ማህበረሰብ አንቂነት (አክቲቪዝም) ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ለውጥን ለማምጣት የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም የሚደረገውን ትግልን ያጠቃልላል። ማህበረሰብ አንቂዎች በዓለም ላይ ትላልቅ ለውጥ እንዲመጣ ተኪ የሌለው ሚና ተጨውተዋል። ባርነትን በማስቆም ፣ አምባገነናዊ አገዛዞች ስር እንዳይሰዱ ብሎም እንዲወገዱ በማድረግ፣ ሠራተኞች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በመከላከል፣ አካባቢ እንዲጠበቅ፣ የሴቶች እኩልነት እንዲረጋገጥ ፣ ቀለምን መሰረት ያደረገ ዘረኝነት እንዲቆም እና ሌሎች በርካታ ለሰው ልጆች ጠቃሚ የሆኑ ጉዳዮችን በማስቻል ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። ከዚህ አልፎ ማህበረሰብ አንቂዎች ለሀገር ግንባታም ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ።
በሌላ በኩል የአንቂነት ሚናን በመጠቀም አሉታዊ እሳቤዎችም ሊራመዱ ይችላሉ። በተለይም የአጭር ጊዜ ጥቅም በመፈለግ ማህበረሰብ አንቂዎች ተጽዕኖ ፈጣሪነታቸውን ተጠቅመው አፍራሽ ሚና ሊጨወቱ ይችላሉ። በኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ያለውን አገራዊ ለውጥ እውን እንዲሆን ማህበረሰብ አንቂዎች የራሳቸውን ሚና ተጫውተዋል። ሀገሪቱ የለውጥ ጉዞዋን ከጀመረችበት ዕለት አንስቶም ወጣት ማህበረሰብ አንቂዎች ለለውጡ ቀጣይነት ሚናቸውን ሲወጡ ቆይተዋል፤እየተወጡም ይገኛሉ።
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በማህበረሰብ አንቂነት የሚንቀሳቀሱ በርካታ ወጣቶችን ማየት የተለመደ ነው። ሞቲ ኦሮ በማህበራዊ ሚዲያ በማህበረሰብ አንቂነት በመንቀሳቀስ ላይ ከሚገኙት ወጣቶች አንዱ ነው። በተለይም በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በሚጽፋቸው ጽሁፎቹ ይታወቃል።
ማህበረሰብ አንቂዎች በሀገር ግንባታ ላይ ከፍተኛ ሚና የመጫወት አቅም አላቸው የሚለው ሞቲ፤ የሀገር ግንባታ ሀገራዊ ማንነት መገንባት ወይም ማዋቀር ነው ይላል። የሀገር ግንባታ ዋነኛው ዓላማው የህዝቦችን አብሮነትና አንድነትን በማጠናከር ፖለቲካዊ መረጋጋት የሰፈነበት ማህበረሰብ መፍጠር ነው። ለዚህ መንግስት የሚጫወተው ሚና የላቀ ቢሆንም ማህበረሰብ አንቂዎችም ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ።
በአሁኑ ወቅት ከመደበኛው ሚዲያዎች በፈጠነ መልኩ ለማህበረሰብ መረጃ በማድረስ ረገድ ማህበረሰብ አንቂዎች ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ ናቸው። በተለይም ለህብረተሰቡ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ በማድረስ፣ ህዝብን በማረጋጋት፣ ህዝቡ መብቱን እንዲያስከብር በማነቃቃት፣ ብሄራዊ መግባባት እንዲፈጠር፣ እርቀ ሰላም እንዲፈጠር፣ ብሄራዊ መግባባት እንዲመጣ፣ ህዝቡ ለልማት እንዲነሳሳ፣ የአካባቢውን ጸጥታ እንዲያስከብር በማነቃቃት በሀገር ግንባታ ላይ የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ሞቲ ያብራራል።
በኢትዮጵያ ውስጥ በማህበረሰብ አንቂነት የሚንቀሳቀሱት ሁለት መልክ እንዳላቸው ያብራራው ሞቲ በአንድ ወገን ለሀገር አንድነት፣ ሰላም፣ ለህዝቦች እኩልነት እና ፍትህ ተጨንቀው የሚጽፉ ሲሆኑ በሌላ በኩል የማህበረሰብ አንቂነትን ሚና የዘነጉ ሀገርንና ህዝብን ወደ ችግር የሚከቱ ለዚህም ሀሰተኛ መረጃ እና የጥላቻ ንግግር በማሰራጨት ተግባራትን የሚፈጽሙ መኖራቸውን ያብራራል። በማህበረሰብ አንቂነት በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙት አብዛኞቹ ችግሮችን ለማባባስ ሚና ያላቸው አሉባልታዎችን እና ሀሰተኛ መረጃዎችን በመንዛት ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ ይናገራል።
