ጋምቤላ፡- ከክልሉ አቅም በላይ የሆኑ ችግሮች በመኖራቸው የፌዴራል መንግስት ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ የጋምቤል ክልል ጠየቀ፡፡ የክልሉ ምክር ቤት አባላት በክልሉ ሁሉም ቀበሌዎች፣ ወረዳዎችና ዞኖች በመንቀሳቀስ ሕዝባዊ ውይይት እያደረጉ ሲሆን በዚህም የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች፣ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችና ማህበራዊ ትስስሮችን ማጠናከር ትኩረት ተሰጥቷል፡፡
የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ ላክዴር ላክባክ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል እንደገለፁት፤ የምክር ቤቱ አባላት ከታህሳስ 19 ቀን 2012 ዓ.ም በሁሉም የክልሉ ወረዳዎች በመንቀሳቀስ ከህዝብ ጋር ውይይት ጀምረዋል፡፡ አመራሩ ጠንካራ ሱፐርቪዥን ሥራ እያከናወነ ሲሆን በጅምር የቀሩ የልማት ሥራዎች እንዲፋጠኑ፣ ያልተጀመሩ ትኩረት እንዲሰጣቸው እና እየተሰሩ ያሉት ደግሞ መፋጠን በሚችሉበት ላይ ምክክር እየተደረገ ነው፡፡
እንደ አቶ ላክዴር መግለጫ በአሁኑ ወቅት በዋናነት በክልሉ በተለያዩ ወቅቶች የተፈናቀሉ ዜጎች ወደቀዬያቸው እየተመለሱ ነው፡፡ ይሁንና ያልተሟሉ መሠረተ ልማቶች በመኖራቸው ሥራው የታሰበውን ያክል ስኬታማ አልሆነም፡፡ ከህዝብ ጋር በተደረገ ምክክር እንደ ክልል የመንገድ፣ ውሃ፣ መብራት፣ ቴሌኮም እና ሌሎች መሠረተ ልማቶች ተደራሽነት በቂ ባለመሆኑ ጥያቄዎች በሰፊው ተነስተዋል፡፡
ከመልካም አስተዳደር ጋር በተያያዘ ውስጣዊና ውጫዊ ክፍተቶችን በመጠቀም የፀጥታ ችግር እየተፈጠረ ነው፡፡ በተለይም የእርስ በእርስ ግጭት ዋነኛ ውስጣዊ ችግር ሆኖ ቆይቷል፡፡ ከውጭ ደግሞ ከደቡብ ሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ድንበር በመግባት ጥቃት የሚያደርሱ የሙርሌ ጎሳዎች ስጋት ሆነዋል፡፡
ቀደም ሲል ከተከሰቱ ድንበር ዘለል ጥቃቶች 75 ከመቶ የሚሆነውን የፌዴራል መንግስት ጣልቃ ገብቶበት መፍትሄ ተበጅቷል፡፡ የታገቱ ህፃናትም ወደቤተሰባቸው ተመልሰዋል፡፡ ይሁንና የተዘረፉ እንስሳት እስካሁን አልተመለሱም፡፡ ይህ ጉዳይ እስካሁን አጀንዳ ሆኖ የቀጠለ ሲሆን፤ በቀጣይ ችግሮች እንዳይከሰቱም ዳር ያሉ ወረዳ እና ቀበሌዎች ላይ በሰፊው እየተሰራ ነው፡፡ ይሁንና እነዚህ ጥያቄዎች በክልሉ አቅም ብቻ የሚመለሱ ባለመሆናቸው የፌዴራል መንግስት ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ አቶ ላክዴር ጠይቀዋል፡፡
እንደ አቶ ላክዴር ገለፃ፤ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያም ዝውውርም ከፍተኛ ስጋት ሆኗል፡፡ በደቡብ ሱዳን ያለው ችግር በኢትዮጵያ በተለይም ደግሞ በጋምቤላ ክልል ላይ ጫና ፈጥሯል ይህንንም በመጠቀም አንዳንዶች ህገ ወጥ የመሣሪያ ዝውውርን ቢዝነስ አድርገውታል ብለዋል፡፡ ከባሮ ወንዝ ውሃ ሙላት ጋ በተያያዘም ተማሪዎች በወቅቱ ትምህርት ቤት እንደማይሄዱና ትምህርት ሳይጠናቀቅ እንደሚያቋርጡ ጠቁመዋል፡፡
አፈጉባኤው እንዳሉት፤ በክልሉ ያለው የኤች አይ ቪ ስርጭትም አሳሳቢ በመሆኑ ትኩረት የተሰጠው ሲሆን የጤና ተቋማትም በሚገባ መሰራት እንዳለባቸውና ከአምቡላንስ ተደራሽነት አኳያም ክፍተት በመኖሩም በዚህም ላይ እየተመከረ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የእናቶችና ህፃናት ጤና ላይም በሰፊው መመከር እንዳለበት አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ ትምህርት ያልደረሰባቸው አካባቢዎች ጋር በተያያዘም የክልሉ ምክር ቤት ትኩረት ሰጥቷል ብለዋል፡፡ በክልሉ አንዳንድ ወረዳዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የመኪና ጎማ የረገጣቸው በ2011 ዓ.ም ሲሆን በቀጣይ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ በሰፊው መሰራት እንዳለበት ተወስኗል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 2/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር