የተለያዩ ሙያዎችን ሞክረዋል። በህይወት ዘመናቸው ከስፖርት ዘርፉ ጀምሮ እስከ ጥበቃነት የዘለቀ የሥራ መስኮች ላይ ተሰማርተዋል። አንድም ቀን ግን ተስፋ ቆርጬ አላውቅም ይላሉ። በታታሪነታቸው ለሌሎችም አርአያ መሆናቸውን የሚያው ቋቸው የሚመሰክሩት ሐቅ ነው። አሁን ላይ በሚሊዮኖች ብር የሚያንቀሳቅስ ድርጅት ከፍተው እየሠሩ ይገኛል።
አቶ ተመስገን ጌታቸው ይባላሉ። አባታቸው የወንጂ ስኳር ፋብሪካ ፎርማን ናቸውና እዚያው አካባቢ ነው ቤተሰባቸውን የመሰረቱት። አቶ ተመስገንም ፋብሪኳው አካባቢ የሸንኮራ ማሳዎች ሥር እየተጫወቱ አድገዋል። ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ አዋሽ መልካሳ ትምህርት ቤት ተምረዋል። ከመኖሪያቸው ስድስት ኪሎ ሜትር አካባቢ የሚርቀውን ትምህርት ቤት በስኳር ፋብሪካው ሰርቪስ እየተመላለሱ ተከታትለዋል።
የዛሬው እንግዳችን በልጅነታቸው ለኪነጥበብ ልዩ ፍቅር እንደነበራቸው ያስታውሳሉ። በተለይ ቤት ውስጥ ዲኮር አድርገው ነገሮችን ማስዋብ እና ስዕል መሳልን ይወዱ ነበር። ስምንተኛን ሲያልፉ ግን የተሻለ ትምህርት ማግኘት አለባቸው ተብለው በቤተሰቦቻቸው አማካኝነት ወደ አዲስ አበባ ተላኩ።
ከዘጠነኛ ክፍል ጀምሮም አዲስ አበባ የሚገኙ አጎታቸው ጋር አረፈው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ሲደረግ ገና የአስራዎቹ አጋማሽ ዕድሜ ክልል ላይ ነበሩ። በመዲናዋም ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ሳለ በትርፍ ሰዓታቸው ደግሞ የእንጨት ሙያን ለመልመድ ብለው በአካባቢያቸው ከሚገኙ ባለሙያዎች ዘንድ ጠጋ ማለታቸው አልቀረም። ቆየት ብሎ ግን ከትምህርታቸው ይልቅ ወደ እንጨት ሥራው ማድላታቸውን ያዩ አጎታቸው ትምህርታቸውን ብቻ እንዲከታተሉ መገሰፅ ጀመሩ።
የአጎታቸውን ምክር አልሰማ ያሉት የያኔው ጎረምሳ ወጣት ጭራሹኑ ከአጎታቸው ጋር ተጣሉ። በዚህ ጊዜ አዋሽ ወደሚገኙ ቤተሰባቸው እንዲመለሱ ሲጠየቁ አሻፈረኝ ብለው አዲስ አበባ መቅረቱን መረጡ። ከአጎታቸው ቤት ወጥተው ጓደኞቻቸው ባፈላለጉላቸው ቤት አማካኝነት ከአንዲት ሴት ወይዘሮ ጋር ደባል ሆነው መኖር ጀመሩ።
በወቅቱ ከእንጨት ሥራው በወር 60 ብር ያገኙ ነበር። ትምህርታቸውንም በማታው ክፍለ ጊዜ ቀጥለው፤ ቀን ሥራ ሠርተው ከሚያገኟት ገንዘብ ደግሞ ለደባላቸው 20 ብር ይከፍላሉ። እንዲህ እንዲህ እያሉ ቀን ሥራ ማታ ደግሞ በትምህርት አሳልፈው ለመኝታ ብቻ የደባላቸውን ቤት እየተጠቀሙ አንድ ወር ከ15 ቀናትን አሳልፈዋል።
10ኛ ክፍል ሲደርሱ ደግሞ በ1997 ዓ.ም በጥበቃነት የተሻለ ደመወዝ የሚያስገኝላታቸውን ሥራ ያገኛሉ። በሚጠብቁት ግቢም እየኖሩ በወር 147 ብር ያገኙ ጀመር። የግቢውን ንብረት እየተቆጣጠሩ በመሥራት ከግቢው ባለቤት ጋር የነበራቸው ግንኙነት ጠበቀ። ይህን የታዘቡ የግቢው ባለቤት ታዲያ አቶ ተመስገን ትምህርታቸው ላይ ብቻ አተኩረው ስለምግብ እና ማደሪያቸው እንዳያስቡ እግዛ ማድረጉን ገፉበት።
