በነገራችን ላይ ቃሉን በማጥበቅና በማላላት የትርጉም ለውጥ መፍጠር ከሚችሉ ቋንቋዎች አንዱ አማርኛ ነውና ፣ በርዕሱ የገለጽኩላችሁን አባባል ትርጉም እንዲሰጥ አንዱን አላልታችሁ ሌላውን አጥብቃችሁ በማንበብ ትርጉም ሰጪና ድርጊት አሻጋሪ ማድረግ ይቻላል። አንዱ ራስን ሲሆን አንደኛው ሌላውን አመልካች ነውና። ስንችል ሌላውን ሲሆን ስንቻል ደግሞ በተዘዋዋሪ በሌላው ተደግፈናል ማለት ነው።
ይህን ካልኩ ወደርዕሰ ጉዳዬ ልግባ። ሰውን እንዴት ነው፤ ኑሮ ብትሉት ይኸው ችለነው እየሄድን ነው ፤ ነው የሚላችሁ። ብዙ ሰው መቻሉን እንጂ እርሱ እንደተቻለ አያውቀውም። ባል ስለሚስቱ ቢጠየቅ በትዳር ውስጥ የሚያጋጥምህን ነገር መቻል አለብህ ብሎ ልምድ ሊያካፍልህ ይቃጣዋል እንጂ፤ እርሱን በብዙ ቻል ስላደረገችው ፣ ባለቤቱ እና ልጆቹ አይናገርም ፤ ካልበራለት።
ብዙዎቻችን እኛ ካለንበት ማዕዘን ጥግ እንጂ ሌላው ከሚያየን አንጻር ራሳችንን አናይም ፤ ስለዚህ ተቸገርኩለት ፤ ተውኩለት፤ አለፍኩት እንጂ አለፈኝ፤ ተወልኝ ፣ ተቸገረልኝ አንልም ፤ ከቶም ።
ቢላዋ ቢላዋን ቢያከው ቢፋጨው፤
ይሰላላል እንጂ አንዱ አንዱን አይቆርጠው። (ያልታወቀ ገጣሚ)
ባልና ሚስት በችግሮቻቸው መካከል ሲያልፉ ኑሯቸውም ይቀናል ፤ ፍቅራቸውም ይጠነክራል እንጂ አይደንዝም። እንዲያውም ክቡር ዶክተር፣ ሐዲስ ዓለማየሁ ፣ “ፍቅር እስከ መቃብር” በሚለው ልብ ወለዳቸው ላይ የበዛብህ እናትና አባት ሲጣሉና ባልየው ሲያኮርፉ አለፍ ብለው ከቤት ወጥተው በኩርፊያ ደጅ ቁጭ ይሉና ወደበረት የሚገባውን ከብት እምቧታ፣ የሚጠራሩትን እረኞች ድምጽና ፉጨት፣ የየሰውን ሰላምታና ወደጎጇቸው የሚበሩ አእዋፍን ጭውጭውታ ሲሰሙ ቆይተው፣ አመሻሽ ላይ ሲያልፍላቸው መሰስ ብለው ወደ ቤት ይገባሉ። ያኔም ከጸባቸው ጋር ሳይሆን ሁሉን ረስተው በናፍቆት ነው፤ የሚገቡት።
ግጭታቸውን የሚስታውሱት በሚስታቸው ዝምታ ብቻ ሊሆን ይችላል እንጂ፣ ካልሆነ ወደ ቀደመው ሃሳባቸው አይመጡም። መቻል ብቻ ሳይሆን መቻልንም ማወቅ ደግ ነው።
በቀደም እለት አንድ አገልጋይ ወዳጄ ያጫወተኝን ታሪክ ላካፍላችሁ። ከዚህ በፊት አለኝ፣ ወዳጄ፤ ቤታቸው መለስ ቀለስ ስል የነበርኩበትና ከሄድኩ ዓመት ያህል ወደሆነኝ የአስር ዓመት ያህል ወዳጆቼ ቤት በሄድኩበት ያጋጠመኝ እውነት አሁንም ያስገርመኛል። ሁለቱ ወጣት ባልና ሚስት በአሁን ወቅት በሰላሳዎቹ እድሜ መጀመሪያ ላይ ያሉ ናቸው። ቤት እንደገባሁም ተቀመጥ ብለው ወጥረው ያዙኝና ተቀመጥኩ። ሥራ በዝቶብኝ በየጊዜው ልጠይቃቸው ባለመቻሌ ይቅርታ ጠይቄ ነው፤ ወንበር የያዝኩት።
