እጆቻቸው የቆዳ ምርቶችን አስውቦ ለአልባሳትነት የማዋል ጥበብን ተክነዋል። ከአገር ውስጥ አልፈው በአውሮፓ እና አፍሪካ ሀገራት በጥራታቸው የተመረጡ የቆዳ አልባሳትን አዘጋጅተው በማቅረብ ከእራሳቸው አልፈው ለበርካቶች ገቢ ፈጥረዋል።
ከአባታቸው የቀሰሙት ጠንካራ የስራ ልምድና የትጋት መንፈስ ለውጤት እንዳበቋቸው ይናገራሉ። በርካታ ዓመታትን ስራቸውን በማሳደግ ደፋ ቀና ሲሉ መኖራቸውን እና ያላቸውን ልምድ ለማካፈል የሚታትሩ ሴት መሆናቸውን ደግሞ የሚያውቋቸው ይመሰክራሉ።
ልጅና አባት
ወይዘሮ አባይነሽ በየነ ይባላል ሙሉ ስማቸው። ትውልድና እድገታቸው በአዲስ አበባ አውቶቡስ ተራ አካባቢ ነው። እድሜያቸው በአርባዎቹ መጀመሪያ ላይ የሚገኘው ወይዘሮ አባይነሽ ሰፊ ቤተሰብ ውስጥ ነው ያደጉት። ወንድምና እህቶቿን ጨምሮ ከዘመድ አዝማድ ጋር 13 ልጆች የነበሩበት ቤት ውስጥ ተጫውተው አድገዋል። ይህን ሁሉ ቤተሰብ ደግሞ የሚያስተዳድሩት ጠንካራው አባታቸው አቶ በየነ ናቸው።
በመኪና ወንበር ስራ ወይም ታፒሰሪ ሙያ ላይ የተሰማሩት አባታቸው ፒያሳ አካባቢ ወደሚገኘው የስራ ቦታቸው ማቅናት የዘወትር ተግባራቸው ነበር። ወደስራ ሲሄዱ ግን የያኔዋን ህጻን አባይነሽን የሚሰሩትን የመኪና ወንበር እንዲመለከቱ በሚል አንዳንድ ጊዜ ይወስዷቸው እንደነበር አይረሱትም።
በዚህም ምክንያት ወይዘሮ አባይነሽ በተደጋጋሚ አባታቸው የቆዳ ወንበሮች ሲሰፉ የመመልከት እድል አግኝተዋል፤ እናም በልጅነታቸው ወደስፌቱ መሳባቸው አልቀረም። ከቆዳ ስፌቱ በተጨማሪ ግን የመኖሪያቸው አካባቢ የንግድ እንቅስቃሴ አባይነሽን ይስባቸው ነበር። ይሁንና የአስኳላውን እውቀት መቅሰም ነበረባቸውና ወደንግዱም ወደሙያውም ከመግባታቸው አስቀድሞ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ገቡ።
በመኖሪያ አቅራቢያቸው በሚገኙት የካቲት 23 ትምህርት ቤት እና አዲስ ከተማ ትምህርት ቤት ገብተው ከአንደኛ ክፍል እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። በትምህርት ወቅትም ቢሆን የዕረፍት ሰዓታቸውን በመጠቀም የአባታቸውን ወንበር ስራ የመመልከቱን ልምድ አላስተጓጎሉም ነበር።
ኑዛዜ በህይወት ሳሉ
12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያን እንደተፈተኑ ግን የቅርብ ዘመዳቸው በማረፉ ምክንያት አባታቸው ለለቅሶው ይዟዋቸው ወደ ክፍለ ሃገር ያቀናሉ። ለሃዘን በሄዱበት ቤት ደግሞ ሟች አስፈረውት የነበረው የኑዛዜ ደብዳቤ ሲነበብ ያደመጡት ወይዘሮ አባይነሽ ነገሩ እንግዳ ይሆንቦዋል።
