( ክፍል ሁለት )
ኔል እስኮቬል ” ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩና የተዘነጉ በርካታ እውቅ የጋዜጣ ባለቤቶችን አስታውሳለሁ። ፑሊትዘር ግን በበጎ አድራጎቱ /በኢንዶውመንቱ/ ከሞተ በኋላ ዘላለማዊነትን ተቀዳጅቷል። ” ይላል። የበጎ አድራጎት ስራው በሞት ከተለየ በኋላም ስሙን ከመቃብር በላይ እንዳኖረው ለመግለፅ። እዚህ ላይ ኖቤልን ልብ ይሏል። ከዚህ ዓለም ” በሞት ” የተለዩት እነ ትህነግ ፣ ኦህዴድ ፣ ብአዴንና ደኢህዴን በበጎ አድራጎት ድርጅቶቻቸው በእነ ኤፈርት ፣ ጥረት ፣ ቱምሳና ወንዶ እውነት እንደ ፑሊትዘር ስማቸውን ከመቃብር በላይ አኑረዋል !? መልሱን ለአንባብያን ትቼዋለሁ። መዋቅራዊና ተቋማዊ በሆነ ዘረፋ ቢባል ግን ያው ትህነግን/ኤፈርትን አጠገቡ የሚደርስ የለም። የኤፈርት ጉዳይ ባለስንክሳር ስለሆነ አለመነካካት ይሻላል።
የጥረት ኮርፖሬት በሀገሪቱ የፍትሐ ብሔር ሕግ መሰረት ለትርፍ ያልተቋቋመ በጎ አድራጎት ድርጅት ኢንዶውመንት ቢባልም በክልሉም ሆነ በመላ ሀገሪቱ እየተንቀሳቀሰ ያለው ንግድንና በጎ አድራጎትነትን እያጣቀሰ ነው። ይህ ደግሞ የኮርፖሬቱ ዋና ዋና ተግባራት በሚል በግልፅ የተቀመጠ ከመሆኑ ባሻገር ኩባንያዎቹ የተሰማሩባቸው የንግድ ዘርፎች ራሳቸው ጮኸው ይናገራሉ። ጎላ ጎላ ብለው ደምቀው ይታያሉ። ፍፁም የማይነጻጸር ቢሆንም በቀጭኑ ፣ በስሱ ፣ እንደ አቅሚቲ እንደ ዝሆን ዳና ግዙፍ በሆነው የኤፈርትን ዳን ላይ እየተራመደ ነው ማለት ይቻላል።
“… የጥረት ኮርፖሬት ተልዕኮና ዋና ዋና ተግባራት በብቃት ተወዳዳሪና ትርፋማ የሆኑ ኩባንያዎችን በመፍጠር ክልሉንና ሀገሪቱን ትራንስፎርም በሚያደርጉ የልማት ዘርፎች ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት እና ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ ዕድገት እና ብልጽግና ጉልህ ድርሻ ያለው ልማታዊ ተቋም ሶሻል ቢዝነስ መገንባት ነው ። …” ይላል ጥረት። ይህ በምንም መመዘኛ የአንድ በጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ተግባር ሊሆን አይችልም። ከሀገሪቱ ሕግም ሆነ ከዓለማቀፉ አሰራር ጋርም ይጣረሳል ።