ትንሽ ቆይታ ሚስት ወደ ጓዳ ገብታ እያለች፤ እንግዳውን አጫውተው፣ ስትለው ባዶ አፉንማ አናደርቀውም ፤ ምን ይምጣልህ አለኝ ። “ምንም አልፈልግም አይናችሁን ማየት ፈልጌና ሰላምታ ላቀርብ ነው፤ የመጣሁት” ብዬ ሳልጨርስ፣ ሚስት ከጓዳ እየወጣች ፣ “አልፈልግም ካለ ተወው”፤ አለችና። ከመጣህ አይቀር አንድ ነገር ልጠይቅህ ።
ጠይቂኝ አልኳት።
ባለፈው ዓመት መጽሐፍ ቅዱስ ይዘህ ስናወጋ የነበረውን ወግ ታስታውሳለህ?
አዎ፤ በደንብ አስታውሳለሁ።
እና ለምሳሌ እንዲረዳህ የአንገቴን ሐብል አንዴ ስጭኝ ብለህ ያልከኝንና ስለመያያዝ ምሳሌ የሰጠኸውንም መቼም አትረሳውም።
በትክክል! እንዴት ትምህርቱን አልዘነጋሽውም ?
እንዴት እዘነጋዋለሁ፤ ያንን ካስረዳኸን በኋላ የመያያዝን ጥቅም ከዚያም፣ ወርቅንና የሰው ባህሪንም በማመሳሰል ከዝገትና ብልሽት ለመጠበቅ መኮላትና መጋጨት ያለ መሆኑን ለግንኙነት ማጥራትም ጠቃሚነቱን አውርተኸን ነበረ። በረዥሙ ተነፈሰችና…እ… ስትል አቋረጥኳትና “በሚገባ፤ ወርቅ በእሳት ሰውም በነገር እየተፈተነ ጥራቱ ከፍ እያለ ከሚናገረው በሚያደርገው፤ ከሚያወራው በሚኖረው ራሱን ይገልጣል፤ ነገር አያያዝሽ ግን ገራሚ ነው” አልኳት፤ ከልቤ በመደነቅ።
ወደጉዳዩ ልግባና አለች…ትንፋሹዋን ዋጥ አድርጋ፣ የዛን እለት ለምሳሌ የተጠቀምክበትን የአንገቴን ሐብል፣ ለምን ይዘኸው ሄድክ ፤ አለችኝ፤ ትክ ብላ እያየችኝ። ለጊዜው ድንግር አለኝና የምን ሐብል ብያት መለስ አልኩና፣ አስታወስኩ።
ባልየውም፣ በመሐል ተሳቅቆ ይመስለኛል፤ ጥሎትና ዘንግቶት፣ ጠፍቶበትም ይሆናል፤ አሁን ከዓመት በኋላ ስለተረሳ ነገር ማንሳት ምን ይረባል….ተይው በቃ፤ ሲል እንዳቀረቀርኩ ቆየሁና …”.የዚያን ቀን ያጠናንበት መጽሐፍ ቅዱስ የታል?” አልኳት ።
የት ነበረ ሳትልም፣ መደርደሪያው ላይ ነው፤ ያለው ፤ አለችና ፤ ከፊል ሣቅና ፌዝ በተሞላው ድምፀት ከንፈሮቿን ሸርመም አድርጋ አየችኝ።
ሰውየው ሄድ ብሎ አመጣውና “ለምን ፈለግኸው?” አለኝ።
ወዲህ ስጠኝ አልኩትና መጽሐፈ-ምሳሌ 27(28)ን አወጣሁና ገለጽኩት።
ወደ እርሷም መጽሐፉን እየዘረጋሁ፣ ወርቁ ያለው መጽሐፉ ውስጥ ነው፤ አልኳት ።