<<ለአንዱ ልጅ ይህን ያህል ገንዘብ ለሌላው ደግም ይህን ያህል ንብረት ይሰጠው>> እየተባለ ኑዛዜ ሲነበብ በህይወት እያሉ ለምን አልሰጧቸውም ለምንስ ከሞቱ በኋላ ገንዘቡ ይከፋፈላል ብለው አባታቸውን ይጠይቃሉ። እርሳቸው ግን በተለየ መልኩ አባታቸው በህይወት እያሉ ኑዛዜ እንዲናዘዙላቸው እና በሚሰጣቸው ገንዘብም ስራ መጀመር እንደሚፈልጉ ይገልጹላቸዋል።
አባታቸውም <<ሳልሞት የኑዛዜ ገንዘብ እንዴት ይሰጣል>> ቢሏቸው፤ በገንዘቡ ሰርቼ አባቴን በህይወት እያለ መጥቀም ነው የምፈልገው በማለት ፍላጎታቸውን ይናገራሉ። በነገሩ አባት ቢገረሙም በልጃቸው አርቆ አሳቢነት ግን ተደስተው ነበር።
እናም አባታቸው በሃሳቡ ተስማምተው አምስት ሺህ ብር ከኑዛዜ ላይ እንደሚደርሳቸው ገልጸው ይሰጧቸዋል። ወይዘሮ አባይነሽም ገንዘቡን ይዘው በልጅነት የሚያዩትን የአባታቸውን የቆዳ ወንበር ስፌት ሙያ እና የእራሳቸውን የስፌት ፍላጎት አጣምረው በ1989 ዓ.ም የቆዳ ልብሶች ምርት ላይ ለመሰማራት <<ሀ>> ብለው ለስራ ተነሱ።
ወደ መጀመሪያው ምርት
አዲስ አበባ መሳለሚያ አካባቢ አነስተኛ ቤት በአንድ ሺህ ብር ተከራይተው ጥቂት የቆዳ ጥሬ እቃዎችን ለግብአትነት ገዙ። በወር 150 ብር ኪራይ የሚከፈልበት አንድ የስፌት ማሽን ሲንጀርም ተከራዩ። በመጀመሪያ ሙከራቸው ቤት ውስጥ የነበራቸውን የጅንስ ጃኬት ዲዛይን መሰረት አድርገው የሌዘር ጃኬት ሰፍተው አጠናቀቁ።
ይህ ጥረት ታዲያ ብርታትን ሰጥቷቸው በእራሳቸው ዲዛይን እያዘጋጁ የቆዳ ምርቶችን ወደጃኬትነት የመቀየር ስራውን አጠናከሩት። ስራ ከጀመሩ ከአንድ ወር በኋላ ደግሞ ሁለት የቆዳ ስፌት ባለሙያዎችን ቀጥረው ዲዛይን እያዘጋጁ ማምረቱን ተያያዙት።
የወይዘሮ አባይነሽ አባት ልጃቸውን በሙያቸው ከማገዝ በተጨማሪ የተዘጋጁ የቆዳ ጃኬቶችን ለጓደኞቻቸው በማስተዋወቅ እና በመሸጥ ስራውን ያበረታቱ ነበር። ይህ እገዛ ያጠነከራቸው ወይዘሮ አባይነሽ በእራስ መተማመናቸው እና የእችላለሁ መንፈሳቸው ጎልብቶ የተሻለ ገቢን መሰብሰብ ጀመሩ።
ከመርካቶ አካባቢ ቆዳ እና የተለያዩ ግብአቶችን በመግዛት ወደልብስነት ቀይረው አንዱን ጃኬት በ1ሺህ 500 ብር መሸጡን ተያያዙት። ከአባታቸው ላይ የወሰዱትን የኑዛዜ ድርሻ አምስት ሺ ብር ከአምስት ወራት በኋላ መልሰው ከኑዛዜ ውጭ የሆኑበትን ሁኔታ እንደገና አደሱ። አባታቸውም በሆነው ሁሉ ተገረሙ።
