የሰብአዊነት አስተሳሰብ «ለሰው መድሃኒቱ ሰው ነው፤» በሚለው ህዝባዊ ፍልስፍና ይገለፃል። ይህ በሰው ልጅ በሰው ላይ የመተማመን መንፈስ የኢትዮጵያውያን አንዱ ማህበራዊ መሰረት ተደርጎም ይቆጠራል። በአገራችን በተዘረጋው ጠንካራ ሥርዓተ ማህበረሰባዊ መስተጋብር ህዝቦች ለሃዘንም ለደስታም ተደጋግፈው ይቆማሉ። ድግግፉን መልክና ስርዓት ለማስያዝ፣ ዘላቂና ሁሉንም በእኩልነት የሚያስተናግድ ይሆን ዘንድም ደንብ አበጅተው፣ ልክ ወስነው ያቋቋሟቸው የመደጋገፊያ ጊዜያዊም ሆኑ ዘላቂ መደበኛም ሆኑ ኢ-መደበኛ ተቋማት አሉ።
የግለሰቦች እርስ በእርስ እንዲሁም በግለሰብና ማህበር መካከል ያለው ጥብቅ ቁርኝትና ትስስር ደልዳላ ሚዛን ጠብቆና ጸንቶ እንዲቆይ ምሰሶ ሆኖ ካቆሙት ማህበረሰባዊ ሥርዓቶች መካከል እንደ እቁብ፣ እድር፣ በበዓላት ቀን መጠራራት፣ ደቦ ወይም ወንፈል ያሉ ተጠቃሾች ናቸው።
እንደ እኔ እምነት ከሞላ ጎደል፣ እድር፣ እቁብ፣ ማኅበር፣ የመንደር መረዳጃ ማኅበራት በኅብረተሰብ መካከል ላለው ማኅበረሰባዊ እሴቶቻችን መገለጫዎች ናቸው። በቤተሰብ ደረጃ ያሉትን የማኅበረሰባዊ እሴት መገለጫዎችን ደግሞ የቤተሰብ ጉባዔና የዘመድ አዝማድ ግብዣ ይጠቀሳሉ። በጓደኛሞች ደረጃም የጓደኛሞች ጉባዔ በጓደኛሞች መካከል ላለው ማኅበረሰባዊ እሴት መገለጫ ይመስለኛል።
እቁብ በኢኮኖሚ ፋይዳው በማሰብ በአንድ አካባቢ የሚኖሩና የሚተዋወቁ ሰዎች በራሳቸው ነጻ ፍላጐት ከሚመሰርቷቸው ማህበሮች አንዱ ነው። እቁብ አባላቱ በጋራ በስምምነት ደንብ አዘጋጅተው እንደኑሮ ደረጃቸውና የገቢ ምንጫቸው በየሳምንት፣ በየሁለት ሳምንቱ ወይም በየወሩ ገንዘብ የሚከፍሉበትና የሚያጠራቅሙበት የጋራ ገንዘባቸውንም በእጣ በሚወሰን ቅደም ተከተል በተወሰነ የጊዜ ገደብ እንዲደርሳቸው የሚያደርግ ኢኮኖሚ ጠቀሜታው የጐላ ማህበር ወይም ተቋም ነው።
እቁብ የቆየ መሰረት ያለው ባህላዊ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዘዴ ሲሆን፤ በብዙ ነገሮችም ከባንክ ወይም ከሌሎች የቁጠባ ማህበራት ይለያል። ዘመናዊና የተደራጀ አሰራርን የማይከተል፣ ወለድ የማይታሰብበት፣ የሚመራበት ሕግ ወይም ተቆጣጣሪ አካል ወይም በህግ የታወቀ መብትና ግዴታዎችን መቀበል የሚያስችል ሕጋዊ ሰውነት የሌለው ማህበር መሆኑ በዋናነት ይጠቀሳሉ።
እቁቦች ልዩ ልዩ ደንቦች ሊኖራቸው ቢችልም ተመሳሳይ ይዘት ያለው አወቃቀርና አሰራር ይከተላሉ። እያንዳንዱ እቁብ ሰብሳቢ ወይም ዳኛ ወይም ሰብሳቢ ፀሐፊና አባላት አለው። በደንቡ ውስጥ የእጣ አወጣጥ ፣ የቅጣት አፈፃፀምና የአዲስ አባላት ቅበላ፣ እንዲሁም ዕጣን ለሌላ አባል አሳልፎ የመስጠትና የዋስትና አግባብ ስርዓት በዝርዝር ሰፍሮ ይገኛል። የአባላትን የመክፈል አቅምና ፈቃደኝነት ብቻ መሰረት የሚያደርግ ማህበራዊ ተቋም ነው። ምንም እንኳን ተቋሙ በኢኮኖሚያዊ አቅማቸው ተቀራራቢ ደረጃ ያላቸው ሰዎች የሚደራጁበት ቢሆንም እንደ ዕድር ልዩ ልዩ እምነት፣ ሙያ፣ ቋንቋና ብሄረሰባዊ ማንነት ያላቸውን ሰዎች የሚያስተሳስር መሆኑ ማህበረሰባዊ መሰረቱን ሰፊ ያደርገዋል።