“ምን ? “ አለች በከባድ ድንጋጤ። መጽሐፉንም መቀበልም መንካትም አቃታት፤ አንዴ ወደመጽሐፉ አንዴ ወደ እኔ እያየች።
መጽሐፉ ውስጥ አለልሽ፤ …. እይው። የገረመኝ አንድ ዓመት ሙሉ የጸሎት መጽሐፋችሁን አለመግለጣችሁ ነው፤ ብያቸው ልወጣ ስል ሰውየው ጎንበስ ብሎ ጉልበቴ ላይ ተጠመጠመ።
ወደ በሩ እየወጣሁ ሳለ፣ እርሷ ግን አፈፍ ብላ ወደጓዳዋ እየገባች….. ዓመት ሙሉ አብጠልጥዬው፤ ለአምላክ አሳቅዬውና ስንት ጊዜ ልቻለው ብዬ ስል ኖሬ….” ለካ የተሸከመኝና የቻለኝ እርሱ ኖሯል ፤ ምድር ተከፍታ በዋጠችኝ ፤ እንዲህ ቀልዬም አላውቅ፤ ስትል ሰማኋት፤ ሲል አጫወተኝ።
ብዙዎቻችን እንዲህ ነን። የቻልን እንጂ የተቻልን፣ የታገስን እንጂ የታገሱን መሆናቸውን አናውቅም። እኛ፣ የተሸከምን እንጂ የተሸከሙን፤ ያዘልን እንጂ የታዘልን መሆናችንን አናስብም ወይም ማሰብ አንፈልግም። ራሳችንንም አንፈትሽም። ስለማንፈትሽም የችግራችንን ምንጭ ደጅ ለደጅ እንፈልገዋለን።
በእኛ ሐገር፣ ሰው ለውሻው ስም ሲሰጥ እንኳን “ሰምቶ-መቻል” ና “ብጥር ቀኑ” ማለት ይቀናዋል። አሁን፣ አሁን ግን ይኼ ስም ቀርቶ ኪኪ፣ ዚዚ፣ ቦቢ፣ ቶም፣ (ከቶም ኤንድ ጄሪ ሳይወስዱ አልቀረም) ወዘተ … ማለት ነው የሚቀናቸው እንጂ፤ እነ ሰምቶ መቻል ከከተማው አካባቢ ከራቁ ቆይተዋል። በነገራችን ላይ በመጥፋት ላይ ካሉ ስያሜዎቻችን መካከል እነዚህም ስሞች ቢመዘገቡልን መልካም ነው ። እነ አበበች ፣ ደመቀች፣ አይተንፍሱ፣ እንዳሻው ፣ አስናቀች ፣ ጌታቸው ወዘተ… የሚባሉ ስሞች እየጠፉ ነው። ድሮ እኮ አንድ ከረንቡላ መጫወቻ ስፍራ ሄደህ “ግርማ” ብለህ ብትጣራ በትንሹ ሶስት ሰው ዞር ብሎ “እኔን ነው?” ሊልህ ይችል ነበረ። አሁን ግን በፍለጋ የሚገኙ ስሞች ወደመሆን ደረጃ እየደረሱ ነው። ባለሁለት ፊደሎቹ የቁልምጫ ስሞች እነ ሳሚ፣ ዳኒ፣ ዊኒ፣ ፖል፣ ቢኒ፣ ናቲ፣ ኬሊ (ትንሽ ፈገግ ቢያደርጋችሁ “ኬሊ” የሚለው ቁልምጫ አማከለ የሚለውን ነባር ስም፣ ለማዘመን የተሰጠ ማባበያ ነው) የሥም ገበያውን ተቆጣጥረውታል። (በዚህ ጉዳይ ላይ በሌላ ጊዜ ልመለስበት) እናም እነ ሰምቶ መቻል ለውሻ የሚወጡት ፣ ህብረተሰቡን “ችየሃለሁ እወቅ፤ ታግሼሃለሁ ተጠንቀቅ፤” ለማለት እንጂ ሌላ መልእክት ኖሮት አይደለም።
