ጠዋት ከእንቅልፋችን ስንነሳ ወይም ስንባንን ሰፈር ውስጥ እንቅልፍ የሌላቸውን የማሳኞች ድምጽ እንሰማለን። ቤታችን በተለይ በመንገዶች ዳርቻ ከሆነ የታክሲዎቹ ጥሩምባ፣ የመኪናዎቹ የጉዞ ድምጽ፣ የቆራሌው የማግባቢያ ጩኸት፣ የማለዳ ቆሻሻ አፋሾች ድምጽ፣ የመንገድ ጠራጊዎቹ መጠራራት ይሰማናል። እነዚህን ማለደኞች ያነቃው የህይወት ጥሪ እኛን ባይጎተጉተንም እነርሱ ለእኛ ደህንነት ለራሳቸውም እንጀራ ለመማሰን መነሳታቸውን እንገነዘባለን። ይህንን ያነሳሁላችሁ እኛ ብንተኛ የነቁ፣ እኛ ቸል ብንል የሚቆረቆሩ ሰዎች፣ እኛ ብንዘናጋም የሚያስታውሱ የህይወት ተረኞች በየትኛውም የህይወት ሰፈር መኖራቸውን ለማስታወስና “እኛስ ምን እናድርግ?” ልላችሁ ፈልጌ ነው።
ደርሶ ችግር ሲገጥመን “ምን ላድርግ፣” ወይም “ምን ታደርገዋለህ፤” ብለን እንደምናልፈው ዓይነት የተለመደ መጠቅለያ የመሰለ ንግግር ሳይሆን የእውነት “እኛስ የድርሻችንን እየተወጣን ነውን” ብዬ መጠየቅ ስለፈለግሁ ነው። በዚህ ሁካታና ግርግር በሞላበት ዓለም ምንም ሳላደርግ በፀጥታ አልፋለሁ፤ ማለት መቼም ዘበት ነው፤ ፀጥታ እንኳን ባይኖር በትዝብት ማየት አለመቻል ትንሽ በድንነት ይጠይቃል። ምክንያቱም እኛ የዚህ ግርግር የተሞላው ዓለም አካል ነንና ።
ሃገራችን ኢትዮጵያ ሰሞኑን ሰቀቀናም ከሆነውና ጆሮን ከሚቆረቁር የሽሽትና የግፊያ ወሬ ተንፈስ ብላ ፣ (በአፋቸው የሚጋፉና የሚገፉ ክፉዎች ባይጠፉም ) ደጋግ ዜናዎችን እያሰማችን ነው። የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የኖቤል ሽልማትና የኦስሎው ንግግር፣ የፍሬወይኒ መብራህቱ የሲ ኤን ኤን የዓመቱ ምርጥ የሥራ-ሰው ተሸላሚነት የዶክተር መሐመድ አባኦሊ በተፈጥሮ ሃብት ዘርፍ “በባዮ ማስ ዴንሲቲ” ላይ በሰራው የምርምር ሥራ ፣ ቀዳሚ ተመራማሪ መደረጉና ለሽልማት መታጨቱ፣ እና ሌሎችም በየሙያ ዘርፋቸው… ያገኙት የክብር ስምና ዝና የኢትዮጵያ ነውና ፣ ፍንድቅ የሚያደርጉ ክንውኖቻችን ናቸው።
ጆሮ ደግ ሲሰማ፣ ልብም ደግ ያሰባል፤ አንደበትም እንዲሁ። እኛ ግን፣ ሃገራችን እስካሁን ያየችው ድንቅ ከገጠማት ፈተናና ካየችው አበሳ አንጻር ጥቂት መሆኑን ተገንዝበን ለብዙ ሥራ መዘጋጀት ይጠበቅብናል። ከብዙዎቹ ሥራዎቻችንም ዋነኛው የሚመስለን “ምን ደግ ልንሰራ ይገባናል” ብለን ለማሰብ መዘጋጀትና ያንንም መናገራችን ነው። በመናገር ውስጥ ራስን መግለጽም አለና። ክፉዎች በሚናገሩት የምንቀየመውንና የሚከፋንን ያህል እኛ ደግሞ ስለሃገራችን፣ ስለመሪዎቻችን፣ ስለተመራማሪዎቻችን፣ ስለበጎ ሰዎቻችን እና ስራዎቻቸው ፣ ደጋግና መልካም ነገር በመናገር ክፋትን ማስቀየም አለብን ። “ክፉዎችን” አላልኩም፤ ምክንያቱም ጉዳያችን ከሃሳባቸው እንጂ ከአሳቢዎቹ ጋር አይደለምና።
