ከንግድ ስራቸው ባለፈ በቡራዩ አካባቢ በሀገር ሽማግሌነታቸው በእጅጉ ይታወቃሉ። አንድ አርሶ አደር ካለው መሬት ላይ የተወሰነውን ይዞ በተቀረው መሬት ላይ ባገኘው ካሳ ሰርቶ መለወጥ ይችላል የሚለውን አሳይተዋል። ከአባታቸው ከወረሱት መሬት ላይ በመዝናኛው ዘርፍ ገንዘባቸውን በማፍሰስ ውጤታማ መሆን ችለዋል። በሥራ ቦታቸው አባትነት በተላበሰው ቀረቤታቸው ሰራተኞቻቸውን የቤተሰብ ያህል እንደሚመለከቱ አብረዋቸው የሰሩ ይመሰክራሉ።
አቶ አለሙ ጫላ ይባላሉ። ትውልድና እድገታቸው በቡራዩ ከተማ ነው። ለቤተሰባቸው አራተኛ ልጅ ናቸው። ኦሮምኛን እና አማርኛን አቀላጥፈው ይናገራሉ። አባታቸው ሰፊ የእርሻ መሬት እና ለወተት የሚሆኑ ላሞች እንደነበራቸው ያስታውሳሉ።
ከልጅነታቸው ጀምሮ በእርሻ እና በወተት ምርት ላይ ቤተሰባቸው እያገዙ አድገዋል። እድሜያቸው ከፍ ሲልም አባታቸው ቄስ ትምህርት ቤት አስገቧቸው። በቡራዩ በሚገኘው ፀደንያ ስመሽ ማርያም ቤተክርስቲያን ውስጥ የተጀመረው ቄስ ትምህርት ቤት አድጎ የመጀመሪያ ደረጃ ሲከፈተበት አቶ አለሙም እዚያው ከመጀመሪያዎቹ ተማሪዎች መካከል ሆነው ቀጠሉ።
ከዚያም ሰባተኛ እና ስምንተኛ ክፍልን ፊታውራሪ ሃብተጊዮርጊስ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። ወደሁለተኛ ደረጃ ሲሸጋገሩ ግን አዲስ አበባ ድረስ እየሄዱ መማር ግድ ሆነባቸው። እናም ከመኖሪያ ቤታቸው 20 ኪሎሜትሮችን ርቆ ከሚገኘው መድኃኒያለም ትምህርት ቤት ድረስ በእግር እየተመላለሱ ተም ረዋል።
ከትምህርት ቤት መልስ ደግሞ ከብት በመጠበቅ እና የእርሻ ስራ ላይ በመሳተፍ ቤተሰባቸውን ያግዙ እንደነበር ያስታውሳሉ። አባታቸው ከራሳቸው ላሞች ወተት በማለብ እና በተጨማሪነት ከሌሎች ከብት አርቢዎች ወተት በመግዛት ሰብስበው አዲስ አበባ ወስደው ያስረክቡ ነበር። አቶ አለሙም በርካታ ቀናት ከትምህርት ቤት መልስ ወተት በመሰብሰብ አባታቸውን ይረዱ ነበር።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸው ሲጠናቀቅ ደግሞ በወጣትነታቸው ወደትዳር ገቡ። እናም በ1974 ዓ.ም ላይ ከሰፊው የአባታቸው መሬት ላይ የተወሰነው ተሰጥቷቸው በእርሻ መተዳደር ጀመሩ። ገብስ፣ ተልባ ፣ ስንዴ እና የተለያዩ ሰበሎችን እያለሙ ጠንካራ አርሶአደር መሆናቸው አስመስክረዋል። በወቅቱም የአካባቢያቸው ህብረት ስራ ማህበር ቁጥጥር ኃላፊ ሆነው እስከማገልገል የደረሰ አስተዋጸኦ ነበራቸው።