ድሮ ፌስ ቡክ የለ፤ የሚተነፈስበት ትዊተር የለ የመጣ ሃሳብ ወዲያው የሚለጠፍበት፣ ስለዚህም የዘመኑ ሰዎች ፣ በውሻቸው፣ በድመታቸው፣ በሙክታቸውና በፈረሳቸው ነው፤ በሽሙጥ ወይም በኩራት፤ ሃሳባቸውን የሚገልጹት ።
ብዙዎቻችን ወደልባችን ፣ የሚመጣው ነገር፣ ችለነዋል ችለናታል፤ ታግሰነዋል ታግሻታለሁ ማለት ነው። ተቻልን እንጂ ፣ ታገሱን እንጂ፤ አልታገስናቸውም ፤ ብሎ የሚነግረን ያስፈልገናል።
በቀበሌም ሆነ በንዑስ ቀበሌና መንደር፣ በቢሮና መምሪያ ስር በክልልም ሆነ በሐገር ደረጃ ምንም ዓይነት የሃላፊነት ደረጃ ሲሰጠን፣ ቦታው ከሰጠን ሸክም አንጻር የምንወስዳቸው ሃላፊነቶች ይኖራሉ። በዚያው ልክ ደግሞ የምንስታቸው ፣ የምናሳዝነው የምናስከፋውና አለፍም ሲል የምንጎዳው ሰው እንዳለ ማሰብ ይገባናል።
በሃላፊነት ስፍራ ትልቁ ስህተት ሁሉን ላስደስት ባይነት ነው፤ ማንም ሃላፊ በሚወስደው እርምጃ የሚያስከብረው ህግና ሥርዓት ያለውን ያህል ለህጉ መከበር በወሰደው እርምጃ የቅርቤ የሚላቸው ሰዎች እንኳን ሊያኮርፉትና ሊያዝኑበት እንደሚችሉ ማሰብ አለበት። በዚህም ሳቢያ ለሥራው ሲል ወዳጁን ፣ ለሥርዓት ሲል ዘመዱን ሊያጣ ይችላል። ዘመዴ እንዳይቆጣና እንዳያዝን እፈልጋለሁ፤ ካለ ከሃላፊነቱ ቦታ ራሱን በማንሳት ሌሎች ስርዓት እንዲያስከብሩ ቦታ መልቀቅ አለበት። አለበለዚያ ሥራውም ተቋሙም ይጎዳል።
ይኼኔ ነው፤ ሰው በአዎንታዊ መልክ መቻሉን በማሳየት መጓዝ መቻሉን ማሳየት ያለበት። መልካም የሚሰራን ሰው ይፍጠንም ይዘግይ ጎዳን የሚሉት ሰዎች እንኳን በጊዜ ርዝመት ውስጥ የወሰደውን እርምጃ ቀናነትና ትክክለኛነቱን ይመሰክሩለታል። እርምጃ ሲወስድ የቻለበትን ያህል የቅርቦቹን ሰዎች በመጉዳትም ቻል ማድረጉን አሳይቷል። ከዚህ ውጭም ሲሳሳት ሌሎች ፣ እርሱን እንደሚችሉት አስቦ መንቀሳቀስ አስተዋይነት ነው።
በአንድ ወቅት የነበሩ ያገራችን ንጉስ የነበሩት ሰው፤ ባቡር ወደ ሐገሪቱ እንዲገባ የተቀየሰው መንገድ ከደወሌ ተነስቶ እስከ ድሬዳዋ ፣ ከድሬ እስከ አዲስ አበባ በሚያቋርጥበት መንገድ ላይ ያሉ ሰዎች “መሬቴን ቆረጠ፤ እርሻዬን ነካብኝ” ሲሉ አቤቱታ ለአካባቢው ገዢዎች ማቅረባቸውን ሰሙ። የአካባቢው ገዢዎች ታዲያ ፣ ባላገሩን፣ እንዳትነኩብኝ ይልቅ በስራው የሚሰማራው ራሱ መሆኑን እና ከወደብ ወዳገር ከሀገር ወደወደብ እቃ ማመላለሻ ሰው መውሰጃና መመለሻ መሆኑን ንገሩትና አግባቡት ፤ ሲሉ ይመልሳሉ።
