ጥንታዊና ታሪካዊ ከተማ ነች። ደብረ ታቦር። የታሪክ መዛግብት እንደሚያስረዱት ይህቺ ከተማ የተመሰረተችው በአፄ ሰይፈ አርእድ ዘመነ መንግስት ከ1327-1361 ነው። ከተማዋ የተቆረቆረችው ደግሞ በደብረ ታቦር ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን የቅዳሴ መሬት ላይ ነበር። ከዚህ ባለፈ ከተማዋ ከባላባቶች እጅ ወጥታ ለነዋሪው የተመራችው ደግሞ በ1894 በራስ ጉግሳ ወሌ የግዛት ዘመን መሆኑ ይነገራል። ከተማዋ ደብረ ታቦር የሚለውን መጠሪያ ያገኘችው በዚያው በሚገኘው የደብረ ታቦር ኢየሱስ ተራራ ስያሜ መሆኑን በመዛግብት ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ታሪኳ ያስረዳል። ይህ ቤተ ክርስቲያንና ተራራ የያዙትን ስያሜ ያገኙት ደግሞ በእየሩሳሌም ውስጥ ካለ ተራራ ስም መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ሁለቱም ተራሮች ደግሞ የእውቀት ብርሃን መገለጫ በመሆናቸው ስያሜውን ማግኘት ችለዋል። ጌትነት ከቤ የደብረ ታቦር ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ፅህፈት ቤት ኃላፊ ስለከተማዋ አጠቃላይ መረጃ በሚሰጡበን ወቅት ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ዝርዝር መግለጫዎችን አስረድተውን ነበር። በዚህም ደብረ ታቦር ከተማ ከዘመነ መሳፍንት በፊት 1776 እስከ 1845 ከዘመነ መሳፍንት በኋላ ከአፄ ቴዎድሮስ እስከ ዩሃንስ ዘነመ መንግስት የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ነበረች።
በተጨማሪም በደጃች ወሰንና በንጉስ ወልደ ጊዮርጊስ የግዛት ዘመን የጎንደር ዋና ከተማ ቀጥሎም የማእከላዊ በጌምድር ጠቅላይ ግዛት አንጋፋ ከተማ መሆኗ ይታወቃል። በአሁኑ ሰዓት ደግሞ የደቡብ ጎንደር ዞን ርእሰ ከተማ በመሆን እያገለገለች ትገኛለች። ይህች ጥንታዊት ከተማ በርካታ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ እሴቶች መገኛ ከመሆኗም በላይ አኩሪ ባህልና ታሪክ ያላቸው ነገስታት ተነስተው አንፀባራቂ ስራ የሰሩባት ነች።
ደብረታቦር ከላይ ከተነሱት ሀሳቦች ባሻገር በተፈጥሮ ይዘቷም ለሰው ልጆች መኖሪያ ተስማሚ አየር እንዳላት ይገለፃል። በተለይ የከተማዋ አመሰራረትና መልክአ ምድር ብሎም የህዝቡ አሰፋፈር ልዩ መስህብነቷን አጉልቶ ማሳየት የሚችል ነው። ከዚሁ ሁሉ በላይ መስህብነቷን አጉልቶ የሚያሳየው በአፍሪካ የመጀመሪያው የጋፋት ኢንዱስትሪ መንደር የተገነባባት መሆኗ ነው። ደብረ ታቦር ቀደምት ከተቆረቆሩ ከተሞች መሀከል አንዷ በመሆኗ እንዲሁም የበርካታ ነገስታት መቀመጫ ስለነበረች በውስጧ እጅግ በርካታ የነገስታት ስጦታዎች፣ ቅርሶች ተፈጥሯዊና ታሪካዊ የመስህብ ቦታዎች መገኛ ናት።
