የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ሐሙስ ታኅሣሥ 30 ቀን 2012 ዓ.ም የጦር መሣሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅን አጽድቋል። የአዋጁ መጽደቅ በአደገኛ ሁኔታ እየተስፋፋ የመጣውን የጦር መሣሪያ ዝውውርና አጠቃቀም ሕጋዊ ሥርዓት በማስያዝ ረገድ ወደር የለሽ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሎ ይገመታል።
የጦር መሣሪያ ዝውውርና ሕገወጥ አጠቃቀም በተለይ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ እያደጉና እየሰፉ እንደመጡ አንዳንድ መረጃዎች ይጠቁማሉ። የጉምሩክ ኮሚሽን መረጃዎች እንደሚሳዩት በ2011 ዓ.ም ብቻ በጉምሩክና መከላከያ የተያዙ መሣሪያዎች ብዛት 2020 ሽጉጥ፣ 62 ክላሽንኮቭ ጠመንጃ፣ 4 መትረየስ ነው። በዚሁ ዓመት 917 የመትረየስ ጥይት፣ 15 ሺህ 717 የብሬን ጥይት፣ 80 ሺህ 764 የሽጉጥ ጥይት መያዛቸውን ተቀምጧል። በ2012 ዓ.ም 1 መትረየስ፣ 113 ክላሽንኮቭ፣ 382 ሽጉጦች መያዛቸው ተመዝግቧል።
በዚሁ ዓመት 111 የመትረየስ ጥይት፣ 3 ሺህ 581 የብሬን ጥይት፣ 5 ሺህ 231 የክላሽንኮቭ ጥይት ፣4 ሺህ 910 የሽጉጥ ጥይትና 122 የክላሽ ካዝና መያዛቸውን የጉምሩክ መረጃ ያሳያል።
ከዘጠኙ የጉምሩክ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕገ ወጥ መሣሪያና ጥይት የተያዘው በቃሊቲና ባህር ዳር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ሲሆን ዝቅተኛ መሣሪያ የተያዘው ደግሞ በመቀሌው ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በኩል መሆኑን መረጃው ያሳያል።
በመስሪያ ቤቱ የኢንተለጀንስና ኮንትሮባንድ ክትትል የሥራ ሂደት መሪ የሆኑት አቶ ዘላለም እንደሚናገሩት በ2011 ዓ.ም በልዩ ሁኔታ በቦሌ አየር መንገድ ሴኪዩሪቲ መጋዘን በተደረገው ፍተሻ 3 ስናይፐር፣ 3 የአደን ጠመንጃ፣ 20 ኪሎ ግራም የሚመዝን የጦር መሣሪያ መለዋወጫ እንደተገኘም ተናግረዋል።
አንድ ዓለም አቀፍ ድርጅትም ፈቃድ ሳያገኝ ለጥበቃ ሠራተኞቹ ሊያስገባ የነበረው 59 ሽጉጥና 122 ሺህ ጥይት በጉምሩክና በድርጅቱ ቁልፍ ተቆልፎ እንደሚገኝም ጨምረው አስረድተዋል።
የጦር መሣሪያ የትኛው ነው?
