ኢዜአ፡- የዩኒቨርሲቲ- ኢንዱስትሪ ጥምረት የመፈላለግ ግንኙነትን መሰረት ያደረገ ባለመሆኑና በዕቅድ ባለመመራቱ ምክንያት ውጤታማ ሊሆን አለመቻሉን የቤቶች ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ኢንዱስትሪዎች ተቀናጅተው ባለመስራታቸው ምክንያት ብቁ የሰው ሃይል እየተመረተ አይደለም።
በዚህም ምክንያት ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመርቆ የሚወጣው የሰው ሃይል አንፃራዊ እውቀት ቢይዝም፤ ”እስካሁን በነበረው አሰራር በስራ ላይ ውጤታማ ሊያደርግ የሚችል ክህሎት ግን ይዞ እየወጣ አይደለም” ብለዋል።
”እንደ ሃገር እስካሁን ስንከተለው የነበረው የዩኒቨርስቲ -ኢንዱስትሪ ግንኙነት ትክክል ያልሆነና በእቅድ ያልተደገፈ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
በመሆኑም የትምህርት ተቋማቱ የሰው ሃይል የማስተማሩን ስራ እየሰሩ ተማሪዎቹ የክህሎት ልምምድ እንዲያገኙ ኢንዱስትሪዎችን የሚጠይቁበት ሁኔታ ቀርቶ የመፈላለግ አሰራር መፈጠር እንዳለበት ገልፀዋል።
ይህን ለማስተካከል መጀመሪያ ሁሉም የመንግስት ተቋማትና የግል ኢንዱስትሪ ተቋማት በሚሰሩት የስራ ልክ የሚፈልጉትን የሰው ሃይል በቁጥርና በሚፈልጉት የእውቀት አይነት ለይተው ለትምህርት ተቋማቱ ማሳወቅ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በዚህ መሰረት ዩኒቨርስቲዎች የተጠየቀውን የሰው ሃይል በሚፈለገው የእውቀት አይነትና ልክ ማሰልጠን ኢንዱስትሪዎችም ለጠየቁት የሰው ሃይል የክህሎት ስልጠና እንዲያገኙ ማለማመድ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።
በተለይ እንደ ሃገር በርካታ የስራ እድል ለመፍጠር ትኩረት በተሰጠው የኮንስትራክሽኑ ዘርፍ ይህ ተግባራዊ እንዲሆን ሚኒስቴሩ ድልድይ ሆኖ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በዩኒቨርሲቲና ኢንዱስትሪ መካከል ያለውን ግንኙነትና ትስስር በማጠናከርና ግንኙነቱን በዕቅድ በመምራት በተለያዩ ዘርፎች ውጤት ሊያመጣ የሚችል የሰው ሃብት ለማልማት በትኩረት መሰራት እንዳለበትም ኢንጂነር አይሻ ጠቁመዋል።
የዩኒቨርሲቲ – ኢንዱስትሪ ትስስር የተጀመረው በቅርብ ቢሆንም አሁንም በሚፈለግበት ደረጃ አልደረሰም፡፡
ለችግሩ መንስዔ ናቸው ከሚባሉት ውስጥ ኢንዱስትሪዎች የዩኒቨርሲቲ መምህራንና ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተናገድ እንዲሁም በአብሮነት ምርምር ለማድረግ ፍላጎት ማጣት እንደምክንያት ጠቅሰዋል።
ትምህርት ሚኒስቴር በ2010 ዓ.ም ማገባደጃ ላይ በጉዳዩ ዙሪያ ባዘጋጀው የምክክር መድረክ የመምህራንም ወደኢንዱስትሪ ቀርበው ራሳቸውን ለማብቃትና ለመማር ግዴታ አለብኝ ብሎ አለማሰብ አንዱ ክፍተት መሆኑን መግለጹ ይታወሳል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 14/2012