የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥር 14 ቀን 2012 ዓ.ም ከተመለከታቸው አጀንዳዎች አንዱና ዋናው በሰው የመነገድ እና ሰውን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የቀረበ ረቂቅ አዋጅ ነበር፡፡ አዋጁ በዕለቱ ጸድቋል፡፡
አዋጁ በሰው የመነገድ፣ ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር እና በህገ-ወጥ መንገድ ለስራ ወደ ውጭ ሀገር መላክ ወንጀሎች በዜጎች አካል፣ ህይወት እና ደህንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ እና ለሰብዓዊ መብት ጥሰት እያጋለጡ በመሆናቸው ምክንያት የተዘጋጀ ነው፡፡
እንዲሁም በሰው የመነገድ በተለይም በሴቶችና ሕጻናት መነገድን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና ወንጀል ፈጻሚዎችን ለመቅጣት እና ሰውን በህገ-ወጥ መንገድ በየብስ፣ በባህርና በአየር ማስወጣትና ማስገባት መከላከል የሚያስችሉ አሰራሮችን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በማውጣቱና ኢትዮጵያም ስምምነቱን ያጸደቀች በመሆኑ ለአዋጁ መዘጋጀት ተጨማሪ ምክንያት ነው፡፡
ከዚህ ባለፈም ወንጀሉን ለመከላከል፣ ወንጀል ፈጻሚዎችን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ፣ የተጎጂዎች ጥበቃና መልሶ ለማቋቋም በተለይም ለወንጀሎቹ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰቡ ክፍሎችን ተደራሽ የሚያደርግና የተጎጂዎችን ዕድሜ፣ ጾታና ልዩ ፍላጎት ያማከል ተግባር መፈጸም እና ዓለም አቀፍ ትብብርን ለማጠናከር የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ ማውጣት እና ስርዓት መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑም ነው ተብሏል፡፡
የጸደቀው አዋጅ ለአፈጻጸም የሚረዱ የተለያዩ አደረጃጀቶችን አቅፏል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ወንጀሉን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በብሔራዊ ደረጃ አስተባባሪ ምክር ቤት (ከዚህ በኋላ “ብሔራዊ ምክር ቤት” እየተባለ የሚጠራ) በአዋጁ መሠረት እንዲቋቋም ፈቅዷል፡፡
ብሔራዊ ምክር ቤቱ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ሆኖ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የሰላም ሚኒስቴር፣ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ፣ የሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር፣ የስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን፣ የጤና ሚኒስቴር፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የብሔራዊ ባንክ፣ የማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ፣ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ፣ ክልሎች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ እና እንደ አግባብነቱ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲካተቱ የሚደረጉ ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላትን ያቀፈ እንደሚሆን በረቂቅ ደረጃ የቀረበው ሰነድ ያስረዳል፡፡
