የቤተክህነቱንም ዘመናዊው ትምህርቱንም በጥሩ ሁኔታ ናቸው። በዘመናዊ ትምህርትም ዶክትሬት ወይም ሶስተኛ ዲግሪ ድረስ ተምረዋል፤ በአገር ውስጥም በውጪ አገር ስለአገራቸው ከመመስከራቸው ባለፈ በሥራ አሳይተዋል። ለዚህ የበቁበትን ብዙ ውጣውረዶች በመጽሀፍ መልክ በማሳተም ትውልድ እንዲማርበትም ያደረጉ ናቸው።የዛሬ የህይወት እንዲህ ናት እንግዳችን ዶክተር አያሌው ሲሳይ ናቸው መልካም ንባብ።
ጎቤ
የተወለዱት ልዩ ስሙ “ላፀና” በሚባል ቦታ ሲሆን፤ በቀድሞው በላስታ መንገድ ምክትል ወረዳ ግዛት በአርካ አቦ ሰበካ ውስጥ ይገኛል። ከእናታቸው ወይዘሮ ዓለሚቱ አገኜሁ ከአባታቸው አቶ ሲሳይ ወልደ ገብርኤል የተወለዱት ዲያቆን ዶክተር አያሌው፤ የተወለዱበትን ቀን ወርና ዓመተ ምሕረት በግምት ከመናገር በስተቀር በትክክል አያውቁትም። ስለዚህም በግምት በ1938 ወይም 1939 ዓ.ም እንደተወለዱ የተለያዩ መረጃዎችን በማገላበጥ አግኝተዋል።
ከአስቀመጧቸው ቦታ ትንሽ የሚጫወቱበት ነገር ከሰጡዋቸው ብዙም የማያስቸግሩት ባለታሪኩ፤ የሚንከባከባቸው ጎረቤት ሁሉ በጣም ይወዱዋቸው እንደነበር አይረሱትም። እንደውም ከዚህ ባህሪያቸው አንጻርም ቅጽል ስም አውጥተውላቸው “ጣፈጠ” ይሏቸው እንደነበር ይናገራሉ።
የእንግዳችን ቤተሰቦች የሚተዳደሩት በግብርና ሲሆን፤በቤት ውስጥ የተለያዩ ሥራዎችን በመስራት ቤተሰብ ያግዙ ነበር። በተለይም ከግብርናው ስራ ጋር ተያይዞ ያልሞከሩት ነገር እንዳልነበረ ያስታውሳሉ። ከዚህ በተጨማሪም ልጅ የማዘሉም ሥራ የእርሳቸው ነበር። በዚህም ብዙ ጊዜ ይማረሩ እንደነበር አጫውተውናል።
እናት እንጨት ለቀማና ለውሃ ቅጅ ከቤት ስትወጣ ወገባቸው እስኪጠብቅ ድረስ ታስሮ ነበር የሚያዝሉት። በዚህም ጎብጠው ኖሮ ሌላ ቅጽል ስም እንዲወጣላቸው ሆኗል። ይኸውም “ጎቤ” የሚል ነው።
በቤት ውስጥ የተቆላ ተልባ በመውቀጥ፣ የተፈተገ ገብስ ቆሎ በሙቀጫ በመሸክሸክ የሚታወቁት ዲያቆን ዶክተር አያሌው፤ ወተት በትልቅ ቅል/ላጋ/ በመናጥም ይታወቃሉ። ውሃ በቅል ከወንዝ በማመላለስ፣ እንጨት ከዱር በመልቀምና ጥጆችን እናቶቻቸው ሲታለቡ በመያዝ እንዲሁም ቤተሰቡን ያገለግላሉ።
እንግዳችን በአረም ወቅት ጣቶቻቸው ቀጫጭን በመሆናቸው አረሞች በመንቀል የሚደርስባቸው አልነበረም። በዚያው ልክ በአጨዳ ወቅትም ሆነ ሰብል ተሰብስቦ በሚከመርበት ጊዜ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ነበራቸው።
የቆሎ ትምህርት
አያታቸው የታወቁ የባለጸጋ ቄስ ልጅ በመሆናቸው ከልጆቻቸው መካከል አንዱን ብቻ ለይተው የቤተ ክህነት ትምህርት አስተምረዋል። በዚም የእንግዳችን አባት ይቆጩ ነበርና በልጃቸው ለመወጣት ነበር ዲያቆን ዶክተር አያሌውን ወደ አብነት ትምህት ቤት ያስገቧቸው። በልጆቻቸው እንዳይወቀሱም ወንድማቸውንና እርሳቸውን በቻሉት አቅም አስተማሩ።
ከ”በስመ አብ” ጀምሮ እስከ “ጸሎተ ሃይማኖት” ድረስ ያሉትን “ነአኩተከን” አቡነ ዘበሰማያትን” እና “በሰላመ ቅዱስ ገብርኤል”ለሁለቱም ማታ ማታ በቃል ማስጠናቱንም ቀጠሉበት። እንግዳችን ግን ፈጣንና የተነገሯቸውን የማይረሱ በመሆናቸው ከወንድማቸው ልቀው በአጭር ጊዜ የጸሎት የቃል ትምህርቶችን አጥንተው አጠናቀቁ።