በጸደቀው አዋጅ የጦር መሣሪያ፣ ቀላል የጦር መሣሪያ፣ ትናንሽ የጦር መሣሪያ፣ ሙሉ አውቶማቲክ፣ ግማሽ አውቶማቲክና አውቶማቲክ ያልሆነ የጦር መሣሪያ ምን ማለት እንደሆነ የተተረጎመ ሲሆን ትርጉሙ ለዚህ አዋጅ በሚመች መልኩ አንዳንዶቹም ከዓለም አቀፍ ትርጉማቸው ለየት ባለመልኩ ለመተርጎም ጥረት ተደርጓል። የጦር መሣሪያ ባይሆኑም የጦር መሣሪያን ያክል አደገኛ በመሆናቸው አጠቃቀማቸውን፣ ሥርጭታቸውን እና የአመራረት ሂደቱን መቆጣጠርና በሕግ አግባብ መግዛት አስፈላጊ በመሆኑ «ጉዳት ማድረሻ ዕቃዎች»ን በሕጉ ውስጥ ለማካተት የተሞከረ ሲሆን፣ በዚሁ መሠረት፣ በስለታማነታቸው ምክንያት ወይም የኤሌክትሪክ ኃይል በመጠቀም ወይም መርዛማ በመሆናቸው በሰው አካልና ሕይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ የሚችሉ እንደ ሳንጃ፣ ገጀራ፣ ጎራዴ፣ ሴንጢና ተመሳሳይ መሣሪያዎችን እንዲሁም በእጅ የሚያዙ ቴዘር መሣሪያዎች፣ አስለቃሽ ጢስ፣ እና ተመሳሳይነት ያላቸውን ኬሚካሎች ጉዳት ማድረሻ ዕቃዎች በሚል ትርጉም ተሰጥቷል።
የጦር መሣሪያ መያዝ የማይቻልባቸው፤
ከጦር መሣሪያ የፀዱ አካባቢዎችን በመፍጠር የኅብረተሰቡን ሥጋት በመቀነስ ደህንነትን ለማረጋገጥ ሲባል የጦር መሣሪያ ለመያዝ የፀና ፍቃድ ያለው ሰውም ቢሆን የጦር መሣሪያ መያዝ የማይቻልባቸው ቦታዎች በአዋጁ ተመልክቷል። እነዚህም፡- ሰላማዊ ሰልፍ ወይም አድማ በሚደረግባቸው ስፍራዎች፣ በምርጫ ሕግ ወይም በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሚወሰኑ ስፍራዎች፣ በሆቴሎች፣ በሲኒማና ትያትር ቤቶች፣ በሙዚየሞችና ተመሳሳይ በሆኑ የሕዝብ መዝናኛ ስፍራዎች፣ የተኩስ ስፖርት በሚካሄድበት ስፍራ ከተፈቀደ የመወዳደሪያ የጦር መሣሪያ ውጪ በስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በሃይማኖትና እምነት ተቋማት ግቢ ውስጥ ወይም የሃይማኖትና እምነት ተግባራት በሚከናወንባቸው ማንኛውም ስፍራዎች፣ የገበያ ቦታዎች፣ በሆስፒታልና ክሊኒኮች፣ በመንግሥት መስሪያ ቤቶች እና በሌሎች ተመሳሳይ ለሕዝብ አገልግሎት በሚሰጥባቸው ስፍራዎች እና ወደፊት ተቆጣጣሪ ተቋሙ የሚወስናቸው ተመሳሳይ የሕዝብ መገልገያ ሥፍራዎች ናቸው።
የጦር መሣሪያ ፈቃድ ገደብ
የተጣለባቸው ተቋማት
የጦር መሣሪያ ፈቃድ ገደብ የተደረገባቸው ተቋማትም በአዋጁ ተመልክቷል። እነዚህም የፖለቲካ ፓርቲ፣ የሃይማኖትና የእምነት ተቋም፣ የበጎ አድራጎት ድርጅትና ማህበር እና የትምህርት ተቋም ናቸው። ሆኖም ተቋማቱን ለመጠበቅ የጦር መሣሪያ አስፈላጊ በመሆኑ ለዚህ አገልግሎት የጦር መሣሪያ ይሰጣቸዋል። ይህ ማለት በነዚህ ተቋማት ውስጥ ላሉ ግለሰቦች የጦር መሣሪያ እንዲሰጣቸው ተቋማቱ መጠየቅ አይችሉም ማለት ነው እንጂ ተቋማቱን ለመጠበቂያ የሚሆን የጦር መሣሪያ ይሰጣቸዋል።
