የአገር ፍቅር መገለጫው ብዙ ነው፡፡ የአገር ፍቅር ምሳሌ ሲነሳ ግን ቀድሞ የሚጠቀሰው ወታደርነት ነው፡፡ ምክንያቱም የወታደር መስዋዕትነት በገንዘብ ወይም በጉልበት ሳይሆን በሕይወት ነው፡፡ አንድ ወታደር ወደ ጦር ግንባር ሲገባ ሞቶ ጨርሷል፡፡ ሞት ለወታደር እኛ እንደምንፈራው ሳይሆን ለአገር የሚከፈል ዋጋ ነው፡፡ ጠላት ገድዬ እመለሳለሁ ብሎ ብቻ ሳይሆን ከሞትኩም ልሙት ብሎ ነው የሚገባ። የዛሬው እንግዳችን ወታደር ነበሩ፡፡ የገበሬ ልጅ ነበሩ፡፡ የእርሻ ትራክተር ከመጨበጣቸው በፊት ክላሽ ጨብጠው ነበር፡፡ ክላሽ ከመጨበጣቸው በፊት ደግሞ ሞፈር ቀንበር ጨብጠው ነበር፡፡ ገበሬ ወታደር ገበሬ እንበላቸው ይሆን? አሁንም በእርሻ ሥራ ላይ የተሰማሩ ኢንቨስተር ስለሆኑ ገበሬ የሚለው ስም ማዕረጋቸው ቢሆን ደስተኛ ናቸው፡፡ ወደ እንግዳችን ታሪክ ከመግባታችን በፊት ግን ስለአገር ፍቅር የጀመርነውን በእርሳቸው ሀሳብ እንጨርሰው፡፡
እንግዳችን እንደሚሉት፤ ጠንክሮ መሥራት የአገር ፍቅር ነው፣ ከሱስ መላቀቅ የአገር ፍቅር ነው፣ ሰላምን መሻት የአገር ፍቅር ነው፡፡ ከድህነት መላቀቅ የአገር ፍቅር ነው፡፡ ተስፋ መቁረጥ የስንፍና ምልክት ነው፡፡ ስንፍና የአገር መሰናክል ነው፡፡ ከእንግዳችን ጋር በነበረን ቆይታ ያገኘነውን እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
ትውልድና ዕድገት
ታምሩ አጌሎ ይባላሉ። የተወለዱት በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ሸካ ዞን ማሻ ከተማ ነው። ቤተሰቦቻቸው ገበሬዎች ናቸው። እርሳቸውም ማንኛውም የገበሬ ልጅ የሚሰራውን እየሰሩ አደጉ። ከብት ጠብቀዋል፤ እርሻ አርሰዋል። ከ1ኛ እስከ 10ኛ ክፍል እዚያው ሸካ ዞን ተምረዋል። የወጣትነት ዕድሜያቸው ላይ ሲደርሱ ግን ከቤተሰብ ጋር ያለው አብሮነት አልቀጠለም።
ወታደርነት
1978 ዓ.ም ሌላ ታሪክ ተፈጠረ። ‹‹የአገር ፍቅር መለያ ነው›› የሚሉትን ሕይወት ተቀላቀሉ። ወጣቱ ታምሩ ብሔራዊ ውትድርና ዘመቻ ገቡ። በደርግ ዘመነ መንግስት የነበረው ብሄራዊ ውትድርና በግዳጅ ነበርና እርሳቸውም የገቡት በግዳጅ ነው። የወጣትነት ዕድሜያቸውን ያሳለፉት በተለያዩ ወታደራዊ አገልግሎቶች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ነው። ኢህአዴግ እስከገባበት 1983 ዓ.ም ድረስ በወታደርነት አገልግለዋል።
