ይህች ኑሯችን ብዙ አሳይታናለች። በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥም አሳልፋናለች። አንዳንዱ ሰው፣ አፈር ባፍ ባፍንጫው እስኪሰፈር ድረስ በእንቢታዬ እዘልቃለሁ ብሎ የማለ ነው።አንዳንዱ ደግሞ በነገር ሁሉ እሽታውን የኑሮው ዘዬ ያደረገ ነው።እኒህን መሰል ሰዎች ጠርዝ ለጠርዝ ሆነው ወይ ያደምቁናል፤ አለዚያም ያደቅቁናል።
ለመሆኑ እሺ ባይነት፣ የተፀናወታቸው ሰዎች ምን ዓይነት ተፈጥሮ ያላቸው ናቸው? እኒህን መሰል ሰዎች “እምቢን- ፈሪዎች”ና እሺ ካላልን ሰው ይቀየመናል፤ ብለው የሚያስቡ ዓይነት ሰዎች መሆናቸው የታመነ ነው።ስለዚህ ከአፋቸው “እሺ” አይጠፋም።እሺ ካሉት ነገር ግን ግማሽ በግማሽ ወይም ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ አይሳካላቸውም።
ባለቅኔው ዮፍታሔ ንጉሴን በዚህች ቃል ሳቢያ ደግሜ ላነሳው እወዳለሁ።
“ተስቦ ገብቷል ቤታችን ፣
መቼ ይወጣል በሽታችን።” (1929 እንደጻፈው ይታመናል)
በ1928 ዓ/ም ጣሊያን ኢትዮጵያን በግፍ በወረረበት ጊዜ የአርበኞችን ልብ ለማነቃቃት የገጠመው ግጥም ነው።የግጥሙ ግልጽ ሃሳብ፣ በሽታ ወይም ተስቦ ይምስል እንጂ፣ በሰሜን በኤርትራ ምድር በደቡብ በሶማሊያ /ወልወልን ያስታውሷል/ አድርጎ ጠላት ተስቦ ገብቷል።ይሁንናም በሽታ የሆነው ጠላት እኛ ዝም ስላልነው ሃገራችንን ለቅቆ ወይም “እሺ” ብሎ አይወጣምና፤ “እሺ” አንበለው ዝም አንበለው፤ ለማለት ነው፤ ዋነኛው የዮፍታሔ መልዕክት።በእሺታችን አናሸንፈውም፤ እንዲያውም እሺታችን ጠላት በምድራችን እንዲንሰራፋና እንዲያጠፋን በር ይከፍትለታል፤ ነው ያለው።እሺታ በሽታ እንደሚሆንም ልብ ይሏል።
ሁሉን እሺ ባይ ሰዎች፣ ለእሺ ባይነታቸው፣ እንደ ምክንያት የሚቆጥሩት፣ ከልጅነታቸው ጀምሮ ከልካይነትና የለም ባይነት፣ ክፋትና ኃጢያት ተደርጎ ሲነገራቸው ያደጉና በዚሁ የቀጠሉ ናቸው።አለበለዚያም እምቢ በማለታቸው ወሳኝ በሆነ ጉዳያቸው ላይ ቀደም ሲል ባጡት ነገር ውስጣቸው በሀዘን የተሞላ ነው።ስለዚህ እምቢ ማለትን ይፈራሉ።
በሥነ-ልቡና ተንታኞች ዘንድ ብዙ ዓይነት ፍርሃት ያለ ሲሆን፣ መንዳትን መፍራት፣ አንዳንድ የምግብ ዓይነቶችን መብላትን መፍራት፣ ዝግ ስፍራን መፍራት፣ ጨለማን መፍራት፣ አይጥ መፍራት፣ ከፍታን መፍራት፣ እምቢታን መፍራት….ወዘተ በመሰኘት ይከፋፈላል።ይህ አይነቱ ስሜት ከልዩ ልዩ ፍርሃት ዓይነቶች ውስጥ እንደ አንዱ የሚመደብ ሲሆን ሰዎቹ “እምቢታን ፈሪዎች” በመባል ይታወቃሉ።
