
ኢትዮጵያ ካሏት የምድር በረከቶች አንዱ የወርቅ ሀብት ነው። ወርቅ በዘርፉ ለተሰማሩ ሰዎች ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ባለፈ ለአጠቃላይ ሀገራዊ ገቢ መጨመርም የጎላ ድርሻ አለው። ምክንያቱ ደግሞ ወርቅ ለዘመናት ሳይበላሽ መቆየቱ ብቻ ሳይሆን፤ ተፈላጊነቱም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄድ ማዕድን መሆኑ እንዲሁም የሚያስገኘው ገቢ ከፍተኛነት በሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የሚኖረው ሚና የሚናቅ አለመሆኑ ነው። ይህን መሠረት በማድረግ መንግሥት ልዩ ትኩረት ከሰጣቸው የማዕድን ዘርፎች መካከል አንዱ ወርቅ ነው።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ላይ ጭምር ለወርቅ የተለየ ትኩረት በመስጠት በክልሎች ያለውን ምርታማነት የማሳደግ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። በቀጣይም ተግባራዊ የሚደረጉ በርካታ ጥናቶች በዘርፉ እየተካሔዱ ስለመሆናቸው መረጃዎች ያመላክታሉ። በሀገሪቷ በተለያዩ አካባቢዎች ከፍተኛ መጠን ያለው የወርቅ ክምችት አለ። ይሁንና በፀጥታ ችግሮች፣ በአመራር ክፍተትና ዘርፉ ለዘመናት በተገቢው መንገድ ቁጥጥር ሳይደረግበት በመቆየቱ በሙሉ አቅም ሳይመረት ቆይቷል። ይህም ብሔራዊ ባንክ በየዓመቱ ሊያገኝ የሚገባውን ገቢ እንዳያገኝ ምክንያት ሆኗል።
በሌላ በኩል በኮንትሮባንድ እና ደህንነቱ ባልተጠበቀ መንገድ ወርቅ ከሀገር ሲሸሽ እንደነበረ መረጃዎች ያሳያሉ። ይሁንና ካሳለፍነው ዓመት ጀምሮ የተደረገውን ሀገራዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ፤ ችግሩን ለመቅረፍ የተሠሩ ሥራዎች ውጤት እያስገኙ ናቸው። የጋምቤላ ክልልም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት እድገት በማሳየት ስምንት እጥፍ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ ማድረግ መቻሉን የክልሉ የማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ መረጃ ያመላክታል።
የክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት ኃላፊ አቶ ኡጁሉ ጊሎ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የማዕድን ዘርፉ እስከ ቅርብ ጊዜ በብዙ ችግሮች የተያዘ ነበር። በመሆኑም ባለፉት ዓመታት የነበሩ ሁኔታዎች ግምት ውስጥ በማስገባት በዘርፉ የተቀመጠውን እቅድ ለማሳካት ወደ ሥራ የተገባው በቅድሚያ ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸውን ጉዳዮች በመለየት ነበር። በተጨማሪ የኢኮኖሚ ማሻሻያው ይዞ የመጣውን ምቹ ሁኔታ መጠቀምም አንዱ የትግበራ አቅጣጫ ነበር። በዚህ ረገድ የፌዴራል መንግሥት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ለማዕድን ዘርፉ የሰጠው ትኩረት በዘርፉ ትልቅ ለውጥ እንደሚመዘገብ በር ከፍቷል ለማለት ይቻላል።
