የኢትዮ-ሳዑዲ የሠራተኛ ልውውጥ ስምምነት የመነሻ ደመወዝ መጠን ወለል 1000 የሣዑዲ ሪያል እንዲሆን መግባባት ተደርሷል።
የኢ.ፌዲሪ የሠራተኛ እና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ከሳዑዲ አረቢያ አቻቸው አሕመድ ቢን ሱለይማን አል-ራጂ ጋር በሪያድ እ.ኤ.አ በ2017 በሁለቱ አገራት መካከል የተፈረመውን የሠራተኛ ልውውጥ ስምምነት ተግባራዊ በሚሆንበት ዙሪያ ላይ ውይይት ያደረጉ ሲሆን፣ በጉዳዩም ላይ መግባባት ላይ ደርሰዋል።
በዚህም ውይይት ወቅት የሠራተኛ መነሻ የደመወዝ ወለል መጠን አንድ ሺህ የሳዑዲ ሪያል እንዲሆንና የሠራተኛውና የአሰሪው መብት በሚጠበቅበት ሁኔታ መግባባት ላይ ተደርሷል።
በሁለቱ አገራት መካከል የተፈረመው የሠራተኛ ስምምነት ውል በሚተገበርበት ሁኔታና ብሎም የሠራተኛ ልውውጥ ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ ከሁለቱ አገራት የተውጣጣ የባለሙያዎች ቡድን በየስድስት ወሩ እየተገናኘ አፈጻጸሙን እንደሚገመግም መግባባት ላይ ተደርሷል።
በመጨረሻም የኢ.ፌዲሪ የሠራተኛ እና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ እና የሳዑዲ አረቢያ ምክትል የሠራተኛና ማህበራዊ ልማት ሚኒስትር ዶ/ር አብዱላህ አቡስነይን መግባባት የተደረሰባቸውን ዐብይ ነጥቦች የያዘ ሰነድ ላይ ፊርማቸውን አስቀምጠዋል።
በሳዑዲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ እንደሚያመለክተው ዝርዝር የሠራተኛ ስምምነት አተገባበር ጉዳይ የሚመለከተውን የሠራተኛ ቅጥር ሞዴል በቀጣይ መግባባት በሚደረሰበት ሁኔታ ላይ ሁለቱ መንግስታት በኤምባሲዎቻቸው በኩል የሰነድ ልውውጥ የሚያደርጉ ይሆናል።