ስለፈቃድ ጉዳይ
የጦር መሣሪያ ፈቃድ የሚሰጥበት ሁኔታን በተመለከተ ለግለሰቦችና ለድርጅቶች የሚፈቀደው የጦር መሣሪያ ዓይነት በሕጉ ላይ የተመለከተ ሲሆን፣ የሚሰጣቸውን የጥይት ብዛት ግን በቀጣይ ተቆጣጣሪው ተቋም በሚያወጣው መመሪያ የሚወሰን መሆኑ ተመልክቷል። መሣሪያውን ለሌላ አካል በፈቃድ ለመስጠት አንዱ መስፈርት፣ ፍቃድ የተጠየቀበት የጦር መሣሪያ ከዚህ ቀደም በሌላ ሰው ስም ፈቃድ ያልወጣበት መሆኑ አንዱ ሲሆን፣ በሌላ በኩል የፀና ፈቃድ የወጣበት ቢሆንም እንኳን ባለፈቃዱ የጦር መሣሪያው ለአመልካቹ ቢሰጥ ፈቃደኛ መሆኑን የሚገልጽ ከሆነ፣ መሣሪያው ለአመልካቹ እንደሚሰጥ ተመልክቷል። እዚህ ላይ ፍቃድ የወጣበት ቢሆንም፣ ፍቃድ ያወጣበት ግለሰብ ከፈቀደ የሚለው ከላይ እንደገለፅነው በእኛ ሀገር የጦር መሣሪያ እንደ ንብረት ስለሚቆጠር በቤተሰቦች መካከል ያለን የጦር መሣሪያ ከአንዱ ወደ ሌላው ለማስተላለፍ እንዲቻል የሕግ መሠረት ለማስያዝ በማሰብ ነው።
የጦር መሣሪያ ፈቃድ የሚሰጥባቸው መስፈርቶችን በተመለከተ ለግለሰብ የጦር መሣሪያ ለመያዝና በሕጋዊ መንገድ ለመገልገል ፈቃድ የሚሰጠው ግለሰብ ማሟላት ያለበትን መስፈርት ሕጉ በዝርዝር አመልክቷል። ከነዚህ መስፈርቶች መካከል አንዱ በተቆጣጣሪው ተቋም በሚዘጋጅ ወጥነት ያለው መስፈርት መሠረት የጦር መሣሪያ ለመያዝ በቂ እና አሳማኝ ምክንያት ያለው ስለመሆኑ የታመነበት፣ ሲሆን ነው የሚል ሲሆን፣ ይህ ድንጋጌ ሁለት ነገሮችን ያመለክተናል።
አንዱ የሚመለከተው ተቆጣጣሪ አካል የጦር መሣሪያ የሚሰጥባቸውን መስፈርቶች እንደሚያዘጋጅ የሚያመለክት ሲሆን፣ ሁለተኛው የጦር መሣሪያ እንዲሰጠው የሚጠይቅ አካል የጦር መሣሪያውን የሚታጠቅበት ምክንያት ምን እንደሆነ ማስረዳት ይኖርበታል። ይህ ማለት ይህ አዋጅ ከመውጣቱ በፊት ያሉ ሁኔታዎች እንደተጠበቁ ሆነው ይህ አዋጅ ከወጣ በኋላ ግን የጦር መሣሪያ ፍቃድ የሚጠይቁ ሰዎች ምክንያታቸውን ማስረዳት ይኖርባቸዋል። በመሆኑም የጦር መሣሪያ ትጥቅ ለጠየቀ ሰው ሁሉ የጦር መሣሪያ አይሰጥም ማለት ነው። የጦር መሣሪያ መታጠቅ የሁሉም ሰው መብት ሳይሆን አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ተቆጣጣሪውን ባለሥልጣን የሚያሳምን ነገር ሲቀርብና መስፈርቶቹ ሲሟሉ የሚሰጥ ነው።