ምንም የገቢ ምንጭ ሳይኖራው ተበድረው እቁብ የሚጥሉትን ግን ከትዝብት ማህደራችን ውስጥ መለየቱን ተገቢ አይመስለኝም። እነዚህ ሰዎች እጣ ፈንታቸው በአበዳሪዎቻቸው ላይ የወደቀ ነው። ብድሩን መመለስ ካልቻሉ ደግሞ ብሩን ሲቀበሉ ዋስ የሆናቸው ሰው ተጠያቂ ይሆናል። በሌላ አገላለጽ በተለይ የእቁብ ገንዘብ የበሉ ሰዎች ቀሪ ክፍያ ስለመክፈላቸው የአንድነትና የነጠላ ዋስትና በፅሁፍ፣ ምስክሮች ባሉበት የገንዘቡ መጠን ተገልፆ ዋሶችን ማስፈረሙ በተለያየ ምክንያት እቁብ የበሉ ሰዎች ሲጠፉ ዋሱን ለመጠየቅ ያስችላል።
እቁብ እንጣል በሚል ሽውዳ ገንዘባቸው ተበልቶ የቀረባቸውንም ሳንታዘብ አናልፍም። በዚህ መልኩ በየአጋጣሚው ያነጋገርኳቸው የቅርብ ጓዶቼ እንዳጫወቱኝ እቁብ የጥቅሙን ያህል በሰዎች ኪስ ላይ ትልቅ ኪሳራ የሚያደርስበት አጋጣሚም አለ። ሰዎች የእምነት ቃላቸውን ሲያፈርሱ፤ በተለይም ይህ ትልልቅ እቁብ ላይ የሚከሰት ነው። አስቀድሞ እድሉ የደረሳቸው ሰዎች ብሩን ወስደው ደብዛቸው ይጠፋል። በርካታ ወጣቶች የቆጠቡትን እቁብ ሳይወሰዱ ለኪሳራ እንደተዳረጉም ገንዘብ ወጥቶ የሚቀርበትን መንገድ አበዛዙን በምናባዊ ስሌቶች እያሰሉ አጫውተውኛል።
በአንዳንድ ኢ-ሞራላዊ አስተሳሰቦች ስንቶች የቆጠቡት እቁብ ባክኖ ቀርቶ ይሆን? ጥያቄውን ለባለገጠመኞች ልተወው። እዚህ ላይ ምንም ከማታውቋቸውና ዋስትና ከሌላቸው ሰዎች ጋር እቁብ ከመግባት መቆጠብ የሚበጅ ይመስለኛል። አለበለዚያ ግን አተርፍ ባይ አጉዳይ እንደሚባለው ከማናውቃቸው ሰዎች ጋር እቁብ መጣል ለኪሳራ ይጥሉናል እንጂ ትርፋማ አያደርጉንም። ስለዚህ እንዲህ አይነት ነገሮች ላይ ባለመሳተፍ መሰል ታሪኮች ያሉን ታሪኮቻችንን በመንገር በእኛ ይብቃ ልንልም ይገባል። አብሶ አዳዲስ እቁብተኞች እንዲህ አይነቱን ስህተት በመድገም ገንዘባቸውን እንዳይበሉና ያሰቡት ዕቅዳቸው ሳይሳካ እንዳይቀር ልናስተምራቸው ይገባል።
በተለይ የወጣትነት ዘመንን እምሽክ አርጎ በሚበላው የስደት ህይወትን ለመግፋት ሲባል በእንዲህ አይነት ታሪክ ውስጥ የገቡ ሰዎች መኖራቸውን እንደ መርዶ መስማት አሳዛኝ ክስተት ነው። (የስደቱን ርዕሰ ጉዳይ በሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ)
መቼም ለወገን ደራሽ ወገን ነው የሚለውን ብሂል አንስተን እቁብን መከልክል ባይገባም ራስን አጣብቂኝ ውስጥ ከተው በነገው ህይወታቸው ላይ ቁማር የሚጫወቱትን ግን መደገፍ ተገቢ አይመስለኝም። አንዳንዴ የእቁብ መሠረታዊ እሳቤው መረዳዳት ላይ ያተኮረ በመሆኑ በጎነቱን ብናጎላውም አንዳንዴ ግን በአቋራጭና ዋጋ በሚያስከፍል መልኩ ለመበልጸግ መሞከር አወዳደቃችንን ያባብሰዋል።