አንዳንድ ሰዎች እንዲያውም ብዙ ሰዎች ማለት እንችላለን የሚሳሳቱት፣ ከሃሳቡ ይልቅ አሳቢው ላይ፤ ከንግግሩ ይልቅ ተናጋሪው ላይ በማተኮር ማብጠልጠል ስለሚቀናቸው ነው። “እርሱን አናውቀውም እንዴ?” “የማን ልጅ እንደሆነ ድሮ የሰራውን እያንዳንዷን ነገር ሁሉ ልንንገረው እንችላለን” ይላሉ፤ ቅር ያሰኛቸው ግን ዘንድሮና አሁን የተናገረው ንግግር ነው። ዘንድሮ ላይ ከድሮው ማንነቱ ችግር ይዋሱለትና (ይበደሩና ) ይወነጅሉታል። ብዙ ጊዜ እግዚአብሔርም ሰውም የረሳውን ጥፋቱን ነው፤ የሚያነሱት። ግባቸው ዛሬ ያሳየውን ብርታት በማሸማቀቅ ወደኋላ ለማስቀረትና መንገዱን እንዲለውጥ ለመገፋፋት እንጂ፣ በዘንድሮው ንግግር ውስጥ ስህተት አግኝተው አይደለም። የህመማቸው መንስዔ የእርሱ በዚህ ጊዜ ጎልቶ መውጣቱና የእነርሱን ትንሽነት ማሳየቱ ነው።
በአሮጌ ሃሳብ፣ አዲሱን አካሄድ መታገል ስለማይሆንላቸው፤ በድሮ ሃጢያቱ ሊያስጠሩት፣ ሊያስንቁትና አንዲት ጋት በግስጋሴው ላይ እንዳይጨምር ለማድረግና ለማደነቃቀፍ ነው፤ የሚጥሩት ።
እንዲህ ሲያደርጉ፣ ታዲያ “እኛ ምን እናድርግ ?” ለክፋቱ ክፋት፣ ለጩኸታቸው ጩኸት መመለስ ለአጥፊዎቹ የአነባበሮ እንጀራ፤ አለዚያም ለክብሪታቸው ቤንዚን መሆን ነው። ለቀስቃሹ ቀስቃሽ መድቦ መነታረክም፤ ሁከቱን ማባበስና ክፉዎች የሚፈልጉትን ነገር ማሳካት ነው። ጉዞውን በማሳደግ ከከፍታው ባለመውረድ በአጀንዳውና በመልካሙ ድርጊት መርሐ- ግብር ላይ ማተኮር ይገባል። በከፍታ ለማስቀጠል የሜትር ባንዱን ከፍታና ጥራት ጨምሮ ከላይ መንሳፈፍ ነው። ከዚያ ይልቅ መነታረክ ግን፣ ወደታች መውረድ ነው፤ ከዓላማ መዘናጋት ነው፤ ክብርን መልቀቅ ነው። ሊያወርዷችሁ ሲሞክሩ አትውረዱላቸው ማለት አውራጆቹን፣ አዋርዷቸው ማለትም አይደለም። አብረናቸው አንንጫጫ ማለት እንጂ።
ይህንን ሁልጊዜ የህይወትና የአካሄድ መርህ ማድረግ በማንኛውም የሥራ መስክ አዋጭ ነው። በእምነቶችም ሆነ፣ በተፎካካሪ ድርጅቶች፤ በተወዳዳሪ የዕቃ አምራቾች መካከል፣ በልዩ ልዩ ባንኮችና ኢንተርፕራይዞች አማካይነት ደንበኞቻቸውን ለመያዝ ተወዳዳሪውን በማንኳሰስ ላይ መሰማራት የእነርሱን ክብርና ዝና ከፍ አያደርገውም ፤ የራሳቸውን የአሰራር ጥራት፣ ለደንበኛው ያለውን ጥቅምና ቀሊልነት፣ በስልት በማሳየት መሸጥ ነው፤ ያለባቸው። ዘመኑ ሃሳብ የሚሸጥበት የሀሳብ ገበያ የደራበት እንጂ እንደማፊያ አለቃዎች ሌላው የሰራውን በማፍረስ የራስን ያለፈበት ሸቀጥና ሃሳብ በገበያው ላይ ተፈላጊ ለማድረግ በመጣር “ሁሉንም ወይም ምንም” እያሉ መንገታገት የትም አያደርስንም፤ ለማንም አይጠቅምም።
