ስፖርት ሀገራዊ ግቦችን ለማሳካት የጎላ ፋይዳ ስላለው ባለድርሻ አካላት ሊረባረቡ ይገባል

ባህር ዳር፡- ስፖርት ከራሱ ዘርፍ በዘለለ አጠቃላይ በሁሉም ዘርፎች የተያዙ ግቦችን ለማሳካት ወሳኝ በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለዘርፉ ስኬታማነት ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በባህር ዳር ከተማ “ስፖርት ለአሸናፊ ሀገር” በሚል መሪ ሃሳብ በባህር ዳር ከተማ ባዘጋጀው የስለኢትዮጵያ መድረክ ላይ ሚኒስትሯ እንደተናገሩት በሁሉም ዘርፎች የሚገኙ ግቦችን ለማሳካት ጤናማና ብሩህ አእምሮ የተላበሰ ማህበረሰብ መገንባት ወሳኝ ነው። ለዚህ ደግሞ ስፖርት ትልቅ ሚና አለው።

ስፖርት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት የጠቀሱት ሚኒስትሯ በተለይ በሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ውስጥ ዘርፉ ትልቅ ሚና እንዳለውም ተናግረዋል።

ዘርፉ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች የሚያበረክት ቢሆንም በርካታ ፈተናዎች እንደነበሩበት የጠቀሱት ሚኒስትሯ፤ በአሁኑ ወቅት ግን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ስፖርትን በተግባር እያሳዩ የሚደግፉ መሪዎች በመኖራቸው ዘርፉ ከፍተኛ መነቃቃት ውስጥ እንዳለ አብራርተዋል።

በሀገራችን በአሁኑ ጊዜ ዘርፉን የሚረዱ እና በተግባር የሚኖሩ መሪዎች አሉ ያሉት ሚኒስትሯ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች በተግባር የእለት ተዕለት ኑሯቸው ስፖርትን በተግባር በመኖር ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት መስጠታቸውን ጠቅሰዋል፣ በየደረጃው ያለው አመራርም በዚህ ደረጃ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት አለበት ብለዋል።

መንግሥት ለዘርፉ ከፍተኛ ሀብት እየመደበ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሯ፤ በየደረጃው ባለው መዋቅር ከፍተኛ ሀብት መድቦ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል። በዚህም በርካታ የስፖርት መሠረተ ልማቶች እየተገነቡና እድሳትም እየተደረገላቸው በመሆኑ በዘርፉ በተግባር የሚታይ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።

በዘርፉ ውጤት ለማምጣት ቅንጅታዊ አሠራር ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሯ ፤ አሁን በዚህ ረገድ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል። በየደረጃው ያለው መዋቅርና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላትም ሊተባበሩ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የስፖርት ስኬታማነት የረጅም ጊዜ ጥረት የሚጠይቅ በመሆኑ አሁን እየተሠራ ያለው ሥራ በቀጣይ ውጤት የሚያመጣ መሆኑን ተናግረዋል። ከስፖርተኞች በተጨማሪም አሰልጣኞችና ባለሙያዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ አመልክተዋል።

ይህንን ከሠራን አሸናፊ ሀገር ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህም ሁላችንም በጋራ እንሥራ ሲሉ አሳስበዋል።

በእለቱ አሸናፊ ብሄራዊ ቡድንን እንዴት እንገንባ?፣ የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ምን ይመስላል?፣ አሸናፊ ቡድን ለሀገረ መንግሥት ግንባታና ለሕዝቦች አንድነት ያለው ሚና እንዲሁም አሸናፊ ቡድንን በመገንባት ረገድ ያሉ ስብራቶችና መፍትሄዎቻቸው ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።

የመወያያ ሃሳቦቹን ያቀረቡት የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ መኪዩ መሀመድ፣ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የጥናትና ምርምር ሥራ አስፈጻሚ አመንሲሳ ከበደ (ዶ/ር) ናቸው።

በውይይቱም ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተጋበዙ የስፖርት ቤተሰቦች ተሳትፈዋል።

በእለቱ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ስፖርትን ታሪካዊ ሂደት የሚያሳይ የፎቶ አውደ ርዕይ የቀረበ ሲሆን በፕሮግራሙ ማብቂያ ላይም የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካና ሌሎች የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በባህር ዳር ሁለገብ ስታዲም ጊቢ ውስጥ የችግኝ ተከላ መርሃግብር አከናውነዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ስፖርት ለአሸናፊ ሀገር በሚል ያዘጋጀው ይህ መድረክ ሁለተኛው ምዕራፍ 7ኛ መድረክ ሲሆን የእለቱን መድረክ ጨምሮ እስካሁን በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ 21 መድረኮችን ማዘጋጀቱ ታውቋል

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You