ታላቅ ወንድማቸውን ለግብርና እርሳቸውን ለቤተ ክህነት ትምህርት አባታቸው እንደመረጡ የሚናገሩት ዲያቆን ዶክተር አያሌው፤ አንድ መምህር ያሉበት ሰበካ ቤተ ክርስቲያን በመሪጌትነት እንዲያገለግሉ በመቀጠራቸው እንዲማሩ ልከዋቸዋል።ከእዚያ መምህራቸውን ተከትለው አጎራባች ወደምትገኝ የዛብራ ማርያም ቤተ ክርስቲያን አቀኑ። በዚያም ትምህርታቸውን ቀጠሉ።
የአባታቸውን በጎ ምርጫ በደስታ ተቀብለውም ወደ አዲሱ መምህር መኖሪያ ሠፈር በመሄድ ከሰበካው ደብር ጌቶች ጥቂት ልጆች ጋር በመደባለቅ ነበርም ትምህርቱን የጀመሩት። ይህን በመሰለ ጥንክርና ፉክክርና ትግል የፊደል ዘሮችን ጥንቅቅ አድርገውም ቻሉ። ከዚያ “ፊደለ ሐዋርያ መልእክተ ዮሐንስ . . . “ የሚለውን ቀጣዩን ትምህርት በግዕዝ በውርድ ንባብና በቁም ንባብ ተማሩ። እንግዳችን በመቀጠል የተማሩት እንደ ግብረ ሐዋርያት፤ ድርሳናት ገድላትና ተአምራት ያሉትን ሲሆን፤ በደንብ ማንበብ ችለውበታል። ከዚያ ወደ ዳዊት ደገማ ገቡ።
‹‹አብረውኝ ትምህርት ከጀመሩት የባላገር ልጆች ጥቂቶቹ ሲያቋርጡ የቀጠሉት ደግሞ በድቁና እና በቅስና ደረጃ ተወስነው ቀርተዋል›› የሚሉት ባለታሪኩ፤ ዳዊት ለመማር እንደ ዛሬው በማተሚያ ቤት የተዘጋጁ መጻሕፍት በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ስለሌሉ ብቸኛው አማራጩ ከደብር ጌቶች መዋስ ነበር። ከዚያ በውሰት የተገኘውን አንድ የብራና ዳዊት ለአራትና ለአምስት ተማሪዎች እየተጋሩ ይማሩ እንደነበር ያስታውሳሉ።
ዲያቆን ዶክተር አያሌው በንባብም ቢሆን በጣም የተደነቁ ናቸው። በዚህም ቁመታቸው ከመጽሐፍ ማስቀመጫው አትሮንስ ስለማይደርስ “ተቀምጬ ነጋሪት” የሚባለው ትልቅ አታሞ መሰል ነጋሪት ላይ በመቆም ልዩ ልዩ መንፈሳዊ መጻሕፍትን ሕዝቡ ግሩም ድንቅ እስከሚል ደረስ ያነቡ እንደነበር ይናገራሉ።
ከዳዊት በኋላ ቀጣዩ ትምህርት ‹‹ፀዋትወ ዜማ›› በመሆነ ማታ ማታ ከውዳሴ ማርያም ዜማ ጀምረው እየተከታተሉ በቀኑ ክፍለ ጊዜ ደግሞ ጾመ ድጓ ለመማር “ዘወረደ እምላዕሉ . . .” ማለት እንደጀመሩ ያጫወቱን ባለታሪኩ፤የብራና ቅጠሎቹ ልክ እንደ ዳዊቱ በርከት ብለው ስላልታዩት አባታቸው የሰነፉ ስለመሰላቸው በትርፍ ጊዜ መሪጌታ ይባቤ የሚባሉ የቅኔ መምህር ቤት እንዲማሩ እንዳስገቧቸውም አይረሱትም።
ሌሊት ሌሊት “ግሥ” ሲያወርዱ እየተገናኙ አዳምጠው ቀን የቅኔ መነሻ የሆችውን “ጉባዔ ቃና” እየቆጠሩ ለመምህሩ በመንገር ያሳምሩ እንደነበርም ይናገራሉ። ሆኖም ትምህርት ስለተደራረበባቸው ለጊዜው ቅኔውን አቁመው ጾመ ድጓውን ለመጨረስ እንደሞከሩ አጫውተውናል።
እንግዳችን ትምህርታቸውን ከመከታተል ውጭ በየጊዜው ወደ አቦ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ሌሊት ሌሊት ሰዓታት ሲቆም ቀን ቀን ማኅሌት ሲቆም ቅዳሴም ሲቀደስ እየተከታተሉ አብዛኛውን አባባል ለምደዋል። በዚህም አንድ ዲያቆን ሊያጠናቅቀው የሚገባውን ትምህርት እንዲያውቁ ሆነዋል። ከዚያ በተጨማሪ ከበሮመምታት፤ ጸናጽልና መቋሚያ በማቀበል ሥርዓተ ቅኔ ማኅሌቱን ከነአባባሉ አወቁ።
በ1950 ዓ.ም የድሮው የወሎ ጠቅላይ ግዛት ሊቀ ጳጳሳት የነበሩት አቡነ ገብርኤል የዋግ አውራጃ ዋና ከተማ የሆነችውን ሰቆጣን ለመጎብኜት ጥር 21 ቀን የአስተርእዮ ማርያምን ክብረ በዓል ተንተርሰው ስለመጡ እርሳቸውም አጋጣሚውን በመጠቀም ስንቃቸውን በመያዝ ወደ ሰቆጣ አቀኑ። ይሁንና ክህነቱ የሚሰጥበት ቦታ ወፍላ ወረዳ ኮረም ከተማ በመሆኑ ምንም ሳያርፉ ጥር 22 ቀን 1950 ዓ.ም ቅድሚያ ምዝገባ ተደርጎላቸው።
