የገጠር ኑሮ አስቸጋሪ ነው በተለይ ለሴት ልጅ ብዙ መሰናክሎች ያሉበት የፈተና ቦታ ነው ቢባል ከእውነት የራቀ አይሆንም። በዛ ላይ የዓይን ብርሃንን ማጣት ደግሞ ህይወትን ምን ያህል እንደሚያመሰቃቅለው ለሁሉም ግልጽ ነው። አንዳንዶች ግን ለማድረግ ሳይሆን ለማሰብ የሚከብደውን ጉዞ በመጋፈጥ ውጤታማ ለመሆን ሲበቁ ይታያል። አካል ጉዳተኝነት ሳያግዳቸው ተምረው፣ አግብተውና ወልደው ለወግ ለማዕረግ የበቁ በርካታ ናቸው። ወይዘሮ ቤተልሄምም ገና በማለዳው ቦርቃ ሳትጠግብ የገጠማት ፈተና እንደተራራ የማይገፋ ቢመስልም በነበራት ጽናት በልጅነት ጊዜዋ፤ በለጋ አእምሮዋ ያስቀመጠችውን ህልም ከማሳካት አላገዳትም። የዓይን ብርሃኗን ብታጣም ከተወለደችበት አንዲት ትንሽ የገጠር መንደር አፈትልካ ወጥታ ዛሬ የሞቀ ትዳርና ስኬታማ ቤተሰብ ለመመስረት በቅታለች።
መምህርት ቤተልሄም ገመቹ ትባላለች። ተወልዳ ያደገችው በወለጋ ክፍለ ሀገር ስሬ ሲቡ በምትባል አነስተኛ የገጠር መንደር ነው። ለአቶ ገመቹ ቀነአ እና ለወይዘሮ ደስታ ደሬሳ የመጨረሻ ልጅ ናት። ቤተልሄም እንደማንኛዋም ህጻን ጣፋጭ የልጅነት ዘመኗንም እያጣጣመች አድጋለች። ነገር ግን ሰባት ዓመት ሲሆናት በውሃ ነጸብራቅ የተነሳ አይኗን ያማታል። ከዛሬ ነገ ይድናል ሲባል የነበረው ህመም ስር እየሰደደ ይመጣና አይኗ ላይ ሞራ እየጣለባት እይታዋን ይጋርዳት ይጀምራል።
ወላጆቿም እንደማንኛውም ሰው በአካባቢው የሚደረገውን የባህል ህክምና ይሞክራሉ ከዚህም መካከል ሞራውን በቅጠል ለማንሳት የተደረገው ባህላዊ ህክምና ደግሞ ነገሩን ያባብሰዋል። እናም እየዋለ ሲያድር ተደርጎላት ከነበረው የባህል ህክምና ሙከራ ጋር ተደምሮ በወቅቱ ዘመናዊ ህክምና ባለማግኘቷ ነገሩ ይባባስና አይኗ የማየቱ ነገር ተስፋ እያጣ ይመጣል። ወላጆቿም ከረፈደም ቢሆን ከተጀመረው ባህላዊ ህክምና ፊታቸውን ወደ ዘመናዊ ህክምና ያዞራሉ። ነገሩ ግን ስር ሰዶ ስለነበር የዓይን ብርሃኗን ለማስተካከል አልተቻለም። እናም ቤተልሄም ከዓለም ጋር በዓይኗ ስታደርግ የነበረውን ግንኙነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማቋረጥ ትገደዳለች።
በአካባቢው ማንኛውም አካል ጉዳተኝነት እንደ እርግማን ነበር የሚታየው። ስለዚህም የአካባቢው ነዋሪ ቤተሰቦቿ አንዳች ሀጢያት ሰርተው በእርግማን እሷ ለዚህ እንደበቃች ተደርጎ ነበር የሚታመነው። ቤተሰቦቿ ግን ምንም እንኳ ያልተማሩ ቢሆኑም ጠንካራና አስተዋይ ስለነበሩ የዓይኗን ብርሃን ለማስመለስ ብዙ ጥረው ባይሳካላቸውም ተስፋ ባለመቁረጥ የትምህርት ገበታ እንድትቀላቀል በማሰብ በአካባቢው ወደነበረው ባኮ የዓይነ ስውራን የሚሽን ትምህርት ቤት ያስገቧታል።
ትምህርት ቤቱ አዳሪ ቢሆንም በወቅቱ ለሴቶች የተዘጋጀ ክፍል ባለመኖሩና አዳሪ ተማሪ ሴቶችን ስለማይቀበል በዛ ለጋ እድሜዋ ከቤተሰብ ተነጥላ በትምህርት ቤቱ አቅራቢያ ተከራይታ መኖር ትጀምራለች። በዚህ ሁኔታ ቤተሰቦቿ ቤት ኪራይ እየከፈሉላትና ቀለብ እየሰፈሩላት እስከ ስድስተኛ ክፍል ለመማር ትበቃለች። የዓይን ብርሃኗን ብታጣም ብልህ ልብና አእምሮ የነበራት ቤተልሄም ሰባተኛና ስምንተኛ ክፍልንም እዛው ባኮ ከተማ ሌላ ትምህርት ቤት ተምራ ታጠናቅቃለች።