የእቁብ ጥሩ ሀሳብነት ማህበራዊ ልማዳችንም እንዳይጠፋና ችግርን በሌላ አማራጭ ተጠቅሞ ለመፍታት መሞከሩ ነው። በተለይ አንድ ሰው ከአቅም በላይ የሆነ ችግር፤ አስፈላጊ እቃ ሲያስፈልገው ወሊድ፣ ሰርግ፣ ክርስትና ወዘተ. የመሳሰሉ ድግሶች ሲገጥመው ዕዳው ባይቀርለትም ለችግሩ ጊዜያዊ ማስተንፈሻ እንደ አማራጭ ከሚጠቀማቸው ነገሮች መካከል እቁብ ግንባር ቀደሙ ነው።
ከደመወዛቸው እየቆጠቡ በገቡት እቁብ ህይወታተቸውን ለማሻሻል ቆርጠው የተነሱ በዚህም የተሳካላቸው ወጣቶች በርካታ ናቸው። በእርግጥም እቁብ ከሚሰጠው ከፍተኛ ጥቅም አንጻር የእኛ የባህል ቅርሳችን ስለሆነ እንደሌሎቹ ቅርሶች በዩኔስኮ ተመዝግቦ የቅርሶቻችንን ቁጥር ከፍ ብናደርግ አይጎዳንም ለማለት ያስደፍራል። ቀጥለን ደግሞ እድርን እናካትታለን።
ይህ አይነቱ እሳቤ ማኅበራዊ ዕሴት ከኢኮኖሚ ዕድገት ጋር ባጋመደ መልኩ ሲታይ ግለሰቦች በቡድን በመሆን በትብብር ለጋራ ዓላማ የመንቀሳቀስ አቅማቸውን የሚገልጽ ነው። ማኅበራዊ ዕሴት ለኢኮኖሚ ዕድገት አስፈላጊ ለመሆኑ ማመላከቻው፤ ኅብረተሰቡ ከልዩነት ይልቅ በአንድ ትስስር፣ ለጋራ ጥቅም በአንድነት በመንቀሳቀስ የሚያመጣው ውጤት የላቀ በመሆኑ ነው።
የእቁብ ሌሎች ተጨማሪ መገለጫዎች መኖራቸውን ከግንዛቤ በማስገባት፤ ከላይ የጠቀስኳቸውን የማኅበረሰባዊ እሴቶቻችን መገለጫነቱን መነሻ ስናደርግ፣ ትልቁ ጥያቄ ‹‹ፋይዳው ምንድን ነው?›› የሚለው ይሆናል። እስኪ ፋይዳውን ከአካባቢያዊ እና ከሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ እድገት አንፃር ለማየት እንሞክር።
የእቁብን ጥቅም መግለጽ ለቀባሪው አረዱት አይነት ስለሚሆንብኝ ግለሰባዊም ሆነ ቤተሰባዊ ችግርን ከመፍታት እና ምርታማነትን ከማሳደግ አኳያ ትልቅ ጥቅም እንዳለው ሁላችንም የምንገነዘበው ነው። በእቁብ አማካኝነት የሚፈጠር የጓደኛሞችን እና የቤተሰብ ቅርርብ በጋራ እራስንም ሆነ ኅብረተሰብን የሚጠቅም ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለመከወን ከሚኖረው ኅብረት እና የግለሰብን ችግር በመፍታት ምርታማ የሰው ኃይልን ይፈጥራል።
የእቁብ ሌላኛው በጎ ጎን ሰውን በስራ ማትጋቱ ነው። ለምሳሌ አንድ ሰው በቀን 300 ብር እቁብ መጣል ቢኖርበት እንደምንም ብሎ በቀን 300 ብር እና ከዚያ በላይ ለማግኘት በትጋት ይሰራል። ይህ ሰው ሌላ የቁጠባ አማራጭን ልጠቀም ቢል ምናልባትም መቆጠቡን የግድ ስለማያደርገው ባገኘ ወቅት ያገኘውን የገንዘብ ልክ ብቻ ነው የሚያስቀምጠው። ከዚህ ባሻገር የእቁብ ብር በቋሚነት አንድ ሰው እጅ ላይ ስለማይቀመጥ ስጋት አይኖርም። የመውሳጃ ጊዜ ሲደርስ ወዲያው ተሰብስቦ የሚሰጥ ነው። ምናልባትም አንድ ሰው እጅ ብሩ ለረጅም ጊዜ ቢቀመጥ ሊባክንና ሊጠፋ ይችላል የሚል ስጋት ውስጥ ሊያስገባ ይችላል።