ፈተናውም የቃል ትምህርቶችን ለምሳሌ” ኪዳን ውዳሴ ማርያም አንቀጸ ብርሀን ሊጦን” የመሳሰሉትን ያለምንም ስሕተት ሰተት አድርጎ መዝለቅና ከቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ በዘመናዊ ማተሚያ ቤት በታተመ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተወሰኑ መሥመሮችን በግዕዝ ቋንቋ ማንበብ ነበርና ያለምንም መደናቀፍ አለፉት።
ዲያቆን ከሆኑ በኋላ አባታቸው በእርሳቸው አገልግሎት ምክንያት የታቦት/የመስቀል/ መሬት ለራሱ እንዲያርስ እንደተሰጣቸው የሚናገሩት ባለታሪኩ፤ ጥቅማጥሞቹ አባታቸውን ስላጓጓቸው በዲቁና አገልግሎት እንድቀጥሉ ይገፏፏቸው እንደነበር አይረሱትም። ይሁንና እርሳቸው ግን ዘወትር መማርን ይሻሉና በሌሎች ዘመዶቻቸው ግፊት ቀጥለዋል። ከዓመት የዲቁና አገልግሎት በኋላ በ1951 ዓ.ም ጓዛቸውን ጠቅልለው የመጀመሪያውን የቆሎ ተማሪነት ሕይወት ለመሞከር በድሮው የላስታ አውራጃ እንጃፋት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ መሐጎ ማርያም ከምትሰኝ ደብር ወደ ነበሩት ዝነኛ የድጓ መምህር መሪጌታ ኤልሳዕ ጋር ሄዱ። ሆኖም ቤተሰብ ጋር ችግር ተፈጥሮ ስለነበር መሀል ላይ አቋርጠውት ወደ ተወለዱበት ቦታ ተመለሱ።
ለመማር ቆርጠው ተነስተዋልና ዳግመኛ በ1952 ዓ.ም ወደ ላስታ አውራጃ የተመለሱ ሲሆን፤ ከላሊበላ ከተማ አጠገብ በስተሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ በሚገኘው ‹‹ቀንቀኒት ሚካኤል›› በተሰኘ ቤተ ክርስቲያን ከመሪጌታ ፀዳለ ብርሃን እግር ሥር ቁጭ ብለው የቅኔ ትምህርት ቀሰሙ። ይሁንና በዓመቱ የጥምቀት እለት መፈንቅለ መንግስት ተጀመረ።ስለዚህም ወደ ትምህርታቸውን ሳይቀጥሉ ወደ ትውልድ ቀያቸው ተመለሱ።
በዲቁና ተቀጥሮ የማገልገሉ አላማ እንደሌላቸው የሚናገሩት ዲያቆን ዶክተር አያሌው፤ በትምህርት ማደግ ብቻ ህልማቸው ነበር። ሆኖም ወደ ቤተሰብ የተመለሱበት ጊዜ ጥር በመሆኑ ሠርጎች ይበዛሉና በጨዋታ ተዘናግተው ቆዩ። በኋላ ግን ይህ እንደማያዋጣቸው አውቀውና አባታቸው ቆጣ በማለት”እንግዲህ የጀመርከውን የመሪጌትነት ትምህርት ቀጥል›› ስላሏቸው ዳግም ወደ ትምህርት ተመልሰዋል።
ሲማሩ ስማቸውን እንደ ማንኛውም የቆሎ ተማሪ ቀይረው ‹‹ፍሬ ሕይወት›› እንዳስባሉት የሚናገሩት እንግዳችን፤ አድልባድል ሳሙኤል ወደ ተባለቦታ በማቅናት መሪጌት ይትባረክ ጋር የተማሩትን የቅኔ ትምህርት የበለጠ ለማብሰል ችለዋል። ከዚያ የሁለተኛ ቅኔ ትምህርታቸውን የአድልባድል ሳሙኤል ደብር በዋግ አውራጃ የሚገኝ ሲሆን በወቅቱ ከአዲስ አበባ ከአራዳ ጊዮርጊስ ተነስተው ወደዚያው የሄዱትና ኑሯቸውን የመሠረቱት እውቁ ዓይነ ሥውር የተክሌ አቋቋም መምህር አለቃ መዘምር ጋር በመሆን ነው።
