አዲስ አበባ፦ የሰውን ልጅ ሕይወት እየቀጠፈና ንብረት እያወደመ የሚገኘውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ ትኩረት እንዲደረግ ጥናቶች አመለከቱ፡፡ ጥናቶቹ በዘርፉ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርጉ ትራንስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
ትናንት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ልማት ኮሚሽን (UNECA) አስተባባሪነት በኢትዮጵያ መንገድ ደህንነት አጠቃላይ ሁኔታ ላይ የዳሰሳ ጥናት ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ጌቱ ሰኚ፤ ገንዘብ መመደብ፣ የተጠናከረ የአደጋ መረጃ ምዝገባ ስርዓት መዘርጋት፣ ለመንገድ ደህንነት ቅድሚያ መስጠትና መሰረተ ልማት መዘርጋት ይገባል ብለዋል፡፡
የሰውን ልጅ ሕይወት እየቀጠፈና ንብረት እያወደመ የሚገኘውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ ርብርብ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸው እ.ኤ.አ ከ 2007 እስከ 2018 መረጃ በመውሰድ ያለውን ሁኔታ የገመገመው ጥናት የትራፊክ አደጋ ከዓመት ዓመት እየጨመረ በርካታ ሰዎችን እየገደለ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡
እ.ኤ.አ በ2007 በትራፊክ አደጋ ተመዝግቦ የነበረው 2 ሺ 100 የሞት አደጋ እ.ኤ.አ በ2017 ከአምስት ሺ በላይ መድረሱን የተጠናውን ጥናት ዋቢ በማድረግ አመልክተዋል፡፡ ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘውን መረጃ መሰረት አድርገው እንደገለጹትም፤ አብዛኛው አደጋ የሚደርሰው አስፋልት መንገድ ላይ ሲሆን፤ አብዛኞቹ ተጎጂዎችም ተሳፋሪዎች ናቸው፡፡ በአንድ የተሽከርካሪ አደጋ 27፣ 22 እና 18 ሰዎች ይሞታሉ፡፡ አዝማሚያው የተሽከርካሪ ፍጥነት መኖሩን ያሳያል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
እ.ኤ.አ ከ2016 እስከ 2018 የሶስት ዓመታት መረጃ የዳሰሰው ጥናት እንዳመለከተውም በአማካኝ በዓመት አራት ሺ 732 ሰው በትራፊክ አደጋ ይሞታል:: ይህ ማለትም በቀን 13 ሰው በየሁለት ሰዓቱም አንድ ሰው ይሞታል ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡ አደጋው በአብዛኛው የሚያተኩረው ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች እና አዲስ አበባ ከተማ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
አብዛኛው አደጋ የሚደርሰው በተሳፋሪዎች ላይ መሆኑን ያመለከቱት የጥናቱ አቅራቢ፤ አዲስ አበባና አቅራቢያ አካባቢዎች ከፍተኛ የትራፊክ አደጋ እንደሚመዘገብና ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ መንገዱ የሚሸከመው የትራፊክ መጠን ከፍተኛ መሆኑ እንደሆነም አንስተዋል፡፡
በዘርፉ በርካታ ክፍተቶች እንደተለዩ ጠቁመው፤ የመንገድ ደህንነት አስተዳደሩን ማጠናከር፣ በዘርፉ ጥናቶችን በማካሄድ በሚገኙ የመፍትሄ ሃሳቦች በስራ መተርጎም፣ ለመንገድ ደህንነት ስራዎች በቂ በጀት መመደብ እንደሚያስፈልግ በጥናታቸው ጠቁመዋል::
ደረጃቸውን የጠበቁ በርካታ የመንገድ ግንባታ ስራዎች በትኩረት መሰራት እንዳለባቸውና ጥገና ላይ የሚሰሩ ሰዎችም የመንገድ ቅኝት አስተሳሰብ ላይ ያተኮሩ ተከታታይ ስልጠናዎችን መስጠት እንደሚገባም መክረዋል፡፡
የመሰረተ ልማት ባለሙያው አቶ ዮናስ በቀለ ባቀረቡት ጽሁፍ እንዳመለከቱትም፤ መንግስት በተሽከርካሪ ደህንነት የቴክኒክ ስራ ለግል ዘርፉ መሰጠቱ፤ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ የመልካም አስተዳደርና የተጠያቂነት ችግሮች ስለሚስተዋልበት ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚያስፈልገውና ተቋማቱም በኃላፊነት ስሜት እንዲሰሩ መክረዋል፡፡
የመመርመሪያ ማሽኖቹ አስፈላጊውን መስፈርት ሊያሟሉ እንደሚገባና ተቋማቱ ላይ ድንገተኛ ፍተሻ ማድረግ ሌላው ለችግሩ መፍትሔ ይሆናል ብለው ያቀረቡት ሀሳብ ነው፡፡
በትራንስፖርት ሚኒስቴር የመንገድ ትራንስፖርት ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ፈቲያ ደድገባ በበኩላቸው፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ የልማት ኮሚሽን የተሳተፈባቸው የክለሳ ጥናቶች በዘርፉ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርጉና አደጋ በብዛት የሚደርስባቸው ቦታዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በመንገድ ትራፊክ አደጋ እንደችግር ከሚቀርቡ ጉዳዮች መካከል ፍጥነት አንዱ ነው ያሉት ኃላፊዋ የፍጥነት መገደቢያ መመሪያ በማውጣትና ከሶስት ሺ በላይ ተሽከርካሪዎች ላይ በመግጠም ወደ ስራ ተገብቷል፡፡ በቀጣይም የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ላይ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
በሲኖ ትራክና በሌሎች የጭነት ተሽከርካሪዎች ላይም እንደሚገጠም የገለጹት ኃላፊዋ፤ የተሽከርካሪ ምርመራ ተቋማት ላይ ድንገተኛ ፍተሻ በማድረግ ማሻሻያዎች እንደሚደረጉ አመልክተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 6/2012
ዘላለም ግዛው