እምቢን የሚፈሩ ሰዎች የፍርሃታቸው መነሻ አስተዳደጋቸው ነው፤ ነው የሚባለው። ሰዎች በአስተዳደጋቸው፣ ወቅት ይህንን ባህሪ የሚያሳድጉበት ፍርሃት እያዳበሩ ነው፤ የሚመጡት። ከሚወዷቸውና ከሚያደን ቋቸው ሰዎች ጋር ተግባብተው ለማለፋቸው ምክንያት እሺ ባይነታቸው ነው፤ የሚመስላቸው።
ስለዚህ የማይቻሉ የሚመስሉና አንዳ ንዴም የማይቻሉ፣ ነገሮችን ሲጠየቁ አይቻልም ማለት አይፈልጉም።ስለዚህም እሺታቸው መወደድንና መልካምነትን የሚፈጥር ስለሚመስላቸው ሁሉን እሺ ይላሉ።እምቢ ያሉ ዕለት፤ በሰው ላይ ቅያሜ የሚፈጥሩ አድርገው ስለሚያስቡ እሺታ መለያቸው ነው።
እዚህ ላይ ለአብነት የሚረዳ ከሆነ ላካፍላችሁ። ከወታደራዊ አለቃው የተሰጠ ውን ትእዛዝ ለመፈጸም የሚጓዝ ወታደርን በዓይነ-ህሊናችሁ አስቡ፣ በወታደራዊ ሰዓት አቆጣጠር ስፍራው ላይ ደርሶ፣ መልእክቱን ሊያደርስ ሲገባው፣ በእሺ ባይነት መንገድ ላይ ለሚያጋጥመው ሌላ አካል፣ ጊዜ ሰጥቶ ትንሽ ጊዜ በመስጠቱ ጠላት አካባቢውን በቀላሉ የሚቆጣጠርበት እድል መፍጠሩ ይወሳል።ይህንን ደግነትና እሺታ፣ ብለን ብንል ድርጊቱ ምንም እንኳን ቅንነት ያለበት እግረ- መንገዳዊ ክንውን ቢመስልም፣ ተገቢነት አልነበረውምና ወታደራዊ ተልእኮውን በሰዓቱ ባለመከናወኑ ትልቅ ጥፋት አጠፋ። በዚህ ሁኔታ ላይ እንዲህ ዓይነት ባህሪ ያለው ሰው ሆኖ ሲገኝ፣ ከመንገዱ ተናጥቦ፣ የመድረሻ ሰዓቱን አስተጓጉሏል፤ መልእክቱን በሰዓቱ ባለማድረሱም ድርጊትና ውጤት አደጋ ላይ ወድቋልና ፤ በአለቆቹ ተጠያቂ ነው።ስለዚህም ነው፤ እሺ ባይ ሰዎች፣ አንዳንዴ ሙሉ በሙሉ እምቢ ከሚሉ ሰዎች የላቀ ጥፋት ያደርሳሉ ፤ የሚባለው።
አንድ ነባር ያገራችን ቀልድ አለ። ቁርጥማት ሁለመናዬን እየጠዘጠዘኝ ነበር፤ ያለች አንዲት ሴት ስትናገር የተደመጠ ነው። አንድ ማለዳ ፤ አንድ ሰው ወደግቢያችን በር መጣና አንኳኳ፤ እንደምንም ብዬ ሄጄ በሩን ስከፍት ፣ እንደምን ነዎት ካለ በኋላ ፣ ለስራይ፣ ለግግ፣ ምግብ ለማይስማማው፣ ለሚያልበው፣ ለጨጓራ፣ ለደም ማነስ፣ ለቁርጥማትና ሌላ ደዌ ማላቀቂያ ፍቱን መድሃኒት እጄ ላይ አለ፤ እያለ ወደያዘው ቦርሳ ሲያመለክት መላእክቱ ናቸው ያመጡት ብዬ ግባ እስቲ አልኩት።
