ትምህርት የዕድገት መሰረት ነው። ያለ ትምህርት ህይወትን ማሻሻል፤ ኑሮን መለወጥ አይታሰብም። ሆኖም ግን የሀገራችን ትምህርት ባለበት ዘርፈ ብዙ ችግሮች በትምህርት የታሰበውን ያህል ሀገርን ማሳደግ፤ ኑሮንም ማሻሻል አልተቻለም። ብዙዎች ተምረው ከዕለት ጉርስ ባለፈ የተድላ ህይወት ሲመሩ አይታዩም። እንደውም የተማረ በራሱ ላይ ድህነትን እንዳወጀ ተደርጎ የሚታሰብበትም ሁኔታ ብዙ ነው። ጥቂቶች ግን አሉ የሚብጠለጠለውን የትምህርት ጥራት በራሳቸው ጥረት ሞልተውና አቅም ፈጥረው ህይወትን ብሩህ ማድረግ የቻሉ።
መርዕድ በቀለ ይባላል። በ1975 ዓ.ም በአዲስ አበባ ተወለደ። እስከ ሁለተኛ ደረጃ ድረስ ዳግማዊ ሚኒሊክ ትምህርት ቤት ትምህርቱን ተከታተለ። በትምህርቱም ጎበዝ ስለነበረ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተናን በጥሩ ውጤት አለፈ፤ መቀሌ ዩኒቨርሲቲንም ተቀላቀለ። በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ሙያ ዘርፍም ትምህርቱን ቀጠለ። እስከ ሁለተኛ ዓመትም ዘለቀ። ሁለተኛ ዓመት ሲደርስ ግን ኮምዩፒዩተር ከሚባለው ግዑዝ ነገር ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ተዋወቀ። እዚህ ደረጃ ላይ እስኪደርስ ድረስ ግን ለዛሬው ስኬቱ መሰረት የሆነውን የኮምፒውተር ቴክኖሎጂ እንደ ልዩ ፍጡር በሩቁ ከመመልከት ውጪ በእጁም ነክቶ አያውቅም። ሆኖም ግን ወጣቱ መርዕድ ወዲያው በኮምፒዩተር ፍቅር ወደቀ፣ ሃሳቡም፤ ህልሙም ኮምፒዩተር ሆነ።
በተለይም ደግሞ የኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ አስተማሪ የነበረውን አሜሪካዊው ሌክቸረር የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፍቅር እንዲሰርጽበት እንዳደረገው መርዕድ ይናገራል። መምህር የተማሪን ህይወት ይቃኛል የሚለው ተለምዷዊ አባባል በመርዕድ ህይወት ውስጥ ጉልህ ስፍራ አለው። ውሎውንም አዳሩንም ከኮምፒዩተር ጋር ያደረገው ወጣትም ፍቅሩንም ከመወጣት በሻገር በርካታ ዕውቀቶችንም መሸመት ጀመረ። ታታሪው መርዕድ ሶስተኛ ዓመት እንደደረሰ ‹‹state of the art››የተባለ ክበብ ከጓደኞቹ ጋር አቋቋመ። ክበቡንም በፕሬዚዳንትነት በመምራት በርካታ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ስራዎችና ፈጠራዎች ዕውን እንዲሆኑ አድርጓል። በመርዕድና ጓደኞቹ የተቋቋመው ክበብም እስካሁን ድረስ ለበርካታ ተማሪዎች የአይን መግለጫ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል።
መርዕድ አራተኛ ዓመት ሲደርስ ከሚማርበት የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የስራ ዕድል መጣለት። አሜን ብሎ ተቀብሎም ዩኒቨርሲቲውን ወደ ፊት ሊያራምዱ የሚችሉ የዳታ፤ የሲስተምና የኔትወርክ ስራዎችን በመስራት ሀገሩን ማገልገል አንድ ብሎ ጀመረ። ለብዙዎቻችን ለአደጉት ሀገራት ብቻ የተተወ የሚመስለንን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዕውቀት መርዕድ ገና በተማሪነቱ በብቃት ይወጣው ጀመር።
