ሩያል ባንክ ኦፍ ካናዳ በየዓመቱ ምርጥ አዲስ ወደ ካናዳ የገቡ ስደተኞችን ይሸልማል። በካናዳ ዙሪያ ከተጠቆሙ 3000 አዲስ ስደተኞች መካከል 25ቱ በበጎ ተግባራቸው ነጥረው የወጡ ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል አንደኛ በመሆን የተሸለሙ ናቸው። በሚሰሩት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከራሺያ እስከ ካናዳ ሲሸለሙና ሲመሰገኑ ኖረዋል። አሁን ደግሞ ፊታቸውን ወደአገራቸው አዙረው ከትምህርት ቤት እስከ ላይብረሪ ማሰራት የደረሱና በርካታ ድጋፎችን ለሀገራቸው ህዝብ ያደረጉ ናቸው። ሀገር ወገኑን የሚረሳ ኢትዮጵያዊ በውጪው ዓለም እንዳይኖር የእሳቸው ተሞክሮ ትልቅ ትምህርት ነውና ለዛሬው የ”ህይወት እንዲህ ናት “ አምዳችን እንግዳ አድርገናቸዋል ዶክተር ገዛኸኝ ወርዶፋን።
ውልደትና እድገት
ዶክተር ገዛኸኝ ተወልደው እስከ ዘጠኝ አመታቸው ያደጉት ዱከም አካባቢ በምትገኘው ወለንጪቲ ከተማ ሲሆን፤ ቀጣዩን የልጅነት ጊዜያቸውን ደግሞ ወላጆቻቸው ጡረታ በመውጣታቸው የተነሳ ወደ ትውልድ ቀያቸው በመሄዳቸው እርሳቸውም በቤተሰቦቻቸው ትውልድ ቦታ በ‹‹ድረገታ›› እንዲያሳልፉ ሆኑ። ቤተሰቦቻቸው እርሻ ባይኖራቸውም ከአያቶቻቸው የወረሱት በመኖሩ ለአዛውንቱ አባታቸው ከባድ የሆነውን ሥራ በመረከብ ሲያግዙም ነው ያደጉት።
ዶክተር ገዛኸኝ በቤተሰቡ ውስጥ ካሉት 15 ልጆች መካከል 14ኛ ናቸው። ሆኖም ታላላቆቻቸው ትዳር ስለያዙ ወላጆቻቸውንና ታናሽ ወንድማቸውን የማገዝና የመደገፍ ግዴታ የእርሳቸው ሀላፊነት ነበር። ስለዚህም ከግብርናው ስራ በተጨማሪ እንቁላልና ጋዝ በመሸጥ ቤቱን ይደጉሙ እንደነበርም አይረሱትም። የከብት እረኝነቱ የታናሽ ወንድማቸው ብቻ ሳያደርጉ እርሳቸውም እያገዙት ከብት ጠብቀዋል።
እንግዳችን ለቤተሰቡ ብቻ ሳይሆን ለጎረቤትም ደራሽና ታዛዥ ናቸው። በዕድሜ ለገፉት ውሃ ይቀዳሉ፣ አጥራቸው ለፈረሰባቸው አጋምሾህ በመቁረጥ አጥራቸውን ያጥራሉ። ከዚያም አልፈው በገንዘብ ጭምር የሚያግዟቸውም እንደነበሩ ያስታውሳሉ። በተለይ ለእርሻ ዘር የሌላቸው ሰዎች ካሉ ከሚነግዱትና ካተረፉት ገንዘብ ላይ በመቀነስ ይሰጧቸው ነበር። ይህ ደግሞ በአካባቢው ዘንድ ተወዳጅነትን አትርፎላቸዋል።
ዶክተር ገዛኸኝ ወለንጪቲ እያሉ ቦታው ከተማ ቀመስ በመሆኗ ብዙ አይነት ጨዋታ ለምደዋል። ግን ደረገታ ሲመጡ እርሳቸው የሚያውቁትን ጨዋታ የሚያጫውታቸው የለምና ለብዙ ጊዜ ለጓደኞቻቸው በማለማመድ ነው ጊዜያቸውን ያሳለፉት። ከዚያ ግን በጣም የሚወዱትን የብይ ጨዋታ በጭቃ በመስራትና በማድረቅ ጓደኞቻቸው ሲለምዱት መጫወት ጀመሩ። በተመሳሳይ ኳስ በካልሲ መስራት ስለማይችሉ ጭድ እየጠቀጠቁ ኳስ በመስራት ይጫወቱ እንደነበር ያስታውሳሉ።
