ወይዘሮ አትክልት ጃንካ የተወለዱት አዋሳ አካባቢ ቢሆንም በስራ ምክንያት ወደ አዲስ አበባ በመምጣት እንጦጦ ኪዳነምህረት አካባቢ ረዘም ያለ ጊዜ አሳልፈዋል። እዛ እያሉም ስራቸው በአንድ የእርዳታ ድርጅት ውስጥ ስለነበርና ስራቸው ስለሚያገናኛቸው በአካባቢው ያሉ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ልጃገረዶች ለቅጠል ለቀማ ሲሰማሩ የሚደርስባቸውን በደል በቅርበት ለመመልከት ይበቃሉ። እነዚህ ቤተሰብን ለመደገፍ ርሀብን ለማስታገስ ብለው በየደኑ የሚዘዋወሩ አብዛኛዎቹ ልጆች እናትም አባትም የሌላቸው ቀሪዎቹ በፍቺና በሞት ቤተሰባቸውን የተነጠቁ ሲሆኑ የተወሰኑት ደግሞ እናት ብቻ ያላቸው ነበሩ። ይህም በለጋ እድሜያቸው ራስን መቻል ብቻ ሳይሆን ለታናናሾቻቸው አንዳንዴም እቤት ለዋሉ አረጋውያን በቅጠል ለቀማ የእለት ጉርስ የማቅረብ ሃላፊነት እንዲጣልባቸው ያስገድዳቸዋል። ቅጠል ለቀማውም ቢሆን ግን እንዲህ ቀላል አልነበረም። ዋናው ችግር ደግሞ በደን ጠባቂዎች መደፈር ነው። እናም ብዙዎቹ ልጆች ከፈረሰ ቤተሰብ መምጣታቸው ሳያንስ ያለፈቃዳቸው አርግዘው ሌላ የፈረሰ ቤተሰብ ለመመስረት ይገደዱ ነበር። እናም ወይዘሮ አትክልት እነዚህን ልጆች ከመምከርና ባሉበት ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ አንዳንድ ግዜ ወደቤት በማምጣት ማልበስ መመገብ ይጀምራሉ።
በዚህ የተጀመረው አለሁ ባይና ፈላጊ ያጡ ልጆችን የመደገፍ ሀሳብ ተወልደው ወዳደጉባትና ከአዲስ አበባ 317 ኪሎሜትር ርቃ ወደምትገኘው ይርጋለም ከተማ ይጠራቸዋል። በልጅነት እድሜያቸው በሴት ልጆች ላይ ይደርስ የነበረውን ትምህርት ማቋረጥ መደፈርና ያለእድሜ ጋብቻ ያውቁ ስለነበር ሸገር የጀመሩትን አላማ ይዘው ወደ ትውልድ ቀዬአቸው ያቀናሉ። እዛ ሲደርሱ ግን በአካባቢው በሳቸው የልጅነት እድሜ ከሚያውቁት ችግር የተለየ አዲስ ነገር ይገጥማቸዋል። ከረጅም አመታት በፊት በሳቸው ዘመን ሴቶች ከጋብቻ ውጪ ማርገዛቸውን ሲያውቁ አልያም ነገሮች መስመር ስተው ሲወልዱ አካባቢያቸውን ጥለው መሰደድ የተለመደ ድርጊት ነበር። በዛ አካባቢ ማህበረሰቡ ከጋብቻ በፊት የምትወልድን ሴት «ባና» የሚል ስም በመስጠት እንደ ትልቅ ነውር ይቆጥርበት ስለነበርና ልጅቱን የሚያገባትም ስላልነበር ስፍራ መቀየሩ የግድ ነበር። አሁን ግን የባህሉ መክረርና የኑሮ ውድነት ነገሩን አባብሶት ያገኙታል። ዛሬ ዛሬ ልጃገረዶቹ የሚመርጡት መንገድ ሳይፈልጉ የጸነሱትን ከዚያም ሲያልፍ የወለዱትን ልጅ አዝሎ መሰደድ ሳይሆን በድብቅ ወልዶ መጣል ሆኗል።
