ህይወት በብዙ ስንክሳሮች የተሞላች ናት! ይህ የኑሮ ዑደት ደግሞ በጊዜ ውስጥ ይዘወራል፤ ይመሻል ይነጋል፤ ይነጋል ይመሻልም። የጊዜን ዑደት ማን ሊገታ ይቻለዋል? በዚህ ሂደት ውስጥ የአንድን ስጋ ለባሽ ሕይወት የሚያስጨንቅ ከተራራ ናዳ በላይ ጨፍላቂ ሸክም ምን አለ? ከቀንብር በላይስ ምን አንገት የሚያስደፋ ይገኛል?
ፈጣሪ እና ዕድል ከጎኑ ከቆሙለትና የተጋረጡበትን ፈተናዎች እንደ አለፈ ክረምት የሚያስቆጥር ጸጋ ከተሰጠው በስተቀር! በእንግዳችን ህይወት የሆነባቸውና የሆነላቸው ይኼው ይመስላል። የአንዳንዶቻችን የሕይወት ታሪክ ሸለቆ ደርሶ መቆም እንደተገደደ ከተራራ አናት ላይ እንደተፈነቀለ ዕለት ከዕለት ወደ ዕለት ከማናልፈው ሞት እስከምንደርስ ድረስ እንደመንከባለል ያለ ሂደት ነው።
ሌሎቻችን ደግሞ ሕይወታችን በዓላማ የምንመራው እንኖርበታለን ያልነውን ዓላማ የሚገዳደሩ ሁኔታዎች እስካልገጠሙንና ኑሮ “አልጋ በአልጋ” እስከሆነልን ድረስ ነው። ዓላማቸው እና ግባቸው አድሮ መገኘት ከሆነው በየምዕራፉ ተግዳሮት ሲገጥማቸው ጎመን በጤና እያሉ መንገድ ከሚቀያይሩት … ለየት ያለ ለዓላማቸው የጨከነ ማንነት ያላቸው ጥቂት ሰዎች አሉ።
ለረዥም ዓመታት በውትድርና ዓለም ውስጥ ነው የቆዩት። በወታደር ቤት ውስጥም ወታደሮችን ፈረስ ግልቢያ በማስተማር፣ ምልምል ሚሊሻዎችን ውትድርና በማስልጠን አገልግለዋል። በፈረስ ስፖርት ውድድርም ክቡር ዘበኛን በመወከል የተለያዩ የአገር ውስጥ እና የዓለም አቀፍ ውድድሮችን ተሳትፈዋል፤ በአሁኑ ወቅት ጡረታ ወጥተው እንዲሁም የአካል ጉዳት አጋጥሟቸው በቤታቸው ውስጥ ተቀምጠው ይገኛሉ፤ የዛሬ የ“ሕይወት እንዲህ ናት” እንግዳችን ሃምሳ አለቃ በቀለ መርጋ ፤መልካም ንባብ!
ልጅነት
ትውልዳቸው ምዕራብ ሸዋ ዞን ደንዲ ወረዳ ጊንጪ ከተማ ነው። ቤተሰብ በነገራቸው መሰረት ሲያሰሉት መጋቢት 1948 ዓ.ም እንደተወለዱም ይናገራሉ። ታዲያ የትናንቱ ህጻን የዛሬው አዛውንት ፈረሰኛው በቀለ እንደማንኛውም የገጠር ታዳጊ በትውልድ ስፋራቸው ከብቶችን ጠብቀው ነው ያደጉት። ከታዳጊ የዕድሜ አቻዎቻቸው ጋርም ጨዋታን ተጫውተዋል።
ታዳጊው በቀለ እናቱን በህጻንነቱ ያጣ ልጅ ሲሆን፤ በእንጀራ እናት ነው ያደገው። ይሁንና እንጀራ እናት ተብሎ የተሰጠውን መጥፎ ስያሜ የእንጀራ እናቱ እንደማትገባበት ይናገራል። እንደውም የዛሬው አዛውንት ሃምሳ አለቃ በቀለ ሲናገሩ ‹‹ለእኔ ከእናት በላይ ተንከባክባ ያሳደገችኝ በመሆኗ እንጀራ እናት ልላት አልፈልግም። በእርግጥ ይህ ስም መጥፎ የሆነበት ምክንያት ከባህሪያቸው ስህተት ስለሚመነጭ ነው። እርሷ ግን ሩህሩህና ቸር በመሆኗ ትክክለኛ እናት ነበረች። በዚህም ልዩ እናቴ ነበረች›› ይላሉ።
