አዲስ አበባ:- የአገሪቷን የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ጠንካራና ደካማ ጎኖች በመፈተሽ የአገልግሎት አሰጣጡን ከፍ ለማድረግ የሚያስችል ስትራቴጂክ እቅድ ለማዘጋጀት አጠቃላይ ጥናት ሊያካሂድ መሆኑን የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ አስታወቀ።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙጅብ ጀማል በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በኤጀንሲው ድንገተኛ ምልከታ ባደረጉበት ወቅት እንዳብራሩት፤ ኤጀንሲው ከሐምሌ 30 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ የጀመረ ሲሆን፤ በአገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ምዝገባው እየተሻሻለ ቢመጣም ከሌሎች የአፍሪካ አገራት አንጻር ሲመዘን አፈጻጸሙ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። የአገልግሎቱን ጠንካራና ደካማ ጎን በመፈተሽም በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ከፍ ለማድረግ የሚያስችል ስትራቴጂክ እቅድ በማዘጋጀት ተግባራዊ ለማድረግ አጠቃላይ ጥናት በመጪዎቹ ሦስት ወራት ይካሄዳል።
ዋና ዳይሬክተሩ የአፍሪካ ህብረትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ካስቀመጡት የልማት ግብ አንጻር አገሮች እ.አ.አ በ2030 የልደት ምዝገባ መቶ በመቶ እና የሞት ምዝገባ ደግሞ 80 በመቶ መድረስ ይገባቸዋል። ከዚህ አንጻር አብዛኞቹ በቅኝ ግዛት ተይዘው የነበሩ የአፍሪካ አገራት ስራውን ቀድመው በመጀመራቸው ከወዲሁ ግቡን ማሳካት የቻሉ ሲሆን፤ ለአብነት ቦትስዋናና ናሚቢያ የልደት ምዝገባን መቶ በመቶ አድርሰዋል። ደቡብ አፍሪካና ግብጽ ደግሞ 40 እና 50 በመቶ መድረሳቸውን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ምዝገባውን ዘግይታ እንደመጀመሯ አፈጻጸሟ ጥሩ ቢሆንም ከሌሎች የአፍሪካ አገሮችና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ካስቀመጠው ግብ አንጻር አፈጻጸሙ ወደ ኋላ መቅረቱን የሚናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፤ እንደ አገር አዋጅ ወጥቶ ተግባራዊ መሆን ከተጀመረበት አንስቶ የልደት ምዝገባ 12 በመቶና የሞት ምዝገባ ስድስት በመቶ መደረሱን ተናግረዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ በ 2030 ይደረስበታል ተብሎ የተቀመጠው ግብ እንዲሳካና የኢትዮጵያ አፈጻጸም እንዲሻሻል የአፍሪካ ህብረትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ትልቅ ትኩረት መስጠታቸውን ገልጸው፤ መረጃው ለስታስቲክስ፣ ለህግና ለአስተዳደር መሰረት ከመሆኑ ባሻገር አገሪቷ ካስቀመጠችው 17 የልማት ግቦች 12ቱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከወሳኝ ኩነት ምዝገባ ጋር ስለሚገናኙ አገልግሎቱ መሻሻሉ ፋይዳው ብዙ መሆኑን አብራርተዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ የአፍሪካ ህብረት አገራት የወሳኝ ኩነት ምዝገባ አቅማቸውን ሊያሻሽሉበት ይገባል ብሎ ያስቀመጠውን ዓለም አቀፍ መስፈርት ተከተሎ በመጪዎቹ ሦስት ወራት በዘጠኙ ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች በሚካሄደው አጠቃላይ ጥናት አማካኝነት፤ የአገሪቷን የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ደካማና ጠንካራ ጎኖች እንዲሁም የመፍትሄ አቅጣጫዎች በመለየት በቀጣይ አምስት ዓመታት ለመተግበር የሚያስችል ስትራቴጂ እቅድ ይወጣል።
እንዲሁም ከስትራቴጂ እቅዱ የተመነዘረ ማስፈጸሚያ ዕቅድ ወጥቶ ከ 2013 ጀምሮ እስከ 2017 ዓ.ም ድረስ በአገር አቀፍ ደረጃ ስራው በተጠና መንገድ ተግባራዊ ይደረጋል። የጥናቱን ወጪ የተባበሩት መንግሥታት የህፃናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ ሙሉ ለሙሉ የሚሸፍን ሲሆን፤ ለጥናቱም ዓለምና አገር አቀፍ ልምድ ያላቸው አማካሪዎች መቀጠራቸውም ታውቋል።
አዲስ ዘመን ጥር 27/2012
ሶሎሞን በየነ