ግራ ተጋብተናል።ግራ የሚያጋቡን ጉዳዮችና ጉዶች አበዛዝም አስጨንቆናል።እንደ ሀገር፣ እንደ ሕዝብ፣ እንደ ዜጋ ሁሉም በየፊናው አፍ አውጥቶ ጨፍጋጋ ስሜቱን ግለጽ ቢባል ያለ ይሉኝታ የሚዘረግፈው ብዙ ብሶትና ምሬት እንዳለው ሣር ቅጠሉ ሳይቀር አፍ አውጥቶ ምስክርነት ይሰጣል።ከበርካታ አሥርት ዓመታት በፊት በዘመነ የኮሌጅ ተማሪነታችን የማከብራቸው መምህሬ በጻፉት ግጥም መንደርደሩ ለርዕሰ ጉዳያችን ጥሩ መረማመጃ ይሆናል።ይህንን ግጥም ከአሁን ቀደምም በአንዱ ጽሑፌ ውስጥ የጠቀስኩ ይመስለኛል፡፡
ገጣሚው የማከብራቸው መምህሬ ዶ/ር ኃይሉ አርአያ ናቸው።በወቅቱ ግጥሙን ሲጽፉ ምን ስሜት አጥልቶባቸው እንደጻፉ ሰበቡን ለተማሪዎቻቸው አልገለጹም።እንደ ሥነ ጽሑፍ ተማሪዎች ግን የመልዕክቱን ይዘት ለመረዳት እጅግም አላስቸገረንም።የወቅቱን ዝንጉርጉር ሀገራዊ መልክና ፖለቲካዊ ሥርዓቱን በጥቂት ስንኞች መግለጹ ቢከብድም ለእርሳቸው ግን ከነፍሳቸው ውስጥ ተጨምቆ ስለወጣ መልእክታቸውን በጥቂት ቃላት ለማስተላለፍ የከበዳቸው አይመስልም።ሙሉው ግጥማቸው ቢዘነጋኝም ኃይለ ቃላቱ ያረፉባቸው አራት ስንኞች ግን አልተዘነጉኝም።ሀረጋቱ በአግባቡ መሰደራቸውን እርግጠኛ ባልሆንም መልእክቱ ስላልተዛባ የማስታውሳቸውን ያህል ጥቂት ዘለላዎችን ልጥቀስ፤
«እኔስ መስሎኝ ነበር ዘመድ የሞተባት፣
የእናት ሞት የአባት ሞት የልጅ ሞት ያጠቃት፣
ፊቷን ያጠቆራት ጥቁር ያለበሳት፣
ለካ እርስዋስ ኖራለች ዘመን የሞተባት፡፡»
ይህ ስዕላዊ ገለጻ የዛሬውን የወየበ ሀገራዊ መልክ ለመግለጽ ብቃት ያንሰዋል የሚል ግምት የለኝም።በጸሐፊው የግል አስተያየት ዛሬም ቢሆን ብዙ ጉዳዮቻችን ሞተውብን ሀገር ማቅና ከል ከለበሰች በርካታ ወራት ተቆጥረዋል፤ ወይንም ሊሞቱብን እየተንፈራገጡ ስላሉት ጉዳዮቻችን ቀድምን የሟቾቹን ሞት እስካልገታን ድረስ የሀዘን ቱቢት መልበሳችን አይቀሬ ይመስላል።ይህ ገለጻ በቀቢፀ ተስፋ የቀረበ ሟርት አይደለም።ሽብርና መዓት የሚጠራ እዮታም አይደለም።ስጋቱ እውነትም፤ በገሃድ የሚታይ ሀቅም ነው።ዘመኑ መረጃና ማስረጃ እንዲቀርብ የሚያስገድድ ስለሆነ “ከብዙ በጥቂቱ” በማለት ጽሁፋቸውን እንደሚጀምሩት ቀደምት ጦማር አርቃቂ አበው፤ እኔም ለነፍስና ሥጋ ኡኡታ የዳረጉኝን ሀገራዊ እፍረታችንን ቀጥዬ ልጠቃቅስ።የብዕር ኡኡታዬ ለአንባቢያን እንግዳ እንዳልሆነ ይገባኛል።