በዚሁ ሪፖርት ላይ፤ “… አምባሰል ንግድ ስራዎች ኃ/ የተ/የግ/ማ ፣ ጥቁር አባይ ትራንስፖርት ኃ/የተ/የግ/ማ፣ ገንደውሀ የጥጥ መዳመጫ ኃ/የተ/የግ/ማ ፣ ባህር ዳር ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ አ.ማ ፣ ኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ አ.ማ ፣ ተላጄ ጋርመንት ኃ/የተ/የግ/ማ ጨምሮ 14 ኩባንያዎች እና ከሌሎች ባለሀብቶችና ድርጅቶች ጋር በአክሲዮን የተቋቋሙትን እነ ዳሽን ቢራ ፋብሪካን፣ ዓባይ ባንክ አ/ማን ፣ ዓባይ ኢንሹራንስ አ/ማን ጨምሮ 12ቱ ላይ የአክሲዮን ድርሻ አለው ። ” እነዚህ በጥረት ስር 14 ኩባንያዎች ከሌሎች ግለሰቦችና የንግድ ድርጅቶች ጋር በሽርክና 12 በድምሩ 26 ድርጅቶች በተለይ በጥረት ስር ያሉት ሁሉም ማለት ይቻላል ለትርፍ የተቋቋሙና የሚሰሩ ናቸው ማለት ይቻላል።
በፍትሐ ብሔር ሕጉ ቁጥር ፬፻፹፫ ላይ የበጎ አድራጎት ድርጅት ትርጓሜን ” የበጎ አድራጎት ድርጅት ተግባር ማለት አንድ ሰው አንድ ሀብት ወይም ብዙ ሀብቶች ትርፍ ለማግኘት ሳይሆን በማይመለስ አኳኋንና ለዘላለም አንድ የተወሰነ የጠቅላላ ጥቅም ግብ ላለው የሚያውልበት ስራ ነው። ” ይላል ። እንግዲህ ከላይ የተዘረዘሩ ኩባንያዎች ከሕጋዊ ትርጉሙ ጋር ስናስተያያቸው አፍን ሞልቶ ኢንዶውመንት ናቸው ለማለት ይቸግራል። የተሻሻለው የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማህበራት አዋጅም ስለ በጎ አድራጎት ድርጅት የሰጠው ትርጉም ከዚህ ብዙም የተለየ አይደለም። ዓለማቀፍ አሰራሩም ሆነ ተሞክሮውም ይሄን ጥሬ ሀቅ የሚያረጋግጥ ነው። በዘርፉ የተጻፉ ድርሳናትም በማያሻማ ሁኔታ እንዲህ ይበይኑታል ።” ኢንዶውመንት ለትርፍ ላልተቋቋመ በጎ አድራጎት ድርጅት የሚለገስ የሚሰጥ ገንዘብ ወይም ንብረት ነው ። ሆኖም በብዛት ጥቅም ላይ የሚውለው የተለገሰው ገንዘብ አይነቱ ወይም ንብረቱ ራሱ ሳይሆን የሚያመነጨው ሀብት ነው ። በኢንዶውመንት የተሰጠው ሕንፃ ቢሆን ለተለገሰለት አላማ የሚውለው ኪራዩ እንጂ ሕንፃው ተሽጦ አይደለም። ”
ለዚህ ነው ላለፉት 20ና ከዚያ በላይ ዓመታት ” የኢህአዴግ ኩባንያዎች ” በተለይ የትግራይ መልሶ ማቋቋም ድርጅት ፤ ትእምት/ትካል እግሪ ምትካል ትግራይ ወይም EFFORT / Endowment Fund For the Rehabilitation of Tigray / ላይ የሕጋዊነትና የፍትሐዊነት ጥያቄ ሲነሳ የኖረው።
ይህን ቅሬታ ሕዝብ ፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የግል ጋዜጦችና ሌሎች ሀገር ወዳድና ተቆርቋራ ዜጎች አንስተው ከጣሉት፣ አኝከው ካመነዠኩት በኋላ ነው በኢህአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች ጓዳ ፣ ኮሪደር በሹክሹክታ በሀሜት ደረጃ መነሳት የጀመረው። ከዚያ በፊትማ በአንድም ሆነ በሌላ በኩል ሁሉም በሚባል ደረጃ መሰሪው መለስ የተተለመውን ፤ ” የኤፈርት ኢምፓወርመንት ፕላንና ፍኖተ ካርታ 1985 – 2025 ዓ.