እንግዳችን ለጎረቤት ታዛዥ፣ ተላላኪና ምርቃት የሚወዱ ልጅ እንደነበሩ፤ ሁሉም ጎረቤት የሚመርቃቸውና ሲነኩም የማይወዱ እንደውም ሆዳቸው ቂም አርግዞ የተበደሉትን ለመመለስ ዛፍ ሳይቀር የሚንጠላጠሉም እንደነበሩ ያስታውሳሉ።
ቤተሰብን በእርሻ ሥራ ያግዙ የነበሩት ሃምሳ አለቃ በቀለ፤ ስማቸው እንኳን የተሰጣቸው አደገ፣ ጎለመሰ ደረሰልን ከሚል እንደነበር ይናገራሉ። በልጅነታቸው ፈጣን ሯጭ፤ በፈረስ ብቻ ሳይሆን በአህያና በበሬም ጋልበው የአካባቢው ሰዎችን ያስደመሙ ነበሩ፤ ስለሆነ እድገታቸውን በዚህም ያሳዩ እንደነበር ይገልጻሉ። ዛሬ ድረስ በአገር ብቻ ሳይሆን በዓለም ደረጃ የሚታወቁበትን የፈረስ ጉግስ እውቅናን ያስገኘላቸው ይህ መሰረታቸው እንደነበርም አይዘነጉትም።
ሃምሳ አለቃ በቀለ የአካባቢው ሰው ደዎሻ እያለ በቅጽል ስም ይጠራቸው እንደነበር ይናገራሉ። ይህንን የተባሉበት ምክንያት ደግሞ ድንቡሽቡሽ ያሉ ወፍራም በመሆናቸው የተሰጣቸው ስያሜ እንደነበር አጫውተውናል።
የትውልድ ቀያቸው በደን የተሸፈነ እንደነበር የሚያስታውሱት ባለታሪኩ፤ ብዙ የፍራፍሬ አይነቶችን ተመግበው አድገዋል። ይህ የሆነው ግን እስከ 11 ዓመታቸው ድረስ ብቻ ነው። ምክንያቱም ከዚህ በኋላ ትምህርትን ፍለጋ ይህንን ቦታ ለመልቀቅ ተገደው ነበር፤ ከዚያ የትምህርት ጥማታቸውን ለማርካት በወቅቱ የተሻለ ትምህርት ወደሚሰጥበት አዲስ አበባ አቀኑ።
መጀመሪያ አዲስ አበባን ለመርገጥ ምክንያት የሆነቻቸው እህታቸው ስትሆን፤ ለዓመታት እርሷ ጋር አርፈው ነበር እየሰሩ የተማሩት። በዚህም ከተማዋን፣ ሰፈሩን፣ መንደሩንም ለማየት የመውጣት እድሉን አገኙ።
በወቅቱ የሃምሳ አለቃ በቀለ እህት የጣሊያኖች ጎረቤት በመሆኗ ይህ እድል ጣሊያንኛ እንዲችሉ ከማድረጉም በላይ ከአንድ የሚወዳቸው ጣሊያናዊ ጋር አስተዋወቃቸው። ከዚያም አልፎ ጣሊያኖቹ ብዛት ያላቸው ፈረሶች ነበራቸውና ጠዋትና ማታ ፈረስ ይጋልቡ ነበር። እርሳቸውም የግልቢያው ሜዳ እየሄዱ ጊዜ ማሳለፍ ሆነ ስራቸው። ያለማቋረጥ በቦታው እየተገኙ ግልቢያውን ሲመለከቱ ያያቸው ሪኮ ዳሞቶኒ የተባለ ጣሊያናዊ ሰው ፈረስ መጋለብ እንደሚወዱ ጠየቃቸው፤ በደስታ ፍላጎቱ እንዳላቸው ሲነግሩት በበጎ ፍቃድ ሁሉም ቁሳቁስ በማሟላት ወደ ራሱ ቤት ወስዶ አሰለጠናቸው።
በወቅቱ ከቀለብ እና ለስፖርታዊ እንቅስቃሴ ለሚገለገሉበት ከሚሰጣቸው ቁሳቁስ በቀር የወር ደመወዝ የሚባል ነገር አልነበራቸውም። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሪኮ በወር 30 ብር ይከፍላቸው ጀመር። ይህ ክፍያ ደግሞ ለሃምሳ አለቃ በቀለ ትልቅ ብርታትና ሞራል እንደሆናቸው ይናገራሉ። የሚከፍላቸውን ብር በመያዝ ከእህታቸው ቤት በመውጣት በ14 ዓመታቸው ቤት ተከራይተው የራሳቸው ምግብ እያበሰሉም የላጤነት ህይወታቸውን ጀምረዋል።