ለሌላ ቀጣይ ትምህርት ወደ ሰቆጣ ከተማ ያመሩት እንግዳችን፤ በሰቆጣ ከተማ ደብረ ፀሐይ ወይብላ ማርያም በመግባት ከአስተዳዳሪው መልአከ ፀሐይ መርዓዊ ወልደ ሚካኤል እግር ሥር ቁጭ በማለት የዜማ፤ የዝማሬና መዋሥዕት፣ የጾመ ድጓ፤ የምዕራፍና የቅዳሴ እንዲሁም የአቋቋምና ትጓሜ መጻሕፍትን ተማሩ። ባሕረ ሐሳብንም ከእርሳቸው ዘንድ ቀሰሙ። ስለዚህም በዚህ ትምህርት ቤት ከ1954 እስከ 1959 ዓ.ም ድረስ በመቆየት ትምህርቱን አጠናቀው ሙሉ የመሪጌትነት ሙያን አግኝተዋል።
በቆሎ ተማሪነት ሕይወት ከቤተሰብ መራቅ አለና በየመንደሩ እየዞሩ “በእንተ ስማ ለማርያም” ማለት ግዴታ ነበር። ይሁንና እንግዳችን በአካል ያልጠነከሩ በመሆናቸው ከውሾች ታግለው ቁራሽ እንጀራ ማግኜቱ ፈተና ሆኖባቸው እንደነበር የሚያስታውሱት ዲያቆን ዶክተር አያሌው፤ በዚያ ዘመን ወረቀት እንደልብ ስለማይገኝ በየሜዳው የወዳደቁ የከብቶችን የትከሻ ላይ አጥንት መጋፊያ የሚባሉትን በማሰባሰብና ከሰል በውሃ በመበጥበጥ በስንጥር እንጨት ጽህፈት እንደተለማመዱ ይናገራሉ። ስለዚህም ከሀሁ እስከ መሪጌትነት የደረሰ ትምህርትን በተለያዩ ደረጃዎች በማለፍ ተምረዋል።
ዘመናዊ ትምህርት
የአባታቸው ጉትጎታ ነበር ይህንን ትምህርት እንዲመለከቱት ያስቻላቸው። ምክንያቱም አባት በከተማዋ የሚመላለሱ ተማሪዎች ያስቀኗቸው ነበር። ብዙ ነገራቸው የተሻለ የሆነው በዚህ ትምህርታቸው የተነሳ ነው ብለው ያምናሉም። ከዚያ ባሻገር በማህበረሰቡ ልጁን የማያስተምር ሰው እንዳይባሉም ይፈልጋሉ።
በዚህም ‹‹ይህንን አስኳላውን ከዚሁ ሰቆጣ እያለህ ለምን አትሞክረውም” በማለት ጥያቄ አቀረቡ። እርሳቸው ግን በወቅቱ የነበራቸው የብስለት ደረጃ ዝቅተኛ ስለነበር “የአስኳላ ትምህርት መሬት ትዞራለች ይላል ሃይማኖትም ያስክዳል ወዘተርፈ” ሲሉ መለሱላቸው። ሆኖም ከዓመታት በኋላ ግን ጥቅሙ እየገባቸው ስለመጣ ለመማር ወሰኑ።
ያለ ክፍያ ይሰጥበት ወደነበረበት የወጣቶች ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር (ወወክማ) ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ከሚከታተሉ ተማሪዎች ጋር በመሆን አንድ ምሽት ላይ ሄዱ። ክፍል ውስጥ እንደገቡም አማርኛ መጽሐፍ እንዲያነቡ ተሰጣቸው። ንባብ ብርቃቸው ያልሆነው እንግዳችንም በሚገባ አነበቡላቸው። ይሁንና መምህራኑ ይህን ችሎታቸውን ተመልክተው ‹‹አንተን አንቀበልም እኛ የምናስተምረው የፊደል ሠራዊትን ማለት ማንበብና መጻፍ የማይችሉትን ብቻ ነው›› በማለት መለሷቸው።
ለመማር ተስፋ ያልቆረጡት ባለታሪኩ፤ አንድ ምሥራቅ የሚባል የዋግ ተወላጅን ያውቁ ኖሮ ለእርሱ የተባሉትን ሁሉ ይነግሩታል። እርሱም ‹‹ችግር የለም ትማራለህ››በማለት መምህራኑን አስፈቀደላቸው። መምህራኑ ተቀበሏቸውና ወዲያውኑ ትምህርታቸውን ጀመሩ። በዚያ የሚማሩትን ይበልጥ ለማጠናከርም እንግሊዝኛ ያለ አስተማሪ የሚል መጽሐፍ በመግዛት ማንበብም እንደጀመሩ ያስታውሳሉ።
ሌሎች የትምህርት አይነቶችን በሚገባ ለመረዳት ደግሞ “ግሪን ፕራይመር” ሪደር ዋን” የሚል የእንግሊእኛ መጻህፍት በተጨማሪ በመግዛት ያነቡ እንደነበር የሚያነሱት ዲያቆን ዶክተር አያሌው፤ በዓመት ውስጥ ከ135 አጠቃላይ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች መካከል አንደኛ ወጥተው የአራተኛ ክፍል ሰርተፊኬት ተሰጥቷቸዋል። “ገብረ መስቀል ባሪያው” የሚል ርዕስ ያለው መጽሐፍም መሸለማቸውን አይረሱትም።