ም ” ሲያስፈፅሙ ነበሩ ማለት ይቻላል። በዚህ የመለስ የ40 ዓመት እቅድ 40 በመቶ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የፊጥኝ አስሮ ለኤፈርት ማስረከብ እቅድን በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊት ስም ” ከድርጅቱ/ ከመለስ ” የሚወርድ አቅጣጫን ያለምንም ማንገራገር አስፈፅመዋል። የኢህአዴግ አባልም ሆኑ አጋር ድርጅቶች ተገደውም ሆነ ወደው ለትህነግ / ኤፈርት አይን ያወጣ ዘረፋ ተባባሪ ነበሩ ማለት ይቻላል። ወርቁ ፣ ቡናው ፣ ቅመማቅመሙ፣ ደኑ ፣ ለም አፈሩ ፣ … ፤ ሲጋዝ ኮንትሮባንድ ኬላ ጥሶ በኮንቦይ ታጅቦ መርካቶ ሲራገፍ ፤ ጨረታ ተሰርዞ ለእነሱ ሲሰጥ አይተው እንዳላዩ አልፈዋል። ሆኖም የኤፈርት ጉዳይ ኢኮኖሚ ሙሉ በሙሉ እስከ መቆጣጠር ደርሶ ነበር ። ከለውጡ ወዲህ ግን ጀንበሯ አዘቅዝቃበታለች። ትህነግን እንደ ሕጻን የሚያነጫንጨው ዋናው ምክንያት ይህ መሆኑን ልብ ይሏል ።
ይሁንና ለኤፈርት በአሻሻጭነት/ በመናጆነት ተቋቁመው የነበሩት የብአዴኑ ጥረት ፣ የኦህዴዱ ቱምሳ ኢንዶውመንት የኦሮሞ ልማት እና የደኢህዴን በወንዶ ከጡት አባታቸው ትህነግ / ኤፈርት ጋር ማነጻጸር የሚታሰብ ባይሆን እርስ በእርሳቸውም ሆነ በተናጠል ከየአንዳንዳቸው ጋር ስናነጻጽራቸው ካላቸው ሀብት ፣ የሕዝብ ሀብትና ከመልማት አቅማቸው ጋር ስናመዛዝናቸው የሰሩት ስራዎች እዚህ ግባ የሚባሉ አይደለም። ይህን ድክመታቸውን የማነሳው እንደ ኤፈርት ለምን አልዘረፉም ሳይሆን ሕጉንና ሕጉን ብቻ ተከትለው ያላቸውን ሀብት በአግባቡ ቢጠቀሙ ኖሮ የተሻለ ስራ መስራት ይችሉ ነበር ከሚል ቁጭት የተነሳ ነው። ለነገሩ እንዝረፍ እንኳ ቢሉ ትህነግ ቆርሶ ከሰጣቸው ኩርማን እና ከኤፈርት ትርፍራፊ ውጭ አያገኙም ነበር ።
ጥረት ኮርፖሬትን ለአብነት ብናነሳ ፤ አጠቃላይ ሀብት ከ11 ቢሊዮን ብር የማይበልጥ ሲሆን ለዛውም ከዚህ ውስጥ ወደ 5 ቢሊዮን ብር የሚጠጋው የባንክ እዳ ነው። የፈጠረውን የስራ እድል ስንመለከት በቋሚነትምም ሆነ በጊዜያዊ ከ12ሺህ አይሻገርም። ምን አልባት የኤፈርቱ አልሜዳ ጨርቃጨርቅ ከፈጠረው የስራ እድል ሊያንስ ይችላል። ኤፈርት ግን አባ ስብሀት በተደጋጋሚ በኩራት ደረታቸውን ነፍተው እንደተናገሩት ” በሀገሪቱ ካሉ ኩባንያዎች ትልቁ ነው። የሀገራችን ጥቅል የሀገር ውስጥ ምርት ሁለት ትሪሊዮን ብር መድረሱን በሰማነው መሰረት፤ የኤፈርት ድርሻ ስንት ሊሆን እንደሚችል መገመት ትችላላችሁ። ትህነግ / ኤፈርት የ40 ዓመት እቅዱን በ25 ዓመት ከእቅድ በላይ አሳክቶታል የሚል እምነት ስላለኝ አጠቃላይ ሀብቱ ከ600 ቢሊዮን እስከ አንድ ትሪሊዮን ብር ሊደርስ ይችላል ብዬ እገምታለሁ። የጥረት ፣ የቱምሳና የወንዶ ሀብት አንድ ላይ ቢደመር የባንክ እዳቸውን ጨምሮ ግፋ ቢል ከ 25 እስከ 40 ቢሊዮን ብር እንደማይበልጥ መናገር ይቻላል። ይሄንንም እኔ ቸር ሆኘላቸው ነው። ኤፈርት በኩባንያዎቹ በ100ሺህዎች የሚቀጠር የስራ እድል ከመፍጠር በላይ የክልሉን ኢኮኖሚ በማነቃቃት በኩልም ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን የተለያዩ መረጃዎች ያረጋግጣሉ። ከላይ የጠቀስኋቸው ሶስቱ የኢህአዴግ ” ኢንዶውመንቶች ” የፈጠሩት የስራ እድል ግን ከ20ሺህ አልተሻገርም ማለት ይቻላል። ለምን !?
የየክልላቸውን ማህበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ችግር መቅረፍ ለምን ተሳናቸው ? ለሚለው ጥያቄ፤ ውጫዊና ውስጣዊ ተግዳሮችን ማንሳት ይቻላል። ትህነግ ከኤፈርት በስተቀር እነዚህ ” ኢንዶውመንቶች” ውጤታማና ተገዳዳሪ እንዳይሆኑ ሆን ብሎ በደባና በአሻጥር ሲደፍቃቸው መኖሩ እንደ ውጫዊ ጫና የሚወሰድ ሲሆን ፤ የማይነጥፍ ሀብት ማፈላለግ ፣ የተገኘውን ሀብት ማስተዳደርና ስትራቴጂካዊ አመራር መስጠት ላይ ያሉባቸው ውስንነቶች ደግሞ በውስጣዊ ተግዳሮትነት የሚነሱ ናቸው። በአብነት በጥረት ላይ የሚነሱ ድክመቶችን አጠር አጠር አድርገን እንመልከት ።
በ 2010 ዓ.ም የብአዴን / አዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ የጥረት ኮርፖሬትን ተጠሪነት ከግለሰቦች ወደ ክልሉ ምክር ቤት ለማዛወር የሄደበት እርቀት በጀ የሚባል ቢሆንም ዛሬም ከቀድሞ የጥረት ” ባለቤቶች ” ከእነ በረከት ሰምኦን ፣ ታደሰ ካሳ / ጥንቅሹ / ፣ ሰለሞን ተቀባና ካሳ ተክለብርሀን ጥላ ፣ አዚምና ድንዛዜ አለመላቀቁን የሚያሳብቁ አንኳር አንኳር ነጥቦች እንመልከት። የኮርፓሬቱ አመራሩ የክልሉን ሕዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ ቁጭትም ሆነ እልህ የሚታይበት አለመሆኑ፤ ስትራቴጂካል እይታ ስለሌለው በስሩ ያሉ ኩባንያዎች ለኪሳር እየተዳረጉ መሆናቸው ፤
ከሶስቱ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚዎች አንዷ በዩኒቨርሲቲ መምህርነታቸው ላይ ተደርቦ በትርፍ ሰዓት የሰው ሀብት ዘርፉን የሚመሩ መሆናቸው በጋብቻ፣ በአብሮ አደግነት ፣ በክፍል ጓደኝነት ፣ በድርጅት አባልነት ፣ በዘመድ አዝማድ ፣ … ያለ በቂ የትምህርት ዝግጅትና የስራ ልምድ የተሰገሰገውን የሰው