ትምህርቱን አጠናቆ እንደወጣም ጂኤስሲ በተባለ ኩባንያ ውስጥ ተቀጥሮ ልምዱን አካፈለ፤ በርካታ ተሞክሮዎችንም አገኘ። በመቀጠልም ኤሲቲ ዴቨሎፕመንት ኤጀንሲ በተባለ መንግስታዊ ተቋም በማገልገል በርካታ የመንግስት ፕሮጀክቶች ከአይሲቲ ጋር እንዲተዋወቁ አድርጓል። በዚህ መሃልም በጃፓን ሀገር የሚገኝ ሲስኮ ሰርቲፋይድ ከተባለ ተቋም የትምህርት ዕድል በማግኘቱ በዘርፉ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሆኖ ትምህርቱን ተከታትሎ ለማጠናቀቅ ችሏል።
መርዕድ እንደሚናገረውም ጃፓኖች በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ያላቸው ዕውቀት የዛሬዋን ጃፓን ዕውን ያደረገና የህልውናቸውም መሰረት ነው። ከጃፓን ከተመለሰ በኋላም የኢትዮጵያ ቴሌኮሚኒኬሽን ኮርፖሬሽን የሞባይል ኔትወርክ የማስፋፋት ስራዎችን የጀመረበት ወቅት በመሆኑ በስራው የመሳተፍና ያገኘውንም ዕውቀት ለሀገሩ የማካፈል ዕድል አገኘ። በአጭር ጊዜ ውስጥም አንድ ሚሊዮን ብቻ የነበረውን የሞባይል ተጠቃሚዎች ቁጥር ወደ 30 ሚሊዮን የማሳደግ ስራዎች በመላ ሀገሪቱ ዕውን ሆኑ።
ገና የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለ ‹‹በትልቁ አልም ከትንሽ ተነሳ›› የሚል መርህ ያለው ታታሪው መርዕድ የራሱን ቢዝነስ መጀመር እንዳለበት ልቡ ይነግረው ጀምሯል። በትንሽም ነገር መርካት የውድቀት መጀመሪያ መሆኑንም ጠንቅቆ አውቋል። ስለዚህም በየጊዜው በሚያገኛቸው ስኬቶች ሳይረካ ትልቁን ህልም መሬት ለማውረድ ተዘጋጀ። በ2002 ዓ.ም አካባቢ አይ.ኢ.ኔትወርክ ሶሉሽን (IE NETWORK SOLUTIONS) የተባለ ድርጅት ከባለቤቱ ጋር ሆኖ አቋቋመ። በወቅቱ የኮምፒዩተርና ተዛማጅ ዕቃዎችን ከውጭ ማስመጣት፤ ለባንኮችና ለተለያዩ የመንግስትና መንግስታዊ ላልሆኑ ተቋማት ኔትወርክ መዘርጋት፤ ዳታ ማደራጀትና መተንተን የመሳሉትን ስራዎች በማከናወን ስራውን ማስፋፋት ጀመረ። በጊዜውም 50 ሺህ ብር በማትረፍ ለዛሬው ማንነቱ መሰረት ጣለ።
በአሁኑ ዘመን ያለ ኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዕድገትን ቀርቶ የዕለት ተዕለት ህይወትንም ማሰብ አዳጋች መሆኑን የሚናገረው ወጣት መርዕድ ሀገራችን ከዘርፉ ገና መጠቀም አልጀመረችም ሲል ይደመጣል። ኢትዮጵያ ገና በመልማት ላይ ያለች ሀገር በመሆኗና በየተቋማቱ የሚሰጡ አገልግሎቶችም ከባህላዊ መንገድ ያልተላቀቁ በመሆናቸው መጠነ ሰፊ የሆነ የኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ዝርጋታ ያስፈልጋታል። ነጋዴው ግብር ለመክፈል ጊዜውን ወረፋ በመያዝ ማሳለፍ የለበትም። ዜጎች ውሃና መብራት ለመክፈል በአገልግሎት አሰጣጥ መጓደል መማረር አይገባቸውም። ገንዘብ ዝውውሮች ከደረቅ ገንዘብ መላቀቅ አለባቸው። እነዚህና መሰል የዕድገት ማነቆዎች ሊፈቱ የሚችሉት ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ዕውን ስናደርግ መሆኑን መርዕድ አበክሮ ይመክራል።