ይህንን የሰሙት ወይዘሮ አትክልትም አይናቸውን ከፍተው ጆሯቸውን አስፍተው ነገሩን መከታተል ይጀምራሉ ። በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ በከተማዋና አጎራባች ቀበሌዎች በጅብ ጎሬ፤ በቆሻሻ ማጠራቀሚያና በገበያ መሀከል ሳይቀር ይህችን አለም ከተቀላቀሉ አንድ ቀን ያልሞላቸውን ልጆች በፌስታል፤ በጨርቅና በማዳበሪያ ተጥለው ማግኘት አንዳንድ ግዜ ደግሞ ህጻናቱን እንደ እቃ ጠቅልለው ለጫማ ጠራጊ አልያም በአካባቢው ላለ ሰው አደራ ይጠብቁልኝ ብለውም እልም ብለው መጥፋት የተለመደ ሆኖ ያገኙታል። እንዲህ ተጥለው ከሚገኙት መካከልም የአውሬ ሲሳይ የሆኑና ባሉበት አልያም ሆስፒታል ደርሰው ለዘላለም ይህቺን አለም የሚሰናበቱ ህጻናትም ነበሩ።
«ማንም እናት የማህጸኗ ክፋይ የሆነውን ልጇን ጠልታ አትጥልም» የሚልም ጽኑ እምነት የነበራቸው ወይዘሮ አትክልትም ነገሩን ለመጋፈጥና በየቦታው የሚጣሉ ህጻናትን ለመታደግ ይወስናሉ። እናም ውለው ሳያድሩ ከመንግስት ጋር በመነጋገር ተጥለው ለሚገኙ ህጻናት አለሁ ማለትን ቤት ተከራይተው ለመጀመር ይወስናሉ። ነገሩን እንዲህ እንደዋዛ መገላገል እንደማይቻል ቢረዱትም አንዲት የራሳቸውን ቤተሰብ በመመስረት አለፈቃዳቸው ይህቺን አለም ተቀላቅለው ለስቃይ የሚዳረጉትን ህጻናት ለመታደግ ማቄን ጨርቄን ሳይሉ ወደስራው ይገባሉ። በዚህም «ጣሊታ ራይዝ አፕ» የተባለውን ጣሊታ ደጋፊ ያጡ ህጻናት ልጃገረዶችና አረጋውያንን መደገፍ አላማው ያደረገውን ማህበር የዛሬ አስር አመት ያቋቁማሉ። ጣሊታ ከመጽሀፍ ቅዱስ የተወሰደ ቃል ሲሆን “አንቺ ሴት ልጅ ተነሽ ቁሚ እንደማለት ነው” የሚሉት ወይዘሮ አትክልት ሴትን መደገፍ ማብቃት ቤተሰብን ማጽናት ነው። ሴት ስትነካ ቤተሰብ ይናጋል በትዳር መፍረስ ደግሞ ቀዳሚ ተጎጂ ልጆች ናቸው፤ የሚል እምነት አላቸው። ለዚህ ደግሞ እሳቸው በልጅነት ማግባታቸው ነገሮችን በአስተውሎት እንዲያዩ እንዳደረጋቸው ይናገራሉ።
እንዲህ አይነት በሰው በጎ ፈቃድ ላይ የተመሰረተና በቤት ኪራይ የሚኖርን ህጻናት የተሰባሰቡበት ቤተሰብ መምራት ግን ቀላል አልነበረም። ነገሩ ሲከፋና ጊዜው ሲረዝም አለሁ ብሎ ስራ ያስጀመረውም መራቅ ይጀምራል። የለጋሾች እጅ ሲቀዛቀዝና ወር ሲሞላ ደግሞ የጀርባውን ጉድ የማያውቅ አከራይ ብሬን ክፈይ አልያም ልጆችሽን ይዘሽልኝ ውጪ ብሎ አይኑን አፍጦ ይመጣል። በዚህ ላይ ምንም እንኳ ህጻናቱን በሀገር ውስጥ ጉድፌቻ የሚወስድ ቢኖርም በአካባቢው ህጻን ሰብስባ የምታሳድግ አለች የሚለው ወሬ በመሰማቱ ተመሳሳይ ችግር ሲፈጠር ወደማቆያው የሚመጡት ህጻናት ቁጥር ቀላል አልነበረም። የወደቁ ህጻናትን ያዩ የአካባቢው ነዋሪዎችም ሆኑ ፖሊሶችና የከተማዋ ሴቶችና ህጻናት ቢሮ መንገዳቸውን ሁሉ ወደነሱ ያደርጋሉ። አንዳንዴም ሀይለኛ ዝናብ ሲጥልና በውድቅት ሌሊት ህጻናትን ማቆያው በር ላይ እንደ አደራ እቃ አስቀምጠው የሚሄዱም ነበሩ። ማቆያው በአንድ ወቅት ከተወለዱ ቀናትን ብቻ ያሳለፉ የቆርቆሮ ወተት ብቻ የሚጠቀሙ ሀያ አራት ልጆችን አጨናነቆ ለመያዝ ተገዶም ነበር። አብዛኛዎቹ ልጆች በድብቅ ተጥሎው ከነበረበት የተነሱ በመሆናቸውም ጤናቸው የታወከና ህይወታቸውም ለአደጋ የተጋለጠ ነበር።
ይህ ሁላ ሲሆን አብረዋቸው ያደጉና የተማሩ በውጪ የሚኖሩ ጓደኞቻቸው ብቻ በቋሚነት «የእትክልትና የቡና» ፕሮግራም ብለው አንድ አትክልትና ቡና የሚጠቀሙበትን ብር እየሰበሰቡ ይልኩላቸው ነበር። ይህም በየወሩ ሲመጣ ለቤት ኪራይና ሲተርፍም ለልጆች ጉርስ ይውላል። በነጋ በጠባ የችግሩን አሳሳቢነት በደብዳቤም በቃልም እየገለጹ እርዳታ ማሰባሰብ ደግሞ የዘወትር ስራቸው ነበር። ግን ሁሌ አይቀናም፤ አንዳንዱ ይሰጣል፤ አንዳንዱ ቃል ብቻ ይገባል፤ አንዳንዱም ፊት ነስቶ ይመልሳቸዋል። አንዳንዴም ደግሞ ከፋ ያለ ችግር በተለይ ልጆቹን ህመም ሲገጥማቸው የወርቅ ጌጣቸውን አውጥተው ይሸጣሉ። ይሄ ሁላ ሆኖ ብር ሲያጥር ሰራተኞች ለወራት ደመወዛቸውን ሳይወስዱ ለመስራት ይገደዱ ነበር። ከሰራተኞቹ መካከል በዚህ ሁኔታ ያለፉት ሞግዚት፤ ምግብ አብሳይና አንድ አባትም እስካሁን አብረው ይገኛሉ። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ወይዘሮ አትክልት በዚህ ውጥረት ውስጥ ባሉበት ወቅት ሌላ ችግር ደግሞ ከወደ ቤተሰብ ብቅ ይላል።
ወይዘሮ አትክልት የአምስት ልጆች እናት ናቸው። የሚኮሩበት አለኝ የሚሉትም ትዳርና ቤት ነበራቸው። ስራው ትንሽ ከተጠናከረ በኋላ ግን ሁሉ ነገር አልሟላ ሲል ማይግሪን የተባለ ከፍተኛ የራስ ምታተና የጨጓራ ህመም ሲገጥማቸው አንዳንድ ድጋፎችን ለማግኘት ፊታቸውን ወደ ቤተሰብ ያዞራሉ። ነገር ግን ነገሩ ረጅም ጊዜና ከፍተኛ መስዋእትነት እንደሚጠይቅ የተረዱት ቤተሰቦቻቸው «ማድረግ ያለብሽን አድርገሻል ከዚህ ውጪ ልጆቹን መንግስት ይንከባከብ አርፈሽ ተቀመጪ ሁሉንም ትተሽ ልጆሽን አሳድጊ» ይሏቸዋል። እሳቸው ደግሞ ለነፍሴም ለስጋዬም የጀመርኩት ነው፤ ይህን ትቼ የምኖረው ህይወት ህይወት አይሆነኝም፤ ህሊናዬም እረፍት አያገኝ ብለው ጅምራቸውን ይቀጥላሉ። ግን ነገሩ እንዲህ በቀላሉ የሚለቅ አልነበረም። ምንም እንኳ ባለቤታቸው ስራውን ሲጀምሩ ደጋፊያቸው የነበሩ ቢሆኑም ቀን ቀንን እየወለደ ነገሮች እየተወሳሰቡ ሲመጡ አንዱን ሊመርጡ እንደሚገባ ያሳስቧቸዋል። እሳቸው ግን በሀሳባቸው በመጽናታቸው ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ከባለቤታቸው ጋር ለመለያየት ይገደዳሉ። ይህ ደግሞ አምስት ልጆቻቸውን የማሳደግና የመንከባከብ ሃላፊነትን ብቻቸውን እንዲሸከሙ ያደርጋቸዋል።
ይህን ሁላ ነገር በቅርበት ሲከታተሉ የነበሩት የይርጋለም ከተማ አስተዳደሮችም ከከተማው ሴቶችና ህጻናት ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር መጠነኛ የቀበሌ ቤት ያረፈበት 250 ካሬ ቦታ ይሰጧቸዋል። ያቤት ለልጆቹም ለሁሉም ትልቅ እረፍት ያመጣ ነበር። ነገሩን የተመለከቱ ለጋሾችም ባደረጉት እርዳታ በግቢው የመታጠቢያ ቤትና የምግብ ማብሰያ ለመገንባትም ይበቃሉ። ከቤት ኪራይ መላቀቃቸው ፋታ የሰጣቸው ወይዘሮ አትክልት አርቀው ባሰቡት መሰረት ስራቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉ። ይሄ ደግሞ ሌላ የቤት ፍላጎት ያመጣል። በቅርቡ ደግሞ ቦታው ለልጆች ምቹ እንዲሆንና አሁን ያለው ጠባብ በመሆኑ በድጋሚ 400 ካሬ የቀበሌ ቤት ያረፈበት ቤት እዛው ጎረቤት እንዲሰጣቸው ይደረጋል። ዛሬ በዛ ቦታ ላይ ለልጆች መዋያና መጫወቻ ቦታዎች ማዘጋጀትና የመኖሪያ ቤት ግንባታ ለማከናወን እርዳታ በማሰባሰብ ላይ ይገኛሉ።
“ሳይደግስ አይጣላም” እንዲሉ ከቤተሰባቸውም ለመጣባቸው መገፋትም መፍትሄውን ከልጆቻቸው እንዳገኙት ይናገራሉ። ልጆቻቸው በትምህርታቸው ጎበዝ ፈጣሪን የሚፈሩና ስነ ምግባር የተላበሱ በመሆናቸው ብዙ ሸክም አቅለውላቸዋል። የእናታቸው ጅማሮ የእነሱም ሆኖ ስራው የት ደረሰ ምን ጎደለ በማለት የአቅማቸውን እያበረከቱ ይገኛሉ። ሁለቱ ተምረው ስራ ይዘው የራሳቸውን ህይወት እየመሩ ሲሆን አንዱ በዩኒቨርሲቲ የህክምና ትምህርቱን እየተከታተለ ነው። ሁለቱ ገና በትምህርት ላይ ሲሆኑ ለከፍተኛ ችግር ተጋልጣ አዲስ አበባ ህክምና መከታተል የነበረባት ልጅ የቤተሰቡ አካል ሆና እየኖረች ትገኛለች።
«በአንድ ወቅት አንዲት የእስረኛ ክፍል ተማሪ ልጅ ብቻዋን ወልዳ ለመጸዳጃ ቤት የተዘጋጀ ጉድጓድ ውስጥ ልጁን ትጥለዋለች። የአካባቢው ሰው ጥርጣሬ ስለነበረው ህጻኑን ለጣሊታ አስረክቦ ተጠርጣሪዋን ፍለጋ ሄዶ ያገኛታል። ልጅቷም በወሊድ ወቅት ተጎድታ ስለነበር ተገኝታ ወደህክምና ትወሰዳለች። የልጁ ህይወት ሲያልፍ እሷ ተርፋ ለእስር ትዳረጋለች። እንዲህ አይነት ቅስም ሰባሪ ችግሮች ደግሞ ለሁሉም ጉዞ የሚፈታተን ነበር» የሚሉት ወይዘሮ አትክልት በአካባቢው ነዋሪ ዘንድ ያለውን አመለካከት እንዲህ ያብራሩታል። ተጥለው ለተገኙ ህጻናትም ሆነ ወላጅ አልባ ልጆች የህብረተሰቡም አመለካከት እየተስተካከለ በመምጣቱ ድጋፉም ትብብሩም እየጨመረ መጥቷል። በግለሰብ ከሚደረግ ተሳትፎ ባለፈ የአካባቢው ነዋሪዎችና የእምነት ተቋማትም በአካል በመገኘት የተለያዩ ድጋፎችን እያደረጉልን ይገኛሉ። በተለይም የጣሊታ ቤተሰብን በተመለከተ የይርጋለም አካባቢ ነዋሪ በየአመቱ በሚከበሩ በአላት አብሮን ተሰብስቦ ያከብራል። በአካባቢው ያሉ የተለያዩ የሀይማኖት ተቋማት ክርስትና ልደት ምርቃትና አንዳንድ ፕሮግራሞች ሲኖራቸውም በተቋሙ እየተገኙ ማክበር ጀምረዋል ይላሉ።
የህጻናት ማቆያ ማእከሉም ባለፉት አስር አመታት በተለያየ ቦታና ሁኔታ ተጥለው የተገኙ 61 ህጻናትን ለመቀበል በቅቷል። በአሁኑ ወቅትም ማእከሉ አንድ የአስርና አንድ የአስራ አራት አመት ታዳጊ ልጆችንና አስራ ሶስት ህጻናትን እየተንከባከበ ሲሆን ለአስራ ስምንት ዜጎችም በቋሚነት የስራ እድል መፍጠር ችሏል። በተጨማሪ ባጠቃለይ በፕሮግራሙ በአዲስ አበባና በይርጋለም 460 የሚደርሱ ድጋፍ የሚደረግላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ያሉ ሲሆን፤ ከነዚህም