አለማቀፉ የሰላም ፣ የእርቅ ፣ የሽምግልናና የግልግል ረቡኒ
/መምህር/ ፕሮፌሰር ሕዝቅያስ አሰፋ ዘላቂ ሰላም እውን እንዲሆን ሰው በመጀመሪያ ከፈጣሪ ጋር ከዚያ ከራሱ ጋር በማስከተል ከተፈጥሮ ጋር ሰላም ፣ እርቅ ማውረድ አለበት ይላሉ ። ከተፈጥሮ ጋር ሰላም ለመፍጠር የሰው ልጅ ተፈጥሮን እንዳይኑ ብሌን መንከባከብ ይጠበቅበታል ። ከዚህ ጎን ለጎን የሰውን ልጅ ከተፈጥሮ ጋር የሚያሸማግሉ ፣ የሚያስታርቁ የኖቤል የሰላም ተሸላሚ የሆኑትን የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋች ኬኒያዊቷን ዋንጋሪ ማታይ ፣ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትርን ማንሳት ይቻላል ። የዛሬ መጣጥፌ ትኩረት የልጅ አዋቂዋና ሸምገጋዯ ስዊድናዊ
ብላቴና ናት ።
በዚህም ሆነ በዚያኛው አለም ገና በልጅነታቸው በሰው ልጅ ህይወት ላይ አርዓያነት ያለው ተግባር በመፈፀም አሻራቸውን ያኖሩ እንደማላላ ዩሱፍ ፣ ግሬታ ተንበርግና እዮስያስ ያሉ እልፍ አእላፍ ብላቴናዎች አሉ ። እንዲሁም ታዳጊዋን አቀንቃኝ ሎርዴን ፣ ተአምረኛዋን አትሌት ሲሞን ባይልስን ፣ የሆንኮንጉ የጃንጥላ አብዮት ምልክትና ፊት አውራሪ ጆሹዋ ማንሳት ይቻላል ።
የዛሬው ትኩረቴ የእናት ምድር ጠበቃ ስለሆነችውና ከልጅ እስከ አዋቂ ፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ፣ ከሀገር መሪ እስከ ተራው ዜጋ ፣ ከትምህርት ቤት የአካባቢ ጥበቃ ክበብ እስከ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአጠቃላይ ከአፅናፍ እስከ አፅናፍ ስለ የአየር ንብረት ለውጥ አለማቀፍ ንቅናቄን ስለ አቀጣጠለችው ፤ የኖቤል የሰላም አሸናፊ እጩ ፤ የተወዳጁ TIME መፅሔት የ2019 ዓም የዓመቱ ሰው ተብላ ስለተመረጠችው ስዊድናዊት ብላቴና ግሬታ ተንበርግ ነው ።
ተንበርግ የአየር ንብረት ለውጥ ተሟጋችነት እንቅስቃሴዋን አሀዱ ብላ የጀመረች በወርሐ ነሐሴ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2018 ከስዊድን ፓርላማ ፊት ለፊት ድንኳኗን ደንኩና በስዊድንኛ በነጭ ሰሌዳ ላይ በጥቁር የተጻፈ
” ለአካባቢ ጥበቃ ትምህርት እናቁም ” የሚል መፈክር በማንገብ ነው ። ዓመት ከመንፈቅ ባልሞላ ጊዜ ዝናዋ በዓለም ተናኘ ። በመንግሥታቱ ድርጅት ተገኝታ ስለ አየር ንብረት ጥበቃ አስፈላጊነት እና ስለ አለም ሙቀት መጨመር ለሀገራት መሪዎች በአግራሞት እጅን በአፍ የሚያስጭን ንግግር አደረገች ። ወዲያው ከካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ፓፓስ ጋር ተገናኘች ። የዓለም ሙቀት መጨመርን ከሴራ ኀልዮት ጋር የሚያዛንቁትን ፕሬዚዳንት ትራምፕን ስማቸውን ሳትጠራ በአሽሙር ጎሸም አደረገቻቸው ።