ከዚያም ወደቤቴ በረንዳ መጣና ይህኛውን ትኩስ ውሃ አፍልተው ቢጠጡት የህመም ስሜት ይወገዳል፤ ይሄኛውን ደግሞ ትንሽ ውሃ ጠብ አድርጎ በማሸት ከማንኛውም ምች ይፈወሳሉ።ይህንን የብርድ ስሜት በተሰማዎት ቦታ ላይ በቅባት ለውሰው ቢቀቡት ቁርጥማቱ በጥቂት ደቂቃ ውስጥ፣ የት እንደገባ አያውቁትም ሲል ሰማሁና የምፈልገው እርሱን ነው፤ ብዬ ስንት ብር ያሰወጣኛል ስለው 200 ብር ብቻ ነው፤ አለኝ።
ኧረ ፣ በሞቴ 100 ይበቃሃል፤ ስለው እሺ ሲለኝ መድሃኒትነቱን ለመፈተሸ ልቤ ክፉኛ ጓጓና ብሩን አውጥቼ ሰጠሁት።የት ጋ ነው፤ የሚቆረጥምዎት ብሎ ሲል እግሬንና እጄን ወገቤን ነው አልኩት፤ ለዚህ “ድንገተኛ ሐኪሜ”።ቀላል ነው፤ እስቲ እጅዎን ሰብሰብ ያድርጉት ሲል እሺ ብዬ እጄን መሰብሰብ፤….. የእጁ ልስላሴ ግን ይገርማል፤ ትንሽ ቆይቶ ደግሞ እስቲ እግርዎን አንዴ ልሽዎት ፤ እጅህ መድሃኒት ነው ፤ ይሉኛል ብዙዎች፤ ሲል እሺ አልኩት።እግሬን ቀስ እያለ ሲያሸኝ እንቅልፉ ይዞኝ ጭልጥ፣ አይል መሰላችሁ? ስባንን ያለሁት በሳሎን ክፍሌ ወለል ላይ ብርድ ልብሴን ለብሼ፤ ሳይ በድንጋጤ ጩሂ ጩሂ ነው፤ ያለኝ።
ማነህ አንተ?….ብልም መልስ ሰጭ አልነበረም፤ ወዲያው እንዳልኳችሁ ጩሂ ጩሂ የሚል ስሜት ነበር፤ ያደረብኝ። ተማሪዎቹ ልጆቼ ወደቤት መጥተው ያንኳኩት በር እንደቀሰቀሰኝ ያወቅኩት ዘግይቼ ነው።አድርጊ ያለኝን ሁሉ ሳደርግ ለካ አጅሬ እያደነዘዘኝ ፤ ነበረ።ለልጆቹ በር ለመክፈት ስነሳ ግርግዳው ላይ የነበረው ባለቤቴ ፎቶ ዞሯል፤ ግራ ገባኝ።ወደ በረንዳው ስወጣ መድሃኒት ነው፤ ያላቸውን ነገሮች ሁሉ በረንዳው ላይ በትኖ ሄዷል።ቦርሳውን ምን ይዞበት ሄዶ ነበረ፤ እንጃ።ለልጆቼ በሩን ከፈትኩና ወደጓዳዬ ስገባ ቁምሳጥኑ ወለል ብሎ ተከፍቷል።በቀደም ከእቁብ አምጥቼ ያስቀመጥኩት 12 ሺህ ብር ትዝ አለኝ።ነገር ግን “ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ፤” ነው፤ ነገሩ።አልጮህኩም ፤ ስንት አስቤ ነበረ፤ ሃሳብ ብቻ ሆኖ ቀረ። ወለሉ ላይ በድንጋጤ ኩርምት አልኩኝ ።ውስጤ ግን ክፉኛ ጮኋል።እና….. አለች፤ ይህች እናት… እና…. የተጠየቃችሁትን ሁሉ ለማንም፣ “እሺ” አትበሉ።
ጊዜያዊ ችግራችሁ እሺ ሊያስብላችሁ ይችል ይሆናል፤ ያላችሁበት ገፊ ሁኔታ የማትፈቅዱትን ነገር “እሺ በሉ” ሊላችሁ ይችላል።ነገር ግን እሺታችሁ የሚሰብረው ነገር የከፋ መሆኑን ከጠረጠራችሁ፣ እሺ አትበሉ።እሺታችሁ በቀላሉ የማትወጡበት ነገር ላይ ሊጥላችሁ ይችላልና ፤ “እሺ አትበሉ”።