ሃምሳ አለቃ በቀለ ከ11 ዓመታቸው ጀምረው ራሳቸውን ለመቻል ከመላላክ ጀምሮ በሰው ቤት ተቀጥረው እስከመስራት ደርሰዋል። ስለዚህም ልዩ የሥራ ፍቅርም የነበራቸው ልጅ ናቸው።
ትምህርት
ሃምሳ አለቃ በቀለ ትምህርታቸውን ሀ! ያሉት ያልተማሩት ቤተሰቦቻቸው ጋር እያሉ ነው። ያው በቤተክህነቱ ማለት ነው። ከዚያ ጠንከር ብለው ዘመናዊውን የሚማሩበት አማራጭ አልነበራቸውምና ወደ እህታቸው ጋር አዲስ አበባ አቀኑ። በዚያም ቢሆን መቆየት የሚችሉበት ሁኔታ አልተፈጠረም። ስለዚህም በሰው ላይ ጥገኛ ላለመሆን ሲሉ በመጀመሪያ ከእዚያው ከእህታቸው ጎን ይኖር የነበረ ጣሊያናዊ ይተዋወቃሉ። ከዚያም በፈረስ ሰበብ ወደቤቱ ይወስዳቸዋል። የተለያዩ ሥራዎችንም እየሰሩ ማታ ማታ ላይ መካኒሳ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ገቡ።
አንደኛ ክፍልን ካጠናቀቁ በኋላ ደግሞ ሁለተኛና ሦስተኛ ክፍልን ለመማር አጋዚያን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመዘገቡ። ቀጥለው ደግሞ አሁንም ሌላ ቤት እየሰሩ አጼናኦድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብተውም ከአራት እስከ ስምንተኛ ክፍል ተማሩ። የመጨረሻውን ትምህርታቸውን የተከታተሉት ደግሞ ክቡር ዘበኛ ገብተው ሲሆን፤ በዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው:: በዚህ ትምህርት ቤት እስከ 11ኛ ክፍል ዘልቀውበታልም። ከዚያ ግን አላለፉምና ተከታታይ የዘመናዊ ትምህርታቸው እዚህ ላይ ነው ያከተመው።
ለዚህ ግን ምክንያት እንዳላቸው የሚናገሩት እንግዳችን፤ በተከታታይነት ትምህርታቸውን ለመማር የሚያስችላቸው ሁኔታ ላይ አልነበሩም። በመንግስት ደረጃ መሬት ለአራሹ በመምጣቱ ሳቢያ እርሳቸው ከባድ መሳሪያ አጓጓዥና ተኳሽ ናቸው። በዚያ ላይ ልዩ የፈረስ ጉግስ ተወዳዳሪ በመሆናቸው ከቦታ ቦታ አገርን ወክለው ይዘዋወራሉ። ስለዚህም የሰለጠኑትን ሙሉ የውትድርና ትምህርት ለሌሎች በማሰልጠን፤ የፈረስ ውድድሮችንም ለወጣቱና ለአምባሳደር ሚስቶች እንዲሁም ፍላጎት ላላቸው ሰዎች በመስጠት ነው ልምዳቸውን እያካበቱ የተጓዙት። እናም ትምህርት ያበቃው 11ኛ ክፍል ላይ ነው ይላሉ።
ከመላላክ እስከ አሰልጣኝነት
የስራ ጅማሯቸው ወደአዲስ አበባ መጥተው ለመማር በሚጥሩበት ጊዜ መላላክና ልጆችን ትምህርት ቤት ማመላለስ ነው። ከዚያ ብዙ ጊዜ ሲመላለሱ ያያቸው ጣሊያናዊ ይወዳቸውና ‹‹ቤቴ ሆነህ እየተማርክ ፈረስ ግልቢያ ላስተምርክ፣ ሌሎች ሥራዎችንም ታግዘኛለህ›› አላቸው። እርሳቸውም የመጣላቸው ተስፋ እንዲያመልጣቸው አልፈለጉምና በሀሳቡ ተስማሙ። ጓዛቸውንም ጠቅልለው በዚያ መስራት ጀመሩ።