እንደ ሞቲ ማብራሪያ፤ በማህበረሰብ አንቂነት የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ወጣቶች አዎንታዊ ሚናቸውን ከመጫወት ይልቅ ህዝብንና ሀገርን ሊጎዱ የሚችሉ ተግባራትን የሚያከናውኑት በዋናነት በግንዛቤና በእውቅት እጥረት ነው ይላል። በእውቀት ላይ ያልተመሰረተ በስሜት ብቻ ወደ አክቲቪስትነት በብዛት መሳተፍ ሀገርን ዋጋ እያስከፈለ ነው። አብዛኞቹ በማህበረሰብ አንቂነት የሚንቀሳቀሱት መረጃን አስቀድመው በማውጣት ጊዜያዊ ውዳሴ የሚሯሯጡ በመሆናቸው የውሸት መረጃ ጭምር በማውጣት ከንቱ ተወዳጅነትን ሲያጋብሱ ይስተዋላል።
“በኢትዮጵያ ውስጥ ማህበረሰብ አንቂነት ወደ መጥፎ አቅጣጫ እየሄደ ነው፤” ሲል ሞቲ፤ በአገሪቱ ጽንፍ የያዘ አክቲቪዝም በስፋት እየተስተዋለ መሆኑን ያነሰል። አሉታዊ ሚና የሚጫወቱት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ ለሀገርና ለህዝብ ሰላምና አንድነት የሚጠቅሙ ተግባር የሚፈጽሙ ማህበረሰብ አንቂዎች ላይ የሚደርስባቸው መገለልና ውግዘት እጅግ ከባድ መሆኑን ያብራራል። ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ደፍሮ ሰውን ለመተቸት እጅግ አስቸጋሪ የሆነ ሁኔታ እየተፈጠረ ነው ብሎ ለዚህም በአገሪቱ በተደራጀ መልኩ የሚሰራ ሀይል መኖሩን ጠቁሟል። ሰላማዊ ስራ የሚሰሩት ዋስትና እንዲያጡ የማድረግ ስራ ሲሰራ በግልፅ እንደሚታይም አልደበቀም።
በኢትዮጵያ ውስጥ ማህበረሰብ አንቂነት ለሀገር ሰላምና ለሀገር አንድነት የሚጠበቅበትን እንዲያበረክት የተለያዩ ስራዎች መሰራት አለበት የሚለው ሞቲ በተለይም የማህበረሰብ አንቂዎች ፎረም ቢቋቋም አንቂዎቹ ህብረተሰቡን በሚያነቁበት ወቅት መረጃና ማስረጃ ላይ ተደግፈው ለሀገርና ለህዝብ ጠቃሚ ስራ መስራት እንዲችሉ እንደሚያስችላቸው ይናገራል። ፎረሙ ከአክቲቪዝም መስመር በመውጣት ሀገርን ሊጎዱ የሚችሉ ተግባራትን የሚያከናውኑትንም አደብ ለማስገዛት እገዛ የሚያደርግ በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል ብሏል።
በማህበረሰብ አንቂነት የምትሳተፈው ሃና ረጋሳ በበኩሏ እንደምትለው አክቲቭዝም በተገቢው መልኩ ከተተገበረ ለሀገር ሰላምና አንድነት በጣም ወሳኝ ነገር ነው ትላለች። በኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን ባለው ሁኔታ ግን አብሮነትና ሰላምን በሚያሰፍን መልኩ ተተግብሯል ብላ አታምንም። ከሀገራዊ ጉዳዮች ይልቅ ብሄር እና ሰፈርተኝነት ማዕከል ያደረጉ የአክቲቪዝም ስራዎች ሲሰሩ ይታያል ብላለች። የሀሰት ዜናዎችን ጭምር በማሰራጨት ለችግሮች መንስኤ ሲሆኑ ይስተዋላል።
ከዚህ ቀደም ነጻነት በመነፈጉ ምክንያት እጅግ ታፍኖ የነበረው ህዝብ አሁን ልቅ ነጻነት በመገኘቱ ምክንያት በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በይፋ መውጣት የሌለበትንና ያለበትን ያለመለየት እውቀት አጠር ሁኔታ አለ የምትለው ሃና፤ በአብዛኛው በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ሊወጡ የማይገቡ ሀገርን ያስተሳሰረውን ድርና ማግ የሚበጣጥሱ ጭምር በማህበራዊ ሚዲያ ሲሰራጭ ማየት የተለመደ ነው ትላለች። በጣም ከባድ የሆኑ የሃይማኖትና የብሄር ጉዳዮች ጭምር በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ሀገርን በሚጎዳ መልኩ ህዝብን ለማነሳሳት ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑ አደገኛ ነው ትላለች።
በማህበራዊ ሚዲያ አካባቢ የሚታየውን ልቅነት ፈር ለማስያዝ መንግስት የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን የሚከላከል ህግ ለማውጣት የጀመረውን ጥረት በበጎ ጎኑ እንደምትመለከተው የተናገረችው ሃና መንግስት ህግ የማውጣት ሂደቱን በማፋጠን ተጠያቂነትን ሊያሰፍን ይገባል ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት የለውጥ ጉዞ የማህበረሰብ አንቂዎች ሚና ከፍተኛ ለመሆኑ የሚያከራክር ጉዳይ አይደለም። ይሁን እንጂ በሌላ ጎኑ በአክቲቪዝም ስም አገርን የማተራመስ የተለየ አጀንዳ ያላቸው ሀይሎች ደግሞ የማህበረሰብ አንቂዎችን መልካም ስም እያጠፋ ይገኛል። በመሆኑም ችግሩን ለመቅረፍ የማህበረሰብ አንቂዎቹ ጥረትና ትግል እንዳለ ሆኖ መንግስት ይህን ችግር ለማስወገድ የሀሰተኛ መረጃ እና የጥላቻ ንግግር ረቂቅ ህግ ተስፋ ተጥሎበታል።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 23/2012
መላኩ ኤሮሴ