መካከል ማሳደጊያዎች ቆይተው አስራ ስምንት አመት ከሞላቸው በኋላ የሚወጡትን የቡድን ቤት በማዘጋጀት የትምህትት ቤትና የቤት ወጪያቸውን መሸፈን፤ ያረገዙና በተለይ ለማስወረድ የሚሞክሩትንም በመታደግ እንዲወልዱና አዲስ ህይወት እንዲጀምሩም ማስቻል፤ በኤች አይ ቪ ለተጠቁ የስራ ፈጠራ እድል መፍጠር፤ ለጎዳና ህይወት ለተዳረጉ ህጻናትንና ለችግረኛ ቤተሰብ ልጆች ከትምህርተ ቤት መልስ የምገባ ፕሮግራም ማቅረብ፤ እንዲሁም በየአመቱ ቦርሳና የደንብ ልብስ ማቅረብ ዋነኛ ተግባራቸው ነው። ሰላሳ ልጆችን ሊያስተናግድ የሚችል ቤተ መጻህፍትም በማዘጋጀት እንዲገለገሉ እያደረገ የሚገኝ ሲሆን በዚህም እስከ ኮሌጅ ተምረው የተመረቁና በዩኒቨርሲቲና በቴክኒክና ሙያም በመማር ላይ ያሉ እንደሚገኙ ወይዘሮ አትክልት ተናግረዋል።
የይርጋለም ከተማ ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ትእግስት ቆሮሮ በበኩላቸው «ጣሊታ ራይዝ አፕ» በይርጋለምና አካባቢዋ ባሉ ወረዳዎች ለመንግስትም አስቸጋሪ የነበረውን ችግር እያቃለለ ያለ ተቋም ነው ይላሉ። የይርጋለም ሴቶችና ህጻናት ጽህፈት ቤትም «ጣሊታ ራይዝ አፕ» ባይኖር እዚህ ግባ የሚባል ህብረተሰቡን የሚጠቅም ስራ መስራት አይችልም ነበር። ችግሩ ከመንግስትም አቅም በላይ እየሆነ መጥቶ ነበር። ይህን ሁላ ሲሰሩ ደግሞ በምቹ ሁኔታ ውስጥ ሆነው አልነበረም። ዛሬም ከከተማ መስተዳድሩ ጋር በመተባበር የተሰጣቸው ቦታ ቢኖርም እየሰሩ ካሉት ስራ አንጻር ግን በቂ አይደለም። በመሆኑም እኛም በተቻለን አቅም ዞንና ክልል ድረስ በመሄድ ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገር ድጋፋችንን አጠናክረን የምንቀጥል ይሆናል። የጣሊታ ራይዝ አፕ ስራ የህብረተሰቡንም የመደጋገፍ ባህል እያጎለበተ ያለ ነው። በዚህም እኛንም ህብረተሰቡንም ከብዙ ችግር ለመታደግ በቅተዋል። ከገጠር መጥተው በከተማዋ ለተቀመጡና አቅም ለሌላቸው አቅመ ደካሞች በየወሩ ቀለብ የሚሰፍሩ ሲሆን በእነሱ ስር እየተደገፉም ሆነ የስራ እድል ተፈጥሮላቸው እየተዳደሩ ያሉትም በርካቶች ናቸው ይላሉ።
ወይዘሮ ትእግስት ጨምረው እንደተናገሩት «ጣሊታ ራይዝ አፕ» የሚሰራው አበረታች ስራ እንዳለ ሆኖ ችግሩን ከመሰረቱ ለመቅረፍ የሚያስችል ባለመሆኑ እንደመንግስት የተጀመሩትንም ስራዎች እንደሚከተለው ጠቁመዋል። ከትምህርት ቤቱ ጋር በመነጋገር ችግሩ እንዳይፈጠር በልጃገረዶችና በማህበረሰቡ ዘንድ የግንዛቤ ማስጨበጫ የመስጠት እና ተመሳሳይ ድርጊቶች እንዳይከናወኑ ተጥሎ የተገኘን ልጅ የሚያነሳ የቀበሌና ወረዳ አስተዳደር ራሱ ሀላፊነት በመውሰድና በማጣራት ባለጉዳዮቹን ወደ ህግ እንዲያቀርቡ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን አርብ ጥር 22/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