በተጨማሪም የብሔራዊ አስተባባሪ ጥምረት እንዲቋቋም ይፈቅዳል፡፡ በሰው የመነገድ፣ ሰውን በሕገ- ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር እና በህገ ወጥ መንገድ ሰውን ለስራ ወደ ውጭ አገር መላክ ወንጀሎች ተከላካይ ብሔራዊ የትብብር ጥምረት (ከዚህ በኋላ “ብሔራዊ የትብብር ጥምረት” እየተባለ የሚጠራ) በዚህ አዋጅ ተቋቁሟል፡፡ የብሔራዊ የትብብር ጥምረቱ ተጠሪነት ለብሔራዊ ምክር ቤቱ ይሆናል፡፡
ጥምረቱ በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የሚመራ ሆኖ ክልሎችን ሳይጨምር በዚህ አዋጅ አንቀፅ 33 ንዑስ አንቀፅ 3 ላይ የተመለከቱትን አካላት ያካተተ ይሆናል፡፡
የብሔራዊ የትብብር ጥምረቱ የውስጥ አደረጃጃት እና አሰራር ብሔራዊ ምክር ቤቱ በሚያወጣው መመሪያ ይወሰናል፡፡
ክልሎች ይህን ህግ ለማስፈፀም እንደየክልሉ ነባራዊ ሁኔታ አግባብነት ያላቸውን አካላትን ያቀፈ እና በዐቃቤ ህግ ተቋም የሚመራ የክልል የትብብር ጥምረት ማቋቋም አለባቸው፡፡
የብሔራዊ የትብብር ጥምረቱ ተግባርና ኃላፊነት መካከል በሰው የመነገድ፣ ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር እና በህገ ወጥ መንገድ ሰውን ለስራ ወደ ውጭ አገር መላክ ወንጀሎችን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚያስችሉ ጥናቶችን በማጥናት፣ ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎችን፣ ህጎችን በማዘጋጀት ለብሔራዊ ምክር ቤቱ ያቀርባል፤ አግባብ ባለው አካል ሲጸድቅም ተግባራዊነቱን ያስተባብራል፤
ተጎጂዎችን ማዳን፣ መልሶ ማቋቋም፣ ልዩ ልዩ ድጋፍ ስለሚያገኙበት ሁኔታ፣ ከህብረተሰቡ ጋር ሊቀላቀሉ ስለሚችሉበት እና ተያያዥ ጉዳዮችን የተመለከተ አገር አቀፍ የቅብብሎሽ ስርዓት መመሪያ እና የአሰራር ስርዓት ያዘጋጃል፤ በብሔራዊ ምክር ቤቱ ሲጸድቅ ተግባራዊነቱን ይከታተላል፡፡
ስለአገር ውስጥ መፈናቀል፣ ስደትና ፍልሰት፤ የስራ ዕድል ፈጠራና መሰል ጉዳዮችን የተመለከተ የፖሊሲ፣ የህግ ወይም የስትራቴጂ ማዕቀፍ እና የአሰራር ስርዓት እንዲዘጋጅ የሚመለከታቸውን አካላት ያስተባብራል፣ በሚመለከተው አካል ሲጸድቅም አፈጻጸሙን ይከታተላል፤
የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት ተግባራዊ ለማድረግ ዕቅድና የድርጊት መረሐ-ግብር ያዘጋጃል፤ ለብሔራዊ ምክር ቤቱ በማቅረብ ሲጸድቅ ተግባራዊ ያደርጋል፡፡
በዚህ አዋጅ የተሸፈኑ ጉዳዮች ተግባርና ኃላፊነት በተናጠል የተሰጣቸው ተቋማት ተግባርና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ስለመወጣታቸው ይከታተላል፣ አፈጻጸሙን ለብሔራዊ ምክር ቤቱ ያቀርባል፡፡
