የሰው ልጆች በዚህ ምድር ላይ መኖር የጀመሩትና ማህበራዊ መስተጋብር እንደ ህብረተሰብ ክፍል ብሎም እንደ ሀገር መኖር የጀመሩበት ጊዜ እና ቦታ ላይ የታሪክ ሊቃውንት በእርግጥ ይሄ ጊዜና ቦታ ባይሉንም ረጅም ዘመናትን እንዳስቆጠሩ ይገልፃሉ። የአንድ ሀገር ወይም ማህበረሰብ መሠረት የሆነው ቤተሰብ እንደሆነ ይታወቃል። ይህ የሕብረተሰብ መሠረት የሆነው ቤተሰብ የሚመሰረተው በተለያየ መልኩ ቢሆንም ዋናው ግን የህብረተሰቡ አካል የሆኑት ሰው (ወንድ እና ሴት) በሚፈጸሙት ጋብቻ ነው። ቤተሰብ የህብረተሰቡ ዋና ምሶሶ በመሆኑ ትልቅ ቦታና ከበሬታ የሚሰጠው ነው። ይህ ትልቅ ቦታና ከበሬታ የሚሰጠው የህብረተሰቡ መሠረት የሆነ ተቋም እንደ ተቋም ከመቋቋሙ አንስቶ እስከ መጨረሻው ጊዜው ድረስ በሕግና እና ሥርዓት መመራት ይኖርበታል።
ትዳር ተፋቅሮና ተሳስቦ ለመኖር ለራስና ለዘመድ ወዳጅ ደስታ የሚለግስና ለአገር ጥቅም የሚሰጡ ልጆችን ለማስገኘት ይረዳል። የኅብረተሰብ የአገር መሠረት መሆኑ ስለታበነበትም በእምነት እና በአስተዳደር ሕግጋት ጥበቃ ይደረግለታል።
ትዳር እንዲጸና የአገር ባህል የእምነት እና የመተዳደሪያ ልማዶች ሁሉ ይተባበራሉ። እንዲሁም ሆኖ በድረ ዘመናዊነት በሚሰኘውና የቆዩ አሰራሮችና ልማዶችን በአብዛኛው እየተጻረረና እያፈረሰም በሚገኘው በእዚህ ዘመን ትዳር የመፍረስ አደጋ ተጋርጦበታል። አንዳንድ የትዳር ተጣማሪዎች ድል ያለ ድግስ ደግስው ውጪ ነፍስ ግቢ ነፍስ በሆነ ግርግር ተጋብተው ወር ሳይሞላ የሚፋቱበት ጊዜ እያጋጠመ ነው። አንዳንድ አገሮች እንዲያውም ከሁለት ዓመት በታች ፍች እንዳይፈቀድ ደንግገዋል።
ይሁንና በተቃራኒው ብዙ ትዳሮች ትወፊት ሕግና ሥርዓታቸውን ጠብቀው በባልና በሚስት መተሳሰብ ፍቅር መተጋገዝና መረዳዳት ደምቀው ይገኛሉ። ዛሬም እንደ ጥንቱ እምነት ባህላቸውን ጠብቀው የአኗኗር ሕይወታቸውን አሳምረው ከእዚህም ጋር መልካም ልጆችን ያስገኙ ባልና ሚስት ባለ ትዳሮች ሞልተዋል። ልጆችና የልጅ ልጆችን በስጋ ብቻ ሳይሆን በመንፈስ በተፈጥሮ ግብር ብቻ ሳይሆን በስነምግባር በእውቀት እና በማስተዋል ወልደው አሳድገው ወግ ማዕረግ ያዩ አያሌ ናቸው።
መልካሙ ጋብቻ
ከእንዲህ ዓይነት የተቀደሱ ትዳሮች አንዱ የወይዘሮ ደመቀች ናማጋ እና አቶ ተረዳ እንዳሻው አንዱ ነው። ይህ ትዳር ባሳለፍነው ሳምንት ጥር 3 ቀን 2012 ዓ.ም የ50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩውን አክብሯል። ትዳሩ የተመሰረተው በ1962 ዓ.ም ጥር ወር ላይ ነበር።