በነገራችን ላይ እቁብን ስናነሳ ከብር ውጭ የመጻህፍት፣ የእቃ የመሳሰሉት የእቁብ ዓይነቶችም አሉ። በተለይ በመጻሕፍት ዕቁብ ባለዕድል የሚያገኘው ጠቀም ያለ ገንዘብ ሳይሆን በርከት ያሉ መጽሐፍትን ነው። በመጻሕፍት ዕቁብ፣ መጻሕፍት ከመግዛት ባሻገር ስለ መጻሕፍቱ መወያያ መድረክ መፍጠር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተለመደ የመጣ ነገር ነው። የእቁቡ አባላት ከሚያዘወትሯቸው የመጻሕፍት መደብሮች ከ20 እስከ 25 በመቶ ቅናሽም ይደረግላቸዋል። ይህ አይነቱ እቁብ መስፋፋት ደግሞ በአገር ደረጃ የንባብ ባህል እንዲዳብር ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወትም ያደርጋል።
የመጻሕፍት ዕቁብ የሚገቡ አንባቢዎች መጻሕፍት በመግዛት የተሻለ ልማድ ያላቸው በመሆናቸው ደራሲያን ይጠቀማሉ። ሻጮችም በአንድ ጊዜ በርካታ መጻሕፍት የሚገዙ ደንበኞችና ቀጣይነት ያለው ገቢ ያገኛሉ። አንባቢዎች በቡድን ሲሆኑ መጻሕፍት የመግዛት ተነሳሽነታቸው ይጨምራል። የመጻሕፍት ወጪ ሳይከብዳቸው እንዲገዙም ያበረታታቸዋል። እንዲህ አይነት ዕቁቦች አንባቢዎች ሒሳዊ ንባብ እያደረጉ ስለመጻሕፍት በጥልቀት እንዲወያዩ መንገድ ይከፍታሉ።
የማኅበረሰባዊ እሴት አንዱ አካል የሆነው እቁብ ግለሰቦች በቡድን በመሆን በእምነት፣ በትብብር ለጋራ ዓላማ መንቀሳቀሳቸው እንደመሆኑ፣ በእምነት እና በትብብር የሚከወን ስራ ትልቁ ፋይዳው የእንቅስቃሴ ወጪን የመቀነሱ እና የማስቀረቱ ሁነት እንዲሁም ነፃ እና ገለልተኛ የሆኑ ተቋማት እንዲፈጠሩ መንስዔ መሆኑ ነው። ከኅብረተሰባዊ ፋይዳ አንጻር በእቁብ የሚከወነው እንቅስቃሴ ኅብረተሰቡን ለአንድ አላማ በጋራ ከማንቀሳቀሱ ባለፈ ለኅብረተሰቡ ችግር ፈጣን ምላሽ ይሰጣል።
የማኅበራዊ ዕሴትን ጥቅም ከኢኮኖሚ እና ከፖለቲካዊ ጥቅም አኳያ ስናየው፣ በአንድ አካባቢ የሚኖሩ ኅብረተሰቦች ከሁለት በላይ የሆኑ የግለሰቦች ስብስብ አንድ በሚያደርጋቸው የጋራ ልማድና መተማመን በጋራ በሚያደርጉት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ወጪን የመቀነሱ እና የማስቀረቱ ሁነት የሚጠቀስ ነው። ከፖለቲካዊ ፋይዳው አኳያ ስናየው ደግሞ ነፃ እና ገለልተኛ የሆኑ ተቋማት እንዲፈጠሩ መንስዔ በመሆን ለዴሞክራሲ መዳበር ያለው ፋይዳንም እቁብን መነሻ አድርገን መጥቀስ እንችላለን። እቁብ ያለምንም ተፈጥሯዊና ማህበረሰባዊ መድልዎ ሁሉንም ሰው እኩል የሚያሳትፍና ጠቀሜታው ከፍ ያለ በመሆኑ ሊበረታታና ዘላቂነት ሊኖረው ይገባል። ከተቻለም ዘመናዊነትን ጠብቆ መዋቀር ቢችል ከዚህም በላይ የጎላ ጠቀሜታ ይኖረዋል።
አዲስ ዘመን አርብ ጥር 29/2012
አዲሱ ገረመው