በወቅቱ ደግሞ አባታቸው በቆዳ ጃኬት ስራው በመደሰታቸው እና ለስራ ማስጀመሪያ የሰጡት የኑዛዜ ብር ሲመለስ ይበልጡን ልጃቸውን ማበረታቱን ገፉበት። ወይዘሮ አባይነሽም ስራውን እና ገበያውን እየተላመዱ በመምጣታቸው ከጃኬቱ በተጨማሪ የቆዳ ቦርሳዎችን ወደ ማዘጋጀቱ ተሸጋገሩ።
ተጨማሪ አምስት ሰራተኞችንም ቀጥረው ኤቢ በተሰኘው የምርት ስማቸው አማካኝነት የቆዳ ምርቶች ገበያው ላይ የእራሳቸውን አሻራ ማሳረፉን ሲቀጥሉ ምርታቸውም በጥራቱ ተወዳጅ ሆነ። ከዚያም ከጃኬት እና የጉዞ ቦርሳዎች የሚተርፈውን ቆዳ ለኪስ የወንድ ቦርሳ እና ቀበቶ መስሪያ እያዋሉ በስፋት የቆዳ ምርቶች ላይ መሳተፉን ተካኑበት።
ከጊዜ በኋላም እህታቸው አብረዋቸው የቆዳ ጫማ ማምረት ጀመሩ። ለአምስት ዓመታት አብረው ካመረቱ በኋላ ግን እህታቸው በትዳር ምክንያት የጫማ ስራውን ሲያቆሙት ወይዘሮ አባይነሽ የቆጃ ጃኬትና የጉዞ ቦርሳዎች ላይ አተኩረው ስራቸውን ቀጠሉ። በአምስት ዓመታት ውስጥ ገቢያቸው እያደገ ስራቸው በመላ ሀገሪቷ መዳረስ ሲጀምር ደግሞ ተጨማሪ ማምረቻ ቦታ እንዲፈቀደላቸው ጠየቁ።
ስራ ሲጎለብት
የቆዳ ጃኬቶቹ ለተጨማሪ ሰዎች የስራ እድል መፍጠር የሚያስችል በመሆኑ እና ወይዘሮ አባይነሽም የካፒታል አቅማቸው በማደጉ ጎሮ አካባቢም ለኢንዱስትሪ ዘርፍ በሚል ቦታ ተሰጣቸው። እናም የተለያዩ የቆዳ ማዘጋጃ ማሽኖችን ገዝተው ከመሳለሚያው ስራ ቦታ በተጨማሪ ጎሮ ላይ ምርቶችን ማዘጋጀቱን ተያያዙት።
በእራሳቸው ዲዛይን ሰርተው የሚያመረቱትን የጃኬት እና የጉዞ ቦርሳዎችንም ኬንያ፣ ኖርዌይ እና ዱባይ ድረስ በመሄድ እያስተዋወቁ በመሸጥ ለሀገርም የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት ችለዋል።
ምርቶቹ በተለይ ወደውጭ ሀገራት ሲሄዱ በጥራታቸው እና በዲዛይን ምቹነታቸው የተነሳ ተፈላጊነታቸው ከፍተኛ መሆኑን የሚናገሩት ወይዘሮ አባይነሽ፤ አቅምን አጠናክሮ መስራት ከተቻለ እሴት ተጨምሮባቸው የሚላኩ ኢትዮጵያ የቆዳ ምርቶች ከፍተኛ ገቢ ማስገኘት የሚችሉበት እድል ሰፊ መሆኑን ያስረዳሉ።
አሁን ላይ 20 የሚደርሱ የቆዳ ማዘጋጃ ማሽኖች ባለቤት ናቸው። በድርጅታቸው ስርም 30 ሰራተኞችን ቀጥረው የስራ እድል መፍጠር ችለዋል። ስራ ካለ በቀን ውስጥ የተለያየ የቀለም አይነት እና ዲዛይን ያላቸውን 75 የቆዳ ጃኬቶችን ማምረት የሚያስችል አቅም እንዳላቸው ያስረዳሉ።