ቤተ እምነቶች በእብሪተኞች ተቃጥለው ወደሙ የሚል ዜና በብሔራዊ የሚዲያ ተቋሞቻችን ሳይቀር እንደ ወትሯዊ የእድር መርዶ በነጋ በጠባ ማድመጥና ወላፈኑ ሲንቦገቦግ ምስላቸውን መመልከት የጀመርነው በዚሁ በእኛ ጨፍጋጋ ዘመን ይመስለኛል።ወንዛችንን ተሻግሮ የደፈረን ወራሪ ጠላት መሰል የከፉ ድርጊቶችን ፈጽሞ እንደነበር በታሪካችን ውስጥ ተደጋግሞ ተጠቅሷል።የዛሬው ትውልድ፣ በቀዬውና በሠፈሩ አባት እናቱ፣ ወንድም እህቱ፣ አክስት አጎቱ ለጸሎት የሚንበረከኩበትን ወይንም ለሶላት የቀደሱትን ቤተ አምልኮ በእሳት አጋየ፣ ዘረፈ፣ ታቦት ደፈረ፣ የሶላት ምንጣፍ አረከሰ ብሎ ማድመጥ ግን ድርጊቱ ብቻ ሳይሆን መታሰቡ በራሱ ቀድሞ እዬዬ አሰኝቶ ያስነባል።ሀገርን የገጠማት የዘመን ሞት ከዚህ ከፍቶ የሚገለጽበት ሌላ መንገድ ካለ ለመማማሪያነት ስለሚረዳ ቢገለጽልን አይከፋም፡፡
ሌላው ጥቁር ከል ያለበሰን የዘመን ሞት ከከፍተኛ የትምህርት ተቋሞቻችን በየእለቱ እየደረሰን ያለው የልጆቻችን ተገዳደሉ መርዶ ነው።በሀገራችን ታሪክ ይህንን መሰል ክፉ ድርጊት በስፋት ተፈጽሞና አጋጥሞን ስለመሆኑ እርግጠኛ አይደለሁም።ይህ ክስተት እንደ ጸሐፊው እምነት የዘመንን ብቻ ሳይሆን የትውልዱንም በቁም ማሸለብ ገላጭ ይመስለኛል።ይህንን መሰሉ እኩይ ተግባር ፊታችንን እንድንነጭ፣ ደረታችንን እንድንደቃ ብቻ ሳይሆን የሀዘን ቱቢት ለብሰንና ፍራሽ ጎዝጉዘን ጭምር እንድንቀመጥ ያስገደደን ሀገራዊ ክስተት ነው።የተማሪዎች ዶርም ነደደ፣ ቤተ መጻፍት ተቃጠሉ፣ የመማሪያ ክፍሎች ጋዩ ወዘተ. የሚሉት ክፉ ዜናዎች ለትውልዱ ብቻ ሳይሆን ለሟቹ የትምህርት ስርዓታችን መርዶ አስረጋጆች ጭምር መሆናቸውን ብንክድ አያምርብንም፡፡
“እንዴት እንዲህ ይጻፋል!” የሚሉ የፖለቲካ ሹመኞች ፊታቸው ቢጠቁር በትዝብት እናልፋቸው ካልሆነ በስተቀር ማስተባበያ ለመስጠት አይዳዳንም።የናይጄሪያው ቦኮ ሀራም የፈጸመውን “የታዳጊ ሴት ልጆችን የጠለፋ ትራዤዲ” ሰምተን ያማተብንበት አሰቃቂ ድርጊት የሚዘነጋ አይደለም።ዛሬ ይኼው ጥቁር መከራ በእኛ ጠራራ ጀንበር በፖለቲካ እብዶችና ግፈኞች ተፈጽሞ ለማየት ዕጣው ወድቆብናል።ጀንበራችን በለገሰችን እኩለ ቀን ላይ የተጠለፉት ልጆቻችንን መርዶ ከሰማንበት ዕለት ጀምሮ “እንባ በነጠፈበት ዓይን” እዬዬ ብለን በማልቀስ ዓይናችን ሞጭሙጯል።“ልቅሶና ብዙ ዋይታ፤ ራሔል ስለ ልጆቿ አለቀሰች፤ መጽናናትም አልወደደችምና፣ የሉምና” የሚለው የቅዱስ መጽሐፉ መራራ ታሪክ በእኛ “ራሔሎች” (እናቶች) ተደግሞ ማስተዋል እንኳንስ አምባ ደም እንኳ ቢያስነባ ይፈረድብናል።ይህን መሰሉ ክፉ ድርጊት የዘመናችንን ሞት ለማመላከት ከበቂ በላይ ምስክር መሆን ይችላል፡፡