በሰው ልጅ ታሪክ ወደር ያለተገኘለትንና 4 ሚሊዮን ተማሪዎችን ትምህርት አዘግቶ ለዓለም የአየር ንብረት መዛባት ተገቢው ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ የሚያስተላልፍ ሰልፍ በመስከረም 20 ቀን ፣ 2019 ዓም በተመሳሳይ ጊዜ በምዕራባውያን ከተሞች ተካሄደ ። ከዚያማ ምስሏ በአውሮፓና አሜሪካ ከተሞች በየህንጻው ግድግዳና ጣራ በትላልቅ እስክሪኖች ተለቀቀ ህጻናት በጥቅምት መጨረሻ አሰፈሪ ጭምብል አድርገው በሚያከብሩት በዓል Halloween ሳይቀር ምስሏ ማድመቂያ ሆነ ። ኮሊንስ የተሰኘው የእንግሊዘኛ መዝገበ ቃላት የተንበርግን ” climate strike ” / አድማ ለየአየር ንብረት / የሚለውን ሀረግ የዓመቱ ምርጥ ሀረግ ብሎ እስከ መሰየም ደረሰ ።
ታይም የ2019 ዓም ” የዓመቱ ሰው ” በሚል በፊቱ ገፁ ላይ ይዟት ወጣ ። የመፅሔቱ ጋዜጠኞች እነ ቻርሎቴ አልተር ፣ ሱይን ሀይኔስ እና ጀስቲን ወርላንድ በጋራ ባጠናቀሩት የተንበርግ ዘካሪ ፁሑፍ ፤ የአየር ንብረት ጉዳይ ምንም እንኳ ውስብስብና አሳሳቢ ቢሆንም ታዳጊዋ ግን የአመለካከት ለውጥ በማምጣት ውጤታማ እየሆነች ነው ። አለማቀፋዊ ንቅናቄ በመፍጠር አዲስ አተያይ መፍጠር ችላለች ። የልጅ አዋቂዋ ከከንቲባ እስከ ሀገር መሪዎች ስለ አየር ንብረት ግድ እንዲላቸው ተፅኖ መፍጠር ችላለች ። የእንግሊዝ የፓርላማ አባላትን ካነጋገረችና ከእንግሊዝ የአየር ንብረት ተሟጋቾች ጋር አደባባይ ሰልፍ በወጣች ማግስት እንግሊዝ የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ የሚያስገድድ ሕግ አፅደቀች ።
የተንበርግ ሌላው የትኩረት አቅጣጫ የየሀገሪቱ ተሟጋቾች ለዓመታት የወተወቱት የአየር ንብረት ጉዳይ ከሌሎች አንገብጋቢ ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ፓለቲካዊ ጉዳዮች እኩል ትኩረት እንዲሰጠው ግፊት ማድረግ ነው ። ይህ የብላቴናዋ ጥረት ከዓለም ሙቀትና ከባሕር መጠን መጨመር ፣ ከጎርፍ ፣ ከሀሪካን ፣ ከሰደድ እሳት ። ሰሞኑን በዓለማቀፍ የቴሌቪዥን ኔትወርኮች እንደተመለከተው በአውስትራሊያ የተከሰተው ሰደድ እሳት ዓለማችን በታሪኳ አይታው የማያውቅ ሲሆን ወደ 18 ሚሊዮን ሄክታር መሬት የሚጠጋ ደን ወድሟል ። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የዱር እንስሳት ሞተዋል ። እርሻዎች ፣ መኖሪያ ቤቶች በሰደድ እሳቱ ወድመዋል ። ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑ ቤተሰቦች ከቀዬ ፣ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል ። ከዚህ በላይ ቃጠሎው የከባቢ አየር ሙቀት እንዲጨምር ከማድረጉ ባሻገር ከፍተኛ የአየር ብክለት አስከትሏል ። ጠቢቡ ሰለሞን ለሁሉም ጊዜ አለው እንዳላው የታዳጊዋ ጩኸት እንደ አውስትራሊያ ካለ የአየር ንብረት ቀውስ ጋር አብሮ ዓለም ጆሮውን አዝንብሎ እንዲሰማት መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል ።
ለዚህ ይመስላል የቀድሞው የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ፣ የኖቤል የሰላም አሸናፊና የአየር ንብረት ተሟጋች አል ጎር ” ያለንበት ጊዜ ለአየር ንብረት ተሟጋችነት የተመቼ ይመስላል ፤ ” ያሉት ። የዝክረ ተንበርግ የTIME ፀሐፍት ሰፊ ዘገባ በመቀጠል ፤ ብላቴናዋ እድሜዋ 16 ሲሆን ሲያይዋት ግን ገፅታዋ በአራት ዓመት ቀንሶ የ12 ዓመት ህጻን እንደምትመስል ፤ ከኦቲዝም ቤተሰብ የሚመደብ አዝፔርገር ሲንደረም ታማሚ ( ሰው በተሰበሰበበት ስፍራ መገኘት ምቾት የሚነሳት ፤ ) መሆኗን ፤ ስለ ባህር ከፍታ መጨመርና ይህን ተከትሎ በሚከተል የባህር ዳርቻ ከተሞች በውሃ መጥለቅለቅና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ሊፈናቀሉ ይችላሉ ብላ ሌት ተቀን የምትጨነቅ መሆኑን ያወሳሉ ። ” ነገ እንደሌለ ለዛሬ ብቻ የምንኖረውን የህይወት ዘይቤ መቀየር አለበን ። ምክንያቱም ነገ አለ ።” አዎ ! ብላቴናዋ እንዳሳሰበችው ለመጭው ትውልድ የወደመ ደን ፣ የተራቆተ መሬት ፣ በርሀማ ሀገር ፣ ውሃቸው የነጠፈ ምንጮችና ወንዞች ልናወርሰው አይገባም ።
በሀገራችን ከረፈደ ቢሆንም እየተሰሩ ያሉ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ይበል የሚያሰኙ ናቸው ። በሀገራችን የተፈጥሮ ጥበቃ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውና በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ፊት አውራሪነት የተመራው የ” አረንጓዴ አሻራ ” ሀገራዊ ንቅናቄ ከ4 ቢሊዮን በላይ ሀገር በቀል ችግኞችን መትከል ተችሏል ። ይህ ለነገው ትውልድ ጭምር ለምለም ፣ ነፋሻ ፣ ምንጮች የሚንፎለፎሉባት ፣ ወንዞች የሚገማሸሩባት ፣ ወዘተ . ሀገር ለማቆየት ያስችላል። አይደለም የዛሬ ብላቴናዎችና ወጣቶች እኔ እንኳን ዝግባ፣ ቀረሮን፣ ኮሶን በቅጡ ለይቼ አላውቃቸውም። ደደብ ስለሆንሁ አይደለም ። ያ ራስ ወዳድ ስስታም ትውልድ ዛሬን ፣ እኔን ቀድሞ አስቦ ስላላቆየኝ እንጂ ።
ይሄ ትውልድ ከመሰል ተወቃሽነት ተከሳሽነት ለመዳን ኃላፊነቱን መወጣት አለበት። ተንበርግ የዛሬውን ትውልድ በ74ኛው የተመድ ጠቅላላ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ እንዲህ እንደወቀሰችው ” …የሰው ልጅ ገንዘቡን ከማሳደድና ስለዘላለማዊ ምጣኔ ሀብት እድገት እንጂ ስለአየር ንብረት ለውጥ ግድ አይለውም ። የአካባቢ የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት ጠንካራ እርምጃ መውሰድ አልቻለም ። ‘ እኔ እዚህ መምጣት አልነበረብኝም ። ከውቅያኖስ አጠገብ ወደ ሚገኘው ት/ ቤት መሄድ ነበረብኝ ። ይህ ስህተት ነው ። በባዶ ቃላት ህልሜን ፣ ልጅነቴን ቀምቶኛል ።… ‘ ”
ሀገራት የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ ካልተስማሙ ከየኢንዱስትሪ አብዮት ወዲህ የከባቢ አየር ሙቀት በ1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴንትግሬድ ይጨምር ይሆናል ሲል ስጋቱን ያጋራው የTIME ዘገባ እስከ አውሮፓውያኑ 2030 ዓም 350 ሚሊዮን ሕዝብ ለድርቅ ፣ 120 ሚሊዮን ሕዝብ ለከፋ ድህነት ሊጋለጥ ይችላል ሲል አበክሮ ያስጠነቅቃል። የዓለም ሙቀት በሽርፍራፊ ሴንትግሬዶች በጨመረ ቁጥር የአየር ንብረት ለውጡ እየተባባሰ ይሄዳል ። ይህ ፍርሀትን ለማንገስ ሳይሆን በሳይንቲስቶች የተረጋገጠ ጥሬ ሀቅ ነው ። የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች ፣ የዘርፉ ተመራማሪዎች ላለፉት አስርት ዓመታት ፓለቲከኞች ለአሳሳቢው የአየር ንብረት መዛባት ፓለቲከኞች ትኩረት እንዲሰጡት ነጋ ጠባ ቢወተውቱም ሰሚ ሳያገኙ ቆይተዋል ።
በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ግን ያልተጠበቀችው ብላቴና የአየር ንብረት መዛባት ፣ የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይና የዓለም ሙቀት መጨመር በመሪዎች ዘንድ ትኩረት እንዲያገኝ የአንበሳውን ድርሻ ተወጣለች ። አሁን አሁን የአየር ንብረት መዛባት ጉዳይ በተነሳ ቁጥር ቀድሞ የሚነሳው የብላቴናዋ ስም ነው ። ይህ በአጋጣሚ አልያም በሚዲያውም ሆነ በፓለቲከኞች መልካም ፈቃድ አይደለም ። በተንበርግ ደፋር ውሳኔና አርቆ አሳቢ እርምጃዎች እንጂ ። ባለፈው ጥር በዳቮስ በተካሄደ ኢኮኖሚክ ፎረም ለታላላቅ ኩባንያዎች ዋና ሥራ አስፈጻሚዎችና ለሀገራት መሪዎች ያለምንም ማቅማማትና ፍርሀት የተናገረችው ለዚህ ጥሩ አብነት ነው ። ” እንድትደናገጡ ፣ እንድትረበሹ እፈልጋለሁ ። በየቀኑ የሚሰማኝ ፍርሀት እናንተንም እንዲሰማችሁ እሻለሁ ። ይህን ተከትሎ ኃላፊነትን እንድትወስዱ እጠይቃለሁ ።” ለዚህ ነው ተንበርግ ለአየር ንብረት ለውጥ ብቻ ሳይሆን ለአሜሪካ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ተሟጋች ወጣቶች ለሆንግኮንክ የዴሞክራሲ ወትዋቾች ብላቴናዎች ሁሉ የልዩነት ምልክት ልትሆን የቻለችው ሲል TIME ያትታል ።
ዛሬ የብላቴናዋን ጥሪ ወሰን ፣ ዘር ፣ ቀለም ፣ ሀይማኖት፣ የኑሮ ደረጃ ፣ አድማስ አይበግረውም ከአፅናፍ አፅናፍ ናኝቷል ። አለማቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አመነስቲ ኢንተርናሽናል በዚያ ሰሞን ባካሄደው የዳሰሳ ጥናት፤ “… በ22 ሀገራት የሚገኙ ወጣቶች የአየር ንብረት ለውጥ ከሁሉም ነገር በላይ እንደሚያስጨንቃቸው ተናግረዋል ። ”
ምስጋና ለብላቴናዋ ይሁንና የአውሮፓ ሕብረት ከአዲሱ ዓመት ጀምሮ የአየር ንብረትን ለመከላከል በሚያመነቱ ዳተኛ በሆኑ ሀገራት ላይ ታክስ መጣል እንደሚጀምር ይፋ አድርጓል ። ተንበርግን አርዓያ በማድረግ በየሀገራቱ የሚካሄዱ የብላቴናዎች ተቃውሞ ተቋማትን ብቻ ሳይሆን ለሀገራቱ መሪዎችም እንደ ማንቂያ ደወል እየሆነ ነው ። የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑየል ማክሮን ለዚህ ጥሩ ማሳያ ናቸው ይላል TIME መፅሔት ” ወጣቶች በየሳምንቱ የሚያካሂዱትን የተቃውሞ ሰልፎችን እየተመለከትህ ገለልተኛ መሆን አትችልም ። እንድለወጥ ረድተውኛል ። ”
“ ዓለምን የማየው እንደወረደ በነጭና በጥቁሩ ነው። መመቻመች አልፈልግም ። እንደሌሎች ህፃናት ብሆን ይህን ቀውስ ልረዳው አልችልም ነበር ። ” የምትለው ተንበርግ ራሷን እንደ ህፃን አታይም ። ስለትምህርት ቤቷ በተጠየቀች ጊዜ የሰጠችው መልስ ለዚህ ዋቢ ነው ። ” ህጻናት በጣም ጩኸታም ናቸው ። ” በእሷ ቤት እሷ ህፃን አይደለችም ።
እንደ መውጫ