በ1980 ዓ.ም ላይ ደግሞ ከግብርናቸው ጎን የሚሰሩት ሥራ አገኙ። በደን ልማት ላይ የሚሰራ አገር አቀፍ ፕሮጀክት ውስጥ የደን ጥበቃዎች ተቆጣጣሪ ሆነው በ180 ብር ተቀጠሩ። ለደን ልማቱ ከነበራቸው ፍላጎትም የተነሳ ሌሊት ጭምር ይሰሩ እንደነበረ ይናገራሉ።
ከአዲስ አበባ እሰከ ባህር ዳር የደን ልማት በሚያከናውነው ፕሮጀክት የአቶ አየለ የደን ጥበቃዎች ቁጥጥር ስራ ውጤታማ በመሆኑ የሞራል ስንቅ ያገኙበት ጊዜ ነበር። በወቅቱ ለማገዶ የሚሆን እንጨት ወደ መጥፋት የደረሰበት እና ለሬሳ መቅበሪያ የብረት ሳጥን እንደነበር የሚያወሱት አቶ አየለ ያ ችግር ታልፎ በአካባቢው አሁን በተሻለ መልኩ ዕጽዋት እንዲበቅሉ ያደረገው የያኔው ሥራ ነው በማለት የፕሮጀክቱንም አስተዋጽኦ ያስረዳሉ። እስከ 1986 ዓ.ም በደን ልማቱ ተቆጣጣሪ ሆነው የተለያዩ የአማራ እና ኦሮሚያ አካባቢዎች ላይ ከሰሩ በኋላ ስራውን ለቀው ወጡ።
ከቅጥር ስራው ከለቀቁ በኋላ ግብርናቸው ላይ ሙሉ ለሙሉ ትኩረት አድርገው አባታቸው የጀመሩት የወተት ንግድ ላይ መሰማራቱን መረጡ። በጎን እርሻቸውን ሲከውኑ በጎን ደግሞ ላሞች ማርባት ጀመሩ። ረዳት የሚሆን አንድ ሰው ቀጥረው ወተት ከሚሸጡ ሰዎች ላይ እየሰበሰቡ ወደአዲስ አበባ መሸጡን ተያያዙት።
የወተቱ ንግዱ የተሻለ ገቢ ማምጣት በመጀመሩ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ቡራዩ ከታ በተባለ ቦታ ላይ አንድ መጠነኛ መጋዘን ገነቡ። መጋዘኑ በማከራየትም ኑሯቸውን ይደጉሙ ነበር። በ1991 ዓ.ም ላይ ደግሞ መጋዘኑን ለልማት ባንክ አስይዘው 250 ሺህ ብር ተበደሩ። ከዚያም አንድ የጭነት ተሽከርካሪ ገዝተው እንጨት ወደአዲስ አበባ በማመላለስ መነገድ ጀመሩ። ሾፌር ቀጥረው ንግዳቸውን ሲከውኑ ግን በመኖሪያ ግቢያቸው አካባቢ ደግሞ ከብቶች ያረቡ ነበር።
የግብርና ህይወታቸውን ከንግዱ ጋር አጣጥመው የቀጠሉት አቶ አለሙ ስለቀጣዩ ስራቸው ሲያስቡ አንድ ነገር ማድረግ እንዳለባቸው ያስባሉ። የቡራዩ ከተማ እድገት በየጊዜው መጨመሩን ሲረዱ እርሳቸውም ዘርፋቸውን ከከተማዋ እደገት ጋር ማጣጣም እንዳለባቸው ተገነዘቡ።
የቡራዩ ከተማ አስተዳደርን ለኢንቨስትመንት የሚሆን ቦታ ከአባታቸው መሬት ላይ እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ። አባታቸው አርፈው ስለነበር በአካባቢ ያሉት ወራሽ በመሆናቸው ከብዙ ልፋት በኋላ ከጠበቁት ያነሰ መሬት ተሰጣቸው። አቶ አለሙ እንደሚሉት የአባታቸው ሰፊ የእርሻ መሬት አንድ ቀበሌ ያክል ነበር። እናም 6ሺ900 ካሬ ሜትሩ ብቻ ለኢንቨስትመንት ተፈቅዶላቸው ቀሪው ከሁለት እጥፍ በላይ የሆነው መሬት ካሳ እንዲሰጣቸው ተወሰነ።