ባኮ የዓይነ ስውራን ትምህርት ቤት የተቋቋመው በ1961 ዓ.ም ስለነበርና በርካታ ተማሪዎችን በውስጡ ስላሳለፈ የአካባቢው ማህበረሰብ ለዓይነ ስውራን ያለው አመለካከት ከሌላው አካባቢ በእጅጉ የተሻለ ነበር። የአካባቢው ነዋሪም ሆነ መምህራን ዓይነ ስውር መስራት፤ መማር፤ ማግባት መውለድ የሚለውን ነገር ሁሉ ማድረግ እንደሚችል ያምኑ ነበር። ነገር ግን ለዓይነ ስውራን የሚሆን ብሬልም ሆነ ሌሎች መሳሪያዎች በበቂ ሁኔታ የማይገኙ በመሆኑ እዛም ቢሆን ትምህርቱም ኑሮውም አስቸጋሪ ነበር። ቤተሰብም መንግስት ሁሉን ያደርጋል ብለው ስለሚያስቡ በገንዘብ ረገድ ድጋፋቸው የተቀዛቀዘ ስለነበር በቀለብም በቁሳቁስም ተደራራቢ ችግሮች ይገጥሟት ነበር። በዚህም የተነሳ ሁሌም የተሻለ የትምህርት እድልና ምቹ ሁኔታ ወዳለበት ለመሄድ ስታስብ ቆይታ በ1994 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ታቀናለች።
ከባኮ ስትነሳ የመጀመሪያው መዳረሻዋ ልታረገው ያሰበችው አዲስ አበባን ሳይሆን ባኮ አብራት ትማር የነበረች ጓደኛዋ ያቀረበችላትን ጥሪ ተቀብላ በወቅቱ የተሻለ የዓይነ ስውራን ትምህርት ወደሚሰጥበት ወላይታ ነበር። ጓደኛዋ ትምህርት ቤቱ መግባት ባትችል እንኳ ለሷ የሚሰጣትን ቁሳቁስ ተጠቅማ እንደማንኛውም ተማሪ ትምህርቷን እንድትከታተል ከጎና እንደምትቆምም ቃል ገብታላት ነበር። ይህንን ተስፋ ይዛ አዲስ አበባ ከደረሰች በኋላ ግን መምጣቷን የሰሙ ሌሎች ጓደኞቿ «አዲስ አበባን አልፈሽ ወላይታ አትሄጂም እዚሁ መፍትሄ እንፈልጋለን» ብለው ሸገር ያስቀሯታል።
እናም በጓደኞቿ መሪነት ወደ የምስራች የብሬል ማሰልጠኛ ተቋም ታቀናለች። እዛ ደግሞ ስውዲንና አንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት ተማሪዎችን ይረዱ ነበር። እናም በእነሱ በኩል የሚደረገው ድጎማ እንዲፈላለግ ይደረግና አዲስ አበባ በገባች ሁለተኛ ወሯ አንድ መቶ ሀያ ብር በየወሩ ማግኘት ትጀምራለች። በዛም ዘመን ቢሆን ግን 120 ለቤት ኪራይ፤ ለቀለብና ለቁሳቁስ ሟሟያ የሚበቃ አልነበረም። በመሆኑም ያንን አስቸጋሪ ጊዜ ለማለፍ አንድ ክፍል ለአምስት ተከራይቶ መኖር አንዳንዴም ጾም ውሎ ማደር የግድ ነበር። ይህም ሆኖ በምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እየተማረች እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል በነበራት የትምህርት ጉዞ ከአንድ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ አጥታ አታውቅም ነበር። አስረኛ ክፍል 3ነጥብ6 በኋላም አስራ ሁለተኛ ክፍልን አጠናቃ ጥሩ ነጥብ አምጥታ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ለመቀላቀል ትበቃለች።