በክልሉ በተለያዩ የማዕድን ዘርፎች ላይ የማምረት ሥራ የሚከናወን ቢሆንም፤ በዋናነት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ያለው በወርቅ ዘርፍ ነው። ያሉት አቶ ኡጁሉ በክልሉ ባለፈው ዓመት ከፍተኛ የፀጥታ ችግር እንደነበር አንስተው፤ በዚህም በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች አቅማቸውን አሟጠው ማምረት ሳይችሉ ቆይተዋል። ለአብነትም በጋምቤላ ከተማ የማይደፈሩ አንዳንድ ሰፈሮች እንደነበሩ አመላክተዋል።
እንደሳቸው ገለፃ፤ ከተማው ለሁለት እስከመከፈል የደረሰበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። ይሁንና በዘንድሮው ዓመት መጀመሪያ አካባቢ የለውጥ አመራሮች ሰላምን ለማስፈን ትኩረት ሰጥተው በመሥራታቸው አበረታች ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል። በቀጣይነትም የተገኘውን ሰላም ለማረጋገጥ ወደ ማኅበረሰቡ በመውረድ የተለያዩ ሥራዎች ሲያከናውኑ ቆይተዋል። የተፈጠረውን ሰላም ተከትሎ አመራሩ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ እንዲጠናከርና ማኅበረሰቡ ያለ ስጋት እንዲንቀሳቀስ በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች የእግር ጉዞዎችን አካሂዷል።
በክልሉ ሰላም ተረጋግጦ ሕዝቡ በሰላም የዕለት ተዕለት ሥራውን እያከናወነ የሚገኝ መሆኑን አስታውሰው፤ የተገኘው ሰላምም ወርቅ በማምረት ለተሰማሩት አካላት በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል ሲሉ ተናግረዋል። በስጋት ሲያመርቱ የነበረበት ሁኔታም ተለውጦ ዛሬ ሁሉም አምራች ያለምንም ስጋት እየሠራ ይገኛል። ይህም በክልሉ በከፍተኛ ደረጃ የወርቅ ምርት ጭማሪ ሊመዘገብ አስችሏል ይላሉ።
እንደእሳቸው ገለጻ፤ ሌላው ለወርቅ ምርት ውጤታማነት በሀገር አቀፍ ደረጃ የተወሰደው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ነው። ከማሻሻያው በፊት አብዛኛው አምራች የተሻለ ገቢ ለማግኘት ወርቅ በኮንትሮባንድ የሚሸጥበት አካሄድ ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን ባለሀብቶች ወደ ኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ በመውጣት በቀጥታ ለብሔራዊ ባንክ ማቅረብ በመጀመራቸው በሕጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሰው የወርቅ ምርት መጠን ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል።
በዚህም በበጀት ዓመቱ ጥቂት ወራት ሲቀሩት 1ሺህ 850 ኪሎ ግራም ለብሔራዊ ባንክ ለማስገባት ታቅዶ ስምንት እጥፍ ያህል ጭማሪ በማምጣት 4 ሺህ 254 ኪሎ ግራም ማስገባት ተችሏል። በቀሩት ሶስት ወራት ተጨማሪ አንድ ሺህ 41 ነጥብ 87 ኪሎ ግራም ወርቅ በማስገባት አጠቃለይ በበጀት ዓመቱ አምስት ሺህ 295 ነጥብ 87 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ መደረጉን አስረድተዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለወርቅ አምራቹ ሁለት ትሩፋቶችን ይዞ የመጣ ነው። የመጀመሪያው ከዚህ ቀደም አምራቾች ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ሲያቀርቡና በኮንትሮባንድ ሲሸጡ ከፍተኛ የዋጋ ልዩነት ነበረ። የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ግን ብሔራዊ ባንክ ከጥቁር ገበያው ጋር ተቀራራቢ ዋጋ መስጠት ጀምሯል ይላሉ።