አንድ ቀልደኛ ብጤ አምርሮ ተናጋሪ፤ በታላቁ መጽሐፍ ላይ ፣ ሰው የሚያውቀው አስርቱ ትእዛዛትን ብቻ ነው፤ አለ። አስራ አንደኛውን ማንም አያነበውም ፤ ወይም ሆን ብሎ ገድፎታል፤ ግን “ተጽፏል”፤ በደማቁ ልባችን ላይ።11ኛው ትዕዛዝ የሚለው የእነዚህን ትዕዛዛት በግማሽ ማንበብ ትችላላችሁ፤ ነገር ግን የህይወታችሁን ቅጠል መመልመያ ብርቱ ስለት ይሆንባችኋል ፤ ነው የሚለው።በመንፈሳዊው ዓለም እይታም ነገሮች እንዲሁ ናቸው።አት…. ስረቅን – ስረቅ፣ አት….ግደልን- ግደል፤ አታ….መንዝርን — መንዝር፣ እያላችሁ በከፊል ማንበብ ትችላላችሁ።
ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ አይኑራችሁ ሲል ፡- ሌላ ማምለክ ትችላላችሁ፤ ግን አያድናችሁም።(ገንዘብን ብታመልክ ወይም ዲያብሎስን ሁለቱም ማጥፊያ ስለት እንጂ ማዳኛ ምቾት የላቸውም) ማለቱ ነው፤ ይላል።
አትስረቅ ስትባል መስረቅ አትችልም ማለቱ አይደለም ፤ አይገባም ማለቱ ነው እንጂ፣ መስረቅ ትችላለህ፤ ግን ስርቆትህ ትዝ ባለህ ቁጥር እረፍትና ሰላም ከህይወትህ ይወጣሉ።
አትግደል ስትባሉም መግደል ያቅታች ኋል፤ ማለት አይደለም፤ ከገደላችሁ በኋላ እንቅልፍ ደህና ሰንብች፤ ማለታችሁን ግን አትርሱ።
አታመንዝር ይላል መጽሐፉ ፣ የማመንዘር አቅሙ የለህም ማለቱ ግን አይደለም፤ ትችላለህ ነገር ግን የሁሉም የሆነ ወንድ፣ የራሱ እንኳን አይደለምና ወዮልህ።ለሴቷም ልጅ እንዲሁ ነው።በነገራችን ላይ አመንዝራነት በዚህ ዘመን መልከ-ብዙ ነው፤ ሰዎች በኢኮኖሚ ስልተ-ምርት ላይ ያመነዝራሉ፤ በፖለቲካ አመለካከትም እንዲሁ ነው፤ በማህበራዊ ግንኙነታቸው ክፉ አመንዛሪዎች የሉም ማለት አይደለም።
በሐሰት አትመስክር፤ ብትባልም አት ችልም አልተባልክም፤ በሐሰት መመስከር ይቻላችኋል፤ ነገር ግን የመሰከራችሁበትን ሰው ባያችሁም ሆነ ባሰባችሁት ቁጥር መድረሻ ታጣላችሁ። ይሄ ግን ለባለ “ደንዳና ቆዳዎች” ላይሰራ ይችል ይሆናል፤ ምስክርነቱ ግን “ነፍስ ካጠፋ” ቅጣቱ ሰማያዊ ብቻ ሳይሆን አእምሯዊና አካላዊ ነው።