ማብቂያ የሌለው ጉዳያችንና ጉዳችን ለወደፊቱ የታሪክ ጸሐፍት ሥራ አንደሚያበዛባቸው ሳይታለም የተፈታ ነው።አውሮፓዊያን የሚጠቀሙበት አንድ አገላለጽ በእኛ ሀገር በነጋ በጠባ ሲፈጸም ማስተዋል እንግዳ አይደለም።ለብዙ ችግሮቻችን መቆስቆሻ ረመጥ እንደሆነም መገመቱ አይከብድም።እንዲህ ነው የሚሉት፤ “የአውሮፓ ጦርነቶች በሙሉ የተቀጣጠሉት ከጠብመንጃ አፈሙዝ በወጡ የጥይት አረሮች ጅማሬ አይደለም፤ የክፉ ሰዎች አንደበት ባፈለቋቸው ክፉ ተምዘግዛጊ ቃላት እንጂ፡፡” ግሩም አገላለጽ ነው።
በእኛ ሀገርማ ኢሞራላዊ የሆኑ ስድቦችን በየአደባባዮቻችንና በሕዝብ ሚዲያዎች መስማትና መጋትን ጆሯችን ከለመደው ሰነባብቷል።ሀገርና ሕዝብ አስቀድሞ የማያውቃቸው፣ ለሀገራዊ ችግራችንና መከራችን ለቅሶ ደራሽ መስለው ወንዝ ተሻግረው የመጡ “እከሌዎች” እየጋቱን ያለውን የስድብ ዋንጫ መጎንጨቱ ማንገሽገሽ ብቻ ሳይሆን አንገፍግፎናል፡፡
እነዚህ ምላሰ ረጃጅም ስልጣን ናፋቂዎች ሀገርን ሲያዋርዱ፣ ታሪክን ሲያጎድፉ፣ ሃይማኖትን ሲያንኳስሱ፣ ሕዝብን ከፍ ዝቅ አድርገው ሲሳደቡ፣ መሪዎችን በክፉ ቃላት ሲጋረፉ “በሕግ አምላክ እረፉ!” ብሎ አደብ የሚያስገዛልን የሕግ አንቀጽ ለመጥቀስ ቅጹና ቦታው ጠፍቶን ተቸግረናል።መንግሥት በውስጥ መመሪያ አይዟችሁ ብሏቸው ከሆነም ቢገለጽልን ቁርጣችንን አውቀን አርፈን እንቀመጣለን።“የለም እብሪተኞችን የሚዳኝ የሕግ ጉልበት ቀድሞውንስ መች አጥተን” በማለት ፍንጩን የሚያመላክቱን ባለሙያዎች ካሉም ለህሊናቸውና ለሞራላዊ ግዴታቸው ሲሉ “በአቃቤ ሕዝብነታቸው” አደባባይ ወጥተው ሲሟገቱልን ብናያቸው ከምርቃታችን ባሻገር እንባችንም ስለሚታበስ ለእነርሱ ከጽድቅ ያልተናነሰ ወሮታ፤ ለሕዝባቸው ደግሞ መጽናኛ መሆናቸው ጥርጥር ሊገባቸው አይገባም፡፡
ፖለቲካ በክብረ ነክ ቃላት መሰዳደብና አንዱ የአንዱን ስብእና ማዋረድና ማበሻቀጥ ከሆነ፣ የዲሞክራሲ ባህርይም ልቅነትንና አፈ ሰፊነትን የሚያበረታታ ከሆነ አይደለም ለሀገሬ በሩቅ ለሚመኙት ለሌሎች ሕዝቦችም ሳይቀር “እርም ይሁን!” ብዬ አምርሬ እራገማለሁ፡፡
“ፖለቲካ የሕዝብ አስተዳደር ብልሃት ነው”፣ “ዲሞክራሲም የነፃነት መገለጫ ቋንቋ ነው” ብለው እየዋሹ የሚያስዋሹን የዘርፉ ልሂቃን እውነትም የፖለቲካና የዲሞክራሲ መልክና ትሩፋቱ ይህ እያየነው ያለነው መዘላለፍ ከሆነ ሀገሬ ለዘለዓለም “ሀራም!” ብላ እንድትተፋው እስከመጨረሻው በብዕሬ መሟገቴን አልተውም፡፡