ከወወክማ ከወጡ በኋላ ደግሞ ‹‹ራስ አበበ አረጋይ›› የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ገቡ። ማታ ማታ እየተማሩም ከአራተኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ድረስ አንደኛ በመውጣት አሳለፉም። በዚህ ወቅት የሚረዳቸው ሰው ስላልነበረ አምስት ብር በየወሩ መክፈል ተስኗቸው ነበር። እንደውም ስድስተኛ ክፍልን ሊያቋርጡ ሲሉ አቶ ዘነበ ወልደ ሐና የሚባሉ የዚያን ጊዜው የአዲስ አበባ ምክር ቤት ጸሐፊ ሁለት ብር እየሰጧቸው እርሳቸው ደግሞ ሦስት ብር አክለው ተማሩ።
ከትምህርታቸው በተጓዳኝ ለመማሪያቸው የሚሆን ገንዘብ ለማግኘት ተማሪዎችን ያስጠኑ እንደነበር የሚያወሱት እንግዳችን፤ ከቀኑ 10 ሰዓት ተኩል እስከ 12 ሰዓት ድረስ አስጠንተው በወር 20 ብር ያገኙ በነበር። በዚህም በመጠኑም ቢሆን ችግራቸውን ያቃልሉ እንደነበር ይናገራሉ።
በ1962 ዓ.ም የስድስተኛ ክፍል ሚኒስትሪ ፈተና 98 ነጥብ 6 አምጥተው ወደ ሰባተኛ ክፍል የተዛወሩት ዲያቆን ዶክተር አያሌው፤ በፒያሳ የልደታ ካቶሊክ ካቴድራል ትምህርት ቤት በማታው ክፍለ ጊዜ ለመማር ተመዘገቡ። ከሰባት እስከአስራ ሁለተኛ ክፍልም ተማሩበት። ከጓደኛቸው ገብረ ማርያም ዓለሙ ጋርም ጠንክረው ያጠኑ ነበርና ጥሩ ውጤትም ነው የሚያመጡት።
እንግዳችን የካቶሊክ ካቴድራል ትምህርት ቤት ክፍያ ከደምወዛቸው ጋር ስለማይመጣጠን በአራዳ ጊዮርጊስ የድጓ መምህር የነበሩት ሊቀ ጠበብት ባይነስን አስፈቅደውላቸው ከ12 ብር ሙሉ ክፍያ በየወሩ 4 ብር ተቀንሶላቸው እንዲማሩ ሆነዋል።
የእድገት በኅብረት ዘመቻ ስለነበር የመልቀቂያ ፈተናቸውን የወሰዱት ከዓመት በኋላ እንደነበር የሚናገሩት እንግዳችን፤ በ1970 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቅለዋል። በዚህም በማታው ክፍለ ጊዜ ቢዝነስ እየተማሩ አንድ ዓመት ከአምስት ወር እንደሆናቸው የውጭ አገር የነፃ ትምህርት እድል አገኙ።
በ1970 ዓ.ም የድሮዋ ዩጎዝላቪያ ውስጥ ከትምህርት ዘርፍ ደግሞ ቱሪዝም ተመድቦላቸው እንዲሄዱም ሆነ። በዚያ ከሄዱ በኋላ ግን በቋንቋ መግባባት ስለተቸገሩ በፊሎሶፊ ፋካልቲ የሰርቦ ክሮኤሽያን ቋንቋ መማር ጀመሩ።ተመረቁበትም። ከዚያ በዚያው በሚኖሩበት በዛግሬብ ከተማ በኢኮኖሚክስ ፋካልቲ ውስጥ የቱሪዝም ትምህርት በአዲስ መልክ ተከፈተና መማራቸውን ቀጠሉ። በ1972 ዓ.ም የትምህርት ውጤት መሙያ ኢንዴክስ የሚባል ማስታወሻ ደፍተር ተሰጣቸውናም የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ሆኑ።
‹‹እኔ በምማርበት የቱሪዝም ክፍል ብቸኛው ጥቁር ስለነበርኩ የተማሪዎቹ አስቂኝ ጥያቄዎች ናላዬን ያዞረው ነበር።›› የሚሉት ባለታሪኩ፤ በተለይ “በሀገርህ ፎቅ ቤቶች አሉ፤ምን ዓይነት ቤት ውስጥ ትኖራላችሁ፤ መኪና፤ አውሮፕላን ወዘተርፈ አለ›› የሚለው ያሰለቻቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።
የመጀመሪያው ዓመት ትምህርቱ ስለከበዳቸው ተጨማሪ የውጭ ቋንቋ እንዲመርጡ እድል ተሰጣቸው። በዚህም እንግሊዝኛን ለሁለት ዓመት መርጠው በሦስተኛው ዓመት ጣሊያንኛን በቋሚነት ተማሩ። ፈረንሳይኛን ደግሞ በትርፍ ጊዜያቸው ተከታትለው ትንሽ ለመግባባት በቅተዋል።