በዚህ ወቅት አቶ ተመስገን በሚያገኙት እረፍት በሳምንት ሁለት ቀናት የጭፈራ ቤቶች የምሽት ፍተሻ በመሆን ተጨማሪ ገንዘብ ያገኙ እንደነበር አይዘነጉትም። ብዙ ነገሮችን መሞከር የሚወዱት አቶ ተመስገን ጥረታቸውን በመቀጠል ከወደጂም ስልጠናው ደግሞ ጎራ አሉ።
በአራት ኪሎ ወጣቶችና ስፖርት ማዕከል ጂም ቤት ስልጠና ወሰዱ እና እዚያው በአሰልጣኝነት የሚቀጠሩበት ዕድል ተፈጠረ። ከዚያም ጠዋት እና ማታ ጂም ሲያሰለጥኑ ቀን የቀን ደግሞ ትምህርታቸውን ሳያስታጉሉ ህይወታቸውን መምራቱን ቀጠሉ። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በግቢው ውስጥ የማስታወቂያ እና የተለያዩ የዕጅ ሙያዎችን መሞካከሩን ተያያዙት።
የማስታወቂያ ሥራንም አሁን ላይ ታዋቂ የማስታወቂያ ድርጅት ከከፈቱ ከጓኞቻቸው ጋር በመሆን እንደጀመሩት የናገራሉ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸው ሲጠናቀቅ ደግሞ ይበልጡውን ወደማስታወቂያው ዘርፍ ለመግባት ያላቸው ፍላጎት ጨመረ። እናም በ1999 ዓ.ም ላይ ግቢውን እየተቆጣጠሩለት ያሳደጋቸውን ሰው የማስታወቂያ ድርጅት ለመክፈት ህልም እንዳላቸው ሲያማክሩት እንደሚረዳቸው ይነግራቸዋል።
አሳዳጊያቸው አራት ሺህ ብር ሲሰጣቸው እርሳቸው ደግሞ ያጠራቀሟትን ሁለት ሺህ ብር ይዘው ተነሱ። በመጀመሪያም ባምቢስ አካባቢ የሚገኝ ቆሻሻ ቦታን በማጽዳት እና ከባለቤቱቹ ላይ በ300 ብር በመከራየት ቢሮ ከፈቱ። አንድ አሮጌ ኮምፒውተር እና ስካነር እንዲሁም ያገለገለ አነስተኛ ፕሪንተር በመያዝ ሥራቸውን አሀዱ ብለው ጀመሩ።
ስምንት ካሬ የሆነችውን ጠባብ ቢሮ ውስጥ ገበያ ተቀባይ አንድ ሠራተኛ በስምንት መቶ ብር እና ጥበቃ ቀጥረው እርሳቸው ጠዋት እና ማታ የጂም አሰልጣኝነት ሥራቸውን ያከናውናሉ። ሲመለሱ ደግሞ መደበኛ ሥራቸው ላይ ይገኛሉ። በእንዲህ አይነት ሁኔታ የጀመሩት ሥራ በመጀመሪያው ይዞላቸው የመጣው አንድ ሺህ ሁለት መቶ ብር የተቀበሉበት የልብስ ቤት ማስታወቂያ እንደነበር አይዘነጉትም።
በየቀኑም የቢዝነስ ካርድ፣ የሬስቶራንቶች ማስታወቂያ እና የተለያዩ አነስተኛ ድርጅቶችን የህትመት ሥራ በማከናወን በስድስት ወር ውስጥ 60 ሺህ ብር ማግኘት ቻሉ። ይህ ውጤት አቶ ተመስገንን አበረታታቸው። የተለያዩ የባነር እና ከፍ ያለጁ ህትመት ሥራዎች ሲመጡላቸው የተሻለ ማሽን ወዳላቸው ሰዎች ሄደው በማሠራት ከትርፉ ይካፈሉ ነበር።
አብዛኛውን ሥራ በአሳዳጊያቸው ግቢ ውስጥ እያከናወኑ የተለያዩ ማስታወቂያ ሥራዎችንም ተለማመዱ። በአሳዳጊያቸው ግቢ ወርክሾፓቸውን አቋቁመው ከብየዳ ጋር የተያያዙ እና ሌሎችም የቢልቦርድ እና ሰፋፊ ማስታወቂያዎችን መሥራቱን ተያያዙ።