ወርቅ ከዚህ ቀደምም ሆነ አሁን በጥቁር ገበያ የሚደረግ የንግድ እንቅስቃሴ ከፍተኛ አደጋና ስጋት የተጋረጠበት መሆኑን አስታውሰው ሲያብራሩ፤ በአንድ ወገን ባለሀብቶቹ በማንኛውም አጋጣሚ ንብረታቸውንም ሆነ ገንዘባቸውን ሊያጡ የሚችሉበት እድል ሰፊ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በሌላ በኩል በየደረጃው ያለው ደላላ የሚወስድባቸው ገንዘብ ቀላል አይደለም ሲሉ ይገልፃሉ።
‹‹በሌላ በኩል እነዚህን ፈተናዎች ማለፍ ቢችሉ እንኳን በሕግ አስከባሪዎች በቁጥጥር ሥር ሲውሉ ተጠያቂ መሆናቸው አይቀርም።›› የሚሉት አቶ ኡጁሉ፤ ከብሔራዊ ባንክ ጋር የሚደረግ ግብይት ገንዘቡን በባንክ በሕጋዊ መንገድ ከማንቀሳቀስ ጀምሮ ከማንኛውም ስጋት ነጻ የሚያደርግ ነው ሲሉ ይናገራሉ። አያይዘውም አምራቾቹ ይህንን በመገንዘብ ከጥቁር ገበያ ይልቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ በማስገባት ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው በመረዳት በአሁኑ ወቅት ወደ ጥቁር ገበያ የሚያማትሩ አምራቾች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ሊቀንስ ችሏል ይላሉ።
በክልሉ ከወርቅ በተጨማሪ ከፍተኛ የግራናይት ክምችት መኖሩን የጠቆሙት አቶ ኡጁሉ፤ በዚህ ረገድም እስካሁን ሁለት ባለሃብቶች በቋሚነት ሲያመርቱ መቆየታቸውን አስታውሰው፤ በቅረቡ አንድ ተጨማሪ ባለሀብት ወደ ዘርፉ በመግባት በአሁኑ ወቅት በስራ ለይ ያሉት አምራቾች ሶስት ደርሰዋል ሲሉ ተናግረዋል። በበጀት ዓመቱ ሰባት ባለሀብቶች በዘርፉ ለመሥራት አመልክተው በሂደት ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ በተጨማሪ በአሸዋና በድንጋይ ከሰል ምርት ለመሰማራት በተለያዩ ወረዳዎች ፍቃድ ለማውጣት ተመዝግበው በሂደት ላይ ያሉ በርካታ ባለሀብቶች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።
የክልሉ ማዕድን ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኤልያስ ገዳሙ በበኩላቸው፤ የማዕድን ዘርፉ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እንደክልልም እንደሀገርም ጥሩ እንቅስቃሴ እየታየበት ይገኛል ይላሉ። አቶ ኤልያስ እንደሚያብራሩት፤ በክልሉ በማዕድን ዘርፍ ከፍተኛ ዕምቅ አቅም ያለ ቢሆንም ከዚህ በፊት እምብዛም ትኩረት ሳይሰጠው ቆይቷል። በአሁኑ ወቅት ግን በአጠቃላይ ትኩረት ከተሰጠባቸው ከአምስቱ የልማት ዘርፎች አንዱ የማዕድን ዘርፍ መሆኑን ተከትሎ አዲስ ምእራፍ ተጀምሯል።