የእነ አቶ ተረዳ እንዳሻው እና የወይዘሮ ደመቀች ናማጋ ከአዲስ አበባ ወደ 210 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ዕዣ ወረዳ ልዩ ስሙ ቆጠር ተብሎ በሚጠራው መኖሪያ ቤታቸው ነበር በደስታ እና በፌሽታ ተሰርጎ የተዳሩት። ዘንድሮ ደግሞ 50ኛ ዓመቱን ልጅ እና የልጅ ልጅ ወልደው አሳድገው አስተምረው ኩለው ድረው ለስራ እና ለሃላፊነት አብቅተው መርካቶ ዶሮ ተራ አካባቢ በሚገኘው በራሳቸው መኖሪያ ቤት ተከብሯል።
የእነ ወይዘሮ ደመቀች ናማጋ ትዳር መተሳሰብ መፈቃቀር እና መከባበር የሰፈነበት መልካም ትዳር ተብሎ ተመስክሮለታል። በዕለቱ የወንጌል ትምህርት የሰጡት አባ ወልደ ሩፋኤል”ጋብቻን መልካም ያለው እግዚያብሔር ነው” ካሉ በኋላ ወይዘሮ ደመቀች ናማጋ እና አቶ ተረዳ እንዳሻው መልካሙን ትዳር በመጠበቃቸው ለእነርሱ ብቻ ሳይሆን ለልጅ ልጆቻቸው ለትውልዱም መልካም አርአያ መሆናቸውን ተናግረዋል። እንዲህ ያለ መልካም ጋብቻ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሰረት ያለው እንደሆነ ጠቁመው ወጣቱ ትውልድ እነ አቶ ተረዳ እንዳሻው አርአያ አድርጎ በትዳር እንዲኖር መክረዋል። እንኳን ሰው ሌሎች እንስሳ እንኳን በትዳር ተጣማሪዎቻቸው ላይ ጨዋ እንደሆኑ ገልጸው ማንኛውም ሰው ጋብቻ ከመሰረተ በኋላ እግዚያብሔር “መልካም” ነው ይህንን ተቋም አክብሮ ሊኖር ይገባል። “ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም የሚለውም የጋብቻን አስፈላጊነትንም ለማመልከት ነው” ብለዋል።
ከጋብቻ ወደ ፍቅር
የዘመናችን ጋብቻ ተዋውቆ እና ተፈቃቅዶ ነው። አንዲት ለትዳር የደረሰች ልጀገረድ ከአንድ ወጣት ተዋውቀው ተፋቅረው ለመጋባት ሲወስኑ ለቤተሰብ ያሳውቃሉ። ከዚያ እንዲያው “ለወጉ” ሽማግሌ ይልኩና ይጋባሉ፤ በአሁኑ ወቅት ያለው ጋብቻ ፍቅር መጀመሪያ ቀጥሎ ጋብቻ ይከተላል። የጥንቱ የጠዋቱ ትዳር ግን አመሰራረት ደግሞ ከወቅቱ የትዳር አመሰራረት በተቃራኒው ነው። ጋብቻ ይቀድማል ፍቅር መተሳሰብ ይከተላል።
የጥንቱ የጠዋቱ ትዳር አመሰራረት ቤተሰብ እና ቤተሰብ በተለያዩ መለኪያ እና መሟላት ባለባቸው መስፈርቶች ተጠያይቀው “ልጅህን ለልጄ” ተባብለው ልጆቻቸውን ያጋባሉ።
የወንዱ ቤተሰብ ሽማግሌ ልኮ የሴቷ ቤተሰብ ሽማግሌዎች በአክብሮት ተቀብሎ ጥያቄያቸውን ይሰማል፤ ይስማማሉ፤ ሰርግ ተደግሶ ትዳር ይመሰረታል።
ማንኛውም ሰው ዘመኑን ተከትሎ እንደዘመኑ ነው የሚወጣው ፣የሚገባው … በአጠቃለይ የሚኖረው፤ እነ አቶ ተረዳ እንዳሻው በቤተዘመዶቻቸው እንደነበረው ሥርዓት በቤተሰብ እምነት እና ስምምነት ነው ጋብቻቸው የተፈጸመው።