ወደ ዩኒቨርሲቲ ስትገባ በፍላጎቷ መሰረት ልታጠና አስባ የነበረው የማህበረሰብ ሳይንስ ሶሺዎሎጂን ነበር። በዚህ ዘርፍም አንድ ወር ካሳለፈች በኋላ ዘርፉ ቶሎ የስራ እድል የሚገኝበት ባለመሆኑ ያሳለፈችው ችግር ተመልሶ እንዳይጋፈጣት በመስጋት መምህርነትን ትመርጥና በዩኒቨርሲቲው ያለውን የታሪክ ትምህርት ክፍል ትቀላቀላለች። እዛም የተለያዩ ውጣ ውረዶችን አሳልፋ በ2000 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በታሪክ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ለመያዝ ትበቃለች። «አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሰፊ ነው፤ ነገር ግን በቂ ቁሳቁስ አይቀርብልንም ነበር፤ ተገቢውን እገዛና ድጋፍ የሚሰጠንም አልነበረም። በብሬል የተዘጋጀ መርጃ ቁሳቁስ አልነበረም፤ በድምጽ የሚቀመጥም የለም፤ ስለዚህ አብረው የሚማሩ ልጆችን ሁል ግዜ እየለመኑ በማስነበብ መማር ብቸኛው አማራጭ ነበር። ሁሉም ባይሆኑም አንዳንዶቹ መምህራን ደግሞ በመቅረጸ ድምጽ የሚያስተምሩትን እንድንወስድም አይፈቅዱልንም ነበር። በዚህም የተነሳ አንዳንዴ ካለምንም ጥናትና ክለሳ ክፍል ውስጥ የሰማነውን ብቻ ይዘን ለፈተና እንቀመጥ ነበር። የታሪክ ትምህርት ደግሞ በባህሪው ደጋግሞ ማንበብን በርካታ የቦታና የሰው ስሞችንና ዓመተ ምህረትንም መያዝ የሚጠይቅ ነው። በተጨማሪ ከጥቂት መምህራን በቀር በችሎታችን የሚተማመንም አልነበረም፤ ይሄ በጣም የሚረብሽ ነበር። በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳ ከአንደኛ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል የነበረኝን ደረጃ ለማጣት ተገድጄያለሁ።» ትላለች ቤተልሄም ያለፈ የዩኒቨርሲቲ ትዝታዋን ስታስታውስ።
ቤተልሄም ከምረቃ በኋላ መንግስት መምህራንን ይመድብ ስለነበር ለስራ ፍለጋ መንገላታት አልገጠማትም። ይህም ሆኖ አዲስ ትምህርት ቤት ሊከፈት ስለሆነና እሷ እዛ ስለተመደበች የትምህርት ቤቱ ግንባታ እስኪጠናቀቅ በግዜያዊነት አየር ጤና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስራዋን ትጀምራለች። የአየር ጤና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቆይታዋ ግን ከሁሉም ግዜ የተለየ የሚወደድም እንደነበር እንዲህ ታስታውሳለች «መምህራኑም ሆኑ ተማሪዎች በደንብ ይንከባከቡናል። ፈተናና ደብተር አርመው ማርክ እየሞሉ ስራችንን ያቃልሉልን ነበር። በዩኒቨርሲቲ ከነበረው የመገፋት ስሜት የሚፈጥር ሁኔታ በእጅጉ የተለየ በመሆኑ ከፍተኛ የህሊና እረፍትና ደስታ ይሰማኝ ስለነበር ስራዬን የምሰራው በፍቅር ነበር»።
