ሰዎች ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብታቸውን ሲጠቀሙ ግጭት ወይም ሁከትን የሚቀሰቅስ ወይም ብሄርን፤ ሀይማኖትን፤ ዘርን፣ ጾታን ወይም አካል ጉዳተኝነትን መሰረት በማድረግ በግለሰብ ወይም በተለየ ቡድን ላይ ጥላቻ ወይም መድልዎ የሚያስፋፋ ንግግር ከማድረግ እንዲቆጠቡ ለማድረግ፤ መቻቻልን፣ የዜጎች ውይይትና ምክክርን፣ መከባበርና መግባባትን ማበረታታትና ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን ማጎልበት፤የጥላቻ ንግግርን፣ የሃሰተኛ መረጃና ተያያዥነት ያላቸውን ሌሎች የውሸትና አሳሳች መረጃዎችን ስርጭትና መበራከትን ለመቆጣጠርና መግታት እንዲቻል አዋጅ ተዘጋጅቷል። ለመሆኑ የጥላቻ ንግግር ሲባል ምን ማለት ነው? አዋጁን ጥሶ የተገኘስ ምን ይበየንበታል? አዋጁ ተከታዩን ማብራሪያ አስቀምጧል።
በአንቀጽ 2(2) መሰረት የጥላቻ ንግግር ማለት በአንድ ሰው ወይም የተወሰነ ቡድን ላይ ያነጣጠረ፣ ብሄርን፤ ሀይማኖትን፤ ዘርን፣ ጾታን ወይም አካል ጉዳተኝነትን መሰረት በማድረግ ጥላቻን፣ መድሎን ወይም ጥቃትን የሚያበረታታ ንግግር ነው። በአንቀጽ 5 የሃሰት መረጃን በብሮድካስት፣ በህትመት ወይም በማህበራዊ ሚዲያ በጽሁፍ፣ በምስል፣ በድምጽ ወይም በቪዲዮ ማሰራጨት የተከለከለ መሆኑን ይደነግጋል። በአንቀጽ 2(3) መሰረት “ሃስተኛ መረጃ” ውሸት የሆነና የመረጃውን ውሸት መሆኑን በሚያውቅ፣ ወይም መረጃውን የሚያሰራጨው ሰው ካለበት አጠቃላይ ሁኔታ አንጻር የመረጃውን ሃሰተኝነት ሊያውቅ ይገባ ነበር የሚያስብል በቂ ምክንያት እያለ የሚሰራጭ ሁከት ወይም ግጭት የማስነሳት፣ ወይም ጥቃት እንዲደርስ የማድረግ እድሉ ከፍ ያለ ንግግር ነው።
በአዋጁ አንቀጽ 7 ስር የጥላቻ ንግግር እና ሀሰተኛ መረጃ ማሰራጨት ወንጀሎች የሚያስቀጡትን ቅጣቶች ይደነግጋል። የጥላቻ ንግግርን በተመለከተ በንዑስ ቁጥር 1 ላይ የተቀመጠው በአዋጁ አንቀጽ 4 የተመለከቱትን ወንጀሎች መፈጸም እስከ ሶስት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት ወይም ከመቶ ሺህ ብር ያልበለጠ መቀጮ እንደሚያስቀጣ፤ በዚህ አዋጅ አንቀፅ 4 የተከለከሉት ተግባራት በመፈጸማቸው የተነሳ በግለሰብ ወይም በቡድን ላይ ጥቃት የተፈጸመ ወይም የተሞከረ ከሆነ በአንቀጹ የተከለከሉትን ተግባራት የፈጸመ ሰው እንደነገሩ ሁኔታ እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚቀጣይደነግጋል።
በሌላ በኩል የሀሰተኛ መረጃ ማሰራጨትን በተመለከተ ማንም ሰው በዚህ አዋጅ አንቀፅ 5 የተመለከተውን የተከለከለ ተግባር የፈጸመ እንደሆነ እንደነገሩ ሁኔታ እስከ አንድ ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት ወይም ከሀምሳ ሺህ ብር ያልበለጠ መቀጮ እንደሚቀጣ፤ በዚህ አዋጅ አንቀፅ 5 የተመለከተውን የተከለከለ ተግባር የፈጸመው ሰው ድርጊቱን የፈጸመው ከአምስት ሺ በላይ ተከታይ ባለው የማህበራዊ ሚዲያ ገጽ ከሆነ ወይም በብሮድካስት አገልግሎት ወይም በየጊዜው በሚወጣ የህትመት ውጤት ከሆነ ሶስት ዓመት በሚደርስ በቀላል እስራት ወይም ከብር 100,000 ያልበለጠ መቀጮ እንደሚቀጣ፤ በዚህ አዋጅ አንቀፅ 5 የተከለከለው ተግባር በመፈጸሙ በግለሰብ ወይም በቡድን ላይ ጥቃት የተፈጸመ ወይም የተሞከረ ከሆነ፣ ሁከት ወይም ግጭት የተከሰተ እንደሆነ የአንቀጽ 5 ድርጊትን የፈጸመ ሰው እንደነገሩ ሁኔታ እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚቀጣ ይደነግጋል።
ከዚህ በተጨማሪ ፍርድ ቤት በዚህ አዋጅ የወንጀል ተጠያቂ የሆነ ሰውን ለማረም የተሻለ ነው ብሎ ሲያምንና የተከለከለው ተግባር በመፈጸሙ በግለሰብ ወይም በቡድን ላይ ጥቃት ያልተፈጸመ ወይም ያልተሞከረ ከሆነ፣ ሁከት ወይም ግጭት ያልተከሰተ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ በእስራት ምትክ የማህበረሰብ አገልግሎት ስራን በአማራጭ ቅጣትነት ሊወስን እንደሚችል ይደነግጋል።
አዲስ ዘመን ጥር 1/2012
አዲሱ ገረመው