ለብሔራዊ ምክር ቤቱ በየወቅቱ ሪፖርት ያቀርባል፣ የሚሰጡ ግብረ መልሶችን ተግባራዊ ያደርጋል፡፡
በተጨማሪም አዋጁ በሰው የመነገድ፣ በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር እና በህገ ወጥ መንገድ ሰውን ለስራ ወደ ውጭ አገር መላክ ወንጀል ተጎጂዎችን መልሶ ማቋቋሚያ ፈንድ እንዲቋቋም ደንግጓል፡፡ የፈንዱ የገቢ ምንጭም ከመንግስት ከሚመደብ በጀት፣ በዚህ አዋጅ መሠረት የሚወረሱ ንብረቶችና የሚሰበሰቡ መቀጮዎች፣ ከግለሰቦች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ከሚገኝ ልገሳ እና እርዳታ፣ እና ከሌሎች የገንዘብ ሚኒስቴር ከሚያፀድቃቸው የገንዘብ ምንጮች ከሚገኙ ገቢዎች ይሆናል፡፡
የአዋጁ ጭብጥ ሲዳሰስ
ከአዋጁ ከስያሜው መረዳት እንደምንችለው ሁለት ቁምነገሮችን አዳብሎ ይዟል፡፡ ይኸውም በሰው የመነገድ እና ሰውን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀሎችን፡፡
ማንኛውም ሰው ሌላውን ሰው በባርነት ወይም በባርነት መሰል ተግባር፣ በአገልጋይነት ወይም ዕዳ መያዣነት የያዘው፤ አካሉን በማውጣት ወይም በዝሙት አዳሪነት ወይም መሰል የወሲብ ተግባር ብዝበዛ የፈጸመበት፤ በግዳጅ ሥራ ወይም አገልግሎት፣ በልመና፣ በወንጀል ተግባር፣ በግዳጅ ጋብቻ፣ ወይም በማህጸን ኪራይ ያሰማራ ወይም ህጻናትን በጉልበት ሥራ የበዘበዘ ወይም እነዚህን መሰል የብዝበዛ ተግባራት መፈጸምን ይመለከታል፡፡
በሰው የመነገድ ድርጊትን መሳተፍ ብቻ ሳይሆን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መደገፍ በአዋጁ መሰረት ቅጣትን ያስከትላል፡፡
በወንጀል ሕጉ ስለአባሪነት የተደነገገው እንደተጠበቀው ሆኖ ማንኛውም ሰው በሰው ለመነገድ ዓላማ መጠቀሚያ መሆኑን እያወቀ፡- የራሱንም ሆነ በይዞታው ስር የሚገኝ ቤት፣ ህንጻ ወይም ግቢ ያከራየ ወይም እንዲጠቀሙበት የፈቀደ፤ ወይም የትራንስፖርት አገልግሎት የሰጠ ወይም ተጊጂዎችን ያጓጓዘ እንደሆነ ተጠያቂነት ያስከትልበታል፡፡
ሰውን በሕገ–ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀል በተመለከተ ማንኛውም ሰው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የገንዘብ ወይም ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ ሰውን በሕገ- ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት እንዲገባ፣ ከኢትዮጵያ ግዛት እንዲወጣ፣ በኢትዮጵያ ግዛት እንዲተላለፍ ያደረገ ወይም ሰውን ከኢትዮጵያ ግዛት ለማስወጣት ዝግጅት ያደረገ፣ በሒደት ላይ የተገኘ፣ ያጓጓዘ ወይም የተቀበለ እንደሆነ ይቀጣል፡፡
ማንኛውም ሰው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የገንዘብ ወይም ቁሳዊ ጥቅም ለራሱ ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ ኢትዮጵያዊ ያልሆነ እና በኢትዮጵያ ውስጥ ለመኖር ወይም ለመቆየት የሚያስችል የፀና ፈቃድ የሌለውን ሰው በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ እንዲቆይ ሀሰተኛ ሰነድ በመስራት፣ በማቅረብ ወይም በሌላ ማንኛውም ህገ-ወጥ መንገድ የረዳ እንደሆነ እንዲሁ ተጠያቂነትን ያስከትልበታል፡፡