ፖለቲከኞች በእኛ በተራ ዜጎች ተከልለውና በትከሻችን ላይ ተንጠላጥለው ወደ ስልጣን ኮርቻ ለመፈናጠጥ ሲዋሹንና ሲሸነግሉን አሜን ብለን የተገዛንላቸው ወደ ቀልባቸው ይመለሱ ይሆናል ብለን ተስፋ በማድረግ እንጂ ዘዴያቸውና ጥበባቸው ጠፍቶን አይደለም።መስማቱ በራሱ የሚያንገሸግሸን፣ ሲደጋገምም የሚያጥወለውለን አንዱ የፖለቲከኞች ፌዝ “ለሕዝብ ስንል” የሚለው ማላገጫቸው ነው።“ለሕዝብ ስንል” ብለው ስልጣንና ወንበራቸውን ከተቆናጠጡ በኋላ ኑራቸውን ከማደላደል፣ ልጆቻቸውን ውጭ ሀገራት ልኮ ከማስተማር፣ በእንባ የራሰ የሕዝብ ሀብት ከማጋበስ፣ በሀገር ቤትና በውጭ ሀገራት መድረኮች ላይ “የተከበሩ!” እየተባሉ ከመንቆለጳጰስ ውጭ ለእኛ ለተራ ዜጎች ምን ፈየዱልን? ለራበው ሆዳችንስ መች ዳቦ ወረወሩልን? ሕዝብ ኮርቻቸው፤ ሀገር መጋለቢያ ሜዳቸው እንዲሆን እየሠሩ ላሉት ባለክፉ አንደበት “ሥራ ቤቶች” ልቦና ቢሰጣቸው ይበጅ ይመስለናል፡፡
ማንም ይሁን ማን ነጋ ጠባ ስለዲሞክራሲ የሚሰብከንና የሚግተን ፖለቲከኛ ሁሉ የልቡ ሰሌዳ ቢገለጥ የሚነበበው ለራሱ የሚቃዠው የግለኝነት ህልም ነው።እርግጥ ነው ያለ መሪ ሀገርና ሕዝብ መኖር አይችሉም፤ መሪነትም አይጠላም፤ መመራትም ላያስደስት ይችላል።የአመራር ጥበብ አስኳል በእነዚህ መሠረታዊ ሃሳቦች ላይ መሽከረከሩ እውነት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በእኛ ሀገራዊ ዐውድ ግን ለሀዘንና ለምሬት የዳረጉን ጉዳዮች ስለበዙብን ራእይ አለን የሚሉ መሪዎች የተሳከሩብንን ሀገራዊ ጉዳዮች መልክ ቢያሲዙ ለእነርሱ በቀዳሚነት፤ ለእኛ ለተራ ዜጎች ደግሞ በተከታይነት ይበጀን ይመስለናል፡፡
ለምሳሌ “ሰላማዊ የትግል ስልት” እየተባለ ለስልጣን የሚደረገው ፉክክር መጨረሻው “የየጁ ደብተራ ቅዳሴው ሲያልቅበት ቀረርቶ ሞላበት!” እንዲሉ ጉዳዩ የሃሳብ ስንዘራና ምክቶሽ መሆኑ ይቀርና ወደ ስድብና ማዋረድ ደረጃ ዝቅ ሲል መመልከት የተላመድነው ባህል ሆኗል፡፡
ፈርተናል።ሰግተናል።የፈራነውና የሰጋነው ከፊት ለፊታችን ቀጠሮ የተያዘለትን ሀገራዊ ምርጫ ስናስብ ነው።የስልጣን ጥመኞቹ ፖለቲከኞች ሃሳባቸውን እንዲስሉ ስንጓጓ፤ ወደ ብረት መሳል እየተንደረደሩ መሆኑን ስናስብና ስንሰማ መቼም ነፍስ አለንና መፍራታችንና መንፈራገጣችን አይቀርም።ዛሬ በስድብና በዘለፋ የተጀመረው ቅስቀሳ ነግ ተነግወዲያ ዱላና ብረት እንደማያማዝዝ ምን ዋስትና አለን፡፡
