርን ታሳቢ ያደረገ የቴክኖሎጂ እገዛ፣ የከርሰና የገጸ ምድር ውሃን አሟጦ የመጠቀም፣ ፍራፍሬና አትክልት ላይ ለመሥራት፣ የከተማ ግብርና ትኩረት ማግኘቱ፤ በአርብቶ አደሩ የሚገኙ ጦም ያደሩ ሰፋፊ መሬቶችን በመስኖ ለማልማት አበረታች ጥረትና ርብርብ መደረጉ የሚቆጠር ለውጥ እያሳየ ነው። ባለፈው ሦስት ሚሊዮን ሔክታር ከሚጠጋ መሬት ከ80 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ስንዴ ምርት ይገኛል ተብሎ መጠበቁ የመጣውን ለውጥ በአብነት ያሳያል። ዳሩ ምን ያደርጋል ዛሬም ገበያው እንደተራበ ነው።

በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ እየቀረበ አይደለም። በዱቄቱ በዳቦው ዋጋ ላይ ቅናሽ አልታየም። በነገራችን ላይ በነፃ ገበያ ስም ስድ የተለቀቀው የግብይት ሥርዓት አደብ እስካልገዛ ድረስ ምንም ያህል ቢመረት እጥረቱም ሆነ ውድነቱ አይሻሻልም። በዜጎች ማዕድና ገበያ ላይ ለውጥ ካላመጣ 80፣ 100፣ 120፣ ወዘተረፈ ሚሊዮን ኩንታል ቢመረት ጉዳያቸው አይሆንም። እንደ ድመቷ ሺህ ቢታለብ ያው በገሌ ከሆነ ትርጉም የለውም። መንግሥት የግብይት ሥርዓቱን ማስተካከልና ለሀገር ውስጥ ገበያ ቅድሚያ መስጠት አለበት።

በነገራችን ላይ ችግሮቻችንን ሁሉ ፈታተን፣ በታትነንና አገላብጠን ብንመረምራቸው አብዛኛዎቹ ከአንድ ቅርጫት የሚገኙ ናቸው። የተፈጥሮ ሀብታችንን በአግባቡ ካለመንከባከብ፣ ካለመጠበቅና ካለማልማት ቅርጫት። የዓለም ሙቀት መጨመርን ተከትሎ በመጣ የአየር ንብረት ለውጥ የተነሳ የተፈጥሮ ሀብታችን እየተጎሳቆለ በመምጣቱ ማለትም መሬታችን የተራቆተ፣ ዝናባችን የአጠረና የተቆራረጠ በመሆኑ የከርሰና የገጸ ምድር ውሃችን በመመናመኑ ግብርናው ውጤታማ ሊሆን አልቻለም። በዚህ የተነሳ በግብርና ላይ የተመሠረተው የዜጋው ሕይወት፤ የሀገሪቱ ልማት ችግር ላይ ወድቋል። ይህ የሀብት ውስንነትን ፈጥሯል።

በዚህ የተነሳ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ከዓመት ዓመት እየተባባሱ መጡ። እነዚህን ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ደግሞ የተፈጥሮ ሀብታችን እንዲያገግም ሌት ተቀን መሠራት አለበት። መሬት ማገገም፣ ውሃ መያዝ አለባት። ይህ ደግሞ እውን ሊሆን የሚችለው ችግኝ በመትከልና የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎችን በስፋት በማከናወን ነው። “አረንጓዴ ዐሻራ” የበሽታውን ምልክት ከማከም ይልቅ መነሻውን በማያዳግም ሁኔታ የመፈወስ አቅም እንዳለው በማመን ነው፤ “አረንጓዴ ዐሻራ!” የእንቆቅልሻችን አንዱ መፍቻ ቁልፍ ነው ያልኩት። ለዛሬው መጣጥፌ መነሻ ወደሆነኝ መግለጫ ሳመራ፤ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በአንድ ሰሞን መግለጫው፤ አረንጓዴ ዐሻራ ለኢትዮጵያውያን እንደ ባህል እስኪቆጠር ተግተን በመሥራት አረንጓዴ የለበሰች ኢትዮጵያን እውን እናደርጋለን ብሎናል።

ለእኔ “አረንጓዴ ዐሻራ” ባህል ከማድረግም ሆነ ሀገርን አረንጓዴ ከማልበስ የተሻገረ ነው። ሀገርን ከድህነትና ኋላቀርነት በአንድነት ይዞ የሚነሳ፣ ከተረጅነትና ከተመፅዋችነት በማላቀቅ ነፃነቷንና ሉዓላዊነቷን ሙሉዕ የሚያደርግ፤ ወዘተረፈ ስለሆነ ችግኝ ተከላን ባህል ከማድረግም ሆነ ሀገርን አረንጓዴ ከማልበስ በከባዱ የተሻገረ ነው። ባለፉት ዓመታት በተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በኢትዮጵያ በሁሉም ክልሎች በመጀመሪያው ምዕራፍ ከ40 ቢሊዮን በላይ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን የተተከሉት ችግኞችም በዘርፉ ሙያተኞች በተደረጉት ክትትል 90 በመቶ ለመፅደቅ ችለዋል። የተፈጥሮ ሀብትና የሕይወታዊ ሃብት ጥበቃ ሥራ ሲጠናከርና ተከታታይነት ባለው መንገድ ሲሠራ ከአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ነፃ የሆነና መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥን መሠረት ያደረገ አካባቢያዊ የአየር ንብረት እንዲኖር የበኩሉን አስተዋፅዖ እንዲያደርግ ዕድል ይሰጣል።

በመጀመሪያው ዙር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በመላ ሀገሪቱ በተተከሉ ችግኞች ቀደም ሲል ተራቁተው የነበሩና የአፈር መሸርሸር አጋጥሟቸው የነበሩ አከባቢዎች በአሁኑ ወቅት ወደ ቀድሞ ገጽታቸው እየተመለሱና መሬቱም እያገገመ መሆኑን የግብርና ባለሙያዎች ምስክርነታቸውን እየሰጡ ነው። የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራችን በተለያዩ ዘርፎች ውጤቶችን እያሳየን ነው።ተደጋጋሚ ድርቅ ሲያጠቃቸው የነበሩ አካባቢዎች ዝናብ ማግኘት ጀምረዋል፣ የጎርፍ አደጋን ለመቀነስ ተችሏል፣ የደረቁ ምንጮችና ሐይቆች እንደገና ቀድሞ ወደ ነበሩበት መመለስ ችለዋል፣ ለበጋና የመኸር እርሻ ተስማሚ የሆነ ዝናብ ማግኘት ተችሏል። ከሥራ ዕድል ፈጠራነት አንጻር ለእንስሳት መኖነት፤ ለንብ ማነብ፤ ለካርቦን ሽያጭና ለጎረቤት ሀገራት መልካም ጉርብትና እና የዲፕሎማሲ ግንኙነት ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርጓል።

በዘንድሮ 2017/18 በ132 ሺህ 144 ችግኝ ጣቢያዎች ለአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብሩ ችግኝ ተዘጋጅቶ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል የቅድመ-ተከላ ዝግጅቶች በሁሉም አካባቢዎች እየተሠሩ ይገኛል። በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ 25 በመቶ የሚሆነው በዓባይ ተፋሰሶች የሚተከል ይሆናል። የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ዝግጅትና ተከላ ለበርካታ ወጣቶችና ሴቶች ሰፊ የሥራ ዕድል እየፈጠረ እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ።

በ6 ሺህ 200 ተፋሰሶች የሥነ-አካላዊ ሥራ በመሥራት በሥነ-ሕይወታዊ የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ ተግባራት እየተከናወኑ ነው። በመርሐ ግብሩ ላይ ለተከላ የተዘጋጁ ችግኞች ዘርፈ ብዙ ገቢ የሚያስገኙ አትክልትና ፍራፍሬ፤ ጥምር ደን፤ ለከተሜነት ውበት የሚውሉ እና ለደን የሚውሉ ናቸዉ። ለአረንጓዴ ዐሻራ ስኬት የሁላችንም ተሳትፎና ዝግጁነት ከወዲሁ ይጠበቃል።

ሻሎም ! አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም(ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You