ዋና መዋኘት በጣም ይወዳሉ። ለዋና ሲሄዱ ግን ለመዋኘት ብቻ አልነበረም። ይልቁንም በአካባቢው የውሃ ቦታ ያለው አንድ ሰዓት ከተጓዙ በኋላ በመሆኑ አንድና ሁለት ከብት ያላቸው አዛውንቶችን ይረዱበት ነበር። ምክንያቱም ለሁለትና ለአንድ ከብት እረኛ መቅጠር በጣም ከባድ ነው። ስለዚህም እርሳቸው የእነርሱን ከብት ሰብስበው በመውሰድ ውሃ ያጠጡላቸዋል።
ሰዎችን መርዳት የሚወዱት፣ ወጣቱንም ለመልካም ስራ እንዲነሳሳ የሚያበረቱትና ምርቃትን እንደ ክፍያ የሚቆጥሩት እንግዳችን፤ ብዙ ወጣቶች ያደምጧቸውና ያሉትን ይፈጽሙላቸው እንደነበር ይናገራሉ። ይህ ባህሪያቸው የእናትና አባት ስምን እስከማስቀየር አድርሶ እንደነበርም አይረሱትም። ይህ ስምም “ጌታቸው” የሚል ሲሆን፤ ትልቁም ትንሹም የሚታዘዝላቸው ልጅ ስለነበሩ የወጣላቸው ነው።
ዱከም ለትምህርት ሲሄዱ ለሬስቶራንቶች እንቁላል ያስረክቡ እንደነበር የሚያነሱት ዶክተር ገዛኸኝ፤ በልጅነታቸው የህክምና ዶክተር መሆን ይፈልጋሉ። ለዚህም ዋናው ምክንያታቸው በአካባቢያቸው አንድም ሀኪም ባለመኖሩ ህመምተኛ በቃሬዛ ተሸክሞ ረጅም መንገድ መሄዱ ስለሚያሳዝናቸው ነው። ከበሽታው ድኖ የሚመለስ ሰው አለመኖሩም ያስቆጫቸው ነበር። እናም ሀኪም ሆኜ በተለይ በወሊድ ምክንያት የሚሞቱ እናቶችን መታደግ አለብኝ ብለው ስለሚያምኑ የህክምና ትምህርት ለመማር ይፈልጉ ነበር። ሌላው ፍላጎታቸው በውሃው ዘርፍ መስራት ሲሆን፤ ውሀ የማቆር ሥራ ባለመሰራቱ ውሀ ፍለጋ እርቀው ይጓዙ ነበር። እናም ይህንን ለማስቀረት ሲሉ በውሀ ዘርፍ ማጥናት እንደሚፈልጉም ነግረውናል።
‹‹የንግድን ጣዕም ያወቅኩት፤ ገንዘብን በአግባቡ ለተፈለገለት አላማ ማዋል የለመድኩት፤ ለበጎ ነገር ገንዘብ መሰሰት እንደሌለብኝም የተረዳሁት በዚህ ወቅት ነው። ልጅነት ላይ የተዘራ ዘር ወደፊት የሚለመልም እንጂ የሚከስም እንዳልሆነ ዛሬ ተረድቻለሁ›› ይላሉ ልጅነታቸውን እንዴት እንዳሳለፉት ሲያወሱ።
በሁለት ዓመት 5ኛ ክፍል
ፊደል መቁጠር የጀመሩት በቄስ ትምህርት ቤት ነው። ሆኖም ትምህርቱ እንደማይገባቸውና በየኔታ(በፊደል አስቆጣሪያቸው) ሁልጊዜ እንደሚደበደቡ ያስታውሳሉ። በተለይ ታናሽ ወንድማቸው ከእርሳቸው በልጦ ውጤታማ ሆኖ ሲታይ እያለመጥክ ነው ባዩ ብዙ ነበር። በዚህም በትምህርቱ ብዙ ሳይገፉ ወደዘመናዊው ትምህርት ገቡ። እድሜያቸውም ትምህርት ቤት ከመግቢያው ያለፈ ነበርና ብዙ ጊዜያቸውን በቄስ ትምህርት ቤት ሳያጠፉ አንደኛ ክፍል ገቡ። በአንድ አመትም ሁለቱን ክፍል አጠናቀቁ።