‹‹ወደ አዲስ አበባ በመጣሁበት ወቅት ነው ጣሊያናዊውን አቶ ሪኮ ዳሞቶኒ የተባለ ሰው ያገኘሁት። ደግና ሰው የሚወድ ነው። በተለይ እኔን የሚያዘኝን ሁሉ ስለማደርግ በጣም ይወደኝና የምፈልገውን ያደርግልኝ ነበር። ቤት ውስጥም ከጽዳት ጀምሮ እስከ ቤት ውስጥ ምግብ ሥራ እንድሰራ ያበረታታኝ ነበር። አሮስቶና ዶሮ መስራት ያስቻለኝም እርሱ ነው። በአጠቃላይ የቤት ውስጥ ሙያ በሚገባ አስተምሮኛል። ከብቶችን ያረባ ነበርናም ከወተት ተዋፅኦ የተለያዩ ክሬሞችን እያወጣሁ ሰርቼ ይከፍለኛል። በዚህም ደስተኛ ሆኜ እስከ ህይወት ህልፈቱ ድረስ አብሬው ኖሬያለሁ›› ይላሉ።
በሁለተኛ ደረጃ መስራት የጀመሩት አንድ አሜሪካዊት ቤት ሲሆን፤ ፈረሶችን ይንከባከቡ ነበር። በዚያ ላይ ሰራተኞችንም ሥራ ያግዛሉ። ከእርሷ ጋር የተገናኙበት ምክንያት የፈረስ ግልቢያ ውድድር አሸናፊ መሆናቸው ሲሆን፤ ገና ቤት እንደያዘች ነበር የወሰደቻቸው። ከዚያ በውድድሩ አሜሪካ ኤምባሲን፤ ፈረንሳይ ወዘተ እያሉ ኤምባሲዎችን በመወከልም ተወዳድረው ማሸነፍ የቻሉ ናቸው። ቀጥለው መስራት የጀመሩት ደግሞ ሙሉ የውትድርና ስልጠና ወስደው በክቡር ዘበኛ የሚባለው የመከላከያ ሰራዊት ቡድን ውስጥ ተቀላቀሉ።
ከደብረ ብርሃን ለስልጠና በተላኩበት ወቅት ደግሞ የፈረስ ጉግስ ተወዳዳሪ በመሆን ቡድኑ ደመወዝ ሊከፍላቸው አስፈረማቸው። ታዋቂ የነበረው አሰልጣኝ ሚንዳ አበጋዝ እንዲያሰለጥናቸው ተደርጎ ስልጠናው ቀጠለ። ከውድድሩ ጎን ለጎንም በተለያዩ ሀገራት ውድድሩ ስለሚደረግ ኢትዮጵያን በመወከል የተለያዩ ሜዳሊያዎችን ለአገራቸው ማምጣታቸውን ቀጠሉ። በዚሁ በክቡር ዘበኛ እያሉም ለ27 ዓመታት ሰርተዋል።
ማንን አሰለጠኑ
‹‹ከወጣትነቴ ጀምሮ ኑሮዬ ከወጣቶችና ከፈረሶች ጋር ነው። በፈረስ ጉግስም በማሰልጠን እኔን የሚያክል የለም። የመጀመሪያው አሰልጣኝም
ነኝ። ፈረሶችን አሰልጥኛለሁ፤ ወጣቶችንም እንዲሁ የሌሎች ሀገራት ወጣቶችንም አሰልጥኛለሁ። ፈረሶችን ሳሰለጥን ገብስና ካሮት በመመገብ ነው። ካሮትና ገብስ የሚመገብ ፈረስ አይደክምም፤ ትልቅ ጉልበትና ረጅም ትንፋሽ ይኖረዋል።›› የሚሉት ባለታሪኩ፤ የኤምባሲ ሰራተኞችንና የአምባሳደር ሚስቶችን ሳይቀር እንዳሰለጠኑና ትልቅ ደረጃ የደረሱ ሰልጣኞችም እንዳሏቸው አጫውተውናል።
ከፈረሶቹ ባለቤት ጋር በመሆን ትንንሽ ፈረሶችን፤ አካላቸው ትንሽ የደከሙትን በመምረጥ ወደ ስልጠና ማዕከሉ በማምጣት ያሳለጥኑ የነበሩት ሃምሳ አለቃ በቀለ፤ የሚታወቁ ፈረሶች እንዳደረጓቸውም ይናገራሉ።
በአጠቃላይ በሥራ ህይወታቸው ከመላላክ ልጅን ትምህርት ቤት ማድረስና የቤት ጽዳት እስከ ውትድርና ቤት ስልጠና ሰርተዋል። በተለይ ረጅም እድሜ ለቆዩበት ክቡር ዘበኛ ወታደሮችን ፈረስ ግልቢያ በማስተማር ፣ ሚሊሻዎችን መልምሎ ውትድርና በማስልጠን ማንም አያክላቸውም ነበር። ከዚያ ባሻገር ደግሞ በፈረስ ስፖርት ውድድርም ክቡር ዘበኛን በመወከል የተለያዩ የአገር ውስጥ እና የዓለም አቀፍ ውድድሮችን ተሳትፈው ብዙ ሜዳልያ እንዲወስድም ያደረጉ ናቸው። አሁን ግን ቀደም ሲል ያልደረሱለት አይናቸው ችግር ሆኖባቸው መታከም አይችልም ተብለው በጡረታ ቢገለሉም መሥራት የሚችል አቅማቸውን አሟጠው እንዳይጠቀሙት አድርጓቸዋል። በዚህም አይነስውር ሆነው በቤታቸው ተቀምጠዋል።
የፈረስ ጉግስ ወድድር እና ድሎች
ሃምሳ አለቃ በቀለ የፈረስ ጉግስ ውድድር ጅማሮአቸውን ሲያስረዱ “ሪኮ ለስድስት ወራት በደንብ አሰልጥኖኝ ስለነበር በ14 ዓመቴ በ1962 ዓ.ም ነው በወጣቶች ደረጃ በሚደረግ ውድድር ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፍኩት። ውድድሩ ደግሞ 600 ሜትር መሰናክል ነው። በዚህም አንደኛ በመውጣት አሸነፍኩ። በዚያው እለት ሁለተኛ ውድድር በማድረግ ሁለተኛ ወጣሁ። በዚህ ደግሞ አሰልጣኜ አቶ ሪኮ ተደስቶ ነበርና የተለያዩ ሽልማቶችን አበርክቶልኛል።”ሲሉ ያስታውሳል።
“ከተሰጡኝ ሽልማቶች ትልቁ የነበረው ካሜራ ነው›› የሚሉት ባለታሪኩ፤ በዚህ ሽልማት በመበረታቴ 1963 ዓ.ም ከታወቁ ስፖርተኞች ጋር እንድወዳደር ሆኛለሁ። በከፍተኛ ውጤት አንደኛ በመውጣት አሸንፌያለሁ። ስለዚህም በብዙዎች ዘንድ ተመራጭ ያደረገኝም ይህ ሥራዬ ነው ብለውናል።
ሃምሳ አለቃ በቀለ “አሰልጣኜ በሀገር ውስጥ ውድድር በወጣቶች ደረጃና ከታዋቂ ስፖርተኞች ጋር በመወዳደር ጥሩ ውጤት ማስመዘገቤን በማየት ለመጀመሪያ ጊዜ በ1964 በጅቡቲ በተደረገ የፈረስ ውድድር ሻምፒዮን እንድካፈል እድሉን አመቻችቶልኛል። በወቅቱም በተደረገው ውድድር በወጣቶች ደረጃ በመሆን በሀገር ውስጥ ያገኘሁትን ልምድ በመጠቀም ሻምፒዮን በመሆን ለራሴ የወርቅ ሜዳሊያና ዋንጫ ፣ለሀገሬ ደግሞ እውቅናን አስገኝቻለሁ።” ይላሉ ወደኋላ የነበረውን ነገር ሲያስታውሱ።
በዚያው ዓመት የጣሊያን ኤምባሲ ባዘጋጀው ውድድር ላይ ኮኒ በሚባል ፈረስ በወጣቶች ደረጃ ተወዳድረው ሻምፒዮን በመሆን የሁለት ዋንጫ ባለቤት እንደነበሩ የገጹት እንግዳችን፤ ውድድሩ የሚካሄደው በየዓመቱ ስለሆነ ሽልማቱን የሚሰጡት የአጼ ኃይለስላሴ ቤተሰቦች ናቸው። በዚህም ከልጃቸው አስፋው ወሰን ኃይለስላሴ እጅም ብዙ ጊዜ ዋንጫ፣ ሚዳሊያና የምስክር ወረቀት እንዲወስዱ ሆነዋል።
በተለያዩ ውድድሮች መልካም ስምና ዝናን ያተረፉትና በተለያዩ ወቅቶች ሀገር ውስጥ የሚገኙ ኤምባሲዎች ጥሪ እያደረጉላቸው የሚወዳደሩት ባለታሪኩ፤ በተለይ በጣሊያን፣ በእንግሊዝ፣ በቤልጂዬምና ፈረንሳይ ኤምባሲዎች ለብዙ ጊዜ ተሳትፈው ሽልማቶችን ወስደዋል። እንደነ ኢሬሳ ማሩ መልካ፣ መቶ አለቃ አሰፋ ሚንዳ ከመሳሰሉት ጋር በመሳተፍ ኢትዮጵያ በቡድንም በግል ውድድር አንደኛ እንድትሆን አድርገዋል።