በዚህም በዘርፉ ከተቋማዊ ሪፎርም አንስቶ እስካሁን ሰፋፊ ሥራዎች ተከናውነዋል። ለምሳሌ አዲሱን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ የማያሠሩ አዋጆችን አስወጥቶ አዳዲስ አዋጆችን ቀርፆ በመተካት ውጤታማ ሥራ ለማከናወን ተችሏል። በዚህም የማዕድን ዘርፉ በጋምቤላ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር ተስፋ ሰጪ እድገት ላይ ይገኛል። በዚህ ረገድ አዋጆችን ተግባራዊ ከማድረግ አንፃር አሁንም በፌደራል መንግሥት በኩል ሥልጠናዎች ተጀምረዋል። በቀጣይ በክልሉ ያለውን ተዋረድ ተከትሎ በአዲሱ የማዕድን ዘርፍ አዋጅ ላይ ግንዛቤ የማሳደግ ሥራዎች የሚሠሩ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት የክልሉ መንግሥትና በመስኩ የተሠማሩ የፌደራል ተቋማት በቅንጅት እስከታች በጋራ በመሥራት ላይ ናቸው። አዳዲስ የማዕድን ሳይቶችም እየተለዩ ሲሆን፤ በአጠቃለይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውና የሰላም ሁኔታ መስተካከል የክልሉን የማዕድን ሀብት ወደ ተሻለ ደረጃ እያሳደገው ይገኛል ብለዋል።
በ2016 ዓ.ም ለብሔራዊ ባንክ 650 ኪሎ ግራም ገቢ ተደርጎ ነበር። ይሁንና የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ከተደረገ በኋላ ከፍተኛ ደረጃ ለውጥ ማምጣት ተችሏል። በዘንድሮ በጀት ዓመትም በክልሉ እስከ 2ሺህ 850 ኪሎ ግራም ወርቅ ለማምረት ዓመታዊ እቅድ ሲያዝ፤ ይህን ያህል ምርት ይገኛል አይገኝም? የሚለው ሲያከራክር ነበር። ነገር ግን ተዓምራዊ በሆነ መልኩ እስከ ሰኔ 12 ቀን 2017 ዓ.ም የተጣራ ወርቅ 5 ሺህ 295 ነጥብ 87 ኪ.ግ ለማግኘት ተችሏል ሲሉም ነው የተናገሩት።
አሁን ላይ በየወሩ ዕድገት እያሳየ የመጣበት ሁኔታ መኖሩን አስታውሰው፤ የጭማሪው ዋነኛ ምክንያት ከላይ የተጠቀሱት እንደተጠበቁ ሆነው እሳቸው እንዳስረዱት፤ ከክልል ጀምሮ እስከ ወረዳ እና ቀበሌ ድረስ በከፍተኛ ደረጃ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑም ሌላኛው ምክንያት ነው። የቁጥጥር ሥራው በኮማንድ ፖስት የሚመራ መሆኑን አስታውሰው፤ በክልል ደረጃ ኮማንድ ፖስቱ በክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት የሚመራ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በወረዳ ደረጃ ደግሞ በዞኑ አስተዳዳሪዎች የሚመራ፤ በወረዳ አስተዳደሮችና እስከ ቀበሌ ድረስ መዋቅር ተዘርግቶ ወርቅ ላይ ቁጥጥር የሚደረግበት ሰንሰለት ተበጅቷል ይላሉ። ይህም ሁኔታ የወርቅ ምርቱን ይበልጥ ከፍ እንዲል ያደረገው ሲሆን፤ የቁጥጥር ሥራው በተመሳሰይ የኮንትሮባንድ እንቅስቀሴውንም እንዲቀንስ እያደረገው ይገኛል።
ሌላው እና ዋነኛው በአቶ ኤልያስ በምክንያትነት የተነሳው፤ መንግሥት ያወጣው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሚዛናዊ መሆን ነው። ኮንትሮባንድ በከፍተኛ መጠን በጨመረበት ወቅት መንግሥት ምንዛሪውን ማስተካከሉ ሁኔታዎች ለአምራች ባለሀብቶች ዋስትና የሚሰጡና ምቹ እንዲሆኑ እያደረገ ይገኛል የሚለው ነው።