አቶ ተረዳ እንዳሻው 1930 ዓ.ም የተወለዱ ሲሆን ባለቤታቸው ወይዘሮ ደመቀች ናመጋ ደግሞ በ1944 ዓ.ም ተወለዱ። የያኔው ወጣቱ አቶ ተረዳ እንዳሻው የ24 ዓመት አካባቢ ዕድሜ ፤ ልጃገረዲቱ ወይዘሮ የ 14 ዓመት ዕድሜ ላይ እያሉ “ሙሽራዬ…” ተባለላቸው።
እዚያው በተወለዱበት ፣ በአደጉበት በሚያውቁት ከተማ ከወላጆቻቻው ሳይርቁ እዣ ወረዳ ልዩ ስሙ ቆጠር ለተወሰነ ጊዜ ጎጇቸውን ቀልሰው ኖረዋል ፤ ህይወት መስመር አስቀይራቸው አሁን የሚኖሩበት መርካቶ ከመምጣታቸው በፊት ።
ምንም እንኳን በቤተሰብ ትጭጭቱ ቢፈጸምም አቶ ተረዳ እንዳሻው በሚስጥር ወይዘሮ ደመቀችን ለማየት ጥረት አድርገው ከጋብቻ በፊት ሊያይዋቸው ችለዋል። በድብቅም ቢሆን ከቤተሰብ ምርጫ ጋርም የእርሳቸው ፍቃደኝነትና ውዴታም አለበት። በ50ኛ ዓመቱ ክብረ በዓላቸው ላይ እንዳሉት “ባሳለፍናቸው የትዳር ዓመታት ለእኔ ከሆነችው አንጻር ከቀድሞ ይልቅ ከነብሴ ወደድኳት፤ ከእራሴ በላይ እንዳስብላት ሆንኩኝ ያሉት አቶ ተረዳ እንዳሻው ፤ በትዳሩ መጀመሪያ ወቅት እንዳኮረፈ ሰው ሆነው ወይዘሮ ደመቀች ናመጋ ለአንድ ሁለት ቀን ማስቸገራቸውን ጠቁመው ባለቤታቸውን ያሳዩት ትዕግስት አድንቀው ወደፍቅር ሕይወት ማምራታቸውንም ተናግረዋል።
ወይዘሮ ደመቀች ናመጋ እንደ አቶ ተረዳ እንዳሻው ቀድሞ የማየት ዕድል አልገጠማቸውም። ይሁንና “ቤተሰብ የመረጠልኝን አሺ! ብዬ ነው የተቀበልኩት” ያሉን ወይዘሮ ደመቀች ነመጋ ከቤተሰብ ሲለዩ መጨነቅ ማልቀስ ባይቀርላቸውም አቶ ተረዳ እንዳሻው ወደዋቸዋል። ከአዩአቸውና ከአገቧቸው በኋላም ደስ ብለዋቸዋል። “ወግ ነው ሲዳሩ ማልቀስ !” አይደል የሚባለው …
“ሙሽሪት ልመጂ!
ሙሽሪት ልመጂ!
ከእናትሽ ከአባትሽ
ባልሽን ውደጂ! ቢባል ልክ ነው ማለት ነው።
ቁጣ የሰው ልጅ ከሚያሳያቸው ያልተገባ ጠባያትና የስሜት መግለጫ መንገድ አንዱ ነው። የማይቆጣ ሰው ይኖራል ለማለት ያስቸግረኛል። በተለያዩ የማይስማሙ ጉዳዮችና አጋጣሚዎች እንቆጣለን። አንዱ ለሌላው የተሰማውን መጥፎ ስሜት በቁጣ በሃይለ ቃል ይገለጻል።
ቅዱስ መጽሐፍ “ተምዑ ወኢተአብሱ … ተቆጡ ኃጢያትን ግን አታድርጉ !” ይላል። ሰው መቆጣቱ እንደማይቀር አስገንዝቦ “ተቆጡ” አለና “አጢያት ግን አታድርጉ” ብሎ ደግሞ ከቁጣ ወደ ቁጣ ከኃይለ ቃል ወደ ኃይለ ቃል ተግባር መሄድ እንደማይገባ ያስገነዝባል። ወይዘሮ ደመቀች ናመጋ እና አቶ ተረዳ እንዳሻው እንደማንኛው ሰው ይቆጣሉ። ነገር ግን ቁጣቸው ችግር አያስከትልም። አንደኛ እንደ የሃይማኖት ቀኖና እንደገባው ሰው ተቆጥተው መጥፎ ነገር አይሰሩም። ሁለተኛ የሚነጋገሩት በተራ ነው። ወይዘሮ ደመቀች ናመጋ ሲቆጡ አቶ ተረዳ እንዳሻው ቁጣው የሚበርድበትን መልካም ቃል ይናገራሉ። አቶ ተረዳ እንዳሻው ሲቆጡ ወይዘሮ ደመቀች ናመጋ በሰላማዊ ምላሽ ከቁጣቸው ያበርዷቸዋል። ልጃቸው ወይዘሮ ዙሪያሽ ተረዳ “አብረው ሲጨቃጨቁ ወይም ሲቆጡ አላየሁም ፤ አንዳቸው ሲበሳጩ ወይም ሲቆጡ ሌላው ተረጋግቶ ይመልሳል። የሚገርመኝና ትልቁ ስጦታቸው በተራ መናደዳቸው ነው” ትላለች ።
ወይዘሮ ደመቀች ናመጋ እንደሚሉት ህይወት ከባድ ናት ማለፊያ መንገድ ግን አላት ለምሳሌ ንዴትና ቁጣ ሲመጣ ባልና ሚስት በእኩል ሰዓት መናደድ የለባቸውም ፤ አንዱ ሲቆጣ ሌላው ችሎ ንዴቱ ከበረደ በኋላ ለብቻቸው በመሆን መወያየት ነው ያውም ልጆች በሌሉበት ።
ትዳርም ሆነ ኑሮ እንዲሁም ህይወት እንከን አልባ ሆነው አያውቁም የእነወይዘሮ ደመቀች ናመጋ ትዳርም ከዚህ የተለየ አይደለም፤ ሁለቱ ባለትዳሮች የፈተነ፣ ያሳዘነ፣ ያስጨነቀና ፈተና ገጥሟቸው ነበር። ባለቤታቸው አቶ ተረዳ እንዳሻው በደረሰባቸው አደጋ አልጋ ላይ መዋላቸው ነበር። እግራቸው ላይ በደረሰ አደጋ ቤት የዋሉት አቶ ተረዳ እንዳሻው እንደ ቀድሞ ቤተሰብን መምራት ማስተዳደር አቃታቸው፤ታዲያ እነዚህ ፈተናዎች ኑሮና ህይወታቸውን ፣ ትዳርና አንድነታቸውን ፈትኖታል። ሆኖም ባጋጠማቸው ችግር ምክንያት የሚፈታ አንድነት በሰበብ የሚለያይ ህብረት አልነበረምና ሁለቱንም ችግሮች አሳልፈው ለሃምሳኛ ዓመት የትዳር ዘመን ክብር በቅተዋል። የትዳሩ የመጀመሪያ አደጋ ከተከሰተ በኋላ የነበሯቸው ልጆችና የልጅ ልጆች እጥፍ ሆነዋል ።
የትዳር ጣዕምና ደስታ
ከማንኛውም ነገር ሁሉ በላቀ ሁኔታ ደስታን የሚለግስ አንድ ነገር አለ ፤ ምን ይሆን?… በጣም ቀላልና በእጅ የሚገኝ ነው። ይህን ምስጢር ለጨረታ ላቀርበው ብችል ምን ያህል ሰው በጎረፈ! ዋጋውም ምንኛ በናረ! ብልሆች ብቻ ናቸው ምንነቱን የሚገምቱት። አንዳንዶቹ ጤንነት ፣ ወይም ገንዘብ ፣ ወይም ብዙ ወዳጅ ፣ ወይም ይህን ወይ ያን ሀብት ይሉ ይሆናል። ግን ፣ እነዚህ ሁሉ ተሟልተው ደስታ ሙሉ ላይገኝ ይችላል። ዝናና ሥልጣንም ደስታን አያስገኙም። ጤንነት ፣ ገንዘብ ፣ ባልንጀራ ፣ የሞቀ ቤት … ሁሉም አስፈላጊ ቢሆኑም ደስታ አያጎናጽፉምና ከእነዚህ ሁሉ የሚልቅ አንድ ነገር አለ። እርሱም እውነተኛ ባልንጀራ ሰው የጠፋ ዕለት ሰው የሚሆኑ ሰው የደስታህ ምንጭ ብቻ የሚሆን ሸክምህን የሚገባው ሁሌም ለባልንጀራው የሚኖር ሰው የደስታ ምንጭ ነው። ስለዚህም እውነተኛ አጋር ካለ ምንም እንኳን ህይወት በፈተና የተሞላች ብትሆንም እውነተኛ አጋር ካለ ደስታ የጸና ይሆናል።