ትምህርት በማይኖርባቸው ወራት በየፋብሪካው እየተዘዋወሩ በመሥራት ገንዘብ ያገኙ የነበሩት ዲያቆን ዶክተር አያሌው፤ ሦስተኛውንና የአራተኛውን የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን በሚያስመሰግን ሁኔታ አጠናቀው የመመረቂያ ጽሑፋቸውን በእንግሊዝኛ ቋንቋ በማዘጋጀት በ1975 ዓ.ም መመረቅ ችለዋል።
ለነጻ ትምህርት ቢሮው ገና የመጀመሪያ ጽሑፌን ለማዘጋጀት ስድስት ወር ይቀረኛል በማለት ወዲያውኑ የማስተርስ ዲግሪያቸውን የጀመሩት እንግዳችን፤ በግላቸው እየከፈሉ ነበር በዓመት ከስድስት ወር ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት። አሁንም መማር የማይሰለቻቸው ባለታሪኩ፤ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ለላካቸው አካል አሳወቁና ፈቃድ ጠየቁ።
እንደ ሌሎቹ ተማሪዎች ብዙ ጊዜ ፈተና ሳይደግሙ፤ዓመት ሳያባክኑ በመቆየታቸው ኃላፊዎቹ ተደስተው የተወሰኑ ወሮች ደምወዛቸውን እየከፈሉ እንዲቆዩ ፈቀዱላቸው። እንግዳችንም ይህንን አጋጣሚ ተጠቅመው የማስተርስ መመረቂያ ወረቀታቸውን ሰሩ።በ1977 ዓ.ም ተመረቁ። ወዲያውም ዳግመኛ ዶክትሬታቸውን ለመማር የዩኒቨርሲቲውን አስተዳደር እንደ ገና ለመኑና ስለተፈቀደላቸው ተመዘገቡም። ይሁንና የቤተሰቦቻቸው ጉዳይ ስላስጨነቃቸው እንዲሁም መመረቂያ ጽሁፋቸውንም በተጨማሪ ለመስራት 75 ቀኖች ተሰጥቷቸው ወደ አገር ቤት ተመለሱ። ከብዙ ውጣውረዶች በኋላም መመረቂያቸውን ሰርተውና ለቤተሰቦቻቸው ደርሰው ወደ ትምህርታቸው ተመለሱ።በዚያም የተሻለ ጽሁፋቸውን አቅርበው በጥሩ ውጤት ተመርቀው ዳግም ወደ አገራቸው ተመለሱ።በአገራቸውም ሥራ ጀመሩ።
ከተላላኪነት እስከ ኮሚሽነርነት
ሰቆጣ ከተማ በትምህርት ላይ እያሉ ነበር በክህነታቸው በማገልገል ሥራን የጀመሩት። ከዚያ ወደ ትውልድ ቀያቸው በመሄድ ዋግ አውራጃ የዋግ ልማትና ተራድኦ ማኅበርን ከሌሎች የአካባቢው ተወላጆች ጋር በመሆን በመመሥረትና በመምራት መስራታቸውን ቀጠሉ። አሁንም እየተማሩ በወር 20 እና 25 ብር የሚያገኑበትን የማስጠናት ሥራም ይሰሩ ነበር።
የመንግሥት ሥራ ለመያዝ ከፍተኛ ጉጉት የነበራቸው እንግዳችን፤ በመንግስት መስሪያቤት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀጠሩት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ መብራትና ኃይል ባለሥልጣን ውስጥ ሲሆን፤ በተላላኪነት የሥራ መደብ ነበር። ፒያሳ ደጎል አደባባይ በሚገኜው የድሮው የባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤትም ለረጅም ዓመታት ሰርተዋል።
ከ1963 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ መብራትና ኃይል ባለሥልጣን ተቀጥረው እስከ 1791 የሰሩት እንግዳችን፤ በ1966 ዓ.ም ነበር የ10ኛ ክፍል ውጤታቸው በመያዝ ተወዳድረው ወደ ቆጣሪ አንባቢነት ከፍ ያሉት። በዚህ ሙያ ላይ ለአምስት ዓመታት ከሠሩ በኋላ ደግሞ በ1970 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ሌላ የከፍተኛ ጸሐፊ ቦታ የእድገት ማስታወቂያ ወጥቶ ስለነበር ተወዳድረው አለፉ። አምስት ወር ከሰሩ በኋላ ግን የነፃ ትምህርት እድል በማግኘታቸው ሥራውን ትተው ወደ አውሮፓ ተጓዙ።