በህገ–ወጥ መንገድ ሰውን ለሥራ ወደ ውጭ አገር መላክ በተመለከተም ማንኛውም ሰው ወደ ውጭ አገር ሰውን ለሥራ ለመላክ ፈቃድ ሳይኖረው፣ ፈቃዱ ታግዶ ወይም ተሰርዞ እያለ ወይም እንዲልክ ፈቃድ ወዳልተሰጠው አገር ሰውን ለሥራ የላከ እንደሆነ ከሰባት ዓመት እስከ አስራ ሁለት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራትና ከሃያ ሺህ እስከ አንድ መቶ ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል፡፡
ወንጀሉ የተፈጸመው የጉብኝት፣ የህክምና፣ የትምህርት ወይም የመሰል ጉዳዮች ቪዛን ሽፋን በማድረግ እንደሆነ በገንዘብና በእስራት ይቀጣል፡፡
የወንጀል ድርጊት ምክንያት የተላከው ሰው በሰብዓዊ መብቱ፣ በህይወቱ፣ በአካሉ ወይም በስነ-ልቦናው ላይ ጉዳት የደረሰበት እንደሆነ የላከው ሰው ገቢውን ቅጣት ያገኛል፡፡
የውጭ አገር ስራ ስምሪት አገልግሎት ጋር በተያያዘ ስለሚፈጸም ወንጀል በተመለከተ፤ ማንኛውም የውጭ አገር ሥራና ሰራተኛ ማገናኘት ፈቃድ ያለው ሰው የሥራ ስምሪት አገልግሎቱን ምክንያት በማድረግ ከሰራተኛ ገንዘብ ወይም ቁስ የተቀበለ፤ የሠራተኛውን መታወቂያ፣ ፓስፖርት፣ የጉዞ ሰነድ ወይም ሌላ ማንኛውም ሰነድ ሰራተኛው ወደ ሥራ ከመሰማራቱ በፊትም ሆነ በኋላ ያለሰራተኛው ፈቃድ የያዘ ወይም የከለከለ፤ በማታለል ወይም በማንኛውም የማስገደጃ መንገድ ሰራተኛው ባለመብት የሆነበትን ጥቅም እንዲተው ያደረገ፤ ወይም የሰራተኛውን ደሞዝ፣ ንብረት ወይም ሰራተኛው የሚልከውን ገንዘብ በሰራተኛው ፈቃድም ቢሆን እንኳን የያዘ እንደሆነ እንደነገሩ ሁኔታ በእስራት እና በገንዘብ መቀጮ ይቀጣል፡፡
ስለወንጀል መከላከል እና ንብረት መውረስ፣ ፖሊስ በሰው የመነገድ ወይም ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል የተፈጸመ፣ እየተፈፀመ ወይም ሊፈፀም የተቃረበ ለመሆኑ በበቂ ምክንያት የጠረጠረ እንደሆነ፦
ማንኛውንም ማጓጓዣ፣ ቤት፣ ስፍራ ወይም ይዞታ በመፈተሽ ለድርጊቱ የተጋለጡ ወይም በድርጊቱ የተጎዱ ሰውን ለማዳን ይችላል፡፡ በተጨማሪም ድንበር እያቋረጡ ወይም ድንበር ለማቋረጥ በሂደት ላይ ያሉ ሰውን ለማስቆምና ለማጣራት ይችላል፤ ሆኖም የማጣራቱን ተግባር ወዲያውኑ የማከናወን እና ተጎጂ ወይም ተጠርጣሪ ያልሆኑ ሰውን ወዲያው የመልቀቅ ኃላፊነት አለበት፡፡
ፖሊስ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) (ሀ) መሰረት ቤት እና ይዞታን መፈተሽ የሚችለው በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ብቻ ነው፡፡ አስቸኳይ ሁኔታ ሲኖር ፖሊስ ፍተሻውን ያለ ፍርድ ቤት ማድረግ የሚችል ሲሆን በሰባ ሁለት ሰዓት ውስጥ ለፍርድ ቤት ማቅረብ አለበት፡፡ ፍርድ ቤቱም አስቸኳይ ሁኔታ የነበረ መሆኑን ጭምር በመመርመር ተገቢ ነው የሚለውን ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡
ፖሊስ ሥራውን ሲያከናወን ተጎጂዎችን ያገኘ እንደሆነ ተገቢው እንክብካቤና ድጋፍ ወደሚያገኙበት ማዕከል ያደርሳል፡፡
