ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ፕሬዝዳንት ሆነው በተሾሙበት ቀን ባደረጉት ንግግር ስለአገር ግንባታና ስለ ሰላም አፅኖት የሰጠ እንደ ነበር አይዘነጋም፡፡ ለማስታወስ ያህልም፤ ‹‹የሚለያዩንን ጉዳዮች ከማስፋትና ወደ ጠብ ከመቀየር ይልቅ አንድነትን የሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ ለውጡ በተጀመረው መንገድ አንድነትን እንዲያጠናክር ስር የሰደደ ጥላቻ፣ መናናቅና አልፎ አልፎ የሚታየውን ጠብ በኢትዮጵያዊ ጨዋነት በዳበረ የሀይማኖትና የሽምግልና ሥርዓት በማጠናከር ለትውልድ የምታኮራ አገር መፍጠር ይኖርብናል፡፡ ታላቅ አገር የመገንባት ህልማችንን እውን ለማድረግ ከሰላም ውጭ ምንም አቋራጭም አማራጭ የለም፡፡ ሁሉም ሰላሙን አጥብቆ እንዲጠብቅ እና ከሁሉ በላይ ሰላም ሲታወክ በምትሰቃየው እናት ስም ከአደራ ጋር አጥብቄ እጠይቃለሁ፡፡ በሰላም እጦት ዋነኛ ተጠቂዎች ሴቶች ናቸው›› ብለዋል፡፡
የፕሬዝዳንቷ ንግግር እንደ መግቢያ የተጠቀምነው ሴቶች የሰላም እጦት ቀዳሚ ተጎጂዎች መሆናቸውን ለመጥቀስ ብቻ ሳይሆን ሰላም እንዲመጣም በስነምግባር የታነጸ ትውልድን ለመቅረፅም ቀዳሚ እንደሆኑ የሚጠቁም ተግባርን ለመዳሰስ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሰላሟ የተጠበቀች አገር እንድትሆን እናቶችን የወከሉ የሰላም አምባሳደሮች ስለ ሰላም ለማስገንዘብም ቀዳሚ ሆነዋል፡፡
ከዘጠኙ ክልሎችና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ ሴት የሰላም አምባሳደሮች ቡድን ተቋቁሟል፡፡ በቅርቡ በኢትዮጵያ ሰላም ጉዳይ በሁሉም ክልል በመዘዋወር መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ በቁጥር 21 የሆኑት የሰላም አምባሳደሮች ሁሉም እናቶች ሲሆኑ ስለ ሰላም በእናትነታችን መምከር አለብን በማለት የተሰባሰቡ ናቸው፡፡ በብሔር ብሔረሰብ ባሸበረቀ አልባሳትና የሰላም ምልክት የሆነችውን ነጭ እርግብ ያለበትን ዓርማ ይዘው የሚጓዙት እናቶች ጥሪያቸውንም ሁሉም እንዲሰማ ከክልል ፕሬዝዳንት፣ አፈጉባኤዎች፣ ከንቲባና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የኢትዮጵያን ሰላም ማስጠበቅ የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የሰላም አምባሳደሮቹ የያዙት የሰላም መልዕክት በህዝብ መካከል ሰላማዊ ግንኙነትና አንድነት እንዲጠናከር እና ኢትዮጵያ እንደ ብዝህነቷ ያካበተቻቸው የመቻቻልና አብሮ የመኖር ባህልና የአንድነት መንፈስ እንዳይሸረሸር አደራ ብለው ለምነዋል፡፡ በየመድረኩ ስለሰላም ተማጽነዋል። የሰላም ምንጭ ከየቤቱ እንዲመነጭ ወትውተዋል።
በሰላም ሚኒስቴር የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ዳይሬክተር ወይዘሮ አበባ ተገኘ የሰላም አምባሳደር እናቶች ቡድን አስተባባሪ ናቸው፡፡ የሰላም አምባሳደር ሴቶች ቡድን የማቋቋም ሀሳብ እንዴት እንደተጀመረ ሲያስረዱ ‹‹የሰላም አምባሳደርነት ሀሳቡ የመጣው ኢትዮጵያ ያለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ላይ በስራ አጋጣሚ የምንገናኝ ሴቶች መንግስት ሰላም በማስከበሩ በኩል እየሰራው ካለው ስራ ውጪ እኛ እንዴት መሳተፍ እንችላለን በማለት በራስ ተነሳሽነት በመመካከር ነው›› ይላሉ፡፡ ከዛ በኋላ የሰላም አምባሳደርነት ሀሳቡ ለሰላም ሚኒስቴር ቀርቦ እውቅና እንዲያገኝ እና በተደራጀ መልኩ እንዲከናወን መደረጉን ያስረዳሉ፡፡ ይሄ የ21 ሴቶች ሀሳብ እንዲሳካም የሰላም ሚኒስቴር እና የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር በጋራ እገዛ ማድረጋቸውን ነው የነገሩን፡፡ ‹‹ሴቶች ለሰላም አገራዊ ጉዞ›› በሚል ሀሳብ ሁሉንም ክልል እና በሁለቱ ከተማ አስተዳደር በመጓዝ የሰላም አምባሳደር እናቶች ጥሪያቸው ማቅረባቸውን ይገልጻሉ፡፡
ወይዘሮ አበባ እንደሚናገሩት፤ በአገር ሰላም ሲሰፍንም ሰላም ሲጠፋም ቀዳሚ ተፅዕኖውን የሚቀበሉት ሴቶች ናቸው፡፡ የእናቶች ጸሎትም ልመናቸውም ሰላምና ጤና በመሆኑ የኢትዮጵያን ሰላም እናቶች ለሁሉም አደራ ቢሰጡ የእናቶች ድምጽ ተሰሚነቱ ከፍ ይላል፡፡ በኢትዮጵያ በየጊዜው በየቦታው እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች በእርቅ እንዲፈቱና በመቻቻል እንዲታለፉ የእናቶች ጥሪ ማቅረብ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረውም ይታመናል፡፡ ምክንያቱም ማንኛውም ሰው እናት አለው፣ እናቱን ይወዳል ያከብራል፤ ስለዚህ የሰላም አምባሳደር እናቶችንም መልዕክት በጎ ምላሽ ይሰጣል።
‹‹በሰላም ዕጦት ቀዳሚ ተጎጂዎች ሴቶች ናቸው ሲባል ወንዶች ምንም አይደርስባቸውም ማለት አይደለም፡፡ በሁሉም መልኩ ለጥቃት የሚጋለጡትም፣ ልጆቻቸውንም ለመከላከል የሚጎዱትም ሴቶችና እናቶች ስለሆኑ ነው፡፡ ልጆቻቸውን ትምህርት ተቋማት የላኩ እንዲሁ እያዳንዱን ቀን በሀሳብና በስቆቃ የሚያሳልፉ እናቶች ቁጥር አነስተኛ አይደለም፡፡ እኛ በየዩኑቨርሲቲዎች እየሄድን ወጣቶችን አደራ እያልን ያለነው የ50 ሚሊዮን እናቶችን ፀሎትና አደራ ይዘን ነው›› ይላሉ ወይዘሮ አበባ፡፡
እንደ ወይዘሮ አበባ ገለፃ፤ ቡድኑ የእናቶች ተሰሚነትን በዋናነት በመጠቀም መልዕክትን ለማስተላለፍ ተጠቅሟል፡፡ በሄዱበት ቦታ ሁሉ በመንግስትም፣ በወጣቶች እንዲሁም በነዋሪዎች የነበረው አቀባበል ይበል የሚያስብል ነው፡፡ ቡድኑ የእናቶችን ተሰሚነት በመጠቀም እንደጀመረው የሰላም ጥሪ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች በየአካባቢው ተሰሚነት ያላቸው የማህበረሰብ አካላት በተለያየ መልኩ ሊጠቀሙበት ይገባል፡፡ ጊዜና ሁኔታ በሚፈጥራቸው መጥፎ አጋጣሚዎች የቤተሰባቸውን ልፋትና የእናቶችን ፀሎትና ጭንቀት እያሰቡ እንዲንቀሳቀሱ አስገንዝበዋል፡፡ እኛ የአገራችን ሰላም ይመለከተናል በማለት ስለ ሰላም ጥሪ ስናቀርብ፣ አደራ ስንል ወጣቶች ተቀብለዋል፡፡ ይሄንንም ልመናችንን በተግባር ይተረጉሙታል ብለን እንተማመናለን።
‹‹በየቦታው ዞረን የክልል ፕሬዚዳንት፣ ከንቲባዎች፣ አፈ ጉባኤዎችን፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አነጋግረናል፡፡ ይህ ግን ከኛ ውጪም በየጊዜው በየአካባቢ ሊደረግ የሚገባ ነው፡፡ የአገር ሰላም ጉዳይ የሁልጊዜም ነው፤ የነገ ተስፋ መሰነቂያ በመሆኑ እያንዳንዱ አካል ማንንም ሳይጠብቅ በራሱ ሊሰራው ይገባል፡፡ የሰላም ጉዳይ የሁሉም ጉዳይ ሊሆን ይገባል፡፡ አገር ተረካቢ ትውልድ ሰላምን መጠበቅ እንደሚያስፈልግ እናቶች፣ አባቶችም፣ ህብረተሰብም በጋራ ሊመክር ይገባል›› በማለት፤ በ21 ሴቶች የተጀመረው የሰላም አገራዊ ጉዞ በየአካባቢው ባሉ ሴቶች ድረስ ደርሶ እንዲቀጥል ያሳስባሉ፡፡
ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር የሥርዓተ ጾታ ማካተት ዳይሬክተር ክትትልና ግምገማ ባለሙያ ወይዘሮ ዮዲት ዘውዴ የሰላም አምባሳደር ቡድኑ አባል ናቸው፡፡ በሥራ አጋጣሚ በመገናኘት የአገር ሰላም ላይ በትንሹም ቢሆን የድርሻችንን ለመወጣት በሚል የመጣው ሀሳብ አቀባበሉ ከጠበቁት በላይ መሆኑን ይናገራሉ፡የቡድኑ ጉዞ ዓላማ ሰላምን የሁሉም እንዲሆን አደራ የማለት በመሆኑ በመንግሥት አካላትም የተደረገላቸው አቀባበል እና ያገኙት ተሰሚነት ጥሩ እንደነበርና ለውጥ ማምጣት እንደሚችል ያመለክታሉ፡፡ የጀመሩት አገራዊ ጉዞ በ21 ሴቶች ብቻ ተወስኖ እንዲቀር እንደማይፈልጉ እርሳቸውም እንደ ወይዘሮ አበባ ያሳስባሉ፡፡
‹‹ዩኒቨርሲቲ ሄደን ከመምህራንና ተማሪዎች ጋር ባደረግነው ውይይት ከወጣቶች ያገኘነው ምላሽ አስገራሚ ነበር፡፡ አሁንም እናቶችን የሚሰሙ፣ ስለሰላም ግድ የሚላቸው ወጣቶች ኢትዮጵያ እንዳላት ለማየት ችለናል፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች የሚፈጠረው ግጭት እንዲህ አርቀው በሚያስቡ ወጣቶች ለውጥ ማምጣት ስለሚቻል ምክሩ ላይ ጠንክሮ መሰራት አለበት›› ይላሉ፡፡
‹‹የአገርም የማህበረሰብም ተምሳሌት የሆነችው እናት ልመናና አደራ ትልቅ ነው›› የሚሉት ወይዘሮ ዮዲት፤ ሁሉም የሰላም ጥሪያቸውን እንዲቀበል ከዚህ በኋላም እንደሚሰሩ ይናገራሉ፡፡ በኢትዮጵያ በየጊዜው በነበሩ ሥርዓቶች የተፈጠሩ እያንዳንዳቸው የራሳቸው አይነትና ይዘት ያላቸው የህዝብ ቅሬታዎችና ጥያቄዎች የአገርን ሰላም ሲያደፈርሱ መቆየታቸውን ያስታውሳሉ። ከዚህ በኋላም ሁሉም ነገር በሰላም መካሄድ እንዳለበት ይናገራሉ፡፡ የጋራ አገር ለማሳደግ ሰላም ወሳኝ በመሆኑ ሁሉም ኃላፊነት መውሰድ እንደሚገባም ያስገነዝባሉ፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ መከፋፈል አብቅቶ፣ በጋራ በእኩልነት፣ በመተሳሰብ እና በአንድነት መኖር እንደሚበጅ ይናራሉ፡፡ ለሰላም አምባሳደር እናቶች የኢትዮጵያ ህዝብ ግማሽ የሆኑትን ሴቶች በተለይም የእናቶችን የሰላም ፀሎትና አደራን አንግበው የጀመሩት በመሆኑ የሁሉም የሆነች ኢትዮጵያን ሰላማዊ የሆነች ኢትዮጵያን ለትውልዱ ለማስተላለፍ እናቶች እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡ የሰላም እጦት የመጀመሪያ ገፈት ቀማሽ ሴቶችና ህጻናት ናቸው የሚሉት ወይዘሮ ዮዲት፤ የሁሉም እናት ፀሎት የአገር ሰላምና የልጆች ደህንነት ነውና የእናቶች የሰላም ጥሪ ሁሉም ተቀብሎ ይተገብረዋል የሚል ተስፋን ሰንቀዋል፡፡
ሰላምን ማስጠበቅ ከእያንዳንዱ ሰው ይጠበ ቃል፤ ሰላም ደግሞ የሚመነጨው ከእያንዳንዱ ቤትና ግለሰብ ነውና ሰላማችን እንዳይደፈርስ የሰላም ምንጩን ከእያንዳንዱ ቤተሰብ ይመንጭ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 27/2011
ሰላማዊት ንጉሴ