ኃይሉ ማጥራት አለመቻሉ ፤ ጥረት ከብአዴን ተፅዕኖ ነጻ ወጥቻለሁ ቢልም ዛሬም የጉምቱ ካድሬዎች ማገገሚያ መሆኑ ፤ የክልሉ ሕዝብ በከፋ ድህነትና ስር በሰደደ ችጋር እየተጠበሰ ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ወጣት ስራ አጥ ባለበት ፤ ሕጻናት ዛፍ ጥላስር በድንጋይ ላይ ተቀምጠው እየተማሩ ፤ …በቅርበት መፈታት ያለባቸው አያሌ ችግሮች እያሉ የጥረት ኮርፖሬት መቀመጫ አዲስ አበባ መሆኑ ፤ ዋና ስራ አስፈፃሚዎች አንድ አልበቃ ብሏቸው ባለ ሁለት ሶስት መኪና መሆናቸው ፤… ዋና ዋናዎች ናቸው ።
አምስት ኩባንያዎቹ ማለትም ተላጄ ጋርመንት፣ ባህር ዳር ጨርቃጨርቅ ፣ ጣና ሞባይል ፣ ደብረብርሃን ከተማ የሚገኘው አዚላ ኤሌክትሮኒክስና የጁ ማር መሆናቸውን እነዚሁ ምንጮቼ ጠቁመው የጁ ማር በወልዲያ ከተማ የሚገኝ ከ40 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ማቀናበሪያ ሲሆን የ20 ሚሊየን ብር ማር ታቅፎ ኪሳራ የሚያውጅበትን ቀን እየተጠባበቀ ይገኛል።
ጥረት ኮርፖሬት ከ958 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ከባንክ ጋር በተሳሰረ ብድር የኮምቦልቻና የባህር ዳር የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎችን መግዛቱ መልካም ቢሆንም የአዋጭነት ጥናት በአግባቡ ሳያካሂድ መግዛቱና ከገዛ በኋላም ተገቢውን አመራርና የቅርብ ክትትል አለማድረጉ በተለይ የባህር ዳር ጨርቃ ጨርቅ ከ40 እስከ 50 ሚሊየን ብር የሚያወጣ ምርት ባክኖ እንደሚገኝና ለባንክ በየወሩ መክፈል የሚጠበቅበትን እዳ መክፈል ስለተሳነው ከስሮ በባንክ እዳ የመሸጥ አደጋ እንዳንዣበበት ፤ በኮምቦልቻ ከተማ ስራውን የጀመረው ተላጂ ጋርመንት የተባለ ጅንስ አምራች ኩባንያ ደግሞ መርካቶ ላይ አንድ የቻይና ጂንስ ከ 5 መቶ እስከ 6 መቶ እየተሸጠ እሱ ግን በ380 ብር መሸጥ አቅቶት ከስሮ ሊዘጋ ጫፍ ላይ ደርሷል። እነዚህ ምንጮቼ በማከል በመተማ ከተማ ገንደ ውሀ የተቋቋመው የጥጥ ማዳመጫ ለእህት ድርጅቱ ለባህር ዳር ጨርቃ ጨርቅ በዱቤ የፈፀመው ሽያጭ ስላልተከፈለው በፋይናንስ እጥረት ላይ እንደሚገኝ ይፋ አድርገዋል። ሰሞኑን የጥረት ማኔጅመንት ያለምንም ጨረታና ህጋዊ አካሄድ ፤ ለራሱ በሙሰና እና በብልሹ አሰራር ጥሩ ስም የሌለውንና በአንድ ሰው አመራር one man show/rule ስሙ የሚብጠለጠለውን ዋፋ ማርኬቲንግ ጥረትን እንደ አዲስ ለማስተዋወቅ (ለብራንዲንግ) ሚሊዮን ብር ለመክፈል መስማማቱ ልግጫ ሲሆን ጥረት ዛሬም ከእነ በረከት የዞረ ድምር hangover ሙሉ በሙሉ አለመላቀቁን ያመለክታል።
