ውልደታቸውና እድገታቸው ደሴ ነው። ለቤተሰባቸው የመጀመሪያ ልጅ ናቸው። በቤተሳባቸው ውስጥ በተለይም አባታቸው ወደ ንግዱ ዘርፍ ማዘንበላቸው እርሳቸውንም ወደዚሁ የህይወት አቅጣጫ መርቷቸዋል። የአባታቸው በከተማ ግብርና ላይ አተኩሮ መስራት ደግሞ በምግብ ማቀነባበር ንግድ እንዲሰማሩ ይበልጥ በር ከፍቶላቸዋል።
በኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬት /ኢ ቢ ሲ/ አማካኝነት በሃገር አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ግዜ በተዘጋጀው የንግድ ስራ ተሰጥኦ ውድድር ቀርበው ከመጨረሻዎቹ አርባ ተዋዳዳሪዎች ውስጥ አንዷ ለመሆን በቅተዋል። በግዜው ያቀረቡት የንግድ ሃሳብ ተቀባይነት በማግኘቱ ከመንግስት የተመቻቸላቸውን የቦታና የብድር ድጋፍ በመጠቀም የራሳቸውን የምግብ ማቀነባበሪያ በመክፈት ስኬታማ ነጋዴ ለመሆን በቅተዋል።
የዛሬዋ እንግዳችን ወይዘሮ ማህደር አድማሱ ይባላሉ። የተወለዱት ደሴ በ1977 ዓ.ም ሲሆን የመጀሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በዳውዶ ካቶሊክ የመጀመሪጃ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እስከ አስረኛ ክፍል በሆጤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። በወቅቱ ወደ መሰናዶ ትምህርት የሚያስገባቸው ነጥብ ስላልመጣላቸው ከአስረኛ ክፍል በኋላ በወይዘሮ ስህን የቴክኒክና ሞያ ትምህርት ቤት ገብተው በሌቭል ሁለት የፐርቼዚንግና ሰፕላይስ ማኔጅመንት ትምህርታቸውን ለሁለት አመታት ተከታትለው ተመርቀዋል።
በ1997 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከአፍሪካ ቤዛ ኮሌጅ በማርኬቲንግ ማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ በ1996 ዓ.ም ከትዳር አጋራቸውና የጋራጅ ባለቤት ከሆኑት ባለቤታቸው የመጀመሪያ ልጃቸውን በመውለዳቸው ለሁለት አመታት ያህል ስራም ሳይሰሩ ትምህርትም ሳይማሩ ይቆያሉ፤ ተጨማሪ ልጅም ይወልዳሉ። ከሁለት አመት በኋላም ልጆቻቸውን እያሳደጉ በዚሁ የትምህርት ዘርፍ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ተምረው አጠናቀዋል።
በባህሪያቸው አንድ ቦታ ላይ መቀመጥና ተቀጥሮ መስራት የማይዋጥላቸው ወይዘሮ ማህደር ተቀጥሮ ከመስራት ይልቅ የራሳቸውን የንግድ ስራ መስራትን ሁሌም ያልማሉ። እንደው ተቀጥረው የመስራቱ እድል እንኳን ቢገጥማቸው የታዘዙትን ስራ ብቻ ሰርተው ከማቆም ይልቅ ተጨማሪ ሃሳቦችን በማፍለቅ ስራን ማጎልበትና ማሻሻል ይወዳሉ።