ከትምህርት መልስ ሙሉ የትምህርት መስካቸው ቱሪዝም ስለነበር በቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ ቱሪዝም ኮሚሽን እንዲገቡ ነበር የሆነው። በቦታውም የፕላን አገልግሎት ንዑስ ክፍል የቱሪስት መስሕቦች ጥናትና ምርምር ውስጥ በጀማሪ ባለሙያነት መስራት ጀመሩ። በዚህም ኮሚሽኑ የኢትዮጵያን የቱሪዝም ማስተር ፕላንና ሌሎች ልዩ ልዩ ቱሪዝም ነክ ጥናቶችን በውጭ አማካሪዎች ባስጠናበት ወቅት በአቻ ባለሙያነት ግልጋሎት መስጠታቸውንም ይናገራሉ።
በኮሚሽኑ ለ14 ዓመታት ያህል አገልግሎት እንደሰጡ ያጫወቱን ዲያቆን ዶክተር አያሌው፤ በ1992 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ቱሪዝም ኮሚሽን የጡረታ መብታቸው ተከብሮ ለመልቀቅ ችለዋል። ይሁንና ዲያቆን ዶክተር አያሌው ለሥራ ደከመኝ ሰለቸኝ አያውቁም። በዚህም ጡረታ ከወጡ በኋላ እንኳን ከመስራት አልቦዘኑም። በቀጥታ አሁንም ለመስራት ወደ ፔሊካን የጉዞ ወኪል የተባለ የግል ድርጅት ነበር የገቡት። በድርጅቱም ሥራ አስኪያጅ በመሆን ለሦስት ዓመት ሰርተዋል።
በ1995 ዓ.ም አጋማሽ ላይ ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ የቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው ለመሾም ችለዋል። ስድስት ዓመት በኋላ ደግሞ ዳግም በፔሊካን ትሬዲንግ የግል ድርጅት ውስጥ በመግባት በነበረ ቦታቸው መስራት ጀመሩ። በመካከል ታመው ሥራ አቁመው ቆዩ። ሆኖም ከሕመማቸው ካገገምኩ በኋላ ወደ ሥራቸው በመመለስ ጮራ አስጎብኚ ድርጅት ውስጥ በቱር ኦፕሬሽን ማኔጀርነት ተቀጥረው ለሁለት ዓመታት ሰሩ።
በድርጅቱ ባለቤት ፍላጎት በባሕል አማካሪነት ብቻ የተወሰነ ገንዘብ በወር እየተከፈላቸው የሚሰሩት እንግዳችን፤ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በቋሚነት ከሚሰሩት በተጨማሪ በአዲስ አበባና ኦሮሚያ ልዩ ዞኖች ተቀናጀት የጋራ ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ውስጥ በአማካሪነት በኮንትራት ተቀጥረው የቅርስና የቱሪዝም ጥናት ቡድን መሪ በመሆን ለሁለት ዓመት አገልግለዋል።
በአጠቃላይ ዲያቆን ዶክተር አያሌው፤ በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ቱሪዝምን የሚመለከቱ ጥናቶችን አድርገዋል። ወደ ተለያዩ ክልሎች በመንቀሳቀስ አውደ ጥናቶችን፣ ሰሚናሮችን፣ ልዩ ልዩ ሥልጠናዎችንም ሰጥተዋል። በመደበኛነት ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ተማሪዎች ስለ ኢትዮጵያ ተፈጥሮአዊና ሰው ሠራሽ የቱሪስት መስሕቦች ሰፋ ያለ እውቀት እንዲጨብጡ አድርገዋልም።