በርካታ ፖለቲከኞች በሕዝቡ መንፈስ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት ከማወጅ ይልቅ ሽብርና አመጽ እየዘሩ ለክፋት ሲያነሳሱት ማስተዋል ሀገራዊ እንቆቅልሻችንን አወሳስቦብናል።በሕግ አምላክ! በጉልበት አምላክ! ብለን መጮኽ ከጀመርን ሰነባብተናል።ድምጻችን በከንቱ ሰለለ እንጂ እስካሁን ሰሚ አላገኘንም።የችግራችን ግዝፈት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተደራረበ ቢሄድም “አለሁ ባይ ታዳጊ!” ፈጥኖ ሊደርስልን አልቻለም፡፡
የመጭውን ምርጫ ጉዳይ በዛሬው ውሃ ልክና ቱንቢ ስንለካው ብዙ የተንጋደዱ ስሌቶችን አመላክቶናል።አንዳንዱ ዘራፍ እያለ ሻምላ ሲያወዛውዝ እየተስተዋለ ሕግ ጥሰሃል ብሎ የሚያስታግሰው በመጥፋቱ ሻምላውን ወደ ሞርታር ለመለወጥ ቀን ከሌት ይንደፋደፋል።አንዳንዱም ገና ከጅምሩ ሰይፉን በአደባባይ ሲስል እየታየ “ምን እንዳያመጣ ነው!” እየተባለ ሲታለፍ ተመልከተን በትዝብት አንገት ደፍተናል፡፡
የሀገራችን ፖለቲካ የሰከነበትን ዘመን ብንመረምር ልክ እንደ አርታኢሌ እሳተ ጎመራ ለአንድም ወቅት ከመንተክተክ እፎይ ያለበትን ጊዜ ለመጠቆም እንቸገራለን።የዛሬው ደግሞ ብሶበታል።ገና በምርጫ ዋዜማ “ፖለቲከኞች ነን በሚሉ ግራ ገቦች” እንዲህ ነገሮች ከተመሳቀሉ ፊሽካው ተነፍቶ ወድድሩ ሲጀመርማ የሚስተዋሉ የከፉ ክስተቶችን ከማሰብ ማማተቡ ይበጃል።የምርጫ ካርድና የጥፋት ሜንጫ እኩል አደባባይ እንዳይውሉ “የሕግ አስከባሪውን ኃይል” የምንማጠነው ገና ከማለዳው ነው።
የሚዲያዎቻችንን ይዘት በአትኩሮት እንዲከታተል የሕግ መብት የተሰጠው የብሮድካስት ባለሥልጣንም በድምጽና በምስል እያስተዋልናቸውና እያደመጥናቸው ላሉት የስመ ፖለቲከኞች ኢሥነ ምግባራዊ ዲስኩሮችና ፉከራዎች እንዳላየና እንዳልሰማ ዝምታን መምረጡን አልወደድንለትም።“ይህቺ ኩስ ኩስ ለመጋለብ ነው!” እንዳለው የሀገሬ አርሶ አደር ዛሬ በምርጫው ዋዜማ እየሰማናቸውና እያየናቸው ያሉት ምልክቶች አሳስበውናል።“ስድብሽና ስድቤ እኩል ነው፤ ትርፉ ሰው መስማቱ ነው” አለ ይባላል የሚስቱ ምላስ ጤና የነሳው አባወራ።ሰላም ይሁን!!!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 16/2012
(ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ)