ኢትዮጵያ በተፈጥሮዋ የታደለች አገር ነች፡፡ መልክዓ ምድሯ ቆላ፣ወይና ደጋና ደጋ የተቸረ ነው፤ የአየር ጠባይዋም ለሰው ለእንስሳትና ዕፅዋት ዕድገት ተስማሚ ነው፡፡ ዓመቱን ሙሉ የፀሐይ ኃይልና ወቅታዊ ዝናብ የማይለያት አገር ነች። ከዚህ ምቹ ተፈጥሮ በመነሳት ለመድኃኒትነት የሚፈለጉት ዕፅዋት ከሌሎች አገሮች በተሻለ ሁኔታ መገኘት እንዲችሉ አድርጓል፡፡ በተጨማሪም የማዳን ሃይላቸው የዚያኑ ያህል ከፍተኛ እንዲሆን ማስቻሉን የዘርፉ አጥኝዎች ይጠቅሳሉ፡፡
እጽዋትን ለመድሐኒትነት መጠቀም መቼ ተጀመረ?
የኢትዮጵያ መድኃኒትና ሕክምና ዕውቀት ከሰው ፍጥረት እንደተጀመረ የሚጠቅሱ አሉ፡፡ በልማድ ብቻ ሳይሆን በየዘመናቱ በሕገልቦና፣ በኦሪት በሐዲስ፣ እስካለንበት ጊዜም በልምድና በጽሁፍ እየዳበረ የመጣ መሆኑ ይነገራል፡፡ ከአዳም፣ ከሄኖክ፣ ከኖህ ከመልከ ጸዴቅ፣ ከሙሴና ከአብርሃም ኮዳሸት፣ ወዘተ ጊዜ ጀምሮ እያደገ የመጣ ስለመሆኑም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
የባህል መድሐኒቶች ከተፈጥሮ እጽዋት፣ማዕድናትና ሌሎች ተፈጥሯዊ ግብዓቶች መጠቀም ከ15ኛው ክፍለዘመን እንደሚጀምር የሚያሳዩ ጥናቶችም አሉ፡፡ መቼም ይጀመሩ መቼ ጠቃሚነታቸውና ፈዋሽነታቸው አጠራጣሪ አይደለም። በኢትዮጵያ እስከ ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ድረስ ሕዝቦች ለሰውና ለእንስሳት ጤና ሙሉ ለሙሉ ባህላዊ ሕክምና እንደሚጠቀሙ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡
ጥናቶቹ እንደሚያሳዩት፤አሁን ላይ የአገሪቱ ሕዝብ 80 በመቶ እና የአርብቶ አደር አካባቢዎች ደግሞ 90 በመቶ የጤና አጠባበቃቸው በባህላዊ መንገድ በእጽዋት ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
መጽሐፍት በሕክምና እውቀት ምንጭነት
በኢትዮጵያ ውስጥ በየዘመናቱ በዕፅዋት፣ በእንስሳት ተዋፅኦ፣ በማዕድናትና በፀሎት ለሚደረጉ ፈውሶች በጽሁፍ እያዳበሩ የመጡ መጽሐፍት መኖራቸው ይነሳል፡ዕፅ ደብዳቤ፣መጽሐፈ ፈውስ፣ መጽሐፈ መድሃኒት፣
መጽሐፈ አድዓኖት፣ ጥበበ ኀልቆ፣ አዕባን፣ መዝሙረ ዳዊት፣ ተግባራትና ገቢር፣ አስማተ ዳዊት፣ መፍት የሥራ ይመርቡብት፣ ሰለሞን ጥበበ፣ ሰለሞን መጽሐፈቡኒ፣ መጽሐፈ ዝንሽዋ ወዘተ የመሳሰሉት ተጠቃሾች ናቸው፡፡
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት መጽሐፍት ለአብዛኞቹ የዓለም ሳይንሳዊ ተመራማሪዎችና ተጠቃሚዎች መነሻ እንደሆኑላቸውም የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ‹‹የባህል መድሃኒትና ሕክምና ለዘርፉ እያደረገ ያለው አስተዋጽኦ፣ በቀጣይነት ከተመራማሪዎችና ጤና ተቋማት ጋር የሚኖረው ሚና“ በሚል ርዕስ ከጥቂት(ከሶስት) አመታት በፊት በተካሄደ የውይይት መድረክ የባህል መድሃኒትና ሕክምና አዋቂዎችን በመወከል የተሳተፉት ‹‹ሐኪም እስጢፋኖስ ኃይለጊዮርጊስ›› የገለጹ ሲሆን ‹‹የሳይንሳዊ ሕክምና አባቱ ባህላዊ ሕክምና ነው›› ሲሉም ሐሳባቸውን ገልጸዋል፡፡