ገዢዎቹም ፣ አካባቢው ፊደል የለየ የለበትም ፤ “ጨዋ”(ማይም) እና ክፉ ነው፤ የሞላው ፈረንጆቹም አፋቸውን የሚችል ሰው ይፈልጋሉ እኮ፤ ሲሏቸው፤ አንተን ከፈረንጅ ( ከፍሬንች ማለት ነው) ያግባባውን ሰው እየለየህ አግባባቸው፤ ነበረ ፤ መልሳቸው።
በአካባቢው የነበሩ ገዢዎች “አይቻልምና አይሆንም”፤ ለማለት የሚሰጧቸውን መልሶች እንዴት እንደሚቻል ለማሳየት የጊዜው ንጉስ አልሰነፉም ። አዎ፣ ዘመናዊነቱና ትምህርቱ በጊዜው ላይኖር ይችላል ፤ ዘመናዊ ለመሆን ግን ሰው መሆን በቂ ነው። ሰው በባህሪው ካየው የሚማር ከሰማው የሚያገናዝብ ፍጡር ነውና ፤ ስለዚህ እናንተ የቻላችሁትን ሌላው ሊችል እንደሚችል መገንዘብ መቻልንና መቻልን ማወቅ ተገቢ ነው።
በሌላ በኩል አልችልም ለማለት ልባቸውን ያቀኑ፣ አላውቅም ለማለት ማልደው የሚተጉ ሰዎች ክፍቱ የተዘጋባቸው ናቸው። ዕውቀትን ለመቀበል፣ አሰራርን ለመልመድ የሚተጋ ልብ ያለው “እስቲ አየዋለሁ፤ እሞክረዋለሁ፤ እነሳለሁ፤ ይላል እንጂ አይቻልም ፤ አይደረግም ፤ አልወጣውም ፤ “ኧረ እኔ-ቴ” ማለት ካበዛ እንደማይችል ሁሉ ሌላውም እርሱን አይችለውም። ከውስጥ በራሱ ላይ በር ቀርቅሮ ለሚያንኳኳ ሰው ማን ይከፈትለታል? ማንም። አሉታዊ ሁነቶችን የሚያራግቡ ሰዎች ስልጣኔ የሚገባበትን በር በብረት መሸጎሪያ ቸንክረው እንደ ቀደመው ጊዜ ልማዳችንንና ባህላችንን አንለቅም ብለው በጨለማ እንደሚዳክሩ ምስኪን ፍጥረታት ናቸው።
ስለዚህ ስለመቻል ልባችን ይቅና ፤ ለመቻልም እኛም ዝግጁ እንሁን ፤ በዚህም ለሌላው ፈተና የማንሆነውን ያክል ሌሎችም በትእግስት አይፈትኑንም ፤ ይለዝቡልናል። ያኔም ነገር ሁሉ ሰላም ይሆናል። ደካማውን በአንደበታችን ጭምር በቃል እንዴት መደገፍ እንዳለብንም ካወቅን፣ ህይወታችን በንቃት የሚመላለስ ይሆናል። ሌሎችን ለመቻል ትከሻችንን እንደ አልማዝ ማእድን ማጠንከር ይገባናል። አልማዝን አልማዝ እንጂ ሌላ ማእድን ችሎ አይቆርጠውምና በተሳለ ትእግስት በመቆም ለተሣለ ህይወት ራሳችንንም ሃገራችንንም እናዘጋጅ። ሌሎች እንደቻሉት፣ እንደታገሱትና እንደተሸከሙት የገባው ሰው ሌላውን ለመቻልና ለመቻቻል አይሰንፍምና።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 16/2012
ከአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