ጋፋት የኢንዱስትሪ መንደር ጋፋት የኢትዮጵያን አንድነት በብርቱ በሚሹትና ባስጠበቁት አፄ ቴዎድሮስ የጦር መሳሪያ እንዲሰራባት የመረጧት ቦታ ነበረች። ይህ ስያሜም በአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎች መገለጫ እንደነበርም ይነገራል። በተለይ አፄ ቴዎድሮስ ይህን ስፍራ ከመምረጣቸው በፊት ነገደ ጋፋት ወይም ነገደ እስራኤል በመባል የሚታወቁ ጋፋትኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች እንደነበሩ ይነገራል። እነዚህ ነገዶች በተለያዩ የእደ ጥበብ ስራ ማለትም በብረታ ብረት፣ በሸክላ፣ በሽመና እንዲሁም ቆዳ በማለስለስና የተለያዩ ስራዎች ላይ ተሳታፊ ነበሩ። በዚህ ምክንያት ንጉሱ እንግሊዞች በምርኮ ይዘዋቸው የነበሩትን ነጮች ከአገሬው ሰው ጋር አስተባብረው ሴባስቶፖል ብለው የሰየሙትን ያሰሩበት ቦታ ነው። ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ይህ ቤተ ክርስቲያን ከደብረ ታቦር ከተማ ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዳለው ይነገራል።
አሁን ያለውን ቅርፅ እስኪይዝ ድረስ ከ1333 ጀምሮ ሶስት ጊዜ ፈርሶ ታድሷል። አሁን ያለው የህንፃው ጥበብ ለእይታ ማራኪ ከመሆኑም በዘለለ በዘመኑ የነበረውን ጥበብ የሚያሳይ ነው። በግቢው ውስጥ በአገራችን ብቸኛው የሆነው የተክሌ አቋቋም ዝማሜ ማስመስከሪያ ዩኒቨርስቲ ከመገኘቱ በላይም የራስ ጉግሳ መካነ መቃብር በውስጥ ይዟል። በርካታ የነገስታት ስጦታ እቃዎች አልባሳትና ማጌጫዎች ተጠቃሽ ከሆኑ ቅርሶች ውስጥ ይመደባል። ሰመርነሃ የአፄ ዩሃንስ አራተኛ ቤተ መንግስት አፄ ዩሃንስ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ተብለው ከነገሱበት ጊዜ ጀምሮ አገራቸውን እየተዘዋወሩ ሲመለከቱ ደብረ ታቦር ሰመርነሃ ከተባለ ቦታ ደረሱ። ቦታውንም ስለወደዱት ስሙን ሰመርነሃ ሲሊ ሰየሙት።
ስያሜው የግእዝ ቃል ሲሆን ትርጉሙም ወደድናት ማለት ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቦታውን የንጉሱ የክረምት ቤተ መንግስት ሆኖ ለረጅም ዓመታት ማገልገል ችሏል። የፈረስ ጉግስ በዓል በደብረ ታቦር የፈረስ ጉግስ በዓል በደብረ ታቦር ጥር 25 ቀን የቅዱስ መርቆሪዮስ ንግስ በዓል አከባበርን ምክንያት በማድረግ አጅባር በተባለ ሰፊ ሜዳ ጥምቀተ ባህር ላይ በደማቅ ሁኔታ የሚከበር ነው።
ይህ በዓል በፈረስ ጉግስ እንዲከበር ካደረጉት ታዋቂ ግለሰቦች መሀል በግንባር ቀደምትነት የነበሩት ፊታውራሪ አለነ ገብሬ እንደሆኑ ይነገራል። እኚህ ግለሰብ በራስ ጉግሳ ወሌ ዘመን የእርሳቸው ባለሟል ነበሩ። ክብረ በዓሉ በትውልድ አገራቸው ይከበር ስለነበርም ለጥረታቸው ስኬት መነሻ ሆኗል። ሀሳባቸውን ለማሳካት የአካባቢውን ህዝብ በማስተባበር በዓሉ በፈረስ ጉግስ በደማቅ ሁኔታ እንዲከበር አድርገዋል። የፈረስ ጉግስ ውድድር በተለይ በደብረ ታቦር በተደራጀ ሁኔታ ከ1940 ዓ.ም ጀምሮ እየተከበረ ይገኛል። ይህ ጨዋታ ፈረሰኞች በቡድን ተደራጅተው በዘንግ ከምትዘጋጅ ልምብጭ የጦር ውርወራ የሚወራወሩበት፣ ጋላቢዎች የሚወደሱበት ለአይን ውብ በሆነ መልኩ ፈረሶቻቸውም ፈረሰኞቹም አምረው ደምቀው የሚታዩበት ነው። በተለይ ታዳሚው ቀልቡን በሚማርክ መልኩ ተጫዋቾቹ ትርኢታቸውን ያቀርባሉ።
ረዳት ፕሮፌሰር መምህር እርጥባን ደሞዝ በደብረ ታቦር ዩኒቨርስቲ መምህርና የባህል ማእከል ዳይሬክተር ናቸው። ባሳለፍነው ሰኞ ጥር 25 እለት ተከብሮ የዋለውን የቅዱስ መርቆሪዎስ ንግስ በማስመልከት የተዘጋጀውን የፈረስ ጉግስ ጨዋታ በማስመልከት በተዘጋጀ የፓናል ውይይት ላይ ‹‹የፈረስ ጉግስ ድርጊቶች እና ተግዳሮቶች›› በሚል ጥናታዊ የዳሰሳ ፅሁፍ አቅርበው ነበር። በዚህም የዚህን ባህላዊ ጨዋታ እና እሴቶች በመዳሰስ ወደፊት ፈር ሳይለቅ ለትውልድ እንደሚተላለፍበት መንገድ ጥቆማና መፍትሄዎችን አመላክተዋል። በተለይ ይህን ውብ ባህላዊ ጨዋታ እንዴት ወደ ቱሪዝም መስህብነት መለወጥ ይቻላል በሚለው ጉዳይ ላይ ለዝግጅት ክፍላችን አጭር ማብራሪያ ሰጥተውናል።
የፈረስ አገልግሎት ታሪካዊ ዳራ እንደ እረዳት ፕሮፌሰሩ ገለፃ የፈረስ ግልቢያ አሊያም የፈረስ ጉግስ ጨዋታ በተለይ በነገሥታቱና መሳፍንቱ ይታወቅ ነበር ከዚህ ባለፈ በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች በታላቁ መፅሐፍ ቅዱስ ላይ ‹‹ዳዊትም ከእርሱ ሰረገላዎችን፣ ሰባት ሺህ ፈረሰኞችን፣ ሃያ ሺህ እግረኞችን ያዘ›› በማለት መዝሙር 2 ሳሙኤል ምእራፍ 8 ቁጥር 4 ላይ መመዝገቡንና ሃይማኖታዊ ይዘቱም ጉልህ እንደነበር ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ ባለፈ የዘመን መገለጫ እንደነበርና ፈረስ ልዩ ስፍራ ይሰጠው እንደነበር ያነሳሉ፡፡