ያንተ ያልሆነውን አትመኝ፤ ሲልም መመኘት ይቻላል ፤ ሰቀቀኑን ግን ለማስከን ስጋን ከነፍስ መነጠል ይጠይቃል።ስለዚህ አስራ አንደኛው ትእዛዝ፣ ትእዛዛቱን ወደግራ ማንበብ ነው።መልሳችሁ እሺታ ነው፤ እምቢታ? አስራ አንደኛውን አንብባችሁ ለመተግበር እምቢ ካላችሁ አምቢታው የሚያስከትለውን ሁለመናን የሚያሳክክ የነፍስ ቅጣት ለመቀበል መዘጋጀት አለባችሁ።እሺ ካላችሁ ግን እሺታችሁ ለጽድቅ የሚያገለግለው ያኔ ነው።ሁሉም ክፋት ሰውን የሚወረውርበት ጥልቅ አእምሯዊና መንፈሳዊ ጉድጓድ አለ።ከዚህ ይልቅ ለክፋት እና ለሐሜት እምቢ፤ ለማቁሰልና ለመግደል እምቢ፣ ለማመንዘርና ለማሸበር እምቢ፣ ለመንቀል እና ለማፈናቀል እምቢ፣ ለማፍረስና ለማፍለስ እምቢ፣ ለመዝረፍ እና ለማጋፈፍ እምቢ፣ ለማስደንገጥና ለማናወጥ እምቢ ማለት ከዚህ በተቃራኒው ለቆመ እውነት “እሺ ማለትም” ነው።ሀገራችን አሁን የምትፈልገው ይህንን ነው።እምቢታ እሺታ የሚሆነውም ያኔ ነው።አሁን ማን ይሙት ወገን በወገኑ ላይ ፋስና መዶሻ ይዞ ከቤቱ መውጣት ይገባዋልን? ምንም ዓይነት ቁጭት በሆዱ ይደር ምንም ዓይነት ቂም ይፈጠርበት አንድ ሰው ሊያደርገው ይችል ይሆናል እንጂ፣ በስፋት ሲሆን ግን ችግሩ ጥልቅ፣ ድርጊቱ ግዙፍ፣ ጥፋቱ ሰፊ ነውና እምቢ ሊባል ይገባል፤ ይህን ለማስፈፀም ያደባ ግዙፍ ጠላት ግን በምድራችን እንዳለ ሁላችንም ማጤን አለብን።
ይህንን በእንቢታና እሺታ የተከፈለ ዓለም አኗኗር መምረጥ የባለቤቱ ነው።ክፉ ማድረግን በፍቅር የሚወድዱ፣ (Cruel with Passion) በክፋታቸው ልክ ደስታ ቸው የሚያስገሳቸውን ጨካኞች ይኼ አይመለከታቸውም። ምክንያቱም ሰው ገድለውና አሰቃይተው ሲያበቁ “መረቅ ያለው ጥብስ አዝዘው፣ በቮድካ እያወራረዱ ያሰቃዩዋቸውን ሰዎች ድምጽ ከመጤፍ ሳይቆጥሩ ለሌላ ስቃይ ሌሎችን የሚያጩ ልበ-ድፍኖች፣ ባለደንዳና ቆዳዎች ናቸውና።(በነገራችን ላይ ቮድካው ይሆን ጨካኝ የሚያደርገው ከኢ-አማንያን ሐገር ተሰርቶ ስለሚመጣ) እነዚህን መሰል ሰው ጤፉና ጨካኝ ገዢዎች፣ ደግሞ ያለፉት የሐገራችን የታሪክ ዓመታት አሳይተውናል።
እምቢና እሺ፣ ባይነት በራሱ በሁለት ይከፈላል።ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት ያልተገቡ ነገሮችን በእምቢታ መቃወምና የተገቡ ነገሮችን ላለማድረግ መቃወም ይለያያል። የመጀመሪያው መልካምነት ሲኖረው ሁለተኛው ግን፣ መልካም ያልሆነ ነው። ሰው ወንድሙን፣ አብሮት የተጓደነውንና መከራና ደስታ የተካፈለውን ሰው ላለማማት እምቢ ሲል በሌለበት ስሙን ማንሳትም ለክፋት መንደርደሪያ ይሆናል ፤ ብሎ ከሚያስብ ቅንነትም የሚመነጭ ጥንቃቄ አለውና የሚደገፍ ነው።ላለማመንዘር እምቢ ማለት መታመን ነው፤ መጀመሪያ ለራስ ቀጥሎ ለተጣማሪ ከሁሉም በላይም ለአምላክ መታመን ነው።