የማስተርስ ዲግሪያቸውን መመረቂያ ፅሁፍ ለማዘጋጀት በኢንተርፕርነርሺፕ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የገቡ ሲሆን በነበራቸው የስድስት ወር ቆይታ በዩኒቨርሲ ቲው የነበረውን የስራ አካባቢ በሚገባ ለመቃኘት ችለዋል። ለእርሳቸው የሚስማማው ቦታ በዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ የአስተዳደር እርከን ላይ መሆን እንጂ እታች ሆኖ እየታዘዙ መስራቱ እንደማይስማማቸውም ለመረዳት በቅተዋል። በዚህ ወቅትም ወደራሳቸው ቢዝነስ እስኪመጡ ድረስ አቋማቸው በምንም መልኩ አለወጡም።
የአባታቸው በሆቴልና ከተማ ግብርና በተለይም ወተትና ማር ንግድ መሳተፍ ወደ ንግዱ ህይወት እንዲገቡ የራሱን አስተዋፅኦ ያበረከተላቸው ቢሆንም ከልጅነታቸው ጀምሮ ምግብ ሲሰሩም ሆነ ሲመገቡም እምብዛም ባለሙያ ባይሆኑም ምግብ ወደ ቢዝነስ ሃሳብ ቢቀየርና በተሻለ መልኩ ለገበያ ቢቀርብ ትርፍ ሊያስገኝ ይችላል የሚል ሃሳብ ዘወትር በአእምሯቸው ውስጥ ይመላለስ ነበር።
ከባለቤታቸው ጋር በመሆን በአዲስ አበባ ኑሯቸውን ከጀመሩ በኋላ በወቅቱ የማስትሬት ዲግሪ ትምህርታቸውን ተከታትለው ሲመለሱ ወደቤታቸው ገዝተው የሚገቡት እንጀራ ባያጡም ወጥ ግን ልክ እንደእንጀራ ሁሉ በቀላሉ በግዢ ሊገኝ ስለማይችል የግድ ወጥ ሰርተው እርሳቸውን፣ ባለቤታቸውንና ልጆቻቸውን መመገብ ነበረባቸው። እንጀራ ከገዙ በኋላ ወጥ ለመስራት የሚፈጀውን ግዜና የሚወጣውን ጉልበት የተረዱት ወይዘሮ ማህደር፤ ልክ እንደ እንጀራ ሁሉ ወጥም ተዘጋጅቶ ለገበያ መቅረብ ይችላል የሚል የንግድ ሃሳብ ድንገት ብልጭ ይልላቸዋል።
በ2004 ዓ.ም ለመጀመሪያ ግዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተዘጋጀው የንግድ ተሰጥኦ ውድድር ደግሞ ይህን የንግድ ሃሳባቸውን ለባለሞያዎች ለማጋራት መልካም አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል። በውድድር ከቀረቡ ስድስት መቶ ሰባ ከሚጠጉ ተወዳዳሪዎች መካከልም ባቀረቡት አዲስ የንግድ ሃሳብ ከምርጥ አርባዎቹ ዝርዝር ውስጥ ለመግባት ችለዋል። ከውድድሩ በኋላም ከመንግስት ባገኙት ብድርና የቦታ ድጋፍ ኮተቤ መብራት ሃይል ኮንዶሚኒየም ፊትለፊት በሚገኘው የመንግስት ሼድ ውስጥ ወጥ አዘጋጅተው በማሸግ ለገበያ ማቅረብ ይጀምራሉ።
በወቅቱ የታሸጉ ወጦችን ለገበያ ማቅረብ እምብዛም ያለተለመደና አዲስ የንግድ ሃሳብ በመሆኑ በተጠቃሚዎች ዘንድ ምርታቸው ተቀባይነትን አላገኘም። በበርበሬ ውስጥ የተለያዩ ባዕድ ነገሮችን ቀላቅሎ የመሸጥ ዝንባሌም በየግዜው ይታይ የነበረ በመሆኑ ህብረተሰቡ የታሸገ ወጥን አምኖ የሚገዛበት ደረጃ ላይ አልደረሰም። የታሸገ ወጥን ገዝቶ ከመጠቀም ይልቅ ሰርቶ የመመገብ ፍላጎትም ይታይ ነበር።