አቅማቸው ሲጠናከር እና ሥራቸው እየሰፋ ሲሄድ ደግሞ ከቻይና ማሽኖችን ስለማምጣት ማሰብ ጀመሩ። ሐሳባቸውን እውን ለማድረግ የማተሚያ ማሽን ገዝተው ሲያስመጡ ግን ገንዘብ አጠራቸው። እናም አሳዳጊያቸው የግቢያቸው ባለቤት እና የሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር ተደጋግፈው አሟልተው አስገቡት።
በጋራ ትብብር በተገኘው ማሽን አማካኝነትም በተሻለ ጥራት እና ፍጥነት በርካታ የህትመት ማስታወቂያዎችንም በማዘጋጀት ገቢያቸውን ማሳደጉን ተያያዙት። እስከ 2004 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ ትላልቅ ሆቴሎች እና የጂም ማሰሪያዎች ውስጥ ካሰለጠኑ በኋላ ሙሉ በሙሉ ትኩረታቸውን ወደ ማስታወቂያ ድርጅታቸው አደረጉ።
ቢሯቸውንም በማሳደግ ተጨማሪ ቅርንጫፍ በዚያው ባንቢስ አካባቢ በሚገኝ ህንፃ ውስጥ ከፈቱ። አምስት ሠራተኞችንም ቀጥረው መሥራቱን ቀጠሉ። በዚህ ሁሉ መሐል ግን አንድ ችግር ተፈጠረ። በ2004 ዓ.ም የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር መስመር ግንባታ በሚከናወንበት ወቅት ዋናው መንገድ ለረጅም ጊዜ በቁፋሮ እና በግንባታ ምክንያት ተዘጋ። በርካታ ደንበኞቻቸው ወደ ቢሯቸው ስላልመጡ ገበያው ሁሉ ጠፋ።
እናም ሠራተኞቻቸውን በአንዱ አቅጣጫ እራሳቸው ደግሞ በሌላኛው አቅጣጫ እየተዘዋወሩ ገበያ በማፈላገል የችግሩን ጊዜ ተቋቁመው አለፉት። አሁን ላይ የአቶ ተመስገን የቢልቦርድ ሥራዎች እና የተለያዩ ማስታወቂያዎች በከተማዋ ዓይን ቦታዎች ላይ ተሰቅለው ይታያሉ።
ለአንድ ቢልቦርድ ሥራ ከስድት መቶ ሺህ ብር እስከ አንድ ሚሊየን ብር ድረስ የተቀበሉባቸው ጊዜያት አሉ። መጽሄቶች፣ ብሮሸር፣ የወረቀት እና አክሊሪክ ህትመቶችንም ከማከናወን ባለፈ የቲሸርት እና የፕላስቲክ ላይ ህትመት አገልግሎትም ይሰጣሉ።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ እስከ ውጭ ጉዳይ እና ትላልቅ የመንግሥት ተቋማት የዘለቀ የህትመት አገልግሎት ሰጥቻለሁ የሚሉት አቶ ተመስገን፣ በተለይ ትላልቅ ኮንፈረንሶች ሲዘጋጁ የህትመት ሥራዎችን በጥራት በማቅረብ ለረጅም ዓመታት እየሠሩ መሆናቸውን ያስረዳሉ።
በአሁኑ ወቅት 10 ሠራተኞችን በቋሚ ነት ቀጥረው እያሠሩ ይገኛል። ሦስት ወርክ ሾፖችንም አቋቁመው ሥራ በሚበዛበት ወቅት እስከ 28 ሠራተኞችን ያሰማራሉ። አቅማቸውን በማጠናከር ስድስት የወረቀት ማሽኖች ባለቤት ሆነዋል። የባነር መሥሪያ ትልቅ ማሽንም ከቻይና አስመጥተዋል። ከዚህ በተጨማሪ የማባዣ እና የቲሸርት ህትመት መሣሪያዎችንም ይጠቀማሉ። አቶ ተመስገን 10 ሚሊየን ብር የደረሰ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ያላቸው ሲሆን፣ በአንድ ዓመት ሽያጫቸው ብቻ ስድስት ሚሊዮን ብር እንደደረሰ ይናገራሉ።