ሌላው እምቢታ ግን ፣ ምንም ነገር ቢቀርብለት እምቢ ወይም አይሆንም ለማለት የተዘጋጀ ማንነት መገለጫ ነው።አንድ አስቂኝ ሰው፤ ዘንድሮ በጥበቃ ላይ የሚሰማሩትን ሠራተኞች፣ የሥራ ሃላፊዎቻቸው የሚያሰ ለጥኗቸው ፣ “ቢኖሩም የሉም” ማለትን ነው። ወደየትኛውም መስሪያ ቤት ብትሄዱና ጥበቃውን ወይም ፀሐፊዋን አግኝታችሁ ሰላም ብትሏቸው፣ ከመጠየቃችሁ በፊትና ሰላምታውን ከመ መለሳቸውም አስቀድሞ አለቆቻቸው አለመኖራቸውን ነው፤ የሚነግሯችሁ።
በአንድ አስቂኝ ቀን ወደ አንድ መስሪያ ቤት ጎራ አልኩ። ለጸሐፊዋም፣ አለቃዋን (በስም ጠርቼ) አግኝተውኝ እንደቀጠሩኝና ለመግባት መፈለጌን ነገርኳት። ከተቀመጠች በት ተስፈንጥራ ተነስታ የሉም፤ አለችኝ። ድንገት አለቃዋ፣ (ወዳጄም ነው) እኔ ስመጣ እንድገባ ሊነግራት ብቅ ብሎ ሳለ ተፋጥጠን ያያል።ሳቅ እፍን አድርጎት፣ እና ጉዳዩ ገብቶት “በቃ ተመለስ፤ የለሁም” ብሎ አስቆኛል።
በነገር ሁሉ ፣ የለንምና እምቢ ለማለት ምክንያት አልባ እንደሆንን ስንቶቻችን ራሳችንን ጠይቀን እናውቃለን።ብዙ ጊዜ ይህንን ጥያቄ አቅርበን በቀኑ መጨረሻ ምን እንዳደረግን አስበን፣ እንዳዘንን የሚያውቀው ልባችን ነው።እምቢ መልካም ላልሆነ ሃሳብ፣ እምቢ ያለጊዜው ለሚፈጸም ድርጊት፣ እምቢ ለክፋት፣ እምቢ ለተስፋ መቁረጥ፣ እምቢ ላለመማር፣ እምቢ ለሽብር፣ እምቢ ለውርደት ከሆነ እጅግ መልካም ነው።በተገላቢጦሽ ግን ደግነትን ፣ ቸርነትን፣ ርህራሄን፣ የዋህነትን፣ ሰላምን፣ ፍቅርንና መቻቻልን በመጥላት ለማመጽ ከሆነ ውጤቱ ያለዕድሜ መቀጠፍ ነው፤ በሽብር ለመመላለስ መወጠን ነው፤ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” ባይነት ነው፤ መደምደሚያውም ሞት ነው።
ስለዚህ እሺታንና እምቢታን በተገቢው ሥፍራ፣ ጊዜና ሁኔታ ውስጥ ካላደረግነው በውጤቱ የምንጎዳው ሁላችንም ነንና ሁሉንም በጊዜው እናድርግ !!!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 30/2012
ከአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