ከተጠቃሚው የነበረው ምላሽ በወቅቱ ተስፋ አስቆራጭ የነበረ ቢሆንም በመንግስት በኩል ሲደረግ የነበረው ድጋፍ ባለመቋረጡና እርሳቸውም ምርታቸውን ለማስተዋወቅ ጠንክረው በመስራታቸው የንግድ ሃሳባቸውን በማስቀጠል እንዲታወቅ አድርገዋል። ከሁለትና ከሶስት አመታት በኋላም በተለይ ውጪ ሀገር ቆይተው የመጡ ሰዎች ምርቱን እየለመዱ በመምጣታቸው ገበያው እየተሻሻለላቸው እንደመጣ ይናገራሉ።
እንዲህ አይነቱን የንግድ ሃሳብ ካፈለቁ በኋላ ወጥ አሽጎ የመሸጡን ሃሳብ ባለቤታቸው ሲሰሙ ብዙም አልደገፏቸውም ነበር። ለዚህም ያቀረቡት ምክንያት እስከ ማስተርስ የዘለቀው ትምህርታቸው ቦታው ይህ ነው ወይ? የሚል እንደነበር ያስታውሳሉ። ይሁንና ውሎ እያደር የንግድ ሃሳባቸው በትክክለኛው በመስመር መጓዝ ሲጀምርና እርሳቸውም ዳግም ወደሌላ ዘርፍ እንደማይመለሱ ሲረዱ ባለቤታቸው ማበረታታትና መደገፍ እንደጀመሩም ይገልፃሉ።
አሽገው ለገበያ የሚያቀርቡት ወጥ በደምብ እየተሸጠ አለመሆኑን የተረዱት ወይዘሮ ማህደር ተጨማሪ የባልትና ምርቶችን ፣ ባህላዊ መጠጦችንና ልዩ ልዩ ምግቦችን አዘጋጅተው ለገበያ በማቅረብ ንግዳቸውን ማስፋፋት ይጀምራሉ። በዚህ ሂደት ያሰቡትን ያህል ትርፍ ባያገኙም ትርፉን ወደፊት እደርስበታለሁ በሚል ተስፋ የቀጠሯቸውን ሰራተኞች ይዘው ንግዱን ቀጠሉ። ቢሂደትም የገጠማቸውን ውጣውረድ ለመቋቋም ችለዋል። በአሁኑ ወቅትም ገበያቸው ተሻሽሎ የህብረተሰቡ የመግዛት ፍላጎት እየጨመረ መጥቷል።
የምግብ ማቀነባበሪያ ንግዳቸውን ቀስ በቀስ እያስፋፉ የመጡት ወይዘሮ ማህደር በአሁኑ ወቅት ልዩ ልዩ የባልትና ውጤቶችን፣ እንጀራ፣ ጠጅ፣ ጠላና መውደድ /ከአልኮል ነፃ ባህላዊ መጠጥ/ ለገበያ ያቀርባሉ። የትዕዛዝና የአገልግል ምግቦችንም አዘጋጅተው ለተጠቃሚዎች እንካችሁ ይላሉ። በዋጋ ደረጃም ምርቶቻቸው ከሌሎች ተወዳዳሪ የምግብ አቀናባሪዎች ብዙም እንድማይራራቅ ይናገራሉ። ለአብነትም ምጥን ሽሮ በኪሎ አንድ መቶ ብር፣ የሽምብራ ሽሮ አንድ መቶ ሃያ ብር፣ ሚጥሚጣ አንድ መቶ ሃያ ብር፣ በርበሬ አንድ መቶ ሃምሳ ብር እንዲሁም ምስር አራት መቶ ብር ይሸጣሉ። ተዘጋጅቶ የታሸገ ሙሉ ዶሮ ወጥ በስምንት መቶ ብር፣ አንድ እንጀራ ስምንት ብር እና ስጋ በኪሎ አራት መቶ ብር ይሸጣሉ።