ቤተልሄም ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዘጠነኛ ክፍል ስትገባ አስራ ሁለተኛ ክፍል ይማር ከነበረና እንደሷው ማየት ከተሳነው አንድ ወጣት ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መስርታ ነበር። በጥናት ጊዜ ቤተመጻህፍት ውስጥ ነበር የተዋወቁት። ወንድሙ አዲሴ ይባላል። እሱ ወዲያውኑ የህግ ትምህርቱን ለመከታተል ዩኒቨርሲቲ ቢገባም ከትምህርት ቤት ውጪም ቤተክርስቲያንና በሌሎችም ማህበራዊ ጉዳዮች ስለሚገናኙ ቀረቤታቸውን እያጠናከሩት ይመጣሉ። እናም መስከረም 30 ቀን 2000 ዓ.ም ሶስት ጉልቻ መስርተው አዲስ የህይወት ምእራፍ ይጀምራሉ።
ትዳራቸውም ፍሬ ያፈራና ወይዘሮ ቤተልሄም መጋቢት ላይ የመጀመሪያ ወንድ ልጇን ትገላገላለች። ዛሬ ደግሞ ዘጠኝ ወር የሞላትን ልጅ ጨምሮ የአራት ልጆች እናት ለመሆን በቅታለች። በልጅነቷ የታላላቅ ወንድሞቿን ልጆች ትንከባከብ ስለነበር ልጅ ማሳደጉ አዲስ አልሆነባትም። ማንም ለልጁ የሚያደርገውን እያደረገችም ልጆቿን እያሳደገች ትገኛለች። «እንጀራ ከመጋገር ውጪ ሁሉንም ነገር መስራት እችላለሁ” የምትለው ወይዘሮ ቤተልሄም “እኔም ባለቤቴም ከስራ ስንወጣ ወደቤት ነው የምንመጣው፤ በጣም ደስተኛ ቤተሰብ ነው ያለን። ከልጆቻችን ጋር አብረን እንበላለን፤ አብረን እንጸልያለን የምናስጠናቸውም እኛው ነን። ባለቤቴ ጠንካራ ሰው ነው፤ በጣም ይረዳኛል ያለፈውን አስራ ሁለት ዓመት በመምህርነት እየሰራሁ አራት ልጆች ወልጄ ለማሳደግ የበቃሁትም እሱ ጠንካራ በመሆኑ ነው። እኔም ሆንኩ ባለቤቴ አንድም ቀን አካል ጉዳተኛ መሆናችንን ከቤተሰባችን ጋር አያይዘን አይተነው አናውቅም። ሁሉንም ማድረግ እንደምንችል ስለምናምን እናደርገዋለን።» ትላለች ።
ወይዘሮ ቤተልሄም ከማህበረሰቡ ጋር ያላትንም ግንኙነት እንዲህ ትገልጻለች። የጋራ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ የማህበራዊ ህይወት የላላ ነው። እስከ 2009 የነበረው ጊዜ ግን በዚህ ረገድ ደስ የሚል ነበር። ድሮ የኔ ቤተሰቦች ለእረፍት ስሄድ በብሬል የተጻፉ ነገሮችን አነብላቸው ነበር። በጣም ነበር የሚያበረታቱኝ። እኔ አንዱን ትምህርት ስጨርስ እነሱ ብዙ ሌላም መማር መስራት እንደምችል ያምኑ ስለነበር ሁሌም ያደንቁኛል፤ ያበረታቱኛል። በአሁኑ ወቅትም በኮተቤ ሜትሮ ፖሊታንት ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዲግሪዬን በማጠናቀቅ ላይ እገኛለሁ። ዛሬ የእኔን ቤተሰብ ከመንከባከብ አልፌ የወንድሜን ልጅ አምጥቼ እያስተማርኩ ነው፤ በስሬም ሰባት ቤተሰብ አለ። ድሮም ከዓይናማ ጓደኞቼ ጋር ሆኜ ወንዝ ወርጄ ውሃ እቀዳ፣ ዱር ሄጄ ማገዶ እለቅም ነበር። ከብት ከሚያግዱትም ጋር አብሬ እውላለሁ። አባቴ ትጎዳለች ብሎ ስለሚሳሳ እንዲህ አይነት ስራዎችን እንድሰራ አይፈልግም። ገደል ትገቢያለሽ፣ ትሰበሪያለሽ፣ ተይ ይል ነበር። አንዳንዴም ይቆጣል። ወንድሜ ግን ሁሌም ይደግፈኝና ያበረታታኝ ነበር። እነዚህ ነገሮች ዛሬ ቤተሰብ ስመሰርትም ውጤታማ መሆን እንደምችል እንደ ስንቅ ሆነው ረድተውኛል። ዛሬ የሚያውቁኝ ሁሉ ቤተሰቤን ጨምሮ በእኔ ይኮራሉም ይደነቃሉም። እኔም ለብዙዎች ምሳሌ እሆናለሁ ብዬ አስባለሁ።