በየዳ ሰስተነብል ኬሚካል ማምረቻ ፣ ባህር ዳር ሞተርስ አሴምብሊ ፣ ላፓልማ ዳይቶማይት ማምረቻ፣ ኢስታንቡል ጋዝ ሲሊንደር ማኑፋክቸሪንግ ፣ ጃሪ የተፈጥሮ ምንጭ ውሀ የአክሲዮን ግዢ ፣ ዲቬንተስ ዊንድ ቴክኖሎጂ ፣ ጂ ኤች. ኢንደስትሪያልና የጥረት ኮርፖሬት 90 ሚሊየን ብር ያወጣበትና መክኖ የቀረው የ ERP/ Enterprise Recourse Planning/ ፕሮጀክት በስትራቴጂካል አመራር ዋግ ከተመቱት ጋር የሚካተቱ ሲሆን አምባሰል ንግድ ስራዎች ድርጅት ፣ገንደ ውሀ ጥጥ መዳመጫና መአድ የምግብ ማቀነባበሪያ ብልሹ አሰራር እንደሚስተዋልባቸው አመራሩ ጥቆማና ማስረጃ ቢደርሰውም በወቅቱ እርምጃ አለመወሰዱን ምንጮቼ ገልጸዋል። በአናቱ ጥረት ለደደቢት እግር ኳስ ክለብና ለመቀሌ ዓለማቀፍ ስታዲየም ግንባታ የገንዘብ ድጋፍ ያደርግ እንደነበር ስትሰማ በዋግ ኽምራ ዞን በስሃላ በዛፍ ጥላስር በድንጋይ ተቀምጠው የሚማሩ ህጻናት እያሰብህ ቆሽትህ ያራል።
እንደ መውጫ
ሆኖም ከላይ በተለይ በኤፈርት ላይ የተነሱ ጥያቄዎች ዛሬ እንደ አዲስ በጥረት ፣ በቱምሳ ኢንዶውመንት የኦሮሞ ልማት ፣ በወንዶ ላይ እንዳይነሱ አበክሮ አሰራርና አደረጃጀት ማስፈን ያስፈልጋል። ሁሉም ኢንዶውመንቶች የየክልሎቻቸውን አንገብጋቢ የልማት ጥያቄዎችን መመለስ ላይ ሊያተኩሩ ይገባል። በጥረት ኮርፖሬት ላይ እንደተመለከትነው የኩባንያን ቁጥር ከማብዛት ይልቅ የየክልላቸውን ተጨባጭ ሁኔታ በመለየት በተመረጡ ፕሮጀክቶች ላይ ማተኮር ያሻል። ያለውን ውስን ሀብት በአግባቡ ስራ ላይ ለማዋል የስራ ማስኬጃ ወጪ መቀነስ ፤ የስትራቴጂካዊ አመራር ባህልን ማጎልበት እና የገቢ ማስገኛ ፕሮጀክቶቹ እርስ በርስ እንዲመጋገቡ ማድረግ ያስፈልጋል። የኤፈርት አይነት ዓይን ያወጣ ዘረፋን ለመከላከል እና የተረኝነት መንፈስን እንዳያጋባ የኢንዶውመንትን አሰራራ የሚመራ እንዲሁ ኢንዶውመንቶች ስልጣን ላይ ካለው ፓርቲ የተለየ ጥቅም እንዳያገኙ ክልከላ የሚያደርግና የሀብታቸውን መጠን የሚወስን ዝርዝር ሕግ ሊረቀቅ ይገባል። በኤፈርትም ሆነ በሌሎች የፓርቲ ኢንዶውመንቶች የተዘረፈ የሀገር ሀብት በጥናት ተለይቶ ለሕዝብ ስለማስመለስ አበክሮ ሊታሰብበት ይገባል ።
ይህ ዓምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ አስተያየታቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሑፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 16/2012
በቁምላቸው አበበ ይማም ( ሞሼ ዳያን )
fenote1971@gmail.com