ቅድመ -ታሪክ
ሱሉልታ ተወልዶ ያደገው ወጣት በበርካታ ችግሮች መሀል ተመላልሷል። ወላጆቹ ድሆች መሆናቸው ያሻውን እንዲያገኝ ዕድል አልሰጠውም። የባልንጀሮቹ ወላጆች ለልጆቻቸው አዲስ ልብስ ሲገዙ እሱ ለእግሩ ጫማ አልነበረውም። ሌሎቹ ጠግበው ሲያድሩ እሱና መላው ቤተሰቡ እህል ባፋቸው ሳይዞር የሚውሉበትና የሚያድርባቸው ቀናት ጥቂት አልነበሩም።
የቤታቸው ችግር መክፋት እንደ ዕድሜ እኩዮቹ ትምህርት ቤት አላዋለውም። የፈለገውን ሳያገኝ ያማረውን ሳይጎርስ ጊዜውን ገፋ። ልጅነቱን ጨርሶ ወጣት እስኪባል ድረስም ከወላጆቹ ሳይርቅ የኑሮ መከራውን ተካፈለ።
ገቢሳ ጥቂት ቆይቶ ወደእነሱ መንደር ከሚመላለሱ የከተማ ሰዎች ጋር ተወዳጀ። ሰዎቹ ውሎ አዳራቸው አዲስ አበባ መሆኑን ያውቃል። ዘወትር በጨዋታ መሀል የሚያወጉት የከተማ ህይወትም ውስጡን ሲማርከው ቆይቷል።
እነሱን ተከትሎ ቢሄድ ከራሱ አልፎ ለወላጆቹ ጭምር የሚተርፍ ጥሪት እንደሚይዝ አላጣውም። የልጅነት ዕድሜውን አንዳች ቀለም ሳይለይ ያሳለፈው ወጣት ከገንዘብ ማግኘት ተሻግሮ ራሱን በትምህርት ሊለውጥ እንደሚችል አሰበ። ይህን ሲያስብ ተስፋ ሲቆርጥ የኖረው ማንነቱ በተለየ ስሜት ተሞላ። ጊዜ ሳይፈጅ ሱሉልታን ተሻግሮ መሀል አዲስ አበባ ከተመ።
ገቢሳ የከተማን ህይወት ለመልመድ አልተቸገረም። ለቀናት ግር ቢሰኝም ራሱን አዘጋጅቶ በርካቶችን ለመምሰል ጎንበስ ቀና ማለት ያዘ። በቀን ስራ ተሰማርቶ እጆቹን ሲያፍታታ የዕለት ጉርሱን ማግኘት ጀመረ። ስራን ለማወቅ የነበረው የተለየ ፍላጎት ደግሞ እያደር ሙያውን አሳደገለት። ከድንጋይ ሸክም አልፎ በአጭር ጊዜ የግንበኝነት ሙያን ለመደ።
ገቢሳ ለስራ መፍጠኑ የዕለት ገቢውን ጨምሮ ተፈላጊነቱን አሳደገው። የአዲስ አበባን ህይወት በወጉ ሲላመድና በቂ ገንዘብ ሲይዝ ወላጆቹን አሰበ። አገሩ ከሚኖርበት አካባቢ የቀረበ መሆኑ በየጊዜው እንዲመላለስ አመቸው። የዕረፍት ቀናትና በዓላትን እያሰላ ወደ ትውልድ ቀዬው መመላለስን ልምድ አደረገ።
በልጅነት ዕድሜው ያለመማሩ ከእኩዮቹ ጎን አላቆመውም። ያም ሆኖ ግን ባለበት ህይወት አልተከፋም። አዲስ አበባ መኖሩ የዘመድ አዝማድና የእንግዶች ማረፊያ አድርጎታል። በዚህም መኩራቱ አልቀረም ።
የትዳር አጋር
ገቢሳ የከተማን ህይወት ተላምዶ በቂ መተዳደሪያ እንደያዘ ብቸኝነቱን የምትጋራ የትዳር ጓደኛ አፈራ። ማለፊያ ቤት ተከራይቶ አብሯት መኖር ሲጀምርም ህይወቱን በደስታ ያስለወጠውን ወንድ ልጅ ታቀፈ። ይሄኔ ውስጡ በተለየ እርካታ ተሞላ። የትናንትናውን የችግር ህይወት ረስቶም ለአዲሱ ጨቅላና ለትዳር ህይወቱ ብቻ ማሰብ ጀመረ።