የእኔ መንገድ ብቸኛውና አዋጪው ነው፤ ወደ ብሩሁ ጎዳናው የሚያወጣችሁ ማረፊያው መንገድ ነው፤ ብሎ መገበዝና ሌላውን ማጣጣል፣ ከሌላው ጋር መቆም ከእኔ ጋር ጦርነት ውስጥ መግባት ነው፤ ብሎ ማስፈራራት የጨለማ አስተሳሰብ ነው። ድሮ ልጆች ሆነን አንዳንድ የሰፈር ጎረምሶች (“መንደር ገነን” ይሏቸዋል አንዳንዶች) ፤ “ሽልንጌን ያዝልኝ” ይሏችሁና ባልታሰበ መንገድ ቢጠፋባችሁና ሌላ ሽልንግ ከቤት አምጥታችሁ፣ ብትሰጧቸው እንኳን አይለቋችሁም። በየጊዜው የምትሰጧቸውን ሽልንግ እየወሰዱ፤ የእኔን ሽልንግ “ራሷን ፈልገህ ስጠኝ” ብለው፣ ችክ ይሉባችኋል። በጉልበታቸው ተመክተው እስኪተውአችሁም ወይም ሰፈር እስክትቀይሩና እስክትገላገሏቸው ድረስ፣ የአዳዲስ ሽልንግ ገባሪ ያደርጓችኋል።
የእኛ ሐገር ነገር እንደዚህ ይመስለኛል፤ ዓላማው አንድ የሆነን ነገር በአዲስና በተሻለ መንገድ ብታቀርቡላቸውም ፣ እኔ ባልኩት መንገድ ካልሆነ ብለው ችክ የሚሉ ገትሮች (መንቻኬዎች ይላቸዋል ወዳጄ) ጥቂት አይደሉም። ሁሉም ወገኖች የሚሸነፉበትን ሳይሆን ወይም አንዱ ወገን ብቻ አሸናፊ ሆኖ የሚወጣበትን ሳይሆን ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበትንና አንዱን በዳይ ሌላውን ተበዳይ፤ አንዱን ጨቋኝና ሌላውን ተጨቋኝ የማያደርግ አካሄድ ነው፤ ሊኖረን የሚገባው። ይህም መገፋፋትንና ሁከትን በማስቀረት መረጋጋትን በቤትም በአደባባይም ያመጣል።
እነርሱ ሊያደርጉ የሚገባው ብቻ ሳይሆን እኛ በእለት ተእለት ህይወታችን ይህን በመፈጸም ህይወትን ቀሊል ማድረግ ይገባናል። ህይወትን ከባድ ማድረግ ለከበደበት ብቻ ሳይሆን ለአክባጁም ሰላምና ጤና አይሆንም። ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን ሮባ፤ በአንድ ግጥሙ ላይ ለሞዛምቢኩ የነጻነት ተሟጋች (ፍሬሊሞን ቀድሞ የመሰረተው እርሱ ነበረ።) ለኤድዋርድ ሞንድላኔ በጻፈው ግጥም ላይ፣ ቅኝ ገዢዎቹን ፖርቱጋሎች በሞዛምቢክ የነጻነት ጉዳይ በአሸማጋይ ወገኖች ከተደራደሩ በኋላ ሲመለስ ገደሉት። ያኔም እንዲህ ሲል ገጠመለት፡-
“ወንድሜ የተወጋ እንኳን ቢረሳም፣
የወጋ እንቅልፍ የለውም ።” (እሳት ወይ አበባ) ብሎ ነበረ።
(እኔም እለዋለሁ።) ወንድም ዓለም፣
የታገልካቸው ክፉዎች አያውቋትም እኮ ይቅርታን ፤
እንደመገዘዝ አቀበት ይሄዳሉ፤ እንጂ ዙሪያዋን ።
የነጻነትን ዋጋ ቢያውቁም ፤
በነጻነት መራመድን ግን፣ ለሌላው ከቶ አይፈቅዱም።
ስለዚህ፣ ክፉዎች ወደልባቸው ቢመጡና ለሁሉም የጋራ ሰላምና መልካምነት ቢቆሙ ለሃገር ደግ ነው። ገና ለገና አልመጡም ተብሎ ግን እንደክፉዎቹ፣ በሁካታና በግርግር መነሳት ለሁላችንም በጎ ውጤት የለውም። ለእኛ የሚጠቅመን አባቶቻችን እንደሚሉት፣ “ለምጣዱ ሲባል ዓይጢቱ እንድታልፍ መፍቀድ” ነው ። ምጣዲቱ ደግሞ ሃገራችን ናት ፤ ምጣዲቱ የተሰራችበት ድርና ማግ እንዳይበላሽ በማድረግ በጥበብና በብልሃት፣ በመቻቻልና በህብረት መስራትና መልከ-መልካሞቹን ነገሮቻችን በማስቀጠል የምጣዷን ልዩ ልዩ እንጀራ በእኩል ለመቃመስ በመደማመጥ መነሳት ነው ፤ ያለብን።
