አውደ ዓመት በመጣ ቁጥር በብዙዎች የሚለበሱት በተለይ እንስቶችንና ህፃናትን የሚያስጌጡት የአገር ባህል ልብሶች ዋነኛ መገኛ፤ የጥበበኞቹ ውሎ ማደሪያ ነው ሽሮሜዳ።ከደዋሪው እስከ ጠላፊው፤ ከቁጭት አከናዋኙ እስከ ሸማኔው በላቡ የሚያድር ታታሪ የሚታይባት፤ ለፍቶ አዳሪና በሙያው የሚኮራ ጥሮ ኗሪ የበረከተባት ሽሮሜዳ የበዓል ሰሞን ውክብያ ይበዛባታል።ከከተማይቱ ልዩ ልዩ አካባቢዎች አቅሙ በፈቀደው ልክ በሀገር ባህል ልብስ በዓሉን ለማድመቅ ለመሸመት ይተምባታል፡፡
አውደ ዓመት በደረሰ ቁጥር ደምቆ መታያ የሆኑት ባህላዊ አልባሳት ዛሬ ከማስጌጥ ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው እጅግ እየጨመረ ይገኛል።እነዚህ የክት ልብስ ሆነው ባህር ማዶ ድረስ በመሻገር አገር በማስተዋወቅ ላይ ያሉት አልባሳት በተለያየ ቀለምና ዲዛይን ተሰርተው ለገበያ እስኪቀርቡ ድረስ ለበርካታ ዜጎች ኑሮ መደጎሚያ ቤተሰብ ማስተዳደሪያ ናቸው።
የአገር ባህል አልባሳት ከጥጥ ለቀማው እስከ ሰፊውና ጠላፊው እንዲሁም ቁጭት እስከሚያከናውነው ድረስ የዘርፉ ተዋንያን በቅብብሎሽ ተጋግዘው አንዱ በሰራው ላይ ሌላኛው እሴት ጨምሮ ለገበያ ይቀርባል።በዚህ ውስጥ የበዛ ተዋናይ የበረከተ በሙያው አዳሪ አለ።የሽሮሜዳ ትጉሃን አሁናዊ የስራ እንቅስቃሴ ገፅታ ዛሬ በኢኮኖሚ አምዳችን በወፍ በረር ለመዳሰስ እንሞክራለን።
የአገር ባህል ልብስ የተጎናፀፉ በጥበብ ልብስ የደመቁ አሻንጉሊቶች በራቸው ላይ ባሰለፉ ተርታ የሀገር ልብስ መሸጫ ሱቆች አንዱ ውስጥ ገባን።ወጣት ግዛው ኃይለማርያም ደንበኞቹን በሚያስተናግድበት በትህትና ተቀበለን።በሽሮ ሜዳ ዝክረ ነዋይ የአገር ባህል አልባሳት መሸጫ ውስጥ የሚሰራው ወጣት ግዛው ስራውን የሚያከናውነው ከሁለት እህቶቹ ጋር ነው።ከዚሁ ስራ በሚያገኘው ገቢ ከአምስት ያላነሱ ቤተሰቦቹን ይመራል፡፡
በሱቁ ውስጥ የሚገኙት የባህል አልባሳቱ እንደተሰራባቸው ጥሬ እቃ ልዩነትና አቅርቦት ከ2ሺ ብር ጀምሮ እስከ 17ሺ ብር ድረስ ለሽያጭ አቅርቦ ገዢዎችን በመጣባበቅ ላይ እንደሚገኝ ይናገራል።
እንደወጣት ግዛው ገለፃ፤ የአገር ባህል ልብስ ፈላጊው ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ ቢጨምርም የጥሬ እቃ አቅርቦት ችግር ግን የልብሱን ዋጋ አንሮታል።በዚህ ሳቢያ ከሌላ ጊዜ አንፃር ሲታይ የሚሸምተው ሰው ቁጥሩ ቀንሷል።በባለፉት ዓመታት የበዓል ወቅት በወረፋ ሰዎች ገዝተው ይለብሱት የነበረው ባህላዊ የአገር ጥበብ ልብስ መስሪያ ግብዓት ለሰሪዎቹ መቅረብ ስላልቻለ የዘርፉ ስራ እጅግ ተቀዛቅዟል።
‹‹በተለይ ለሸማ ስራ የሚውለው ጥሬ እቃ ከፍተኛ እጥረት ታይቶበታል›› የሚለው ወጣት ግዛው፤ እሱ በሚሰራው ስራ ላይ በቀጥታ የግብዓቱ እጥረት ተፅዕኖ ስለፈጠረ የደንበኞቹን አቅም ያገናዘበ የጥበብ ልብስ ማቅረብ እንዳላስቻለ ይጠቁማል።