የአቶ ተረዳ እንዳሻው እና የወይዘሮ ደመቀች ሕይወት ፈተና፣ ኑሮ ችግር እንደማያጣው ለመግለጽ እንጂ የትዳር ጣዕምና ደስታ ከፈተናው ይበልጣል። ትዳር ”መልካም” ነው ካለው ዘርፈ ብዙ ጥቅም አኳያ ሲሆን ብቸኘነት በእምነትም በማህበራዊ ሊቃውንትም ተቀባይነት እንደሌለው ብዙ ማሳያዎች አንዱም ነው። አቶ ተረዳ እንዳሻው እና የወይዘሮ ደመቀች በትዳር ህይወታቸው ከአዘኑበት ይልቅ የተደሰቱበት አያሌ ቀን ነው። ዛሬም ቢሆን ባላቸው ኑሮ በጣም ደስ እያላቸው ነው እንደሚኖሩ ነው የሚናገሩት።
“ከልጅ አልፎ የልጅ ልጅ የሚሰጠው ደግሞ ፍቅር ነው። በቅዱስ ቃሉ ስለተረዳን ይበልጥ ደስ ይለናል” ያሉን አቶ ተረዳ እንዳሻው ናቸው።
የዳቦ ስያሜ
ለሴት ሙሽራ ዳቦ ተቆርሶ ወግ ደርሶ የወንዱ ቤተሰብ የሚጠራበት ስም ይወጣል። ስያሜውም በወርቅ የተደገፈ ነው… አመለወርቅ፣ ዙሪያሽ ወርቅ… የሚልና ጠባዬ ሸጋ ፣ ተግባቢ… እንድትሆን ሙሽሪቷ የሚመኝ ነው። የወይዘሮ ደመቀች የዳቦ ስም ማን እደሆነ የነገረኝ የለም። አንድም ከዳቦ ጋር ተረስቷል። የትዳር አጋራቸው ያወጡላቸውን ስም ግን ራሳቸው የአቶ ተረዳ እንዳሻው ልጆች ነግረውኛል። ወንድ ልጃቸው ብሩክ “እናቴነሽ ፣ መከታዬ” ሲባባሉ እንደሰማ ይነገራል። አቶ ተረዳ እንዳሻው ማን ብለው ባለቤታቸውን እንደሚጠሩ በጠየኳቸው ጊዜ ከፈገግታ ጋር “እኔ የምላት እናቴነሽ፣ መድሐኒቴ፣ ጓደኛዬ…ነው የምላት” ብቻ ምን አለፋችሁ በአንዴ ሺውን ነው የዘረገፉት …እንዴት ይህ ሁሉ ጠየኳቸው ያሳየችኝ ብዙ ፍቅር እና መራራት ነዋ! አጥፊቼም የምታልፈኝ በምክር ነው።
ልጆች ምን ቀሰሙ
ከአቶ ተረዳ እንዳሻው እና ከወይዘሮ ደመቀች ናመጋ በ50 ዓመት የትዳር ዘመናቸው አምስት ሴት፣ አምስት ወንድ ልጆች የወለዱ ሲሆን አስሩንም ልጆቻቸውን በመዳር አስራ አንድ ወንድ የልጅ ልጆች እና ሃያ አንድ ሴት የልጅ ልጆች በማግኘት በአጠቃላይ አርባ ሁለት ልጅ እና የልጅ ልጆችን አይተዋል።
የ50 ዓመት የጋብቻ የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል የምስጋና ፕሮግራም መሪ ከሆኑት መካከል ልጃቸው ገነት ተረዳ ከእናቷ እና ከአባቷ ቤተሰባዊ፣ ማህበረሰባዊ ክብርና ፍቅርን ቀስማለች። የትዳርንና የቤተሰብን ክብር አውቃለች፤ በተለይ ትላለች እናቴ አባቴ በደከመበት ጉዳት ባጋጠው ወቅት ለወንድ እንኳ አስቸጋሪ የሆኑ ስራዎችን ቀጥ አድርጋ በመምራት የሴት ልጅን ጥንካሬ አሳይታኛለች። የሚገርመኝ ነገር የምትለው ገነት እናቴ አሁን ያሉት ሴት ወጣት ያገቡም ለማገባትም በዝግጅት ላይ የሚገኙ እውነተኛ ረዳትን ምን ዓይነት እንደሆነ የሚማሩባት ጀግና ሴት ናት ብላለች። በዚህም ምክንያት ለሴት ልጅ በተለይ ለእናቶች ክብር ሊሰጥ ይገባል ትላለች ።