በዓለም አቀፍ ውድድሮች ከ1963 ጀምሮ እስከ 1989 በተለያዩ ሀገራት ለአብነት በጅቡቲ፣ ስዊድን፣ ጣሊያን፣ እንግሊዝና ፈረንሳይ በተሳተፉበት ውድድር ላይ በመሳተፍ ኢትዮጵያ በቡድንና በግል ውጤታማ እንድትሆን አስችለዋል። በ1966 ደግሞ ጂቡቲ በተደረገ ሻምፒዮና አሸናፊዎች በመሆናቸው የክብር ዘበኛ አዛዥ ተደስተው ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸው እንደነበር አይረሱትም። የተለያየ ሽልማትም እንደተበረከተላቸው አጫውተውናል።
አንድ ፈረስ ከአፍሪካ ሀገር ሄዶ አውሮፓም ይሁን በኢሲያ መሳተፍ አይችልም። ጥሪ በሚደረግበት ጊዜም ቢሆን ፈረስ ሳይሆን ሄዶ የሚሳተፈው ሰው ነው። ምክንያቱም የአፍሪካ ሀገራት ፈረሶች ለተለያዩ በሽታዎች ተጋላጭ በመሆናቸው ወደ ሌሎቹ ያስተላልፋሉ በማለት ስለሚፈሩ ነው። እናም በአዲስ ፈረስ ጋልቦ ማሸነፍ ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነ ሙያው ያለው ይናገረው። ግን እኔ ይህ ሳይበግረኝ ለአገሬ በየጊዜው ታላቅ ድል አቀዳጅ ነበር ይላሉ።
ይህ ፈተና በዓለም አቀፍ ደረጃ የአፍሪካ ተጨዋቾችን በእጅጉ የሚጥል እንደነበር የሚያወሱት ሃምሳ አለቃ በቀለ፤ አንዳንዴ ራሳቸው ባሰለጠኗቸው ፈረሶች ስለማይሳተፉ የሚገኘውም ውጤት ያን ያህል አመርቂ እንዳልነበረ ይናገራሉ።‹‹ እኔ በራሴ ጂቡቲ ከ12 ጊዜ በላይ ተመላልሻለሁ፡፤ ታንዛኒያ፣ ኬኒያና ኡጋንዳ እንዲሁም ደግሞ በኢሲያ አህጉር በተለይ በሳውዲ አረቢያ በሌላ ፈረስ ተወዳድሬ የአራተኛ ደረጃን አግኝቻለሁ። ይህም የአፍሪካ ፈረሶች በሽታ ያመጣሉ ተብሎ ስለሚታሰብ ነው ።›› ይላሉ ይህ ፈተናቸው ደረጃቸውን ምን ያህል እንዳወረደው ሲያስታውሱ።
ሆኖም ፈተናው ሳይበግራቸው በአጠቃላይ ለ36 ዓመታት በውድድር ውስጥ ነበሩና በሀገር ውስጥና በውጪ አገር 259 ዋንጫዎች፣ 270 የወርቅ፣ የነሐስና የብር ሜዳሊያዎችን እንዲሁም የተለያዩ ምስክር ወረቀት አግኝተዋል። ሽልማቶቹንም የተቀበሉት ከታላላቆቹ የአገሪቱ ባለስልጣኖች እጅ እንደነበር ያስታውሳሉ። ለአብነት የሳውድ አረቢያን ከንጉስ ፉዓድ፤ የጂቡቲውን ከፕሬዝዳንት ሃሰን ጉሌድ አብቲዶን፣ የኢትዮጵያዊው ከአጼ ሃይለስላሴ እና ከቤተሰቦቻቸው ነበር።
የፈረስ ውድድር ከአገር ውጪ ብቻ አውሮፓና ኢሲያ ሀገራት ላይ ብቻ አይደለም የሚከናወነው። አገር ውስጥም በጃንሜዳ ይደረጋል። ይህ ሲሆን ደግሞ ተወዳዳሪ አገራት በኤምባሲያቸው አማካኝነት ውድድሩን ያከናውናሉ። ያም ቢሆን ወይ ፍንክች የአባ ቢላዋ ልጅ ነውና ነገሩ አሳልፈን ዋንጫችንን ለማንም ሳንሰጥ ነው የቆየነው። በመጡበት እግራቸው ይመለሳሉ እንጂ አያሸንፉንም ይላሉ።