በአዋጁ ላይ ለልዩ ልዩ ተግባር ስለሚሰጥ የጦር መሣሪያን አስመልክቶ የተደነገገ ሲሆን፣ ለልዩ ልዩ ተግባር የሚሰጥ መሣሪያ ማለት ለስፖርት ውድድር የሚሰጥ ሽጉጥ ወይም ግማሽ አውቶማቲክ ጠመንጃ፣ ሕጋዊ የእንስሳት አደን ለሚያድኑ ወይም ለሚያሳድኑ ሰዎች የሚሰጥ የጦር መሣሪያ፣ ለቲያትርና ፊልም ሥራ እንዲሁም በኤግዚቢሽን ለማሳየት እና ከተሰሩ ሃምሳ ዓመት ያለፋቸው የጦር መሣሪያዎችን በቅርስነት ለመያዝ የሚሆን የጦር መሣሪያን የሚያካትት ሲሆን፣ ይህም በምን አግባብ ፈቃድ ሊሰጥ እንደሚችል ሕጉ አስቀምጧል።
ስለምዝገባ ሥርዓት
ሌላው በአዋጁ ከተመለከቱት ጉዳዮች መካከል አንዱ በአንቀፅ 18 ላይ የተመለከተው፣ የጦር መሣሪያ ምዝገባ ሥርዓትን የሚመለከት ሲሆን፣ ተቆጣጣሪ ተቋም በሀገሪቱ የሚገኙ የጦር መሣሪያዎችን በሙሉ በውል ቁጥራቸው መሠረት በመረጃ ቴክኖሎጂ ሥርዓት መዝግቦ እንደሚያስተዳደር ተመልክቷል። የዚህ ድንጋጌ ዋና አላማ በሀገሪቱ ውስጥ ያሉትን መሣሪያዎች ለማወቅ፣ ለማስተዳደርና ለመቆጣጠር እንዲቻል ማድረግ ነው።
በአንቀፅ 19 ላይ የጦር መሣሪያ ፈቃድ የተሰጠው ሰው ግዴታዎችን በዝርዝር ለማመልከት ተሞክሯል። እነዚህን ግዴታዎችን ለማስቀመጥ የተፈለገበት ዋናው ምክንያት ይህ አዋጅ ከወጣ በኋላ በሀገሪቱ ያለው የመሣሪያ አያያዝና አጠቃቀም ሁኔታ በዘፈቀደ ሳይሆን፣ በሥርዓትና በሕግ የሚመራ እንዲሆን በማሰብ ነው። ስለዚህ ግለሰቦች እነዚህን ግዴታዎች የማክበር ኃላፊነት ያለባቸው ሲሆን፣ እነዚህ ግዴታዎች የማይከበሩ ከሆኑ በሕጉ አግባብ ተቆጣጣሪው አካል እርምጃ ይወስዳል ማለት ነው።
የጦር መሣሪያ ፈቃድ የሚሰጠው መስፈርት ለሚያማላ እና ለሚታወቅ ሰው ብቻ እንደመሆኑ ይህ ፈቃድ የተሰጠው ሰው የጦር መሣሪያውን ለሌላ ሦስተኛ ወገን ወይም ሰው በማናቸውም መልኩ አሳልፎ እንዲሰጥ አይጠበቅም። ሆኖም የጦር መሣሪያውን አገልግሎት ሳይፈልገው የቀረ እንደሆነ ለተቆጣጣሪው ተቋም ማስረከብ አለበት።
ባለፍቃዱ የሞተ እንደሆነ በፍርድ ቤት የመውረስ መብት ያረጋገጠ ወራሽ የጦር መሣሪያው እንዲተላለፍለት ለመጠየቅ ይችላል፣ ሆኖም ወራሹ መስፈርቶችን የማያሟላ እና ፈቃድ ሊሰጠው ያልቻለ ከሆነ መስፈርቶችን ለሚያሟላ ለሌላ ወራሽ እንዲተላለፍለት ሊያደርግ ይችላል። ይህ እንዲሆን የተፈለገበት ዋናው ምክንያት በማህበረሰቡ ዘንድ የጦር መሣሪያ እንደ አንድ የሀብት ዓይነት ስለሚቆጠር፣ በቤተሰቦች መካከል የጦር መሣሪያው ልክ እንደ ውርስ ሀብት ተቆጥሮ የሚወረስበትን ሥርዓት ለመፍጠር ስለተፈለገ ነው። ሆኖም የጦር መሣሪያውን የሚወረስ አካል መስፈርቶቹን መሟላት ይኖርበታል። የመውረስ ሥርዓቱም የሚከናወነው ይህንን ሥራ እንዲሰራ ኃላፊነት የተሰጠው ተቆጣጣሪው አካል ነው። ስለዚህ በቤተሰቦች መካከል የሚደረገውን የጦር መሣሪያ ዝውውር በሕግና በሥርዓት እንዲመራ ለማድረግም ያግዛል ማለት ነው።