በወታደርነት ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ታምሩ 1983 ዓ.ም ላይ ሌላ ታሪክ ተፈጠረ። ኢህአዴግ መላ አገሪቱን ሲቆጣጠር የደርግ መከላከያ ሠራዊት ተበተነ። የአቶ ታምሩም የወታደርነት ታሪክ በዚያው ተቋጨ።
በሕይወት ላይ ሌላ ሕይወት
የወታደር ሕይወት እንዲህ ነው። ወታደር ሰፈር የለውም፤ ወታደር ብሄር የለውም። ወታደር አገር ብቻ ነው ያለው። አቶ ታምሩ ተወልደው ባደጉበት አካባቢ ሳይሆን በብዙ ኪሎ ሜትር ርቀው ሰሜን ሸዋ ውስጥ ትዳር መሰረቱ። የወታደሩ ትዳር የተመሰረተው የደርግ ዘመነ መንግስት ፍጻሜ አካባቢ ነው። በሰሜን ሸዋ ይፋትና ጥሙጋ በወታደርነት ግዳጅ ላይ እያሉ ከተዋወቋት የትዳር አጋራቸው ጋር ተጋቡ። ባለቤታቸው ደግሞ የትግል አጋራቸው ነበረች፤ ቀጥሎ ደግሞ የኑሮ አጋር። አሁን ደርግ ወድቋል፤ የደርግ መከላከያ ሠራዊትም ተበትኗል። የአቶ ታምሩ ትዳር ግን ጸንቷል። ወደ ማሻም አልተመለሱም። ከደርግ ሠራዊት መበተን አንድ ዓመት በኋላ በ1984 ዓ.ም የመጀመሪያ ልጃቸውን ወለዱ። ወታደሩ አይናቸውን በአይናቸው አዩ። አቶ ታምሩ ከመጀመሪያ የትዳር አጋራቸው ጋር ፀንተው አሁንም አብረው ናቸው። አምስት ልጆችን አፍርተዋል።
ሕይወት ከወታደርነት በኋላ
አሁን ሕይወት አስቸጋሪ ሆነ። የደርግ ሠራዊት ከተበተነ በኋላ ወታደሮች ተፈናቃይ ናቸው። ይህ የሕይወት አስቸጋሪነት ለልጃቸው ስም ምክንያት ሆነ። የመጀመሪያ ልጃቸው ‹‹ይስማ ዓለም›› ትባላለች። በእርሳቸው አገላለጽ ‹‹አንድ ዓለም አቀፍ የመከላከያ ሠራዊት ማፍረስ በዓለም የመጀመሪያው ነው›› ለአገሩ ሲያገለግል የነበረ ሠራዊት ፈርሶ ወታደሮቹ ለጉስቁልና ተዳርገዋል። ይሄን የዓለም ህዝብ ይስማው ሲሉ ብሶታቸውን ገለጹ። መደረግ ያለበት የፖለቲካ ለውጥ እንጂ ወታደርን ማሳደድ አልነበረም ይላሉ።
ወደ ትውልድ ቦታቸው
ከዚህ በኋላ አቶ ታምሩ ወደ ትውልድ መንደራቸው ማሻ ተመልሰዋል። ኑሮ ግን ፈተና ሆነ። ኑሮን እንደምንም እየገፉ በ1987 ዓ.ም ትንሽየ ሻይ ቤት ከፈቱ። ይቺን ሻይ ቤት ሲጀምሩ የባለቤታቸው ሥራ ወዳድነት እንዳስጀመራቸው ያስታውሳሉ። ባለቤታቸው ለሥራ ትልቅ ትጋት አላቸው። አንዳቸው ሻይ ሲያፈሉ አንዳቸው አንባሻ ይጋግራሉ፤ አንዳቸው ውሃ ሲቀዱ አንዳቸው ሊጥ ያቦካሉ። የሴትና የወንድ ሥራ ከሚለው ኋላቀር ልማድ ቀድመው ነው የተላቀቁት። አቶ ታምሩ ‹‹ወታደር መሆኔ ጠንካራ አድርጎኛል›› ይላሉ።
በማሻ ከተማ ውስጥ የመጀመሪያው ሻይ ቤት የአቶ ታምሩ ሆነ። ሦስት በአራት የሆነች ቤት ውስጥ ነው ሻይ ቤቱ የተከፈተው። ይቺ ቤት መኖሪያ ቤትም፤ ንግድ ቤትም ናት። ከዚች ሻይ ቤት የምትገኝ ሳንቲም እንደምንም ተጠራቅማ የተሻለ ቤት መሥራት ቻሉ። አሁን ትንሽ ሱቅ ነገርም ጀምረዋል።