ሌላኛዋ ሴት ልጅ ዙሪያሽ ተረዳ የእናቷን እና የአባቷን ሽምግልናና የሽምግልና ምልክት የሆነውን ሽበት በልዩ ክብር እንደምታየው ትናገራለች። ዙሪያሽ ትናገራለች “ሽበት የማህበረሰብ ጠበቃና ጠባቂ አሳዳጊ እና አስታራቂ ነው። በእናት እና በአባት ህብረት ፍቅር እና እንክብካቤ ያደጉ የልጅ ልጆች የተረጋጉ ምድርንም የሚያረጋጉ ይሆናሉ። አባቴ እና እናቴ ይህንን አስተምረውኛል” ።
ሌላኛዋ የወይዘሮ ደመቀች ናመጋ እና የአቶ ተረዳ እንዳሻው የበኩር ልጅ አቶ ደምስ ተረዳ እንዳሉት “በየትኛውም የዕድሜ ክልል ይገኝ ልጅ ለወላጆቹ ልጅ ነው፤ ይህ ደግሞ ወላጆቼ በራሴ ህይወት እንዳየው አድርገውኛል።” ወይዘሮ….. “እግዚያበሔር እንዲህ ያሉ አባት እና እናት ስለሰጠኝ አመሰግናቸዋለው፤ ህይወታቸውን ለእኛ ሲሰጡ፣ ሲያስተምሩ፣ ሲያለብሱ፣ ሲመግቡን ኖረዋል ፤ ያለአንዳች ስስት ለዚያውም የተለያየ የህይወት ፈተናን እየተጋፈጡ፤ ታዲያ ይህ ፍቅር ዛሬም ያው ነው ከእኛ አልፈው ለልጅ ልጆቻችን ያስባሉ” ብለዋል።
አቶ ተረዳ እንዳሻው እና ወይዘሮ ደመቀች ናመጋ ለጋብቻ ሲተጫጩም ሆነ ሲጋቡ በቤተሰብ ፍቃድ ነው፤ ይሁን እንጂ ልጆቻቻው በራሳቸው ፈቃድ ያመጣቸውን “እኛም ወደናል ይሁን (ትሁን)” ብለው ነው የሚድሩት የሚኩሉት። እኛ አናጭም በእኛ ዘመን እንደነበረው ይሁን አንልም። ሁለቱ ተጋቢዎች ተሳስበው ለጋብቻ ወስነው ሲመጡ እኛም እንቀበላለን” ነው ያሉኝ።
በበዓሉ ወቅት አቶ ተረዳ እንዳሻው እና የወይዘሮ ደመቀች ረጅሙን የትዳር እና የህይወት ጉዞ በተለያዩ ጨዋታዎች እያዋዛ ያቀረበው በቤተሰቡ እንደ አማች ሳይሆን ከልጆቻቸው እንደ አንዱ የሚታየው አቶ ይርዳው ፎሌ እነዚህ ጥንዶች በሃይማኖትም በመጠበቅም ሆነ በማህበራዊ ህይወት ምሳሌ እንደሆኑ ጠቅሶ የረጅም ጋብቻ ሚስጥር ሁለቱም ባለትዳሮች እርስ በራሳቸው የሚያሳዩት ደግነት እና የስሜት እንክብካቤ ናቸው። ታዲያ እነዚህ የህይወት አጋሮች ይመካከራሉ ይወቃቀሳሉ ያለአንዳች ሶስተኛ ወገን ማለቴ ነው በተጨማሪም በባለ ትዳሮች መሃከል ያለ የምስጋና ስሜት እጅግ አስገራሚ ነው። ባል እና ሚስት በዚህ ልክ ሲመሰጋገን ስታይ ትገረማለህ፤ በትዳር አጋራቸው የሚመሰገኑ እና የሚሞገሱ ሰዎች ለትዳራቸው ይበልጥ ታማኞች እና ለህይወት መልካም አስተሳሰብ ስላላቸው እንደሆነም ይናገራሉ።
በመጨረሻም አቶ ይርዳው “በረጅሙ የ50 ዓመት ትዳራቸው ለትውልዱ ምሳሌ የሚሆን ነው ፤ ለእኛም ለልጅ ልጆቻችንም አርአያ ሆነዋል። ረጅም ዕድሜና ጤና ይስጥልኝ !”ብለዋል።