ለዚህ ሁሉ ስኬት ለመድረስ የራስ ጥረት እና የመረዳዳት ልምዱ እንዳገዛቸው የሚናገሩት አቶ ተመስገን ያለኝ ዕውቀት እና ገበያ ግን ይበቃኛል ብለው አልተቀመጡም። ይልቁንም በዓመት ሁለት ጊዜ ዱባይ ከተማ ላይ በሚካሄዱ የማስታወቂያ ኤግዚቢሽኖች ላይ በመካፈል አዳዲስ አሠራሮችን ቀስመው ይመለሳሉ። የተለያዩ የውጭ አገራት የልምድ ልውውጦች ላይም ይሳተፋሉ።
ባገኙት እውቀትም ከተሰባበሩ የሴራሚ ክስ ቁርጥራጮችን በመሰብሰብ የሞዛይክ ሥነ ጥበብን የተከተሉ የማስታወቁያ ሥራዎችን እያዘጋጁ ይገኛሉ። በተጨማሪም በውጭ አገራት መቀመጫቸውን አድርገው ማስታወቂያዎቻቸው ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲተላለፍላቸው ከሚፈልጉ ጅርጅቶች ጋር በመነጋገር የውጭ ምንዛሬ ጭምር በማስገባት ላይ ናቸው። በቀጣይም የውጭ አገራትን አዳዲስ የማስታወቂያ ልምዶችን አገር ውስጥ በመተግበር ሰፊ ሥራ የማከናወን ዕቅድ አላቸው።
አቶ ተመስገን ማስታወቂያ ሠሪ ብቻ ሳይሆኑ አሠሪም ናቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ ለማስታወቂያ ያለው ግምት እና እውቀት አነስተኛ በመሆኑ የበርካቶችን ገበያ እየቀነሰው ነው የሚሉት ባለሙያው፤ እራሳቸው ህትመት ላይ እየሠሩ ድርጅታቸውን ለማስተዋወቅ ግን በዓመት ከሦስት መቶ ሺህ ብር ያላነሰ ወጪ እንደሚያወጡ ይናገራሉ። ይህም መልሶ ገበያ በማምጣት ተጨማሪ ሥራ እየፈጠረላቸው ይገኛል።
ከዚህ ባለፈ ግን በኢትዮጵያ ያለው የማስታወቂያ ሕግ በርካቶች ድርጅታቸውን እንዲያስተዋውቁ የሚገፋፋ ባለመሆኑ ቢስተካከል የዘርፉም ዕደገት ወሳኝ ድርሻ እንደሚያበረክት ይገልፃሉ። ሕጉ እንዲስተካከል ጥረት እንደሚያደርጉ የሚናገሩት አቶ ተመስገን እስከዚያው ግን ሙያዬ ብለው የያዙት የእራሳቸውን አሻራ ለሀገር እያሳረፉ መቀጠል ላይ አተኩረዋል።
ከማስታወቂያ ሥራው በተጨማሪ አስመጪነት ዘርፍ ተሰማርተው ለመነገድ ጥናቶችን እያከናወኑ ይገኛል። በማስታወቂያ ዘርፉም ቢሆን ድርጅታቸውን ለጎረቤት አገራት ጭምር ሰፊ አገልግሎት የሚሰጥ ትልቅ ተቋም ለማድረግ በየጊዜው የማሻሻያ ሥራዎችን እያከናወኑ የመቀጠል ዕቅድ አላቸው።
ሥራ ማለት ለእርሳቸው ከጀመሩት የማያቋርጡት፤ በጥራት አከናውነው ውጤት የሚያዩበት ተግባር ነው። በማንኛውም ዘርፍ ውስጥ ቢገኙ አሸነፎ መውጣት ወሳኝነት አለው። ወጣቶችም በቶሎ ተስፋ ሳይቆርጡ በተሰማሩበት ዘርፍ ማሻሻያዎችን እያደረጉ ውጤታማ ስለመሆን ማሳብ ይገባቸዋል የሚለው ደግሞ ምክራቸው ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 25/2012
ጌትነት ተስፋማርያም