እሱ ያቋቋመውም ድርጅት ከትርፍ ይልቅ የህብረተሰቡን እንግልት በሚቀንሱና የሀገሪቱን ዕድገት ወደፊት በሚያራምዱ ስራዎች ላይ ትኩረቱን ያደርጋል። መንግስት በአሁኑ ወቅት ለዘርፉ የሰጠውም ትኩረት በርካታ የተማሩ ወጣቶች በዘርፉ ተሰማርተው ፍሬ እንዲያፈሩ የሚያስችል ነው። በገበያውም ላይ ሰፊ የሆነ የሰው ኃይል ፍላጎት መኖሩን መርዕድ ይናገራል። ይሁን እንጂ ከዩኒቨርሲቲዎች ተመርቀው የሚወጡት ወጣቶች በአግባቡ በተግባር የተደገፈና ዘመኑ የሚፈልገውን ዕውቀት ጨብጠው ስለማይወጡ በቀላሉ የስራ ዕድሉ ተጠቃሚ ለመሆን ሲቸገሩ መመልከቱን ይገልጻል። የሱ ድርጅትም ከዩኒቨርሲቲዎች የወጡ ተማሪዎችን ለአንድ ዓመት ያህል ደሞዝ እየከፈለ የተለያዩ ስልጠናዎችን እንዲያገኙ በማድረግ የስራ ዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያደረጋቸው ይገኛል። ስለዚህም የዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት አሰጣጥ ከተሻሻለ እና በገበያ ተፈላጊ የሆኑ ወጣቶችን ማቅረብ ከተቻለ በቴክኖሎጂው ዘርፍ መፍጠር የሚቻለውን የስራ ዕድል በቁጥር መገደብ እንደማይቻል ወጣት መርዕድ በልበ ሙሉነት ይናገራል።
መንግስት በዚህ ዓመት በኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ዘርፍ ለ250 ሺህ ወጣቶች ስራ ዕድል ለመፍጠር ማቀዱን መርዕድ በበጎ ጎኑ ያየዋል። ይሁን እንጂ መንግስት በዘርፉ ለተሰማሩ የግል ድርጅቶች ማበረታቻና ፖሊሲ መሻሻያዎችን ቢያደርግ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን የስራ ዕድል ባለቤት ማድረግ ይቻለዋል ሚል ዕምነት አለው። በህንድና በቻይና በዘርፉ ለተሰማሩ የግል ድርጅቶች በተሰጠው ልዩ ትኩረትም በየዓመቱ በሚሊዮኞች የሚቆጠሩ ወጣቶች የስራ ዕድሉ ተጠቃሚ ሊሆኑ በቅተዋል ሲል ዕውነታውን ያጠናክረዋል። አፍሪካዊቷ ርዋንዳ ለኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ ትኩረት በመስጠቷ በአፍሪካ በፍጥነት በማደግ ላይ ካሉ ሀገራት አንዷ ለመሆን በቅታለች በማለት በምሳሌነት ያነሳታል።
በተለይም የመንግስት ተቋማት የሚሰጡት አገልግሎት ከተንዛዛ አሰራርና ከእንግልት የጸዳ ለማድረግ በመንግስት በኩል የተጀመሩት ስራዎች (easy of doing business) የቴክኖሎጂውን ዘርፍ ዕገዛ የሚፈልግ ነው። ይህን ደግሞ ጥቂት ድጋፍና ማበረታቻ ከተደረገ በዘርፉ በተሰማሩ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በቀላሉ ሊሰራ የሚችልና በርካታ ወጣቶችም ከሚፈጠረው ዕድል ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉበት ነው። ቴሌን የመሳሰሉ የመንግስት ተቋማት ወደ ግል ሲዞሩም በዘርፉ የሚፈጠረው የስራ እድልም ሰፊ ነው። መርዕድና ባለቤታቸው ያቋቋሙት ኤ.ኢ. ኔት.ወርክ ሶሉሽንስ በዘርፉ ከሚፈጠሩት ዕድሎች ተጠቃሚ ለመሆን ራሱን በማጠናከር ላይ እንደሚገኝ ወጣት መርዕድ ይናገራል። ልዩ ልዩ ባለሙያዎችን ወደ ውጪ ልኮ ከማስተማር በሻገርም ዘመኑን የሚመጥኑ አሰራር ሥርዓቶችን የመዘርጋት ስራዎች በስፋት በማከናወን ላይ ይገኛል።
በባለቤታቸውና በአቶ መርዕድ የተቋቋመው ድርጅት ዛሬ 80 ወጣት ባለሙያዎች ቀጥሮ እያሰራ ይገኛል። ዓመታዊ ገቢውም ከ50 ሺህ ብር ተሻግሮ 100 ሚሊዮን ብር ደርሷል። በሚቀጥሉት አምስት ዓመታትም ወደ 1 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ አቅዶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። ወጣት መርዕድ እንደሚለውም ወጣቶች ትልቅ ህልም ሊኖራቸው ይገባል። ትልቅ ህልማቸውንም ከያዟት ትንሽ ነገር መጀመር ይችላሉ። ዛሬ የተጀመረች ትንሽ ነገር ነገ ትልቅ ሆኖ ከራስ አልፎ ለሌሎችም ይተርፋል። ወጣቶች ጊዜያቸውን በአልባሌ ነገር ከማጥፋት እራሳቸውንም ሆነ ሀገራቸውን ሊለውጡባቸው በሚችሉ ስራዎች ሊሰማሩ ይገባል። ስራዎችን ካልናቅን ልንሰራቸውና ልናድግባቸው የምንችልባቸው በርካታ የስራ ዘርፎች አሉ። በርካታ ወጣቶች ኢንፎርሜሽን ዘመን ላይ ቢገኙም ከፌስቡክ በዘለለ ለፈጠራና ለሀብት ማግኛ ሲያደርጉት አይታይም።
ወጣቶች ከዘመናቸው ሊያተርፉ ይገባል የሚለው ወጣት መርዕድ ዘመን ካለፈና በተለይም ደግሞ ቴክኖሎጂን የመሳሰሉ በፍጥነት ዕድገት ከሚያሳዩ የፈጠራ ውጤቶች ጋር አብሮ መራመድ ካልተቻለ እንደግለሰብም እንደሀገርም ውድቀት መሆኑን አበክሮ ይናገራል። ኢትዮጵያ በርካታ ወጣቶች የሚገኙባትና በልማት ጎዳና ላይ ምትገኝ ሀገር እንደመሆኗ ዘመኑ ከፈጠረው የቴክኖሎጂ በረከት ልትቋደስ ይገባል። በዚህ ዘመን በጥንቱ በሬ ለማረስ መሞከር ተሰባብሮ ከመቅረት የዘዘለ ፋይዳ አይኖረውም። ከ3ሺህ ዓመታት በላይ አንዳችም ማሻሻያ ሳይደረግበት በእንስሳት ጉልበት ስንገለገል የቆየነውን የአስተራረስ ዘዴያችንን ከዘመኑ ጋር ማስታረቅ አለብን። ወጣት መርዕድ እንደሚለውም ዘመኑ የቴክኖሎጂና የፈጠራ እንደመሆኑ ለወጣቶች ምቹ ጊዜ ነው። ዘመኑን በአግባቡ ካስተዋሉት ወጣቶች ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም መትረፍ ይችላሉ።
ኢትዮጵያውያን ወጣቶች አቅምም ችሎታም እንዳላቸው ምስክርነቱን የሚሰጠው ወጣት መርዕድ በተለይም መንግስትና ባለሀብቶች ለወጣቱ ምቹ ነገር መፍጠር ከቻሉ ኢትዮጵያውያን ተአምር መስራት እንደሚችሉ ይናገራል። በተለይም በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ከሚገኘው ሀብት ከ65 በመቶ በላይ ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የሚገኝ እንደመሆኑ መጠን ወጣቶች ይህንን ተዝቆ የማያልቅ ሀብት በአግባቡ ሊጠቀሙበት ይገባል ሲል ምክሩን ያካፍላል። ወጣቶች ከዘመናቸው ያትርፉ የሚለው ደግሞ በመጨረሻ የሚያስተላልፈው መልዕክት ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 23/2012
እስማኤል አረቦ