ምክር ለወጣቶች
በእያንዳንዱ የዕድሜ ክልል ጥንካሬዎችና መልካም ዕድሎች ይኖራሉ። በልጅነት ወቅት ያለው በወጣትነት ጊዜ እንዲሁም በወጣትነት ጊዜ ያለው በጎልማሳነት ጊዜ አይኖርም። በተገቢው ዕድሜ መሰራት የሚገባውን ስራ መስራት ለቀሪው ዕድሜ ብዙ የቤት ስራዎችን ላለማጠራቀም ይረዳል። በመሠረተ ሃሳብ ወንዶችና ሴቶች 18 ዓመት ዕድሜ ከሞላቸው ማግባት ይችላሉ፤ ነገር ግን በብዙ ነገር ዝግጁ የሚሆኑት በ20ዎቹ አጋማሽ አካባቢ ነው። ስለዚህ ከታች ያሉም በዚህ ወቅት ለማግባት፣ እዚህ የደረሱ ደግሞ እርምጃ ለመውሰድ መንቀሳቀስ ጠቃሚ ነው።
አሁን የ50 ዓመት የትዳር አጋሮች ይናገራሉ በዕድሜ በመብሰልና በጋብቻ ግንኙነት እርካታና ዘላቂነት መካከል ቁርኝት ስላለ፣ ቶሎ በለጋ ዕድሜ ወደ ጋብቻ ከመግባት መቆጠብ ያስፈልጋል። የለጋ የወጣትነት ዕድሜን በትምህርት፣ በኢኮኖሚ፣ በህይወት ክህሎትና በማኅበራዊ ግንኙነት ራስን ለማብቃትና ለማስቻል በትጋት መሥራት ይገባል። እነዚህን በሚገባ መስራት ለዘላቂ ጋብቻና ቤተሰብ መልካም መሠረትን ይጥላል።
እስካሁን ድረስ በተለያዩ ምክንያቶች ተገቢ በሚባለው ዕድሜ ወደ ጋብቻ ያልገቡ ደግሞ ጊዜው እንዳለፈባቸው በማሰብ ሊጎዳቸው የሚችል ውሳኔ ከማድረግ መቆጠብ ይኖርባቸዋል። በዓውዳቸው ያሉትን መልካም ዕድሎችን ተጠቅመው የትዳር ጓደኛ ምርጫ በማድረግ ወደ ጋብቻ መግባት ይችላሉ። ሰዎች ያለፈውን ዘመን እያሰቡ ከሚጸጸቱ፣ በፊታቸው ያለውን ቀሪውን ዘመናቸውን በመልካም ሁኔታ እንዴት መኖር እንደሚችሉ ቢያስቡና ቢያቅዱ ፍሬያማ ህይወት መኖር ይችላሉ።
ወጣቶችና ለጋ ጎልማሶች በተገቢው ጊዜ ወደ ጋብቻ ለመግባት ተግዳሮት የሆነባቸው ነገር ካለ ደግሞ ከቤተሰቦቻቸው፣ ከወዳጆቻቸውና ከመንፈሳዊ አገልጋዮች ጋር መነጋገር ይችላሉ። በእነዚህ አካላት ተገቢውን ድጋፍ ካላገኙ ወይም ከእነዚህ ውጭ ሌላ አማራጭ ከፈለጉ የሠለጠኑ አማካሪዎችን ቢያማክሩ ጠቃሚ አማራጮችን ያገኛሉ።
በተገቢ ዕድሜ ማግባት ከተጋቢዎቹ የግል የህይወት ደስታ በላይ ትውልድን ከመቅረጽም አንጻር አዎንታዊ ሚና አለው። ዕድሜያቸው ሳይገፋ የሚጋቡ ወንዶችና ሴቶች ጤናማ ልጆችን የመውለድ እንዲሁም ከልጆቻቸው ጋር መልካም ግንኙነት ለማድረግና ልጆቻቸውንም በጥሩ ሁኔታ ፍቅርና እንክብካቤ ለማሳደግ አቅም ይኖራቸዋል። ልጆችን ለማሳደግ የኢኮኖሚ አቅም መኖር ብቻ መታሰብ የለበትም። ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር መልካም የፍቅር ግንኙነትን ይፈልጋሉ። ሰላም!
አዲስ ዘመን ጥር 10/2012
አብርሃም ተወልደ