ከብዙ ክርክር በኋላ ለመሬቱ ካሳም 450 ሺህ ብር አገኙ። እናም ገንዘባቸውን አጠረቃቅመው የመዝናኛ ንግድ ውስጥ ለመግባት ሲወስኑ በመጀመሪያም መጋዘናቸውን በ230 ሺህ ብር ሸጡ፤ የጭነት ተሽከርካሪያቸውን ደግሞ በ85 ሺህ ብር በመሸጥ አቅማቸው አጠናከሩ።
አንድ አርሶ አደር በወሰደው ካሳ አማካኝነት የተሻለ ሥራ መስራት ይችላል የሚለውን ለማሳየት ጽኑ እምነት ነበረኝ የሚሉት አቶ አለሙ፣ አዲሱን ንግድ ለመጀመር በእልህ እንደተነሱ ይናገራሉ። ለኢንቨስትመንት በወሰዱት ፈቃድ ተመስርተው አንድ ሰርቪስ ቤት እና አምስት በሳር ቤት የተሰሩ ባህላዊ ይዘት ያላቸው መኝታ ቤቶችን ሰርተው መናፈሻቸውን በ2001 ዓ.ም ከፈቱ።
ከነ ድሬ ጫላ ብለው የሰየሙት የመዝናኛ ቦታ ቀስ በቀስ ታዋቂነቱ ሲጨምር ምግብ እና መጠጥ አገልግሎት አክለውበት መነገዱን ቀጠሉበት።መዝናኛ ቤታቸው እየታወቀ እና በብዙዎች ተወዳጅ እየሆነ ሲመጣ ማስፋፊያ በማድረግ ትርፋቸውን ማሳደግ ቻሉ።
ዘመናዊ አልጋዎችንም በመገንባት እና የሆቴል አገልግሎቱን በማሳደግ በቡራዩ ከተማ ተመራጭ መዝናኛ ማድረግ እንደቻሉ ይናገራሉ። አሁን ላይ የአቶ አለሙ መናፈሻ ውስጥ በባህላዊ መንገድ የተሰራ ባር እና የቢሮ አገልግሎት የሚሰጡ ክፍሎች አሉ። ከዚህ በተጨማሪ 20 አልጋዎች አሏቸው። ከ150 ብር ጀምሮ ከፍ እያሉ የሚሄዱ ዋጋ ያላቸው አልጋዎች በየቀኑ ጥሩ ገቢን ይዘውላቸው እየመጡ ነው።
መናፈሻቸውንም በተለያዩ ሃውልቶች እና አበባዎች በማስዋብ በርካታ ሰርጎችን አስተናግደውበታል። በተለይ አንድ ሺህ ሰው የሚይዘው እና ወንበሮች የተሟሉለት ሰፊው አዳራሻቸው በየሳምንቱ የተለያዩ ስብሰባዎችን እና ሰርጎችን ያስተናግዳል። ለአንድ ሰርግ ከ20 ሺ ብር በላይ ያስከፍላሉ። ከዚህ በተጨማሪ በጀመሩት ንግድ ለስራ እና ቤትም የሚሆኑ ዘመናዊ ተሽከርካሪዎች ባለቤት ናቸው።
አቶ አለሙ አሁን ላይ በመዝናኛቸው ውስጥ 17 ሰራተኞችን ቀጥረዋል። በስራቸው ለሚገኙ ሰራተኞች ዝቅተኛው ክፍያ አንድ ሺህ ብር ነው። ምግብ እና የተለያዩ ወጪዎቻቸውን ችለው ሥራ ያስለመዷቸው ወጣቶች መኖራቸውን የሚመሰክሩ በርካቶች ናቸው። ከሰራተኞቻቸው ጋር ቤተሰባዊ ቅርርብ እንዳላቸው እና አባታዊ ምክራቸውን እየሰጡ ቁጥጥር ስለሚያደርጉ መዝናኛውን እንደእራሳቸው የሚንከባከቡ ሰራተኞችም መኖራቸውን አቶ አለሙ ይናገራሉ።