የየኔታ ምክርና ተግሳጽ ፣የሸመደዱት ፊደልና ለትምህርቱ የሰጡት ትኩረት ተዳምሮ ከክፍል ክፍል ደብል እንዲመቱ አድርጓቸው በሁለት ዓመት ውስጥ ነበር አምስተኛ ክፍል የደረሱት። ይህ የሆነው ደግሞ ወለንጪቲ አንደኛ ደረጃ 1ኛእና 2ኛን እና ዱከም ደጃዝማች ፍቅረማሪያም ትምህርት ቤት ነው። ከዚያም እስከስምንት በተከታታይ የደረጃ ተማሪ ሆነው ዘለቁ። ከዘጠኝ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ደግሞ ደብረዘይት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማሩ ሲሆን፤ ያኔ ልዕልት ተናኘወርቅ እየተባለ ይጠራል።
በትምህርት ቤቱ ሰቃይ የሚባሉ ተማሪ ቢሆኑም የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና ውጤት እንዳልመጣላቸው የሚናገሩት ባለታሪኩ፤ ውጤቱ ሳይመጣላቸው ሲቀር ጓደኞቻቸውና መምህሮቻቸው በጣም እንደተናደዱና “ዳግም ተፈትነህ ታሻሽላለህ ውጤታማም ትሆናለህ “ በማለት ተስፋ ይሰጧቸው እንደነበርያስታውሳሉ። ቤተሰቦቻቸው ደግሞ በጣም አዝነው እንደነበርም አይረሱትም።
‹‹መቼም ቢሆን ቤተሰቦቼን አሳዝኜ አላውቅም። ግን ውጤት ሳይመጣልኝ ሲቀር በጣሙን ተናድጄና አዝኜ ነበር›› የሚሉት እንግዳችን፤ ተስፋ መቁረጥ ለበለጠ ችግር እንደሚዳርጋቸው በማመን የሁሉንም ተስፋ ለማለምለም ሲሉ በቁጭት ለውጤት መስራት ጀመሩ። ሁለት ዓመት ሙሉ ሳይፈተኑ ቤተሰቦቻቸውን ብቻ በሥራ እያገዙም ጥሩ ውጤት ለማምጣት መዘጋጀቱን አጧጧፉት። ከዚያ ረጅሙን የእግር ጉዞ ተጉዘው አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብተው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን ወሰዱ። እድል ቀናቸውናም ወደ ራሺያ የሚወስዳቸውን ውጤት ተቀዳጁ።
በእርግጥ ወዲያው ወደራሺያ መሄድ አልቻሉም። ምክንያቱም ወደእዛ ለመሄድ ቀዳሚ ፈተናዎች ማለፍ ነበረባቸው። እናም ፑሽኪን ትምህርት ቤት ቋንቋ ተማሩና የተግባር ፈተና ወሰዱ። በትምህርት ሚኒስቴር የተመቻቸውን የውጪ የትምህርት እድልም እንዲሁ ተፈተኑ። ሁለቱም ጥሩ ውጤት የታየበት ነበርና ጉዞ ወደ ራሽያ ሆነ።
የራሽያ 20 ሩብልስ እየተከፈላቸው ትምህርታቸውን መከታተል የጀመሩት ዶክተር ገዛኸኝ፤ ቁጥጥሩ ቢያስቸግራቸውም ቤተሰቡን የሚያግዝ በቤት ውስጥ ባለመኖሩ ካለቻቸው ላይ እየቆጠቡ ወደ ዶላር በመቀየር ገንዘብ ለቤተሰብ ይልኩ እንደነበር ያስታውሳሉ። ይሄ ደግሞ በችግርም መካከል መማር እንደሚቻል አስተምሮኛል ይላሉ።
‹‹ራሴን በራሴ ነው ያስተማርኩት። ቤተሰብ ለራሱ በቂ ነገር የለውም። ስለዚህ የማልነግደው ነገር አልነበረም። ታናሽ ወንድሜን ጨምሮ ቤቱን የመምራትና የማስተዳደር ሀላፊነት የእኔ ብቻ በመሆኑ ጠንካራ መሆኔን አይቼበታለሁ። እናም መቼም ቢሆን ተስፋ መቁረጥ ለስኬት አያበቃምና ቶሎ ተምሬ በውጤት መቀየር እንዳለብኝ አምኜ ነው ወደራሽያ ያመራሁት›› የሚሉት ዶክተር ገዛኸኝ፤ ውጪ የመማር ፍላጎት ስለነበራቸው ለእንግሊዝና ጀርመን የሚያበቃ ውጤት ባያመጡም ራሽያ መግባታቸውን ይናገራሉ። በዚያም የመጀመሪያ የኮሌጅ ትምህርታቸውን በመሬት አስተዳደርና መስኖ ልማት የትምህርት መስክ ዲፕሎማቸውን ለመያዝ ችለዋል።
መማርን የሚወዱት ዶክተር ገዛኸኝ፤ ወደአገራቸው ሳይመለሱ እዚያው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየሰጡ ማስተራቸውን ‹‹ሩሲያን ስቴት ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ፎር ዘሂውማኒቲስ›› እንደተማሩ ነግረውናል። ሂስትሪ ኤንድ ሂውማኔትሪያል በተሰኘ የትምህርት መስክ መመረቃቸውንም አጫውተውናል። ቀጥለው ደግሞ በሳይኮሎጂ ትምህርት ፒኤችዲ ያቸውን ከዚሁ ዩኒቨርሲቲ ማግኘታቸውን አውግተውናል።
‹‹በእርግጥ ያገኘሁት ዶክትሬት ሳይሆን በጥናት የሚሰጥ ፒኤችዲ ነው። ይሄ እንደማንኛውም ትምህርት ለሶስት ዓመት ዩኒቨርሲቲ ገብቶ በመማር አልተገኘም። እናም ዶክተር የመባል ስም ቢሰጥም በሌላ ቦታ ያለው ዋጋ ልዩ ነው። ስለሆነም አሁን ሌላ ዶክትሬት በመማር ላይ እገኛለሁ›› ብለውናል። የሶስተኛ ዓመት የክሊኒካል ሳይኮሎጂ ተማሪ መሆናቸውንም አጫውተውናል። ትምህርት የማቆም አላማ እንደሌላቸው የሚናገሩት ዶክተር ገዛኸኝ፤ ተፈጥሮ በቃህ ስትላቸው ሊያቆሙ ለራሳቸው ቃል መግባታቸውንም ያስረዳሉ።
የገንዘብን ጣዕም በልጅነት
‹‹የመጀመሪያ ሥራ የምለው በልጅነቴ የተለያዩ ነገሮች እየነገድሁ ገንዘብ የያዝኩበትን ጊዜ ነው›› የሚሉት ባለታሪኩ፤ የበጎ ፈቃደኝነት ሥራ ደግሞ ለህይወታቸው ለውጥ ቀያሽ መሆኑን ያነሳሉ። በበጎ አድራጎት ሥራው ተሳታፊ ባይሆኑ ኖሮ ይሄኔ የችግር አረንቋ ውስጥ እንደሚዘፈቁ ያስባሉ። በዚህም በተሳትፏቸው ዝቅተኛ የሚባል ሥራ እንዳይሰሩ ሆነዋል። ሙያና ሙያን ያማከለ ሥራ እንዲሰሩም እድል አመቻችቶላቸዋል።