የወንጀል ተጠያቂነትን በተመለከተ፣
በ1996 ዓ.ም የወጣው የወንጀል ሕግ አንቀፅ 481 ላይ በጦር መሣሪያ መነገድን አስመልክቶ የወንጀል ድንጋጌ ያለው ሲሆን፣ ይህን የወንጀል ሕግ ማሻሻል ወይም መሻር አስፈላጊ ስላልሆነ፣ የአዋጁን የወንጀል ድንጋጌዎች ከወንጀል ሕጉ ጋር ተናባቢ እንዲሆኑ ተደርጓል። ስለዚህ የወንጀል ሕጉ አንቀፅ 481 ለአዋጁም ተፈፃሚ እንዲሆን የተደረገ ሲሆን፣ ሌሎች በወንጀል ሕጉ ያልተሸፈኑ የወንጀል ድንጋጌዎች በአዋጁ አንቀፅ 23 ላይ የተመለከቱ ሲሆን የእስራትና የገንዘብ ቅጣቱም የወንጀል ሕግ የቅጣት ድንጋጌዎችን አረቃቀቅ መርህ በመከተል ለጥፋቱ ተመጣጣኝ የሆነ የእሥራትና የገንዘብ መቀጮ ተቀምጧል።
በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ 2 ላይ የተመለከተው ብዛት በሌለው አኳኋን ሲፈጸም ሲሆን፣ በንዑስ አንቀፅ 3 ላይ የተመለከተው ድርጊቱ ብዛት ባለው ሁኔታ ሲፈጸም ነው። ብዛት ያለው ማለት ምን ማለት እንደሆነ በትርጉም ክፍል ላይ ትርጓሜ ተሰጥቶታል። የጉዳት ማድረሻ መሣሪያዎችን በተመለከተ ለግል ፍጆታ በሚሆን መልኩ መገልገል፣ መሸጥ፣ መግዛት ወዘተ በወንጀል ተጠያቂ አያደርግም። ሆኖም እነዚህን መሣሪያዎች ለኅብረተሰቡ አስጊ በሆነ አግባብ በብዛት መገልገል፣ መሸጥ፣ማስቀመጥ ወዘተ የወንጀል ተጠያቂነትን ያስከትላል። በጥቅሉ ወንጀሉ እስከአስራ አምስት ዓመት እና እስከ 100 ሺ ብር ቅጣት እንደሚያስከትል በአዋጁ ተመልክቷል።
የችግሩን አስከፊነት ከግምት ውስጥ በማስገባት የጦር መሣሪያ ማዘዋወር ተግባሩ የተፈጸመው በተሽከርካሪ አማካኝነት ከሆነ ተሽከርካሪው በጉምሩክ ኮሚሽን ውሳኔ ሊወረስ ይችላል።
ሌላው የመሸጋገሪያ ድንጋጌዎችን የሚመለከት ሲሆን፣ አዋጅ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ የሚሆንበት አንድ ዓመት የሽግግር ጊዜ ተሰጥቷል። በዚህም መሠረት አስቀድሞ ተመዝገበው ወይም ፍቃድ ተሰጥቷቸው የነበሩ የጦር መሣሪያ የመያዝና የመጠቀም ፍቃዶች በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተቆጣጣሪው ተቋም በሚያወጣው የጊዜ ሰሌዳ በአካል ቀርበው ድጋሚ ፍቃድ መጠየቅ እና በዚህ አዋጅ መሠረት የተመለከቱ መስፈርቶችን አሟልተው ወይም የሚያሟሉ ከሆነ በተቆጣጣሪ ተቋሙ ፈቃድ መውሰድ ይኖርባቸዋል።
(ማጣቀሻዎች፡-የጦር መሣሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር ዐዋጅ ማብራሪያ ሰነድ፣ ቢቢሲ፣ የጀርመን ድምጽ…)
አዲስ ዘመን ጥር 2/2012 ዓ.ም
ፍሬው አበበ