የወይዘሮ አባይነሽ አንዳንድ ምርቶች አሁን ላይ እስከ አስር ሺህ ብር ድረስ ያወጣሉ። በሁለቱም በኩል የሚያዝበት የሴት ልጅ ቦርሳ አራት ሺ ብር ሲሸጡ፣ የቆዳ ጃኬቶችን ደግሞ በሁለት ሺህ አምስት መቶ ብር ለገበያ ያቀርባሉ። ለጉዞ የሚሆን እና በውስጡ በርካታ የልብስ መያዣ ክፍሎች ያለው የመንገደኛ ሻንጣ 10 ሺህ ብር ይሸጣሉ።
ምንም እንኳን አሁን ላይ የቆዳ ስራ ገበያው ቢቀዛቀዝም ስራ በሚኖርበት ወቅት በዓመት እሰከ 500 ሺህ ብር ድረስ የተጣራ ትርፍ የሚያገኙበት ወቅት እንዳለ ይገልጻሉ። አንድ ጊዜ መስሪያ ቦታ ሌላ ጊዜ ደግሞ ሽያጭ ላይ የሚገኙት ጠንካራዋ ሴት፤ ቦሌ መድሃኒያለም አካባቢ በተከራዩት የህንጻ ሱቅ ውስጥ ደግሞ ምርቶቻቸውን በመሸጥ ደንበኞቻቸውን ሲያስተናግዱ ይውላሉ።
ሲያሻቸው ደግሞ ግዥ ላይ ተሰማርተው የሚውሉት ወይዘሮ አባይነሽ፤ ለምርት የሚሆነውን በከፊል የተዘጋጀ ጥሬ ቆዳ ሞጆ እና አዲስ አበባ ከሚገኙ ፋብሪካዎች ተረክበው ይሰራሉ። ቁልፍ፣ ዚፕ እና የተለያዩ ግብአቶችን ደግሞ ከመርካቶ ሸማምተው ይጠቀማሉ።
ስራው ግን ለሴት ልጅ አድካሚ ቢሆንም አንድም ቀን ሊያቆሙት እንዳልፈቀዱ ይመሰክራሉ። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ትችያለሽ፤ ጠንካራ ሴት ነሽ እያሉ አባታቸው የሚሰጧቸው የሞራል ግንባታ ውጤት መሆኑን ነው የሚናገሩት።
ቀጣዩ ውጥን
ወይዘሮ አባይነሽ ቀጣይ እቅዳቸው ምግብ ነክ ምርቶችን እያሸጉ ለውጭ ሀገራት ማቅረብ ነው። ለዚህም የሚሆን የጥናት እና ዝግጅት ስራዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ።
በዝግጅታቸውም ከካፒታል ጀምሮ ምን አይነት ማሽን እና የትኞቹ ምግቦችን አሽገው ቢያቀርቡ አዋጭ እንደሚሆንላቸው ልምዱ ካላቸው ሰዎች ጭምር ግብዓት እየወሰዱ ይገኛሉ። ልክ እንደ ቆዳ ጃኬቶቹ ሁሉ የኢትዮጵያን ስም የሚያስጠሩ የታሸጉ ምግቦችን ወደውጭ በቅርቡ መላክ እንደሚጀምሩ እምነታቸው የጸና ነው።
የሁለት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ አባይነሽ ቤተሰብ ከማስተዳደሩ ጋር ተጨማሪ ስራው እንደማይከብዳቸው አምነዋል። ዋናው ለሰው ልጅ የስራ እድገት እችለዋለሁ የሚል መንፈስ ማዳበር መቻል ነው ይላሉ።
በተለይ ሴት ሆነው ጫና እንዳለባቸው በማሰብ እና ደካማ ነኝና ይህ ስራ ይከብደኛል ብለው ንግድ የሚጀምሩ ሰዎች ውጤታማ የመሆን እድላቸው ዝቅተኛ በመሆኑ ከወዲሁ የጠንካራ መንፈስ ባለቤት መሆን እንዳለባቸው ምክራቸውን ይለግሳሉ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 30/2012
ጌትነት ተስፋማርያም