ዘመናዊ መጸዳጃ በሀገራችን ብዙም አልተስፋፋም ቢባል ዋሾ አያሰኝም፤ ይህን እጥረት መንግሥትም በሚገባ ያውቀዋል። ከዚህ አኳያም የመጸዳጃ ቤት አገልግሎትን በከተማ ለማስፋፋት እየተሰራ ይገኛል። በከተሞች የህዝብ፣ የመንግሥትና የሆቴል መፀዳጃ ቤቶች በስፋት የሚስተዋሉ ሲሆን፣ የመኖሪያ ቤቶች መጸዳጃ ቤቶች በስፋት እየዘመኑ ናቸው። በገጠርም በዚሁ ላይ ግንዛቤ በማስጨበጥ ሰዎች ጤናቸውን ለመጠበቅ በመጸዳጃ ቤት እንዲገለገሉ ለማድረግ በተለይ በጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች በኩል እየተሰራ ነው።
በከተሞች በተለይ በህዝብ መጸዳጃ ቤት አጠቃቀም ላይ ግን ተግዳሮቶች ይስተዋላሉ። መጸዳጃ ቤቶችን በንጽህና እና በአግባቡ አለመጠቀም አንድ መሰረታዊ ችግር ነው። መጸዳጃ ቤት ገብቶ ቶሎ አለመውጣት ሌላው ችግር ነው። አንዳንዶች ከጤና ጋር በተያያዘ በተለይ ድርቀት ያለባቸው ናቸው ይባላል መጸዳጃ ቤት እነዚህ ሰዎች መጽሀፍ ፣ጋዜጣ ወዘተ፣ ይዘው በመግባት እያነበቡ ብዙ ይቆያሉ። ሞባይላቸውን ይዘው ገብተው ኢንተርኔት ይሁን ሌላ የሚከታተሉም ጥቂት አይደሉም። ይህ አይነቱ የመጸዳጃ ቤት አጠቃቀም በተለይ በሆቴሎችና በህዝብ መጸዳጃ ቤቶች ተጠቃሚዎች ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል። የእነዚህ ተገልጋዮች ተግባር የራሳቸውንም የሌላውንም ተጠቃሚ ጊዜ ያባክናል።
ይህ ችግር የሌሎች ሀገሮችም ችግር ነው። ችግሩ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ተከትሎም አዲስ የመጸዳጃ መቀመጫ ዲዛይን ብሪታኒያ ውስጥ እስከ መስራት መደረሱን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ሰሞኑን ይዞት በወጣ መረጃ አስነብቧል። ይህ መቀመጫ ሰዎች መጸዳጃ ቤት ውስጥ ከአምስት እስከ ሰባት ደቂቃ በላይ እንዳይቆዩ የሚያደርግ ነው። ይህ የመጸዳጃ ቤት መቀመጫ እንደ ሌሎቹ መቀመጫዎች ምቾት የሚሰጥ ባለመሆኑም ሰዎች ተቀምጠው እንዲያነቡም ሆነ ሞባይል እንዲነካኩ ብዙም እድል አይሰጥም ይለናል መረጃው።
መቀመጫው ዲዛይን የተደረገው በእንግሊዛዊው መሀንዲስ ማሃቢር ጊል ሲሆን፣ ከመደበኛው መጸዳጃ መቀመጫ በ13 ዲግሪ ቁልቁል ያጋደለ ነው፤ ሰዎችም በዚሁ ልክ አጋድለው እንዲቀመጡ የሚያደርግ በመሆኑ ምቾት ይነሳል።
ጊል የዚህ መቀመጫ ሃሳብ የተከሰተለት መጸዳጃ ቤት ተጠቃሚዎችን ምቾት ስለሚነሳቸው ቶሎ ጣጣቸውን ጨርሰው እንዲወጡና የኪስ ስልክ እያዩ ጋዜጣ ወይም እያነበቡ እንዳይቆዩ በማሰብ ነው። የተቀጣሪዎችን የሥራ ሰዓት ማስፋት ለሚፈልጉ ነጋዴዎችም መልካም አጋጣሚ መሆኑን ይገልጻል።
“በእንግሊዝ ብቻ በአንድ የሥራ ቀን ሰራተኞች አለአግባብ የሚያባክኗቸው ጊዜያት የኢንዱስትሪና የንግድ ባለሀብቶችን በዓመት 4 ቢሊዮን የእንግሊዝ ፓውንድ እንደሚያስወጣቸው ይገመታል።” ሲል ሚስተር ጊል ጠቅሶ፣ አዲሱ የመጸዳጃ ቤት መቀመጫ ሠራተኞቻቸው በመጸዳጃ ቤት አለአግባብ የሚያጠፉትን ጊዜ በማዳን ቀጣሪዎች የበለጠ ሀብት እንዲያፈሩ ያስችላል ይላል።
አዲሱ መቀመጫ ለትርፍ ባልተቋቋመው የብሪቲሽ መጸዳጃ ቤቶች ማኅበር ተቀባይነት ያገኘ ሲሆን ፤ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ግን የመጸዳጃ መቀመጫውን ዲዛይን በስላቅ አጣጥለውታል ።
በመጸዳጃ ቤት ለረጅም ጊዜ መቆየት አይገባም ሲል በድረ ገፅ ላይ አስተያየቱን የሳፈረው ጊል፣ ለእዚህም ሲል አጨቃጫቂውን የመፀዳጃ ቤት መቀመጫ ዲዛይን መስራቱን ለዊርድ መጽሔት ጠቁሟል። አንዳንዴ ሠራተኞች በመጸዳጃ ቤት ተኝተው እንደሚገኙም ጠቅሶ፣ በሕዝብ መጸዳጃ ቤቶችም ወረፋዎች እየበዙ ተራ የሚጠብቁ ተገልጋዮች ሲቆጡ እንደሚሰማ ይገልጻል። በአገልግሎት ላይ ያለው የመጸዳጃ ቤት መቀመጫ ለተጠቃሚዎች ጤና የሚሰጥ እና ተክለ ሰውነትን የሚያሻሽል እንደሆነ ጊል ቢያምንም ፣ አዲሱ የመጸዳጃ ቤት መቀመጫ ግን ቀጣሪዎችን ከኪሳራ እንደሚታደግም ተናግሯል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 21 ቀን 2012 ዓ.ም
ኃይለማርያም ወንድሙ