አቶ አለሙ ከንግድ ህይወታቸው ባለፈ በከተማው ታዋቂ የሀገር ሽማግሌም ናቸው። ሰው ሲጣላ አስታራቂ እና መካሪም ጭምር መሆናቸውን የሚያውቋቸው ይመሰክራሉ። ከ2002 ዓ.ም እስከ 2007 ዓ.ም ድረስ የጨፌ ኦሮሚያ አባል በመሆን ከንግዱ ባለፈ በፖለቲካ እና ማህበራዊ ጉዳዮችም ላይ ሰፊ ተሳትፎ ሲያደርጉ ቆይተዋል።
የመናፈሻው ባለቤት ዘርፈ ብዙ ሰው መሆናቸውን አሁንም እያሳዩ ይገኛል። በመኖሪያ አካባቢያቸው በሚገኝ ከአንድ ሺ ካሬ ሜትር በላይ በሆነ ቦታ ላይ አምስት የፈረንጅ ከብቶችን እያረቡ ይገኛል። ለቤተሰብ እና ለመናፈሻቸው የሚሆን ወተትም ከሚያረቧቸው ላሞች ያገኛሉ። ከዚህ በተረፈ ለሌሎችም ይሸጣሉ። ነገም ከብቶችን በሰፊው በማርባት የተሻለ ሥራ ማከናወን ውጥናቸው ነው።
የአቶ አለሙ ቀጣይ ዕቅድ ለቡራዩ ከተማ የሚመጥን ክሊኒክ መክፈት ነው። ለዚህ የሚሆን አስተዳደራዊ ድጋፍ ከሌላው ጊዜ በተሻለ አሁን ላይ መኖሩን በማስታወስ የመሬት ጥያቄ አቅርበው በጎ ምላሽ ከከተማው ማዘጋጃ ቤት ማግኘታቸውን ይናገራሉ። በመሆኑም ህብረተሰቡን በጤናው መስክ የሚረዳ ብሎም ለእርሳቸው ገቢ የሚያስገኝ ክሊኒክ ለመክፈት ዝግጅት ላይ ናቸው። የክሊኒኩ አጠቃላይ ወጪ ሦስት ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅ ከወዲሁ ቅድመ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
አንድ አርሶ አደር ከነበረው መሬት የተወሰነው ላይ ካሳ ተቀብሎ በቀረው ሰርቶ መለወጥ እንደሚችል የነበረኝ እምነት በእራሴ አሳክቼዋለሁ የሚሉት አቶ አለሙ፤ ይህ ልምድ በብዙዎች ዘንድ እንዲበራከት ሁሉም ሰው ጥረት ሊያደርግ እንደሚገባ ይናገራሉ። አርሶአደሩም የእርሳቸውን ተሞክሮ በመውሰድ በኖርኩበት መሬት ላይ የተወሰነውን ሰርቼበት መለወጥ እችላለሁ የሚል ጽኑ እምነት በማንገብ የተሻለ ደረጃ መድረስ እንደሚችል ያስረዳሉ።
ወጣቱም በየአካባቢው ያለውን የስራ እድል በማጥናት ቢሰማራ ከእራሱ አልፎ ለሀገሩም የሚተርፍ ዜጋ መሆን ይችላል። ሁል ጊዜ የቤተሰብ እጅ ጠባቂ ከመሆን ሰርቶ ስለመለወጥ የሚያስብ ወጣት ለሌሎችም መትረፍ ይችላልና ማንኛውም ሰው ጊዜውን በአልባሌ ነገር ማባከን አይኖርበትም የሚለው ደግሞ ምክራቸው ነው።
አዲስ ዘመን ጥር 2/2012 ዓ.ም
ጌትነት ተስፋማርያም