አንድ ጊዜ ፤ ከአበበ ቢቂላ ተከታታይ የሮምና ቶኪዮ የኦሎምፒክ ድሎች ማግስት፣ አትሌት ማሞ ወልዴ ለእርሱ፣ የመጀመሪያውን የማራቶን ውድድር በሜክሲኮ ኦሎምፒክ ላይ ካሸነፈ በኋላ የውጭ ዜጎች በእንኮኮ ትከሻቸው ላይ ይዘውት ሲጨፍሩ እግሩን ክፉኛ ስለጠመዘዙት፣ ፣ “እግሬን !” ሲል ይጮሃል፤ ይህንን የሰሙት አድናቂዎቹ በቋንቋው የጀግና ጩኸት መስሏቸው ፣ ደግመው “እግሬን!” ሲሉ ጮኹ፤ ህመሙ የባሰበት ማሞ ወልዴም፣ “ኧረ እግሬን” ብሎ ሲጮህ ደግመው “እግሬን!” ሲሉ ተሸካሚዎቹ የሜክሲኮ ሰዎች ጭፈራውን መቀጠላቸው ይነገራል(ምስኪን ማሞ)። እኛ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ነን፤ በምንሰማው ቋንቋ ነው፤ እውነተኞቹም ዋሾዎቹም የሚነግሩን። የተነገረውን ነገር ሁሉ ሳይገባን መልሰን የምናስተጋባ ከሆነ ለማንም አይበጅም። ምን ለምን እንደተባለ ቆም ብለን አስበን ፤ ለሃገራችንና ለህዝቡ የሚጠቅመውን መፈጸም ነው፤ የሚገባን።
ሲዝቱ ከዛትን፣ ሲያቅራሩ ካቅራራን፣ ሲያንኳስሱን ካንኳሰስን፣ ሲጮሁ ከጮህን እነርሱን መሆን ነው። ትርፉ መጩዋጩዋህ ነው፤ የሚሆነው። ስለዚህ በብዙ ማስተዋልና በብዙ ትእግስት የክፋት ትጥቃቸውን በማስፈታትና ግጭት በማስራብ፣ ደም ማፋሰስን ማስቀረትና ወደተፈለገው ሰላማዊ ግብ መገስገስ ነው። ለዚህ ሁሉ ትእግስት የተመላበት እርምጃ ያሻቸውን ስም ቢሰጡትም ከግብ ተናጥቦ አለመደነቃቀፍ ነው፤ የሚያዋጣው።
በአጭሩ፣ ያደመጥነውን ሁሉ ለመናገር ባለመቸኮል ራሳችንን ከመጠበቅ ባለፈ፣ ስናስብም መልካም ማሰብን አንርሳ፤ ስንናገርም መልካም መናገርን አንዘንጋ፤ ስናደርግም መልካም ማድረግን መርሳት የለብንም ። አንዳንዴ ግን የምናደርጋቸው መልካም ነገሮች እውነተኛነት ቢኖራቸውም፣ ከሚጠቅሙት ይልቅ የሚጎዱት፣ ከሚገነቡት ይልቅ የሚያፈርሱት ካለ፣ በጥንቃቄ መናገርና ማድረግ እንዳለብን መዘንጋት የለብንም። ምክንያቱም ማሰብ አይተላለፍም፤ መናገርና ማድረግ ግን የአዎንታዊነትን ያህል አሉታዊ ሃይል እንዳላቸው ማስታወስ ይገባናል። እዚህ ላይ የማሰብ ኃይልን በማቃለል እንዳልተናገርኩ ልብ ይባልልኛል ብዬ አምናለሁ። ግን እኛም፣ መልካም እየተናገርንና እያደረግን የክፉዎችን ክፋት እያረምን እንጓዝ፤ ደግ ያክርመን !
መልካም የዕፎይታ ሳምንት ለእኛና ለሃገራችን ይሁን!!
አዲስ ዘመን ጥር 2/2012 ዓ.ም
ከአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