ፖሊስ… የህመም ስቃይ ወይም ጉዳት ውስጥ የሚገኙ ተጎጂዎች ባጋጠሙት ጊዜ በማናቸውም የመንግስት ወይም የግል የህክምና ተቋም እርዳታ እንዲደረግላቸው ትዕዛዝ ለመስጠት ይችላል፡፡
የህክምና አገልግሎት የሰጠ ተቋም ለአገልግሎቱ ወጪ ከፈንዱ የሚከፈለው ይሆናል፤ የአከፋፈሉ ሁኔታ ስርዓት ስለፈንዱ አስተዳደር በሚወጣው ደንብ ይወሰናል፡፡
ከወንጀል ጋር የተገናኘን ንብረት ስለማገድና መያዝ፣
በሌላ ህግ ስለማይታገዱ እና ስለማይወረሱ ንብረቶች የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ ፍርድ ቤት በራሱ ተነሳሽነት፣ በዐቃቤ ህግ ወይም በፖሊስ አመልካችነት በዚህ አዋጅ መሰረት ሊወረስ የሚችል ከወንጀል ጋር የተገናኘ ንብረት ተጠብቆ እንዲቆይ ለማድረግ የሚያስችሉ ሌሎች አግባብነት ያላቸውን ጊዜያዊ እርምጃዎችን ጨምሮ የማገድ ወይም የመያዝ ትእዛዝ ሊሰጥ ይችላል፡፡
ፖሊስ የወንጀል ክሱ ከመመስረቱ በፊት ወይም ዐቃቤ ህግ የወንጀል ክስ ከተመሰረተ በኋላ ከወንጀል ጋር የተገናኘ ንብረት እንዲታገድ ወይም እንዲያዝ በቃለ መሀላ በተደገፈ ማመልከቻ ፍርድ ቤትን ለመጠየቅ ይችላል፡፡
ተከሳሹ በሌለበት የእግድ ወይም የመያዙ ትእዛዝ ከተሰጠ ፖሊስ ወይም ዐቃቤ ህግ ትእዛዙንና ቃለ መሀላውን ለተከሳሹ ወይም በንብረቱ ላይ መብት ወይም ጥቅም አለኝ ለሚል ሰው ያደርሳል፡፡ ተከሳሽን ማግኘት ያልተቻለ እንደሆነ በቋሚ አድራሻው ትዕዛዙን ይለጥፋል፡፡
ማንኛውም ጊዜያዊ እርምጃ፤ ውሳኔውን በሰጠው ፍርድ ቤት በራሱ ተነሳሽነት ወይም በዐቃቤ ሕግ፣ በወንጀሉ ተጠርጣሪ ወይም በንብረቱ ላይ መብት አለኝ በሚል ሰው አመልካችነት በማናቸውም ጊዜ ሊነሳ ይችላል፡፡
… አስቸኳይ ሁኔታ ሲኖር የወንጀል ጉዳዩ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ስልጣን ያለው ዐቃቤ ህግ ተቋም ኃላፊ ለሰባ ሁለት ሰዓት የሚፀና ጊዜያዊ የእግድ ትዕዛዝ ሊሰጥ ይችላል፡፡ ሆኖም ዐቃቤ ህግ ጊዜያዊ እግድ መስጠት ያስፈለገበትን ምክንያት በመግለጽ ሰባ ሁለት ሰዓቱ ከማለፉ በፊት ለፍርድ ቤት ማቅረብ አለበት፤ ፍርድ ቤቱም ተገቢነት ያለውን ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡
ንብረት ስለመውረስ፣ በዚህ አዋጅ የተመለከተ ወንጀል ጉዳይን ለማየት ስልጣን ያለው ፍርድ ቤት፡-
ሀ) በተከሳሽ ላይ የወንጀል የጥፋተኝነት ውሳኔ የሰጠ እንደሆነ፤ ወይም
ለ) የወንጀሉ ፈጻሚ ባለመታወቁ፣ በመሰወሩ፣ በመሞቱ፣ በተለያየ ምክንያት ምርመራ ወይም ክስ በመቋረጡ ወይም በማናቸውም ሌላ ምክንያት የጥፋተኝነት ውሳኔ ባይሰጥም ንብረቱ ከወንጀሉ ጋር የተገናኘ መሆኑን ሲያረጋገጥ፤ ንብረቱ እንዲወረስ እንደሚደረግ በአዋጁ ተደንግጓል፡፡
አሁን በሥራ ላይ ባለው አዋጅ የወጡ መመሪያዎች በሌላ እስኪተኩ በስራ ላይ እንደሚቆዩ በአዋጁ የተመለከተ ሲሆን “ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ቁጥር 909/2007” በዚህ አዋጅ መሻሩ ተመልክቷል፡፡ በተጨማሪም የወንጀል ሕግ አንቀጽ 243 ንዑስ አንቀጽ (2)፣ (3)፣ ከአንቀጽ 596 እስከ አንቀጽ 599 እና ከአንቀጽ 634 እስከ አንቀጽ 638 የተመለከቱ ድንጋጌዎች በዚህ አዋጅ ተሽረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 16/2012
ፍሬው አበበ