ይህም ሆኖ ዛሬም ስለ አካል ጉዳተኝነት በማህበረሰቡ በኩል ያለው አመለካከት የተዛባ ነው ይሄ ደግሞ በተማሩትና በሀይማኖት አባቶች በኩል ሲሆን ችግሩን ውስብስብ ያደርገዋል። የእኔን ልምድ እንደ ተሞክሮ ባነሳ ተማሪዎቼ ሁሉም እንደምንችል ይገባቸዋል፤ ይደግፉኛልም። ሀላፊዎች ግን የሚያስተናግዱኝ ዜጋ ስለሆንኩ በሚል መንፈስ ብቻ ነው። አምነው ስራ ሀላፊነት ለመስጠት አይደፍሩም። ልክ እንደዚህ ብዙ የአካል ጉዳተኞች ስንት ነገር መስራት እየቻሉ ለልመናና እቤት ለመዋል የሚዳረጉት አቅም ስለሌላቸው ሳይሆን መጀመሪያ አይችሉም፣ የትም አይደርሱም፣ የሚለው አመለካከት አስሮ ስለሚያስቀራቸው ነው። ተማረ የተባለው ማህበረሰብም ስለ አካል ጉዳተኝነት ያለው ግንዛቤ ከሌላው ሰው እምብዛም የተለየ አይደለም።
አንድ ሰው ተምሯል ማለት ስለ አካል ጉዳተኛ ያውቃል ማለት አይደለም። እንዲያውም ብዙ ግዜ ርህራሄና ፍቅር የሚታየው ካልተማረው ማህበረሰብ ነው። ስለዚህ ለሁሉም ስለ አካል ጉዳተኝነት ግንዛቤ ማስጨበጥ ይጠበቃል። የሀይማኖት አባቶችም በኩል በአካል ጉዳተኞች ረገድ የተንሸዋረረ እይታ አለ። እንደ እርግማንና እንደ ፈጣሪ ቁጣ የሚያዩ ብዙዎች ናቸው። እኔን እንደ ምሳሌ ባነሳ ከባለቤቴ ጋር ትዳር ለመመስረት ስንወስን ልንጋባ የነበረው በቤተ ክርስቲያን ነበር። ነገር ግን ሁሉንም ተቀብለው ትምህርቱንም ካስተማሩን በኋላ ሰርጉ ሲደርስ ማመንታት ጀመሩ። እኛም ማዘጋጃ ሄደን ተፈራረምን። አንዳንድ ሰዎች የእኛን ቤተሰብ መመስረት ልጅ ወልዶ ማሳደግ እንደታምር ሲያዩት ይገርመኛል። እያዩ እንኳን የማያምኑም አሉ። እኛ ግን ሁኔታዎች ከተመቻቹልን እኛም ከማንኛውም ስው በተሻለ ሁሉንም ነገር መስራትም ሆነ የፈለግነውን መሆን እንችላለን። በእኛም ሀገር ጥቂቶች ቢሆኑም ከራሳቸው አልፈው ለሀገርም ለህዝብ የሚተርፍ አስተዋጽኦ እያበረከቱና ትልቅ ቦታ የደረሱ አሉ።
መምህርት ቤተልሄም እንደምትለው የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት ከእኛ ከአካል ጉዳተኞች ብዙ ይጠበቃል። በመጀመሪያ የምንችለው ነገር ካለ ሁሌም ቢሆን የሌላ እርዳታ መፈለግ የለብንም። በማህበረሰቡ በኩልም ያለውንም አመለካከት ለመቅረፍ መስራት ያለብን በቅድሚያ እኛው ነን የተዛባውን እይታም ሰብሮ ለመውጣት ተጋፍጦ መስራትና መጣር ይጠበቅብናል። በገጠር ያሉት አካል ጉዳተኞች ብዙ ችግር አለባቸው። ያም ሆኖ አንዲት አጋጣሚ ሲያገኙ በዛች ቀዳዳ ለማምለጥ መጣር አለባቸው። እቤት መዋል የለባቸውም። ሁሉንም ማድረግ ይችላሉ። ቤተሰብ መመስረት፣ ማግባትና መውለድ ይችላሉ። በዚህ በኩል የተወሰንን ብንሆንም የተሻለ ሁኔታ ላይ ያለነውም ደግሞ የበለጠ ሀላፊነት አለብን። ሚዲያውም ቢሆን ወቅት እየለየ የአንድ ሰሞን ብቻ ሳይሆን ሁሌም ማስታወስ አለባቸው። ትኩረታቸውም ከተማ ውስጥ ብቻ መሆን የለበትም።
አዲስ ዘመን አርብ ጥር 15/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