በአሁኑ ወቅት በወርቅ ኢንቨስትመንት ላይ የተሠማሩት አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን አስታውሰው፤ ይህም የሀገር ውስጥ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ከተደረገ በኋላ ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ተሳትፎ ማደግ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የሚያመላክት ነው ሲሉም ተናግረዋል።
በከፍተኛ ደረጃ በማምረትና በሕጋዊ መንገድ በመንቀሳቀስ ከተለዩት መካከል አንዱ በኢትዮጵያውያን የሚመራ «ኢስቴላ» የወርቅ አምራች ኢንዱስትሪ ነው። ሁለተኛው በቅርብ ጊዜ በጠቅላይ ሚንስትሩ የተመረቀው ‹‹ኢትኖ ማይኒንግ›› ነው። «ኢትኖ ማይኒንግ» በዲማ አካባቢ በኖርዌይ ባለሀብቶች የተቋቋመ ሲሆን፤ ስያሜውንም ያገኘው ኢትዮጵያና ኖርዌይ ከሚለው መሆኑን ጠቁመዋል። ይህ ድርጅት የወርቅ ምርት በከፍተኛ ደረጃ የሚያመርት መሆኑን አመላክተዋል።
የማዕድን ዘርፉ አንዱ ጠቀሜታ የሥራ አድል መፍጠር ነው ያሉት አቶ ኤልያስ፤ በክልሉ የተፈጠረውን ዕድል በተመለከተ የሚከተለውን ብለዋል። የወርቅ ማውጣት ሥራ ከአመራረቱ አኳያ በቋሚና በጊዜያዊነት የሥራ አድል ለመፍጠር የሚያስችል በመሆኑ ወጣቶች በዘርፉ በተለያየ መልኩ ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ። በአሁኑ ወቅትም በአጠቃላይ በገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ በቋሚነት የሚሠሩት ከ795 በላይ ደርሰዋል ይላሉ። ከእነዚህ ውስጥ 665 ወንዶች ሲሆኑ፤ 130 ሴቶች ናቸው የሚሉት አቶ ኤልያስ፤ በጊዜያዊ የሥራ እድል ፈጠራም ስድስት ሺህ 890 ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ የተቻለ መሆኑን ተናግረዋል። ከእነዚህ ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ 21 ነጥብ ስድት በመቶ ደርሷል ሲሉ አመልክተዋል።
የማዕድን ልማት ሲታሰብ ጥንቃቄና ቁጥጥር ከሚፈልጉ ነገሮች መካከል አንዱ አካባቢ ጥበቃ መሆኑን የተናገሩት አቶ ኤልያስ፤ ማዕድን አላቂ መሆኑን አስታውሰው፤ ለሕብረተሰቡ ዘላቂ ጥቅም የሚገኝበት አካባቢውም የሚጠበቅበት ሁኔታ መኖር እንዳለበት በጽኑ ይታመናል ሲሉ ይናገራሉ። በመሆኑም በክልሉ በማዕድን ሀብት ልማት የአካባቢ ጥበቃ ቁጥጥር የሚደረገው ፍቃድ ሲወጣ ጀምሮ ሥራውን አጠናቆ እስከሚለቅ ድረስ መሆኑን ያስረዳሉ።
የአካባቢ ተፅዕኖ ጥናት ሲካሔድ ልማቱ በሚከናወንበት አካባቢ የዳሰሳ ጥናት የሚደረግ መሆኑን አስታውሰው፤ ይህ ሳይካሄድና ማረጋገጫ ሳይቀርብ የሚሰጥ ፈቃድ አይኖርም ይላሉ።
በዚህ ረገድ ከማዕድን ልማት ቢሮው ጋር የሚሠሩ ባለድርሻ አካላት መካከል አካባቢ ጥበቃ፣ እርሻና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ፣ ውሃና ኢነርጂ ይጠቀሳሉ። ጥናቱ በተለይ በልዩ እና አነስተኛ ደረጃ በሚሰሩ ባለሀብቶች ወይም ማኅበራት ላይ ይደረጋል። ማዕድኑ ተመርቶ ከተጠናቀቀ በኋላ አካባቢውን መልሶ ለልማት ማዋል ይጠበቃል። በመሆኑም ባለሀብቱ ሁለት ሄክታር ወይም አንድ ሄክታር ካለማ በኋላ አጠናቅቆ ሳይወጣ ጉድጓዷቹን መድፈኑ ተረጋግጦ የመውጫ ፍቃድ ወይም ተለዋጭ የሚሰጠው ይሆናል ሲሉም አስገንዝበዋል።
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 11 ቀን 2017 ዓ.ም