ወጣት ታሪክዋ ሜንታ በወንደሰን የሀገር ልብስ መሸጫ ውስጥ የሽያጭ ሰራተኛ ናት።የሀገር ልብስ መሸጫ ዋጋ ከሌላ ጊዜ መጨመሩን ባትክድም የተጠቃሚው የመግዛት አቅምን ባገናዘበ መልኩ በተለያየ መጠንና አይነት ስለተዘጋጀ ማንኛውም ተጠቃሚ መሸመት የሚያስችለው አጋጣሚ እንደተፈጠረ ታስረዳለች።ከሌላ ጊዜ በተለየ መልኩ ከአቅርቦት ጋር በተያያዘ እነሱ ለመሸጥ ከሚረከብዋቸው ባለሙያዎች የገንዘብ ጭማሪ እንደሚጠቁ የምትገልፀው ታሪክዋ ለዚህም ዋንኛ ምክንያት የጥሬ እቃ አቅርቦት ችግር መሆኑን ትናገራለች።
አብዛኛዎቹ ደንበኞችዋ በትዕዛዝና በሚፈልጉት ዲዛይን ማሰራት እንደሚያዘወትሩና በዚህም ከሸማኔዎች፣ ከጥልፍ ዲዛይነሮች እና ከጠላፊዎች እንዲሁም ከሰፊዎች ጋር በጋር እንደሚሰሩ ትገልፃለች።በዚህ ለጥልፍ ሰሪዎች የስራ ዕድል በመፍጠር በአንድ ጥልፍ ስራ እስከ አራት ሺ ብር ድረስ በመክፈል ለደንበኞችዋ አዳዲስ የጥልፍ ስራዎችን አሰርታ እንደምታስረክብ ትናገራለች።የሀገር ባህል ልብስ መደብሩ ከ3 ሺ እስከ 18 ሺ ብር ድረስ የሚሸጡ የተዋቡ አልባሳት የሚገኙ ሲሆን፤ በዚሁ መደብር ቤተሰቦችዋና ሌሎች ሶስት ባልደረቦችዋ እንደሚተዳደሩበት ትናገራለች፡፡
ወጣት አቢ አሰፋ ይባላል በሽሮ ሜዳ የሸማኔዎች ህብረት ስራ የጥበብ ስራ መስሪያ ማዕከል ውስጥ የጥልፍ ስራ ባለሙያ ነው።ከደንበኞቹ የተቀበለውን የበዓል ትዕዛዝ ለማድረስ አንገቱን አቀርቅሮ ከመጥለፊያ ማሽኑ ጋር ይታገላል።የበዓል ስራ እንደ ሌላ ጊዜው ባይሆንም አቅሙ በፈቀደው ልክ እራሱን ለመለወጥ እና የተሻለ ገንዘብ ለማግኘት እየተጋ መሆኑን ገለፀልን።
አቢ ከፍተኛው የጥልፍ ስራ የሚያስፈልገው የቀሚስ ጥልፍ እስከ 15 ቀን የሚወስድበት ሲሆን ለጥልፍ ሥራው ከ1ሺ እስከ 2 ሺ ብር ድረስ ክፍያን ይጠይቃል።ከዚህ በፊት የገቢ መጠኑ ከዚህ የተሻለ እንደነበር አስታውሶ በአሁኑ ሰዓት የጥልፍ ስራ ክር እንደልብ ማግኘት አለመቻል ገቢው እንዲቀንስ ያደረገው መሆኑን ያመለክታል።
በዛው ማዕከል ውስጥ የሸማ ስራ ከሚሰሩ ሙያተኞች ውስጥ አቶ ሙሉጌታ ገብረማሪያም አንዱ ናቸው።በሸማ ስራ ከ20 ዓመታት በላይ ቆይተዋል።የሶስት ልጆች አባት ሲሆኑ፤ የቤተሰባቸው ዋነኛ የገቢ ምንጭ ይኸው ስራ መሆኑን ይናገራሉ።
‹‹እስካሁን ያሰብኩትን ያህል ተለውጬ የተሻለ ቦታ ላይ መገኘት ባያስችለኝም አቅሜ በፈቀደው መልኩ ኑሮዬን የምመራበት ሙያዬ ሽመና ነው›› ይላሉ።ነገር ግን አሁን ላይ የጥሬ እቃ አቅርቦት ፈታኝ መሆኑ፤ ቤተሰባቸውን ማስተዳደር እንዳያቅታቸው ስጋት እንደፈጠረባቸው ይገልፃሉ።
የእንጦጦ ጎዳና ሸማኔዎች ህብረት ስራ ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ ሲሳይ ናቸው።ማህበሩን ከመምራት ባሻገር እዚያ ማዕከል ውስጥ የሸማ ስራ በመስራት ይተዳደራሉ።ማህበሩን ወክለው በሸማኔዎች ላይ የተፈጠረው የጥሬ እቃ አቅርቦት ችግር የጎላ መሆኑንና ለሚመለከተው አካል በተደጋጋሚ ቢያቀርቡም ምላሽ ማግኘት እንዳልቻሉ ያስረዳሉ።ህብረተሰቡ ለሀገር ባህል ልብስ የሚሰጠውን ትኩረት በዋጋው መወደድ ምክንያት እንዲቀንስ ያደርገዋል የሚሉት የማህበሩ ስራ አስኪያጅ የሚመለከተው አካል ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥ ያሳስባል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 11 /2012
ተገኝ ብሩ