በሀገሮች መሪዎችን ለመምረጥ ምርጫ እንደሚካሄድ ይታወቃል። ለእዚህም ዜጎች ድምጻቸውን ይሰጣሉ ፤ ድምጽ በሚሰጥበት ስፍራ ምንም አይነት ሁከት ሊፈጠር አይገባም። በእዚህ አካባቢ ድምጽ በሚሰጡበት ወቅት ወርቅ፣ ገንዘብ ፣ወዘተ ቢጠፋ ያዙኝ ልቀቁኝ ብሎ መጮህ አይቻልም፤ ሊያስጠይቅ ይችላል። ወርቅን ያህል ጠፍቶ ታዲያ እንዴት ዝም ይባላል ትሉ ይሆናል። ያሎት አማራጭ ተረጋግቶ በሰከነ መንፈስ ችግሩን ለሚመለከታቸው አካላት አሳውቆ ድምፁ እስኪጠናቀቅ በትእግስት መጠበቅ ነው።
በፈረንጆቹ ባለፈው ታኅሳስ መባቻ በእንግሊዝ ትራፎርድ ምክር ቤት ድምጽ ለመስጠት የተገኘች አንዲት እንግሊዛዊት ከወላጅ እናቷ በስጦታ የተበረከተላትን የወርቅ የጣት ቀለበት ድምጽ ሰጥታ እንደወጣች ከጣቷ ላይ ታጣዋለች። ብዙ ስታፈላልግም ትቆያለች። የቀለበቱ መጥፋት በእጅጉ ያሳስባታል። ለእናቷ ምን ብላ እንደምትነግራትም ግራ ይገባታል። ቻርሎቴ የተባለችው ይህች እንግሊዛዊት ጓደኛዋ በአንድ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ በድምጽ መስጫ ሳጥን ውስጥ ቀለበት ስለጣለ ሰው መረጃ መልቀቁን እስከ ገለጸላት ድረስም የት እንደጣለችውም ማስታወስ አልቻለችም።
ቻርሎቴ ማንችስተር አቅራቢያ በሚገኘው በክሎቬራል መጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ድምፅ እስከሰጠችበት ሰአት ድረስ ቀለበቱ ጣቷ ላይ አንደነበር ታስታውሳለች። ጓደኛዋ መረጃውን እስከላከላት ድረስም ቀለበቱ በድምፅ መስጫ ሳጥን ውስጥ ስለመግባቱም አላወቀችም።
ነገሮችን መለስ ብላ ስታሰላስል ድምጽ በሰጠችበት ወቅት ሳንቲም የወደቀባት መስሏት እንደነበር አስታወሰች። ጓደኛዋ የሰጣትን መረጃ መሰረት በማድረግም ድምጽ ወደ ሰጠችበት ትራፎልድ ምክር ቤት ትደውላለች፤ ቀለበት እንደጠፋባትም ትገልጻለች። እነሱም በከተማው መሰብሰቢያ አዳራሽ እንዲቀመጥ ማድረጋቸውን ይገልጹላታል። ቀለበቱ በጠቋሚ ጣቴ ላይ ነበር ፤ ድምፄን ሰጥቼ እጄን ጎትቼ ሳወጣ ሳጥን ውስጥ ወድቆ ሊሆን ይችላል ስትል ትገልጻለች።
ቀለበቱ አመልካች ጣቴ ላይ ነበር፤ ጣቴ ላይ ላላ ያለም ነበር፤ ለእዚህም ነው ድምጽ ስሰጥ በቀላሉ ከጣቴ ወልቆ ወደ ድምጽ መስጫ ኮሮጆ ውስጥ የገባው ያለችው ቻርሎቴ ፣በመገኘቱ በጣም መደሰቷን ተናግራለች። ‹‹የእናቴን ፊት እንዴት አያለሁ ብዩ ሳስብ ነበር፤ ለወደፊቱ እንዳይጠፋብኝ በደንብ ተጠንቅቄ እይዛለሁ። ምክር ቤቱ ላደረገልኝ ትብብር አመሰግናለሁ። “ስትል ገልጻለች።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 21 ቀን 2012 ዓ.ም
ኃይለማርያም ወንድሙ