አቶ ታምሩ አሁን ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ አይደለም። አሁን ነጋዴ ሊሆኑ ነው። ከሻይና ዳቦ የጀመረው እንቅስቃሴ አነስተኛ ሱቅ ላይ ደረሰ። ትንሿ ሱቅ ደግሞ ሌላ ምኞት አስከተለች። ሰውየው የሥራ ሰው ናቸውና በያዙት ብቻ አይገደቡም። ሥራ ሳይንቁ ሌሎች ሥራዎችንም ይሰሩ ነበር። የገበሬ ቤተሰብ ናቸውና በዚያች የገጠር ከተማ ውስጥ እህል በመግዛትና በመሸጥም ሱቋን አጠናከሩ። አሁን ሱቋ ብቻዋን አይደለችም፤ በ1996 ዓ.ም አይሱዙ የጭነት መኪና ገዙ። ይህ የጭነት መኪና ደግሞ ብዙ ሥራዎችን ለመሥራት አስቻላቸው። ከዓመታት በኋላም አይሱዙ የጭነት መኪናውን በኤፍ ኤስ አር ቀየሩት። ቀጥሎም በሕዝብ ማመላለሻ መኪና ገዝተው መሥራት ጀመሩ።
ከ2003 ዓ.ም በኋላ አቶ ታምሩ ወደ ኢንቨስትመንት ሥራ ገብተዋል። አሁን ኢንቨስተር ናቸው። ተወልደው ያደጉበት፣ የእናት አባታቸው ኑሮ የተመሰረተበት፣ ገና ከልጅነታቸው እያስተዋሉት ያደጉበት፤ እርሻ ነውና ኢንቨስተሩ በእርሻ ሥራ ላይ ተሰማሩ። 150 ሄክታር የእርሻ መሬት በመውሰድ የኢንቨስትመንት ሥራቸውን ጀመሩ። ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብድር ወስደውም የተረከቡትን የኢንቨስትመንት ቦታ አልምተዋል። የአቶ ታምሩ የእርሻ ኢንቨስትመንት ሥራ ለእርሳቸው ብቻ ሳይሆን ለወጣቶችም የሥራ ዕድል እንዲፈጠር አድርጓል። 27 የሚሆኑ ሰራተኞችን ቀጥረው እያሰሩ ነው። ከተሰማሩባቸው የግብርና ምርቶች በተጨማሪም ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ያቀርባሉ። ወደ ውጭ ለመላክ ደግሞ በሂደት ላይ ናቸው።
የጥንካሬ ምንጭ
‹‹ወታደር ወጥቶ አደር ነው›› ይላሉ አቶ ታምሩ። የአለቃ ደስታ ተክለወልድ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ደግሞ ሀሳባቸውን እውን ያደርገዋል። ወታደር ማለት ወጥቶ አደር፣ ማትቶ (የሚዋትት) አደር፣ በአጠቃላይ ለሌሎች የሚኖር መሆኑን ይገልጻል። ይሄ የውትድርና ባህሪ ለዚህ አብቅቶኛል ይላሉ። የተነሱት ከከፍተኛ ችግር ነው። ኢንቨስተር ለመሆን የሚያስችል አቅም አልነበራቸውም። በሌላ በኩል ምንም አይነት ሱስ የለባቸውም። ችግሮችን የመጋፈጥና ፈተናዎችን የማለፍ ልምድ አላቸው። ድህነት በወታደርነት