የሕክምና እጽዋት አሁናዊ ሁኔታ
በኢትዮጵያ ብዝኃሕይወት ኢንስቲትዩት የሥነ እጽዋት ከፍተኛ ተመራማሪው ዶክተር ተስፋዬ አዋስ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ለመድሐኒትነት አገልግሎት የሚውሉ ከ6500 እስከ 7500 እጽዋት እንደሚገኙ ይገመታል፡፡ ነገር ግን እስከ አሁን ድረስ ባለው የምርምር እውቀት የተደረሰባቸውና መረጋገጥ የቻሉት 6027 እጽዋት አይነቶች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
መኖራቸው ከተረጋገጡት መካከል 603(10 በመቶዎቹ) የሕክምና እጽዋት በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚገኙ ብርቅዬ እጽዋት እንደሆኑ ማረጋገጥ እንደተቻለ ዶክተር ተስፋዬ ገልጸዋል፡፡
ዶክተር ተስፋዬ እንደገለጹት፤ ኢንስቲትዩቱ ከመደበኛ ሥራው በተጨማሪ ሁለት ፕሮጀክቶች በመድሐኒት እጽዋት ዙሪያ ሰርቷል፡፡ የመጀመሪያው በባሌ ተራራዎች እና አካባቢው እ.ኤ.አ ከ2001 እስከ 2007 የተካሄደ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እ.ኤ.አ ከ2012 እስከ 2016 መካሄድ ችሏል፡፡
በእነዚህ ፕሮጀክቶች አማካኝነት የተለያዩ የመድሐኒት
እጽዋት ባንክ (የመስክ ጅን ባንክ) ከተለያዩ አካባቢዎች ተሰብስበው እንዲተከሉና እንዲባዙ ተደርጓል፡፡
በዚህም የተለያዩ የባህል ሕክምና አዋቂዎች የተለያዩ የመድሐኒት እጽዋትን ከዱር ከሚሰበስቡ ከእነዚህ ባንኮች ችግኞች እየወሰዱ በየቤታቸውና በጓሯቸው አካባቢ የሚያለሙበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
ባሌ ተራራ፣ በጂንካ አካባቢ ኩሬ ጥብቅ ደን፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አንበሳ ደን አካባቢ ባምባሲ ሶንካ ቀበሌ፣ በአማራ ክልል በዘጌ 01 ቀበሌ ዘጌ ደን አጠገብ፣ዶሎ መና በተቋቋሙ የ‹‹ጅን›› ባንኮች ለመጥፋት የተቃረቡ ከ600 በላይ የመድሐኒት እጽዋቶች እንዲባዙ መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ አርሶ አደሮችም ሆኑ የባህል መድሐኒት አዋቂዎች ከመስክ‹‹ጂን››ባንኮች ችግኞቹን በመውሰድ አባዝተው የተጨማሪ ገቢ ምንጭ ማድረግ እንዲችሉ የታሰበ ነው፡፡
በመጀመሪያው ፕሮጀክት ባሌ እና ወንዶ ገነት አካባቢ ብቻ የተሰራ ነበር፡፡ በሁለተኛው ግን ተደራሽ ለመሆን ጥረት የተደረገ ሲሆን በተጎዱ መሬቶች ላይም ችግኞቹ እንዲባዙ ተተክለዋል፡፡ የመሬቱን ለምነት ይጠብቃሉ፤ እየተባዙ ሰፊ የመድሐኒትም ምንጭ ይሆናሉ፤በዚህም ውጤታማ መሆን ተችሏል ብለዋል፡፡
ልዩ ጥበቃ የሚሹ የሕክምና እጽዋት
የሕክምና እጽዋቶች ዝርያቸው በአለም ላይ እየተመናመኑና እየጠፉ የመጡ ሲሆን የቀሩትም አደገኛ ፈተናዎች እንደተደቀኑባቸው በርካታ ጥናቶች ይጠቁማሉ። የእጽዋት ተመራማሪው ዶክተር ተስፋዬ እንደሚሉት፤ ሥራቸው ለመድሐኒትነት የሚውሉት እጽዋቶች ብዙ ናቸው፡፡
እነዚህ እጽዋት የመጥፋት እድላቸው እጅግ የሰፋ ነው። በመሆኑም አጠቃቀማቸው በጥንቃቄ ሊሆን ይገባል። አልፎ አልፎ ሕጻናት ቆፍረው ለገበያ ሲያቀርቧቸው ይስተዋላል ነው ያሉት ተመራማሪው፡፡
ከተመናመኑት የመድሐኒት እጽዋት መካከል ሥራቸው አገልግሎት ላይ ከሚውሉት ቀበርቾና ድንገተኛይጠቀሳሉ። ቀበርቾ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኝ የመድሐኒት እጽዋት ነው። በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል የሚገኝ ቢሆንም አገልግሎት ላይ የሚውለው ሥሩ በመሆኑ ለመጥፋት ተቃርቧል። ማህበረሰቡ በሚጠቀምበት ጊዜ የተወሰነ የሥር አካል በማስቀረት ሊታደገው ይገባል። ድንገተኛም ጥቅም ላይ የሚውለው ሥሩ በመሆኑ ሊጠፉ ከተቃረቡት ይጠቀሳል፡፡ በሸዋ አዳዲ ማርያም አካባቢ፣ በትግራይ የተወሰኑ አካባቢዎች የሚገኝ ነው፡፡ ቅጠላቸው አገልግሎት ላይ ከሚውሉት መካከል ዳማ ከሴ፣ ፍሬያቸው(ዘራቸው) ከሚጠቅሙት መካከል ኮሶና እንቆቆ ጥቂቶቹ ናቸው። ማህበረሰቡ ሲጠቀም ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች
የኢንስቲትዩቱ ተመራማሪዎች እጽዋቱ ተመዝግበው በፍኖተ ካርታው ከተጠቀሱበት አካባቢ መገኘት አለመቻል፤ አልፎ አልፎ ከረዥም(ከ30) አመታት በፊት በኢንስትቲዩቱ የተመዘገቡ የመድሐኒት እጽዋት መረጃዎች በተጠቀሱባቸው ቦታዎች አለመገኘት፤ ሕጻናት ያለ ጥንቃቄ ቆፍረው ወይም ቆርጠው ለገበያ እንዲያቀርቡ መፍቀድ ዋና ዋና ችግሮች ናቸው፡፡
መፍትሔዎቹ
በተለያዩ አካባቢዎች አስር የእጽዋት ‹‹ጂን›› ባንኮች ተቋቁመው እጽዋትን በማባዛት ላይ ይገኛሉ፡፡ ማህበረሰቡ በየጓሮው በመትከል ማባዛት ይኖርበታል፡፡ የሚጠቀሙት አካላት በጥንቃቄ መሆን አለበት፡፡ ልጆቻቸውን ማሳወቅና ማስተማር ተገቢ ነው፡፡ በትምህርት ቤቶች የእጽዋት እንክብካቤ ክበባትና የሥነሕይወት ትምህርት ትኩረት ሊሰጡ ይገባል። ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ የሁሉም ሃላፊነት ነው፡፡
ሌሎች መሰረተ ልማት የሚያሟሉ መስሪያ ቤቶች የአካባቢ ተጽዕኖ የዳሰሳ ጥናታቸውን ሲሰሩ ቀደም ሲል በቦታው ላይ ምን እንዳለበት በጥንቃቄ አስቀድመው መለየት እንደሚገባቸው የእጽዋት ተመራማሪው ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 1/2012
ሙሐመድ ሁሴን