አንዳንዴ ወላጅ አባቱ ከሱሉልታ አዲስ አበባ ይዘልቃሉ። እንዲህ በሆነ ጊዜ የገቢሳ ባለቤት በጥሩ ፈገግታ ተቀብላና እንግድነታቸውን አክብራ በሰላም ትሸኛቸዋለች። የመልካሟ ምራታቸው ጥሩነትና የልጅ ልጃቸው ፍቅር ልባቸው የገባው አባትም ከወትሮው ይልቅ አዲስ አበባን ይመላለሱበት ይዘዋል።
ገቢሳና ወላጅ አባቱ በተገናኙ ጊዜ የቀድሞውን የቤተሰብ ታሪክ እያወሱ በትዝታ ያወጋሉ። አልፎ አልፎ ግን በጨዋታ መሀል የሚታወሱ ጉዳዮች ያነታርኳቸዋል። እንዲሀ አይነቶቹ የቀድሞ ታሪኮች ለሁለቱም ሰላም ፈጥረው አያውቁም። አንዳቸው በይሁንታ ተሸንፈው ካልተውት እስከ ጠብ መካረር ይደርሳሉ።
ገቢሳ ሁሌም ቢሆን ይህ አይነቱ ጨዋታ አይመቸውም። ጉዳዩ ተነስቶ አንዴ ከጀመረው ግን በቀላሉ አይመልስም። አባትና ልጅ ያለፈን ታሪክ እያነሱ መነታረካቸውን ልምድ አድርገውታል። በጨዋታቸው መሀል ሁለቱም መጠጥ ቢጤ ከቀመሱ ደግሞ እስከመቀያየም ሊደርሱ ይችላሉ።
የገቢሳ አባት አያት ከሆኑ ወዲህ አዲስ አበባን በየሰበቡ ይረግጣሉ። የልጅ ልጃቸው ናፍቆትና የእናትዬው በጎነት ቅያሜያቸውን እያሰቡ እንዲርቁ ምክንያት አልሆነም። ገቢሳም ቢሆን ለጊዜው በኩርፊያ ቢቀየምም አባቱን ‹‹ዓይንህ ለአፈር›› ለማለት ደፍሮ አያውቅም።
አባትና ልጅ በተገናኙ ጊዜ ገቢሳ የእንግድነታቸውን ማስተናገድ ልማዱ ነው። ከቤት ወጣ ብለው አንድ ሁለት በሚሉበት ጠጅ ቤትም በግብዣ የፍላጎታቸውን ለመሙላት ያሉትን ሁሉ ያደርጋል።
ገቢሳ አዲስ አበባ ከገባ ወዲህ በትግስት ማጣት ምክንያት ከሰዎች ጋር ተጣልቶ ያውቃል። ይህ እልሁም እስከመደባደብ አድርሶ ለእስር ዳርጎታል። አሁን ላይ ይህን ባህሪውን ላለመድገም ምክንያት የሆነው የትዳር ጎጆውና የህጻን ልጁ መምጣት መሆኑን አሳምሮ ያውቃል።
ገቢሳና ባለቤቱ ከጨቅላው ልጃቸው ጋር ቦሌ ልዩ ስሙ ‹‹እፎይታ›› ከሚባል አካባቢ ተከራይተው ይኖራሉ። ከእነሱ ጋር ጥቂት ጎረቤቶቻቸው ዓመታትን አብረዋቸው ዘልቀዋል። አባወራው በስራ ውሎ ደክሞ ከሚገባበት ጎጆ የሚስቱና የልጁ ፍቅር ይቆየዋል።
መጋቢት 23 ቀን 2005 ዓ.ም
በዚህ ቀን ገቢሳ እንደተለመደው ከቤቱ የወጣው ማልዶ ነበር። ለስራው በሰዓቱ ለመድረስ አስቀድሞ መነሳትን ልምድ ካደረገ ቆይቷል። እናም በየአፍታው በአይኑ ውል የሚልበትን ልጁን ከተኛበት ስሞና ምሳውን ቋጥራና አዘጋጅታ የምትጠብቀውን ባለቤቱን ተሰናብቶ ከቤቱ ርቋል።