ብላቴናዋን ለዓለም ያበረከቱት ወላጆቿ ፣ ትምህርት ቤቷ ፣ ማህበረሰቡ በመጨረሻም ሀገረ ስዊድን ናት ። መምህሯ ከክፈለ ጊዜው በአንዱ ተማሪዎቹን የአየር ንብረት መዛባት የበረዶ ግግሩን እያቀለጠ ፣ የባህር ከፍታን እየጨመረ በባህር ዳርቻ ያሉ ሰዎችንና ከተማዎችን በውሃ እያጥለቀለቀ ፣ የዓለም ሙቀትን እየጨመረ ፣ ሰደድ እሳትን አየቀሰቀሰ እንደ ሆኑ ለተማሪዎቹ ሲገልፅ ለእውቀት ለፈተና እያዘጋጃቸው እንጂ ከመካከላቸው ነገ ተነስታ/ቶ የአየር ንብረት ጥበቃ ተሟጋች ትሆናለች / ይሆናል ብሎ በህልሙም ሆነ በእውኑ አላሰበውም ። ተንበርግ ግን ከዛች ቀን ጀምሮ ስለ አየር ንብረት ተጨናቂ ፣ ተብሰክሳኪ ፣ አንሰላሳሊ ከመሆኖ ባሻገር አጠቃላይ ህይወቷ ተወሰደ ። ተቀየረ ። ለድብርትና ለጭንቀት ተዳረገች ።
ክፍሏን ዘግታ ብቸኛዋን መሆን መረጠች ። ምግብ ቀነሰች ፣ ከሰውነት ጎዳና ወጣች ። በዚህም ወላጆቿ ተጨነቁ ። ተጠበቡ ። በመጨረሻም ከዚህ በፊት ግድ የማይሰጣቸውን የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ መመራመር ፣ መጠየቅ ፣ ማንሰላሰል ጀመሩ ። በመጨረሻም የልጃቸውን መንገድ ተቀላቀሉ ። ስጋ መመገብ አቆሙ ። የኃይል ምንጮቻቸውን ሁሉ በታዳሽ ኃይል ተኩ ። የፀሐይ ኃይል solar energy ተጠቃሚ ሆኑ ። በየሄደችበት መሄድ ፣ በምትሰለፍበት መሰለፍ ጀመሩ ።
የተንበርግ ተፈጥሮ ከእኩዯቿ የተለየ ቢሆንም መልካም ዘር በመዝራት ፣ የተማሪዎቻቸውን መጻኢ እድል በበጎ በመወሰን ረገድ መምህራን ትልቅ ድርሻ አላቸው ። ወላጆች ለልጆቻቸው ዓላማ መሳካት ምን ያህል እርቀት እንደሚሄዱና የትኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ እንደሆኑ በተንበርግ እናትና አባት ተመልክተናል ።
በዛሬዋ የዓለማችን አብሪ ኮከብ ተንበረግ ስሪት ውስጥ የእነዚህ ሁሉ አሻራ ይታያል ። በአለማችን ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ህጻናት ስሪትም ከዚህ የተለየ አይደለም ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወላጆች ፣ መምህራን ፣ ማህበረሰቡ ፣ መንግስት ፣ ሀገር በተወሰነ ደረጃ ስለህጻናት ያላቸው አመለካከት እየተሻሻለ እየተለወጠ ቢሆንም ገና ብዙ ይቀረናል ። አስተዳደጋቸው ፣ የትምህርት ስርዓቱ ፣ የዕምነት ተቋማት በራሳቸው የሚተማመኑ ፣ ራሳቸውን ችለው የሚቆሙ ፣ ርዕይ ሰንቀው የሚያድጉ ህጻናትን አንጾ ማሳደግ ላይ ወጥ የሆነ ጥረት እያደረጉ ነው ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቸግራል ።
በተለይ በገጠሩ የሀገራችን ክፍል የልጆች አስተዳደግና ትምህርት ዛሬም ህጻናትን ማነፅ መቅረፅ ላይ ብዙ ይቀረዋል ። አጠቃላይ ስለ ህጻናትና ስለ ልጆች ብዙ ብዙ ግድ የሚሉን ጉዳዮች ይቀሩናል ። ስለሕፃናት ይዘነው የመጣነውን ስሁት መንገድ ስነ ቃሎቻችን በተለይ ምሳሌአዊ ንግግሮአችን አፍ አውጥተው ጩኸው ይናገራሉ ። ልጅ ከሳቁለት ውሻ ከሮጡለት ፤ ልጅ ለእናቷ ምጥ አስተማረች ፤ ልጅ ቢያስብ ምሳውን አዝማሪ ቢያስብ ጠላውን ፤ ልጅ ከዋለበት ሽማግሌ አይውልም ፤ ልጅ ያቦካው ለእራት አይበቃም ።
መጭው ዘመን ለኢትዮጵያ ሕጻናት
በጎ ይሆናል !!!
አሜን ።
አዲስ ዘመን ጥር 2/2012 ዓ.ም
በቁምላቸው አበበ ይማም ( ሞሼ ዳያን )
fenote1971@gmail.com