‹‹ከ1971 እስከ 1979 ዓ.ም የኔ ጊዜ ነበር ማለት ይቻላል። በእነዚህ ዓመታት በተሳተፍኩባቸው በተለያዩ ሻምፒያና ሁሉ ያጣሁት ዋንጫና ሜዳሊያ የለም። በወቅቱ ኦጋዴን በሚባል ፈረስ ነበር ስሳተፍ የነበረው። ይህን ፈረስ ልክ እንደ ጓደኛዬ ነበር የማየው። ቋንቋ የሚያቅ ነው የሚመስለው›› የሚሉት እንግዳችን፤ ፈረሱን እንደፈለጉት ስለሚያዙት በውጭ ሀገር ጂቡቲ፣ ታንዛኒያ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ተወዳድረው ከ170 በላይ በመዝለል ሪከርድ ያስመዘገቡትም በእርሱ የተሻለ ልምምድ በማድረጋቸው እንደሆነ ይናገራሉ። በ1978 ዓ.ም ደግሞ ‹‹አዋሽ›› የሚባል በጣም የሚታወቅ ፈረስ ስለነበራቸው ጂቡቲ ላይ በተደረገ ውድድር እንዲያሸንፉ ሆነዋል።
በተለያዩ ውድድሮች ያገኘዋቸው ዋንጫዎችና ሜዳሊያዎች አብዛኛው በመከላከያ ሰራዊት ግቢ ውስጥ የቀሩ ሲሆን፤ ከእርሳቸው ፍላጎት ውጪ እንደነበረ ያወሳሉ። በተለይም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ኢታማዦር ሹም የነበሩት ሳሞራ ያገኘዋቸውን የዋንጫና ሜዳሊያ ሽልማቶች ከዛ እንዳይወጣ በማዘዛቸው እዛው መቅረታቸው በጣሙን እንደሚያበሳጫቸው ይናገራሉ። በእርግጥ ሃምሳ አለቃ በቀለ የሜዳሊያና የዋንጫ ችግር የለባቸውም። ይልቁንም የቁም ሳጥናቸውንና የተጋደመውን ትልቅ ሳጥን የሞላው እርሱ ነው። በዚያ ላይ የራሳቸውን ክብር ከፍ ለማድረግ የሚፈልጉ ሰዎች እየተዋሷቸው ወስደው ጨርሰውታል። ግን ይህም ቢሆን ቤቱን ጎዶሎ አላደረገውም።
ፈተና
ብዙ ሰርተው ቤትና ንብረታቸውን ማስተዳደር ይፈልጉ ነበር። ልጆቻቸውንም ተከራይተው እንዳይኖሩ የማድረግ አቅም ይኖራቸዋል። ምክንያቱም በሁሉም ዘንድ በተወዳጅነታቸው ያየለ ነበር። በሥራቸውም የተሻሉ ስለነበሩ በሚያገኙት ገንዘብ ብቻ አንቱታን የሚያተርፍ ተግባራቸውን ያስቀጥሉት ነበር። ግን ምን ያደርጋል በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆነና ነገሩ ያልጠበቁት ነገር ገጠማቸው።
ትራኮማ ይዞሃል ተብለው ያልሄዱበት ህክምና ቦታ አልነበረም። ሆኖም ይባስ ብሎ የነበራቸውን ብርሃን እንኳን እንዳያስቀጥሉት አይናቸው ላይ መርፌ ወግተው 14 ዓመት ሙሉ እንዲታወሩ አደረጓቸው። አሁንም ቢሆን ሰዎችን በድምጽ እንጂ በመልክ አያውቋቸውም። እናም የቤተሰብ ጥገኛ እንዲሆኑና ጡረታ እንዲጠብቁ ተደረጉ። ከዚህ የባሰው ደግሞ በወዳጆቻቸው ተደጋግመው መታለላቸው ነው።