ካሳለፉት ጊዜ በላይ አልሆነም። የመዋጋት ልምዳቸው ድህነትን ለመዋጋት በቃ። ራስን እቀይራለሁ ብሎ ካመኑበት ለመቀየር ያስችላል። ‹‹አሁንም በወታደርነት ሳይንስ ነው እየሰራሁ ያለሁ›› ይላሉ አቶ ታምሩ። የወታደርነት ባህሪ ከሌብነት እጅግ የራቀ ነው። የወታደርነት ባህሪ ከየትኛውም ማህበረሰብ ጋር ለመኖር ያስችላል። የኔነትና የስግብግብነት ባህሪ የለውም።
የወታደርነት አስተዳደጋቸውን አሁንም ከሀብት ጋር ያገናኙታል። ወታደር የቅንጦት ኑሮ አያውቅም። ጥሪት መቋጠር የሚቻለው ደግሞ እንዲህ ሲሆን ነው። ወታደር ቅንጦት የማያውቀው ሀብት ለማጠራቀም አይደለም፤ ለቅንጦት የሚሆን ጊዜም ሁኔታም ስለሌለው ነው፤ ሀብታም ግን ጥሪት ለማጠራቀም ነው። የሚያመሳስላቸው ነገር ሀብታምም ጊዜ የለውም። ብዙ ብር ስላለው የሚጠጣና በያገኘበት የሚዝናና አይደለም። ለሀብታም ጊዜ እጅግ ውድ ነው።
አቶ ታምሩ ወታደር እያሉ ለሁለት ቀን ያህል ውሃ ሳይጠጡ ቆይተዋል፤ ለዚያም ፀሐይና ብርድ እየተፈራረቀባቸውና በከፍተኛ መሯሯጥ። በወቅቱ በጣም ተስፋ አስቆራጭ ትግል ስለነበር በምሬት ያስታውሱታል። ይሄን ፈተና አልፈዋል። ወደ ትውልድ ቦታቸው ከተመለሱ በኋላም ሌላ ፈታኝ ነገር አጋጠማቸው። ባለቤታቸው ታመሙ። በዚሁ ላይ ተደራቢው ጫና ደግሞ የደርግ ወታደር ናቸው በሚል ከአካባቢው የመንግስት አካላት ማሸማቀቅና መገለል ይደርስባቸዋል።
አሁናዊ ሁኔታና ተግዳሮት
አሁን ላይ የጭነት መኪናም፣ የቤት መኪናም አላቸው። አዲስ አበባ ውስጥ ቤት ሰርተዋል። ማሻ ከተማ ውስጥም ትልቅ ግቢ አላቸው። ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል አላቸው።
የሸካ ዞን በመሰረተ ልማት እጦት የተጎዳ መሆኑ ለኢንቨስተሩም ተግዳሮት ሆኖባቸዋል። የሚያመርቱት የግብርና ምርት ወደ ገበያ መሄድ አልቻለም። የፋብሪካ ውጤቶችን ለመጀመር መብራት የለም። ተጨማሪ የጭነት መኪኖችን ለማስገባት ቢታሰብም ባሉት እንኳን በሚፈለገው ልክ መሥራት አልተቻለም። ዝናብ ሲዘንብ ከፍተኛ ጭቃ ይሆንና ለደህንነት አስጊ ይሆናል። በቅርቡ የጎሬ ማሻ ቴፒ የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት የመሰረት ድንጋይ መቀመጡ ለኢንቨስተሩ ትልቅ ተስፋ ሰጥቷቸዋል። የአካባቢው መለወጥ ለኢንቬስተሩ ብዙ ትርጉም አለውና የማሻን ለውጥ ራሳቸው ለውጥ ያህል ሲናፍቁ ኖረዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 16/2012
ዋለልኝ አየለ