በመምህርነት በላዮን ኢትዮጵያ የሆቴልና የቱሪዝም ኮሌጅ፤ በአይቤክስ የሆቴልና ቱሪዝም ማኔጅሜንት ኮሌጅ፤ በማዕዶት የሆቴልና የቱሪዝም ኮሌጅ የሰጡ ሲሆን፤ በመንግሥታዊ ተቋም ደግሞ በቱሪዝምና ሆቴልሥራ ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩትም ቱሪዝም ነክ ኮርሶችን አስተምረዋል። በተጨማሪ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለአብነት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕንፃ ኮሌጅና የስድስት ኪሎ ካምፓስ፣ በአዋሳ ዩኒቨርሲቲ የወንዶ ገነት ኮሌጅ የዋይል ላየፍ ትምህርት ክፍል፣ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ፣ በአክሱምና መቀሌ ዩኒቨርሲቲ እና በጅማ እንዲሁም በቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝም ትምህርት ክፍሎች የቱሪዝም ማርኬቲንግ፣ የቱሪዝም ፕላኒንግ፣ የቱሪስት መስሕብ ወዘተ ትምህርቶችን አስተምረዋል።
ማህበራዊ ተሳትፎ
እንግዳችን አውሮፓ እያሉ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበርን አባል ከመሆን ጀምሮ እስከ ሊቀ መንበርነት ድረስ ያገለገሉ ናቸው። በዚህም ብዙ ሥራዎችን ሰርተዋል። በተለይ አገርን ከማስተዋወቅ አኳያ የማይተካ ሚና ነበራቸው።
የዋግ ልማትና ተራድኦ ማኅበር፤ በላስታ አውራጃ ቅዱስ ላሊበላ ልማትና ተራድኦ ማኅበር፤ በወሎ ልማትና ተራድኦ ማኅበር፤ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በመሆንም ለአካባቢያቸው ማህበረሰብ የደረሱ ናቸው። ከዚያ ባሻገርም በሆቴልና ቱሪዝሙ ዘርፍ ብዙ ተማሪዎችን አፍርተዋል። የቱሪዝሙ ዘርፍ በየጊዜው እንዲለወጥም ከማድረግ አንጻር ትልቅ አስተዋዕጾ ያደረጉም ናቸው።
ሶስት ጉልቻ
የመጀመሪያ ሚስታቸውን ያገቡት በቤተሰብ ፍላጎት ነበር። ቤተሰብ በባሕላዊ መንገድ ወጥቶ ወርዶ፣ ዘሯን አጥንቶ አቻ ለአቻ ጋብቻ ብሎ ፈቅዶ ያገኛትም በመሆኗ እንቢ ማለት አልቻሉም ነበር። ስለዚህም ተታለው ከትምህርት ቦታቸው ካመጧቸው በኋላ ሰርጉ ተደግሶ እንዲያገቧት ተደረገ። አብረውም መኖር ጀመሩ። ሆኖም እርሳቸው ለትምህርታቸው ከፍተኛ ትኩረት ይሰጡ ነበርና ምንም ሳይነኳት ተመለሱ።
ትምህር ቤት ባሉበት ጊዜ ወረርሽኝ በአካባቢው ገብቶ ስለነበር ባለቤታቸውን ከእነቤተሰቧ ያዛቸው። እርሳቸው ግን ይህንን አልሰሙም ነበርና ሳይጠይቋቸው ቀሩ። በዚህም ከዓመታት በኋላ ወደ ባለቤታቸው ሲመለሱ ወቀሳ ጠበቃቸው። ይቅርታ መጠየቅ ግዴታቸው ነበርና አድርገውት ባለቤታቸውን ወስደው በሰላም መኖር ጀመሩ። ግን ብዙም ሳይቆዩ አዲስ አበባ ለመግባት ልባቸው ተነሳሳ። በዚህም እርሷን ትተዋት ጉዞ ወደ ሸገር ሆነ።
ከብዙ ዓመታት የስራና የትምህርት ጊዜ በኋላ ደግሞ በራሳቸው ፈቃድ የመረጧትን ሚስት እንዳገቡ ያጫወቱን እንግዳችን፤ በጣም የሚወዱትን ጓደኛቸውን እህት ነበር ለውሃ አጣጭነት የመረጡት። ፍቅሩ ደግሞ ከሁለቱም የመጣ በመሆኑ እያንዳነዱን ነገር በመወያየት ያደርጉ እንደነበር ይናገራሉ። በዚህም ዛሬ የሦስት ልጆች አባት ሆነዋል። ልጆቻቸው ትምህርታቸውን በሚገባ ተከታትለው ለከፍተኛ ትምህርት በቅተዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 24/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው