– ለካቢኔ አባላትና ለቦርድ አመራሮችም ሹመት ሰጥቷል
አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ባካሄደው 7ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባዔው የተማሪዎች ምገባ ኤጀንሲን ለማቋቋም የወጣውን ረቂቅ አዋጅ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል ። ምክር ቤቱ ለካቢኔ አባላትና ለቦርድ አመራሮችም ሹመት ሰጥቷል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ አበበች ነጋሽ ትናንት በፌዴሬሽን ምክር ቤት የተደረገውን ስብሰባ አስመልክተው ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የከተማ አስተዳደሩ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ መሆናቸውን ጠቅሰው የተማሪዎች ምገባ መርሐ ግብርም በተቋም ደረጃ እንዲመራ ማድረጉ ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል።
የምክር ቤቱ አባልና የሴቶችና ህጻናት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሒሩት አጽብአ የውሳኔ አሳቡን ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት አዋጁን ማጽደቅ ያስፈለገው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለቤትነት የሚተዳደሩ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የተጀመረውን የተማሪዎች የምገባና የትምህርት መርጃ መሣሪያዎች አቅርቦት ሥርዓት ተቋማዊ በሆነ መልኩ ለመምራት በማስፈለጉ ነው። የተማሪዎችን የትምህርት አቀባበል፣ የምግብ እጥረትና የጤና ችግር ለመቅረፍ ያግዛል። ተሳትፏቸውን ለማሳደግና በችግር ምክንያት ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ያስችላል።
ከምክር ቤቱ አባላት በተሰጡ እስተያቶችም የተማሪዎች ምገባ ኤጀንሲ አዋጅ መጽደቁ የመማር ማስተማሩን ሂደት ለማገዝ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትና ለትምህርት የሚሰጠውን ክብር እንደሚያሳድግ ተገልጧል።የተማሪዎችን የአመጋገብ ልዩነት መፍታት የሚደርስባቸውን የስነልቦና ጫና ለመቅረፍም የሚያስችል ነው ተብሏል። በዚህም መሰረት ተጠሪነቱ ለከንቲባው የሆነ አንድ ቦርድ እንዲቋቋምና የምገባ ሥርዓቱን በባለቤትነት እንዲመራ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ በሙሉ ድምጽ ጸድቋል።
በሌላ በኩል ምክር ቤቱ የአሥራ ዘጠኝ የቢሮ ኃላፊዎችና የሃያ አንድ የቦርድ አባላት ሹመትንም አጽድቋል። የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ሹመቱ የተሰጠበትን ምክንያት ሲያስረዱም የከተማውን ህዝብ በቅንነትና በኃላፊነት ለማገልገል የተገባውን ቃል ለመፈጸም እንደሆነ ጠቅሰዋል። የአንድ ዓመት ከስድስት ወር ጉዞም በአንድ በኩል በስኬት የታጀበ በሌላ በኩልም በፈተናዎች ውስጥ ያለፈ እንደነበር አስታውሰዋል። እንደከንቲባው ገለጻ እስከ አሁን በነበረው ሂደት ከከተማዋ ነዋሪዎች አበረታች ሀሳቦች ተሰጥተዋል። ይህንንም አጠናክሮ ለማስቀጠልና ክፍተቶችን ለመድፈን የሥራ ልምድና የትምህርት ዝግጅትን መሰረት ያደረገ ሹመት ለመስጠት አስገድዷል ብለዋል።
በሹመት አሰጣጡ ላይ አስተያየት የሠጡ የምክርቤት አባላት ከስድስት ወር በፊት በሥራ አፈጻጸማቸው የተመሰከረላቸው የቢሮ ኃላፊዎች ያለምክንያት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገቢ እንዳልሆነና ህጋዊ መሰረት የሌለው አካሄድ እንደሆነ ቅሬታቸውን አሰምተዋል። በተሰጠው ምላሽም ከቦታቸው የተነሱ ባለስልጣኖች አንዳንዶቹ ለተሻለ ሥራ የታጩ እንደሆኑና አንዳንዶቹ ያሳዩት አፈጻጸም ዝቅተኛ በመሆኑ እንደሆነ ተገልጿል። በዚህም ምክንያት የካቢኔ ሹመቱ በ79 ድጋፍ፣ በሦስት ተቃውሞና በ7 ድምጸ ተሀቅቦ ጸድቋል።
የተማሪዎች ምገባ ኤጀንሲን በተቋም ደረጃ ለመምራት እንዲያስችልም በበጎ አድራጎት ሥራና በተመሳሳይ ዘርፍ ከትምህርት ሥራው ጋር ቀረቤታ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች በቦርድ አባልነት ተመርጠዋል። ኮሚቴዎቹ ከሃማኖት ተቋማት፣ ከአርቲስቶች፣ ከጋዜጠኞች፣ ከዩኒቨርሲቲ ምሁራንና ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተመረጡ ናቸው።
መደበኛ ስብሰባው የተለያዩ አጀንዳዎችን የያዘ ሲሆን አምስት ሪፖርቶች የሚቀርቡበትና ሦስት አዋጆችም የሚጸድቁበት እንደሆነ ታውቋል።ስብሰባው ዛሬም ይቀጥላል።
አዲስ ዘመን ጥር 16 ቀን 2012
እያሱ መሰለ