ቀኑን በስራ አሳልፎ ቤቱ እስኪደርሰ የሚጣደፈው ወጣት ዕለቱንም በጊዜ ከጎጆው ለመግባት ቸኩሏል። የስራ መሳያሪዎቹን አስቀምጦና ልብሱን ቀይሮ ሲወጣም ሰውነቱ በድካም እንደዛለ ነበር።
ገቢሳ ከቆየበት የስራ ቦታ ወደቤቱ የሚያደርሰውን ታክሲ ይዞ ወደሰፈሩ እየገሰገሰ ነው። ከጎጆው ደርሶ ሲናፍቀው ከዋለው ልጁ ጋር ናፍቆቱን ለመወጣት የተለየ ጉጉት አድሮበታል። ሁሌም እንደሚያደርገው ህጻን ልጁን እየሳመና እያቀበጠ አብሮት ያመሻል።
አሁን ገቢሳ ከመኖሪያ ቤቱ ደርሷል። ከደጅ ቆሞ የውጩን በር ማንኳኳት ሲጀምር ደግሞ ጆሮዎቹ አንድ የተለመደና ለዓመታት የሚያውቀውን ጎርናና ድምጽ አቀበሉት። ወላጅ አባቱ አቶ በቀለ ናቸው።
አባትና ልጁ ገና ከመተያየታቸው አንገት ለአንገት ተቃቅፈው ሰላምታ ተለዋወጡ። አቶ በቀለ ገና መድረሳቸው ነበርና የልጃቸውን መምጣት እንዳዩ ውስጣቸው በደስታ መፍካት ያዘ። ገቢሳ አባቱንና ባለቤቱን ሰላም ብሎ ወደህጻኑ አመራ። ሲናፍቀው የዋለው ጨቅላ የአባቱን ድምጽ እንደሰማ በደስታ መቦረቁን ቀጠለ።
ጥቂት አረፍ ብለው አፋቸውን በእህል እንዳሟሹ ሚስት ቡና ማቀራረብ ጀመረች። የሁለቱም ፍላጎት ቡናውን ማስቀደም አልነበረም። ወጣ ብለው ከለመዱት ጠጅ ቤት አንድ ሁለት ለማለት ተስማሙ።
አባትና ልጅ ተያይዘው ከቤት ሲወጡ ምሽቱ አይሎ ሰዓቱ ገፍቶ ነበር። ያም ሆኖ የጨለማው ብርታት አላሰጋቸውም። ለውሀ ጥማቸው እርካታ ብርሌ ጨብጠው የልባቸውን ሊያወጉ ወደ ጠጅ ቤቱ ገሰገሱ።
ጨዋታው ደርቶ ጫጫታው ካየለበት ጠጅ ቤት ሲደርሱ ቦታ ተመርተው ጎን ለጎን ተቀመጡ። ጠጅ አሳላፊው ደጋግሞ የቀዳላቸውን እየጨለጡ የግል ወሬያቸውን ሲጀምሩ በሞቅታ ውስጥ ሆነው ነበር።
እንደተለመደው የአባትና ልጅ ጨዋታ በሰላም አልቀጠለም። የቀድሞው የቤተሰብ ጉዳይ ሲነሳ በጭቅጭቅ ታጅቦ ባለመግባባት ተጓዘ። መሰማማት የሌለበት ቆይታ በመከባበር አልዘለቀም። በላይ በላዩ በሚጨመረው መጠጥ እየጋለ መቀያየምን አስከተለ።
ሁለቱም ባለመስማማት ስሜት ቆይተው ወደቤት ለመሄድ ባሰቡ ጊዜ ሰዓቱ ገፍቶ እኩለ ሌሊት እየቀረበ ነበር። ገቢሳ እንደምንም አባቱን ከተቀመጡበት አንስቶ ጉዟቸውን ቀጠሉ። መንገዳቸው ሰላማዊ ባይሆንም ሁለቱም ከቤት ደርሰው አረፍ ማለትን ፈልገዋል።
ከጠጅ ቤት መልስ
አባትና ልጅ ከጠጅ ቤቱ ወጥተው ወደመኖሪያ ቤት ጉዞ ጀምረዋል። ሁለቱም በጨዋታ የቆዩበት ስሜት ሰላም እየሰጣቸው አይደለም። በየፊናቸው በንዴት የሚያግላቸው ትኩሳት አብሯቸው ተጉዞ ከቤት አድርሷቸዋል። በዕንቅልፍ እየናወዘች ደጁን ስታይ ያመሸችው ወይዘሮም መምጣታቸውን ስታይ ራት አዘጋጅታ ቡናውን ማቀራረብ ጀምራለች።
አባት ለእሳቸው የተዘጋጀውን መኝታ ባዩ ጊዜ ጎናቸውን ለማሳረፍ ተጣደፉ። ልጃቸው ግን ወደመጸዳጃ እንዲሄዱ በማሰብ ይዟቸው ተነሳ። በእጁ ባትሪ ይዞ መንገዱን እየመራ ሲጓዝ እሳቸው በከዘራቸው እየተመረኮዙ ከኋላው ተከተሉት።
ገቢሳ አባቱ ከስፍራው ደርሰው ጨርሰው እስኪወጡ ከግርግዳው ተደግፎ ጠበቃቸው። ይህ አፍታ በሁለቱም አይምሮ ውስጥ ብሽቀት የሚመላለስበት መሆኑ አልቀረም። የቆዩበትን ሁሉ እያስታወሱ፣የተነጋገሩትን እየከለሱ በሞቅታ መንፈስ ክፉ ደጉን ተመላለሱበት።
ጥቂት ቆይቶ አቶ በቀለ ከመጸዳጃው ቤት ጉዳያቸውን ጨርሰው ወጡ። ወደቤት ከመመለሳቸው በፊት ከበር ቆሞ የሚጠብቃቸውን ገቢሳን ባዩት ጊዜ ግን የያዙትን ከዘራ እንደመሰንዘር ብለው መለሱት። ገቢሳ ድንገቴውን ድርጊት ባየ ጊዜ ስንዘራውን ጎንበስ ብሎ ለማምለጥ ሞከረ። ይህ መሆኑ ብቻ ግን በትዕግስቱ እንዲዘልቅ አላገዘውም።
ገቢሳ አሁን ከመቼውም የበለጠ እልህና ንዴት እያንጨረጨረው ነው። አባቱ የሰነዘሩበት ከዘራ ባይመታውም ስሜቱ ይጠዘጥዘው ይዟል። ይህን እያሰበ አባቱ ላይ አፈጠጠ። አሁንም በድርጊታቸው እንዳልረኩ ገባው። የኋላውን ከአሁኑ እያደባለቀ የሚገፋፋው አልህ እንደርድሮ ከፊት ለፊታቸው አቆመው።
ገቢሳ የአባቱን ከዘራ ነጥቆ በእጁ እንዳስገባ ከጭንቅላታቸው ላይ አሳረፈው። በዚህ ብቻ አልበቃውም።መውደቃቸውን ሲያይ በሌላ ወፍራም ዱላ ደጋግሞ ቀጠቀጣቸው። አባት በልመና ድምጽ እየጮሁ ልጃቸው እንዲተዋቸው ተማጸኑ። ገቢሳ መስሚያ ጆሮ አልነበረውም። ይባስ ብሎ አጠገቡ ባገኘው ትልቅ ድንጋይ ደጋግሞ አሳረፈባቸው።
የአባትና ልጁ መዘግየት ሲያሳስባት የቆየቸው ወይዘሮ ጆሮዋን ጥላ ወደውጭ ማዳመጥ እንደያዘች የተለየ የጣር ድምጽ መኖሩን አወቀች። ወዲያው ጨለማውን አሳብራ ከስፍራው ስትደርሰ ባሏ ወላጅ አባቱን በድንጋይ እየቀጠቀጠ መሆኑን አስተዋለች።
በሆነው ሁሉ ድንጋጤ የገባት ሴት የድረሱልኝ ድምጽ ማሰማት ስትጀምር ባለቤቷ በንዴት ተዋጠ። ከስፍራው እንድትርቅም በያዘው ድንጋይ እያስፈራራ አባረራት። ወይዘሮዋ ጩኸቷን አላቆመችም። ባለችበት ሆና ኡኡታውን አቀለጠቸው።
