. የአቅመ ደካሞችን ቤት አጽድተዋል፤ የጽዳት እቃ አበርክተዋል
አዲስ አበባ፡- በአዲስ ዓመት መባቻ በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አማካኝነት ተጀምሮ በአገር አቀፍ የተካሄደውን «የአዲስ ዓመት ስጦታ ለእናት አገሬ» መርሀ ግብር በማስቀጠል፤ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሠራተኞችና አመራሮች ከደመወዛቸው በማዋጣት ለአቅመ ደካሞች የገና በዓል ስጦታ አበረከቱ።
ትናንት የድርጅቱ ሠራተኞችና አመራሮች ለአዲስ ዓመት የበዓል ስጦታ ያበረከቱላቸውን አምስት አቅመ ደካሞች ዳግም የጎበኙ ሲሆን፤ ለሁሉም ቤተሰብ ለበዓሉ የሚያስፈልገውን ቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ «እንኳን አደረሳችሁ» ሲሉ ቤተሰቡን ጎብኝተዋል።
ስጦታው የተበረከተላቸው ቤተሰቦችም የድርጅቱ ሠራተኞች በወረት ለአንድ ጊዜ ብቻ ጎብኝተው ሳይቀሩ ዳግም አስታውሰው ስለጎበኟቸው መደሰታቸውን ስጦታውን ላበረከቱ የድርጅቱ ሠራተኞችና የሥራ ኃላፊዎች ገልጸዋል።
በአራዳ ክፍለ ከተማ በተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙት አምስቱ ቤተሰቦች በተበረከተላቸው ስጦታ ለተቋሙ ሠራተኞችና የሥራ ኃላፊዎች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የተቋሙ ሠራተኞችና አመራሮች በአዲስ ዓመት ስጦታ ካበረከቱላቸው ቤተሰቦች መካከልም አንደኛዋ እናት በወቅቱ በተደረገላቸው የገንዘብ ድጋፍ አስፈላጊውን ሁሉ ግብአት ገዝተው በጎረቤቶቻቸው የጉልበት ድጋፍ ቤታቸውን አድሰው መጨረሳቸውን በእለቱ ሊጠይቋቸው ለሄዱ ሠራተኞችና አመራሮች ተናግረዋል፤ አስጎብኝተዋልም። በታላቅ ደስታ ውስጥ ሆነውም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የእኝሁ ቤተሰብ ጎረቤቶችም እንደተናገሩት፤ ለአዲስ ዓመት በተቋሙ ሠራተኞች በተደረገው ድጋፍ የአቅመ ደካማዋ ቤት በመታደሱና በዓልን እንደተቀሩት ጎረቤቶቻቸው አክብረው በመዋላቸው ተደስተው ሳይጨርሱ አሁንም ዳግም ስጦታ ማበርከታቸው ለሠራተኞቹ ትልቅ አክብሮት አለን ብለዋል።
ከዚሁ የበዓል ስጦታ ጋር በተያያዘ የድርጅቱ ሠራተኞች ከአምስቱ ቤተሰብ መካከል ሰሞኑን ወደ አቅመ ደካሞች ቤት በማቅናት ቤታቸውንና ልብሶቻቸውን አጽድተዋል፤ የጽዳት መሳሪያዎችንም አበርክተዋል።
የተቋሙ ሠራተኞች በበኩላቸው፤ ይህ ድጋፍ መደረጉ እንዳስደሰታቸው ገልጸው፤ በቀጣይም የዚህ አይነቱን በጎ ተግባር አጠናክረው እንደሚገፉበት ነው ያስታወቁት።
የመርሀ ግብሩ አስተባባሪ ኮሚቴ አባል የሆኑት ወ/ሮ ብርሀኔ ደመቀ እንደተናገሩት፤ ይህ የተቋሙ የስጦታ መርሀ ግብር ሠራተኛውና አመራሩ ያለማንም ቅስቀሳ ያደረገውና ለሌሎች ተቋማትም ምሳሌ ሊሆን የሚችል ነው። ሠራተኛው ገንዘቡን፣ ጉልበቱን ሳይሰስት ለአቅመ ደካሞች ያደረገው እገዛ ከማንም በላይ እርካታው የራሱ የሠራተኛው ነው።
የተደረገውን ድጋፍ በማስመልከት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌትነት ታደሰ፤ ይህ ድጋፍ «የአዲስ ዓመት ስጦታ ለእናት አገሬ» የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ መርሀ ግብር ቀጣይ አካል በመሆኑ ወደፊትም ተጠናክሮ በቋሚነት የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል።
እንደ ዋና ሥራ አስኪያጁ ገለጻ የድርጅቱ ሠራተኞችና አመራሩ በዚህ አይነቱ በጎ ተግባር አንድ ሆነው መሳተፋቸው በተለይም ለተቋሙ ትልቅ ክብር ነው። ድጋፉ በአጠቃላይ ሲታይ ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ አርአያነት በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው መርሀ ግብር የአንድ ሰሞኑን ድጋፍ ሆኖ እንዳይቀር እንደ ሚዲያ ተቋም የሚያስተላልፈው ትልቅ መልዕክት አለው።
በመጨረሻም ሥራ አስኪያጁ፤ በየተቋሙ ያለው አመራርና ሠራተኛ ከዚህ ቀደም ለአዲስ ዓመት ድጋፍ ያደረጉላቸውን ቤተሰቦች መለስ ብለው መጎብኘት ቢችሉ መልካም ስለሆነ ያንን ያደርጉ ዘንድ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 28/2011
በበጋዜጣው ሪፖርተር