ባህላዊ መጠጦችን በሚመለከትም ጠጅ በሊትር አንድ መቶ አርባ ብር፣ ጠላና መውደድ ሰላሳ ብር ይሸጣሉ። የምርቶቻቸው ዋነኛ ተጠቃሚዎች ግለሰቦችና ሆቴሎች ሲሆኑ ለሆቴሎች በመኪና በመታገዝ ምርቶቹን ያቀርባሉ። በቀጣይም በተለይ የባልትና ምርቶቻቸውን በዩኒቨርሲቲዎችም ጭምር ተደራሽ ለማድረግ ግብ አስቀምጠው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። ምርቱ በተጠቃሚዎች ዘንድ ተቀባይነትን እያገኘም መጥቶላቸዋል።
ምርቶቻቸውን ኮተቤ መብራት ሃይል ኮንዶሚኒየም ፊትለፊት በሚገኘው የመስሪያ ቦታና ቦሌ ቡልቡላ አካባቢ ባለው ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት የሚያዘጋጁ ሲሆን ከመቁላት ጀምሮ ያለውን ሂደት በኮተቤ ቅርንጫፍ ያከናውናሉ። የተቆሉ የባልትና እህሎችን በራሳቸው ወፍጮዎች የሚፈጩ ሲሆን ወፍጮዎቹን በማዘጋጀት ሂደት ባለቤታቸው ትልቅ እገዛ እንዳደረጉላቸው ይገልፃሉ።
የምግብ ማቀነባበሪያቸው ስራውን ሲጀምር የነበረው ካፒታል እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም በሂደት ትርፋቸውን እያሳደጉ በመምጣታቸው በአሁኑ ወቅት የካፒታል መጠናቸውን ወደ 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር አሳድገዋል። ለሰራተኞች ከሚከፈል ክፍያና ለጥሬ እቃ ግዢ ከሚወጣው ወጪ የሚተርፈውን ገንዘብ ለተጨማሪ ማስፋፊያ መጠቀማቸው ደግሞ የካፒታል መጠናቸውን ለማሳደግ በእጅጉ ረድቷቸዋል። ከእያንዳንዱ ምርት የሚገኘው ትርፍ ከሰባት አስከ አስር በመቶ ሲሆን በአመትም እስከ 300 ሺ ብር እያተረፉ ይገኛሉ። ቀደም ሲል በተለያዩ ግዜያት ከመንግስት የተበደሩትን ከሁለት ሚሊየን ብር በላይ ለመመለስ በቅተዋል። ማቀነባበሪያው በአሁኑ ወቅት ለአስራ ሰባት ሰራተኞች የስራ እድል የፈጠረ ሲሆን ለሰራተኞቻቸው ከአንድ ሺ አምስት መቶ አስከ ሶስት ሺ ስድስት መቶ ብር ይከፍላሉ።
‹‹ንግድ ለህበረተሰቡ በማሰብ ከተሰራ ጤናማ ነው›› የሚሉት ወይዘሮ ማህደር ንግድን ለለመደ ሰው ሌላ ስራ ቢሰጡት እንደማይስማማው ሁሉ እርሳቸውም ከንግድ ውጪ ሌላ ስራ እንደማይሆንላቸው ደጋግመው ይናገራሉ። ንግድ በርካታ ልምድ የሚገኝበት፣ አእምሮንም ለማስፋት የሚያስችልና በአግባቡ ከተሰራበት ህብረተሰቡንም ራስንም መጥቀም የሚቻልበት ዘርፍ እንደሆነም ይገልፃሉ። ያዛኑ ያህል ንግድ ባልሆነ መንገድ ጥቅም ላይ የሚውል ከሆነ ጉዳቱ ለነጋዴውም ለሸማቹ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
ወይዘሮ ማህደር ከትንሽ ካፒታል በመነሳት የምግብ ማቀናባበሪያቸውን እዚህ ያደረሱት ቢሆንም ነጋዴ አያርፍምና አሁን የጀመሩትን የምግብ ማቀነባበር ስራ በማስፋፋት አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ምግብ የማምረት ውጥን ይዘዋል። ስልጠናና የልምድ ተሞክሮ ለመውሰድ በሄዱባቸው ሀገራት የተመለከቷቸው ነገሮች ደግሞ ይህን ጉዳይ በደምብ እንዲያጤኑት አድርጓቸዋል።