በውድቅት ሌሊት ድንገቴው ጩኸት ያስደነገጣቸው የግቢው ነዋሪዎች ከዕንቅልፋቸው እየባነኑ ከስፍራው ደረሱ። ይሄኔ ገቢሳ ከመያዙ በፊት ‹‹እግሬ አውጭኝ›› ሲል ተፈተለከ። የአባቱን በደም ተነክሮ መውደቅ ያስተዋሉ አንዳንዶች ድርጊቱን ተጠራጥረው አሯሩጠው ያዙት። ሽማግሌውን ለማትረፍ የፈጠኑት ደግሞ ወደሆስፒታል ይዘዋቸው ገሰገሱ።
የአቶ በቀለን ህይወት ለመታደግ ሲጥሩ የቆዩት የየካቲት 12 ሆስፒታል የህክምና ባለሙያዎች ከሌሊቱ አስር ሰዓት ላይ ተጎጂው ስለመሞታቸው ለልጃቸው ባለቤት አረዱ። እሷን ተከትለው የመጡ ጎረቤቶችም ይህን በሰሙ ጊዜ እውነታውን ለህግ ለማሳወቅ ወደ ፖሊስ ጣቢያ አመሩ።
የፖሊስ ምርመራ
ሲነጋ በግቢው የደረሱት የፖሊስ አባላት ሌሊቱን የተፈጸመውን ወንጀል ለማጣራት ምርመራቸውን ቀጠሉ። የዓይን እማኞችን ጠርተውም ያዩትንና የሰሙትን ሁሉ ሲገልጹ ቃላቸውን በማስታወሻቸው መዘገቡ። እንግዳው አባት ልጃቸውን ለመጠየቅ በመጡበት አጋጣሚ የተፈጸመባቸውን የግድያ ወንጀል ማጣራት የጀመረው ፖሊስ ምርመራውን በስፋት ቀጠለ።
በመዝገብ ቁጥር 706/05 የተከፈተው ዶሴም በመርማሪው ፖሊስ ምክትል ሳጂን አለባቸው ፋንታሁን እየታገዘ በየቀኑ አዳዲስ መረጃዎችን በማከል የተጠርጣሪውን ድርጊት በማስረጃዎች አጠናከረ። ገቢሳ በሰጠው የዕምነት ክህደት ቃል በወላጅ አባቱ ላይ የፈጸመውን የግድያ ወንጀል አላስተባበለም። ጉዳዩን በአግባቡ የመረመረው ፖሊስም በተጠርጣሪው ላይ ክስ ለመመስረት የሚያስችለውን በቂ ማስረጃዎችን አጠናክሮ ጉዳዩን ወደዓቃቤ ህግ በመምራት የራሱን ድርሻ አጠናቀቀ።
ውሳኔ
ህዳር 15 ቀን 2008 ዓ.ም የልደታው ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተከሳሽ ገቢሳ በቀለ ላይ ዓቃቤ ህግ ያቀረበውን የክስ ፋይል ሲመረምር ቆይቶ የመጨረሻውን የፍርድ ውሳኔ ለመስጠት በችሎቱ ተሰይሟል። ፍርድ ቤቱ የቀረበለትን የሰው፣ የሰነድና የህክምና ማስረጃዎችን በተገቢው ሁኔታ መርምሮም የግለሰቡን ጥፋተኝነት አረጋግጧል።
ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ በ1996 ዓ.ም የወጣውንና በወንጀል ህግ ቁጥር 539/1-ሀ የተመለከተውን ህግ በመተላለፍ በፈጸመው በከባድ ሰው መግደል ወንጀል ተጠያቂ በመሆኑ እጁ ከተያዘበት ቀን ጀምሮ በሚታሰብ የ 19 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ውሳኔውን አሳልፏል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 30/2012
መልካምስራ አፈወርቅ