በተለይ በግእዝ ቋንቋ ‹‹ርኢኩ ፈረስ ፀዐዳ፣ ወጽአ ካልእ ፈረስ ቀይሕ፣ ፈረስ ጸሊም፣ ፈረስ ሐመልሚል›› በማለት በመፅሐፍ ቅዱስ ራዕይ ዮሐንስ ምእራፍ 6 ላይ የተለያዩ የፈረስ አይነቶች በዝርዝር ይቀመጡ እንደነበር ያብራራሉ። ከዚህ የተነሳ ኢትዮጵያውያን ነገስታት የፈረስ ግልቢያ ሥልቱን መልመድ የግድ ነበር፡፡
አመራርነት ወይም ህዝብን የማስተዳደር ጥበብ እንደሚለምዱት ሁሉ የፈረስ ግልቢያ፣ የአደን ሥርዓት ማወቅ አንዱ መስፈርት እንደነበርም ረዳት ፕሮፌሰርነ እርጥባን ይናገራሉ። ዳሰሳዊ ጥናቱን በተለይ ደግሞ በደብረ ታቦር ደቡብ ጎንደር ፈረስ ያለውን ፋይዳ ለመመራመር ጥረት ያደረጉት ረዳት ፕሮፌሰሩ ታሪካዊ ዳራውን ለማስቀመጥ ሲሞክሩ በዘመኑ ነገስታትም ሆኑ የዘመኑ ማህበረሰብ ከነፋስ የሚፈጥኑ ፈረሶቻቸው ጋር እጅግ ጥብቅ ቁርኝት እንደነበራቸው ይናገራሉ። በተለይ የውጪ ወራሪ ጠላት በመጣ ሰዓት ለማጥቃትና ለመከላከል ፈረሶቻቸው ቀዳሚ ባለውለታ እንደነበሩ ያነሳሉ።
ከዚህም ሌላ ወዳጅ አገራትን በጦርነት በሚረዱ ጊዜ ፈረሶቻቸውን ይጠቀሙ እንደነበር የታሪክ መዛግብት እንዳሰፈሯቸው ይገልፃሉ። ለዚህ ማሳያ ኢትዮጵያዊው ንጉስ ካሌብ የመንን በረዳ ጊዜ ፈረሶችን መጠቀሙን ለማሳያነት ያነሳሉ። አፄ ፋሲል (ዞብል) የተባለ፣ አፄ ምኒልክ (አባ ዳኛው) የተባለ፣ አፄ ቴዎድሮስ (አባ ታጠቅ) የተባለ ፈረሶቻቸው ይጠቀሙ እንደነበርም በታሪክ ማጣቀሻነት ያስቀምጣሉ፡፡ በተለይ ነገስታትና ጀግና የጦር መሪዎች ከፈረሶቻቸው ጋር ያላቸውን ጥብቅ ቅርበት ለማሳየት ስያሜ ይሰጧቸው እንደነበር ረዳት ፕሮፌሰር እርጥባን የተለያዩ መዛግብትን ጠቅሰው የፅሁፋቸውን ዳራ ያጠናክራሉ። በተለይ ፈረሰኞችና አድዋ፣ በልዩ ሁኔታ በጣሊያን ወረራ ትልቅ ታሪክ አላቸው።
ፈረስ በፈረሰኞች ለተለያየ ጥቅም ይውል ነበር። አሁንም ድረስ ለተለያየ አገልግሎት በተለይ በደቡብ ጎንደር ግልጋሎት ይሰጣል። በተለይ ዋነኛውና ተፈላጊነቱ ለትራንስፖርት ሲሆን ድሮ ድሮ ደግሞ ለጦርነት በቀጥታ ይገለገሉበት ነበር። ለዚህ እንደ ማሳያ የሚሆኑት ከላይ ለማንሳት እንደተሞከረው (ንጉስ ካሌብ፣ አፄ ፋሲል፣ ቴዎድሮስ) ልክ እንደ የጦር ጀት ይጠቀሙባቸው ነበር። አሁን አሁን ደግሞ ከትራንስፖርት መገልገያነት ባሻገር ለደስታ ወይም ለሰርግ ማስዋቢያ፣ ለተለያዩ ክብረ በዓል ዝግጅቶችና ለኀዘን ወቅት ለሚደረግ ባህላዊ ስርዓት ይውላሉ። የደቡብ ጎንደር ዞን የፈረስ ጉግስ ቱሪዝም የደቡብ ጎንደር ፈረሰኞች በሁለት ምድብ አሰላለፍ አድርገው በባህላዊና ሃይማኖታዊ ክብረ በዓላት ላይ ጉግስ ይጫወታሉ።
የጨዋታ ሂደት የድሮውን የጦር ስልት የተከተለ ሲሆን እጅግ ማራኪ በሆነ መልኩ በሰፊ ሜዳ ላይ የሚያሳዩት ትርኢት ነው። በጨዋታው አስፈሪ የሆኑ እንቅስቃሴዎች እና ድርጊቶች የታጀበ ሲሆን ድርጊቱ የጦርነት ስልትን የተከተለ ከመሆኑ ጋር የተያያዘ ነው። ሆኖም ግን ከጫዋታው በፊትና በኋላ ፈረሰኞች በፍቅርና በመተሳሰብ ያለምንም ቂምና ጠብ ግብዣ የሚያካሂዱበት ስነ ስርዓት ነው። የመጋለቢያ ወይም የመጫወቻ ወቅት በወርኃ ጽጌ (ቅዳሜ፣ እሑድ) ፣ ወርኃ ታኅሣሥና ጥር ( ታኅሣሥ 24፣ ጥር 18፣ ጥር 19፣ ጥር 21፣ ጥር 25) ውስጥ ይከናወናል፡፡
እንጅባራና የቅዱስ መርቆሬዎስ የፈረስ ግልቢያ በተለይ የደቡብ ጎንደር ደብረ ታቦር ድምቀትና መስህብ ነው። የፈረስ ጉግስ ተግዳሮት ረዳት ፕሮፌሰር እርጥባን ይህ ባህላዊ ስነ ስርዓት ዩደቡብ ጎንደር ህዝብ ማንነት መገለጫ መሆኑን ይናገራሉ። ሆኖም ግን አሁን አሁን እንደ ከዚህ ቀደሙ ፈረሶች የሚሠማሩበት አሊያም የሚቀለቡበት ክልክል ሣር ፈቃድ ያለ ማግኘት ችግር ባህላዊ ስነስርዓቱ ላይ ጋሬጣ እየሆነ መምጣቱን ያነሳሉ። የኮርቻ ዕቃዎች፣ ባለሙያዎች መቀነስ እንዲሁም እንደ ልብ ገበያ ላይ ያለ መገኘት ደግሞ ሌላኛው ፈተና መሆኑን ይጠቅሳሉ። በተለይ የፈረስ ዋጋ መጨመር፣ የፈረስ መጋለቢያ ቦታዎች መጥበብ፣ አንዳንድ ቦታዎችም ጨርሶኑ መጥፋት፣ ጠንካራ የፈረሰኞች ማኅበር ያለመኖርና ተከታታይ ስልጠናዎች ያለመዘጋጀታቸው እንደ ተግዳሮት ያነሱታል።
የደብረታቦር ዩኒቨርስቲ ባህል ማእከል ዳይሬክተር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰሩ ችግሮቹን ብቻ አንስተው ሀሳባቸውን አይቋጩም። ይልቁኑም የማህበረሰቡ የማይተካ እሴት መሆኑን የሚያነሱትን የፈረስ ጉግስ ለማሳደግና በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ ጎብኚዎች ተመራጭ እንዲሆን የሚያስችል የመፍትሄ ሀሳብ ይሰነዝራሉ። ለዚህ ሁነኛ ነው ያሉት ደግሞ ዞናዊ የሆኑ ሰፊ የፈረስ ቱሪዝም ድርጊቶችን እንዲፈጸሙ በሰፊው መስራት ቀዳሚው ነው። በተለይ በመስቀል፣ የአድዋ ድልን በመሰለ የሰማዕታት በዓላትና በሌሎችም ክብረ በዓላት ላይ ማስተዋወቅ አስፈላጊ መሆኑን ይጠቅሳሉ። ከዚህ ባለፈ ሰፋፊ ሜዳዎችን ማዘጋጀት፣ ሥልጠናዎችን መስጠት፣ የተሻሉ የፈረስ ዝርያዎችን ማዘጋጀት አሊያም ማርባት ተወዳጁን የደብረታቦር የፈረስ ጉግስ ጨዋታን ያሳድገዋል በሚል መፍትሄ ሀሳብ ሀሳባቸውን ይቋጫሉ።
አዲስ ዘመን የካቲት 1 / 2012 ዓ.ም
ዳግም ከበደ