በኢትየጵያ በርካታና የተለያዩ ምግቦች ያሉ ቢሆንም የጥራት፣ የምዝገባና የአስተሻሸግ ችግሮች እንዳሉባቸው የሚጠቅሱት ወይዘሮ ማህደር፤ ከዚህ አኳያ በተለይ የቦታ ድጋፍ ከመንግስት ቢያገኙ በምግብ ዙሪያ ሰፊ ስራዎችን በመስራት የተመዘገቡና እውቅና ያላቸው ምግቦችን ለተጠቃሚዎች የማቅረብ ፍላጎት እንዳላቸው ይገልፃሉ። የመንግስት ድጋፍ የተሟላ ከሆነ የምግብ አምራቾችም ህብረተሰቡ የተሻለ ምርት በተሻለ ዋጋ የሚያገኝበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሚኖርባቸው ይጠቁማሉ።
ለትርፍ ብቻ መሯሯጥ ተገቢ እንዳልሆነም የሚናገሩት ወይዘሮ ማህደር፤ ‹‹ምግብ ለሁሉም›› በሚለው ፕሮጀክታቸው በቂ ምግብ ማግኘት ለማይችሉ አንድ መቶ የህብረተሰብ ክፍሎች በየወሩ ምግብ እያደሉ ሲሆን የምግብ ማቀነባበሪያቸውን ማሳደግ የሚችሉ ከሆነ ከዚህም በላይ ድጋፍን ማጠናከር እንደሚፈልጉ ይገልፃሉ። ይህንንም ማድረግ የሚቻለው ፕሮጀክቱን ሰዎች ሲደግፉትና በመተባበር መስራት ሲቻል መሆኑን ይጠቁማሉ። እስከዛው ድረስ ግን በተቻላቸው አቅም በቂ ምግብ ማግኘት ለማይችሉ ሰዎች ምግብ የማቅረብ ተግባራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ይናገራሉ።
ልክ እንደእርሳቸው ሁሉ በምግብ ማቀነባበር ዘርፍም ይሁን በሌሎች የንግድ አይነቶች ለሚሳተፉ ሰዎች ንግዳቸውን ሲጀምሩ ከልጅ ልጅ ሊተላለፍ የሚችል፣ ዘላቂና ህብረተሰቡን የሚጠቅም ሊሆን እንደሚገባ ያሳስባሉ። ከንግድ ትርፍ ሊገኝ የሚችለው በሂደት ነውና ሰዎች የጀመሩት የንግድ አይነት ባልተገባ አቅጣጫ እየሄደ ከሆነ ወዲያውኑ ግንዛቤ በመውሰድ ጥንቃቄ ሊወስዱ እንደሚገባም ይመክራሉ። ንግዳቸው ስኬታማ እንዲሆንላቸውም በቅድሚያ በፈለጉትና በወደዱት የንግድ ዘርፍ ላይ ብቻ መሰማራት እንደሚገባቸውም ምክራቸውን ይለግሳሉ።
ወይዘሮ ማህደር ከአነስተኛ ንግድ ተነስተው ከፍ ወዳለው ንግድ ለመድረስ የበቁ መሆናቸው በተለይ በንግዱ አለም መሰማራት ለሚፈልጉ ሁሉ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥና ሌሎችንም የሚያነሳሳ በመሆኑ ሌሎችም የእርሳቸውን አርአያ በመከተል ቢንቀሳቀሱ በንግዱ አለም ስኬታማ ሊሆኑ ይችላሉ በማለት ፅሁፋችንን እዚህ ላይ እንደመድማለን። ለእርሳቸውም መልካም የጥረትና የስኬት ግዜ እንዲሆንላቸው እንመኛለን። ሰላም!!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 9/2012
አስናቀ ፀጋዬ