ገንዘብ እንሰብስብልህ በሚል የባንክ አካውንት ካስከፈቷቸው በኋላ አንዳንዱ ከመቶው 10 እጅ የማይሆን ይወረውርላቸዋል። አንዳንዱ ደግሞ ሙሉ ገንዘቡን ወስዶ ማንም አልሰጠም ይላቸዋል። እናም ዛሬ የሚያምኑት ሰው እንኳን እንደሌለ ይናገራሉ። ይህንን የተረዱ ግን አለሁልህ ስለሚሏቸው ያመሰግኗቸዋል። በእነርሱም አጋዥነት እንዳሉ ይናገራሉ። ግን አሁን ድረስ አንድ ነገር እንደሚቆጫቸው ያስረዳሉ። ይኸውም ለአገሬ የከፈልኩትን ያህል አለማግኘቴ ነው ብለዋል።
ቤተሰብ
በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ‹‹ልጅህን ለልጄ›› ግድ ነው። በዚያ ላይ ተጋቢዎች የሚተያዩበት አጋጣሚ አንድም ቀን አይኖራቸውም። የጋብቻቸው ቀን ብቻ ነው ተያይተው የተለያዩት። የእንግዳችን ባለቤትም እንደዚሁ ነው የሆነችው። እርሳቸውም ቢሆኑ በጣም የጠነከሩ ስላልነበሩ ራሳቸውን ይቻሉ ተብለው ከአምስት ዓመታት በኋላ ነው ሀይለኛ ድግስ ተደግሶ እንዲጋቡ የተፈቀደላቸው። ከዚያ ለዓመታት በዚያው እንድትቆይ ተደረገ። ምክንያቱም በካምፕ ያለ ሰው ቤት ተከራይቶ በማምጣት እርሷን ማንገላታት እጅግ ከባድ ነው። ስለዚህ በእዚያው እንድትቆይ ፈረዱባት።
ከብዙ ውጣውረድ በኋላም አዲስ አበባ እንድትመጣ ሆነች። እህታቸው ጋር አርፋ ቤታቸው እስኪረከቡ ድረስም አብረው መኖር ጀመሩ። መጨረሻ አሁን ድረስ እየኖሩበት ያለውን የቀበሌ ቤት አገኙ። ዛሬ በዚህ ቤት ስምንት ልጆች ተወልደው ተምረው፣ ተኩለው ተድረውበታል። አንድ የልጅ ልጅ እንዲያዩም ሆነውበታል።
ምክር
በተለይ አሁን አገሬ ያለችበት ሁኔታ ያሳስበኛል ይላሉ፤ “እናንተ ወጣቶች ከሚያለያያችሁ ብዙ ጉዳዮች ይልቅ የሚያቀራርቧችሁ በጣም ብዙ ነገሮች አሉ። ስለዚህ መገፋፋቱን ትታችሁ ለአገር አንድነት፣ ሰላም እና ብልጽግና እንድትሰሩ እመክራለሁ፤ እውነት ነው ከምንም ነገር በፊት መቅደም ያለበት የሀገር ሰላም ነው። አረጋውያኑ ተጡረው፤ ቢታመሙ አስታማሚ አግኝተው መኖር የሚችሉት እና ሲሞቱም በክብር የሚቀበሩት የሀገር ሰላም ሲኖር ነው። ህጻናት የነገ ሀገር ተረካቢዎች ተምረው ለቁም ነገር የሚበቁት ሀገር ሲኖር ነው፤ ሀገር ሰላም ሲሆን ነው።
ችግሮቻችንን ተመካክረንና ተነጋግረን በመፍታት የህዝቦችን አብሮ መኖር እሴት ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል። ይህንን ችግር ፈተን በመላው ሀገራችን ሰላም እንዲጎለብት የበኩላችንን አስተዋፅኦ ማበርከት ይጠበቅብናል ብለዋል። ችግሮች ቢኖሩ እንኳን በመነጋገር መፍታት ይገባናል።
ለአገር አንድነት የተፈጠሩ ችግሮችን በመፍታት የህዝቦች አንድነትና አብሮነት ትስስር ማጠናከር ይገባናል፤ ተሳስበንና ተደጋግፈን መኖር አለብን ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። እኛም የእንግዳችን መልዕክት መልዕክታችን ነው ።ሰላም!
አዲስ ዘመን የካቲት 1 / 2012 ዓ.ም
ጽጌረዳ ጫንያለው እና አብርሃም ተወልደ