ራሽያ ውስጥ እያሉ በበጎፈቃድ ብቻ በ‹‹አፖራ›› የሚባል ድርጅት ውስጥ ለ15 ዓመታት ሰርተዋል። ከዚያ ወደ ሊቢያ ተዛውረው “ኢኩሊብር” በተባለ ለትርፍ ባልተቋቋመ ድርጅት ውስጥ ዳይሬክተር ሆነው አገለገሉ። ሆኖም በበጎ ፈቃዱ ከወራት በላይ ማገልገል አልቻሉም። ምክንያቱም በወቅቱ ሊቢያ በጦርነት ውስጥ ነበረችና መስራት አልቻሉም ነበር።
የበጎ ስራ የሰሩባቸው ሁለቱም ድርጅቶች ዩናይትድ ኔሽን ቮሌንተር ኦርጋናይዜሽን በበላይነት የሚያስተዳድራቸው ሲሆን፤ ምንም እንኳን የአሜሪካ ተቀጣሪ ቢሆኑም የሊቢያ ችግር ውስጥ መሆን ስጋት ፈጥሮባቸዋልና ከገንዘብ ህይወት ይበልጣል በማለት ትተውት ወደ ካናዳ እንዳመሩ ይናገራሉ።
ካናዳ ከገቡ በኋላ ግን ያሰቡት የበጎ ሥራ አልነበረም። ስደተኞች ከፍተኛ ችግር ይደርስባቸው ነበር። እናም በሁለቱ ቦታ የሰሩባቸው ድርጅቶች አይነት ስራ ለመስራት መንቀሳቀስ ጀመሩ። የእስከዛሬ ልምዳቸውን መነሻ በማድረግም በመጀመሪያ ቡና ቤት ከፈቱ።
ጥቃቅን የሚመስሉ ነገር ግን አስቸጋሪ የሆኑባቸውን ችግሮች ሻይ ቡና እያሉ እየፈቱላቸው መምጣትን ቀጠሉበት። ጉዳዩ ተጠናከረና አስፈላጊነታቸው ሲሰፋ ደግሞ የራሳቸውን ድርጅት መክፈትና ይህንን ስራ መስራት ግዴታ እንደሆነ ሲያምኑ ‹‹መልቲ ካልቸራል አሶሴሽን›› ብለው አቋቋሙ። በዚህ ብቻ ሳይገደቡም የበጎ አድራጎት ፈቃዳቸውን አጠናክረው ቀጠሉ። ተግባራቸውን
በተለያየ መንገድ ሲያሳዩም ቆዩ። ይህንን ያየ የካናዳ መንግስትም አከበራቸው፤ እውቅና ሰጥቷቸው በስፋት የሚሰሩበትን ምቹ ሁኔታ ፈጠረላቸው። እናም ዛሬ የካናዳ መንግስት ስደተኞችን ሲቀበል በእነሱ ድርጅት አማካይነት ስደተኞቹ የሚፈልጉትን እንዲያገኙ ያደርጋል።
ኑሮ በሰው አገር
‹‹ኢትዮጵያዊያን በምንም መልኩ የሌላ አገር ዜጋ እንደማይንቀን የተረዳሁት ገና በተማሪነት ላይ እያለሁ ነው›› የሚሉት እንግዳችን፤ ከሌሎች በተሻለ ሁኔታ ይታዩ እንደነበር ያነሳሉ። ለአብነት ያነሱት ሁለቱ ነገሮች በባህልና በሀይማኖት መመሳሰልን ነው።
ራሽያኖችም ሆኑ ሌሎች ዜጎች ስደተኞችን መንከባከብና መመገብ ብዙም የሚወዱ አይደሉም። ወደዚያ አገር የሚመጣው ስደተኛ ደግሞ በጣም ብዙ ነው። በተለይ ወቅቱ በረዶ ሲሆን እግራቸው በቅዝቃዜው ምክንያት የሚቆረጥ ዜጎች ቁጥር ይበዛል። እናም የልጅነት ደግነታቸው አላስቀምጥ ቢላቸው እነርሱን መንከባከብ ጀመሩ። ምግብ ማብላት ብቻ ሳይሆን ልብስ ከየኤምባሲው እየለመኑ ለችግራቸው መድረስን ተያያዙ። ይሄ ደግሞ ብዙዎችን ከእግር መቆረጥ ታድጓቸው እንደነበር አይረሱትም።
ዶክተር ገዛኸኝ፤ በራሽያ የትኛውም ኤምባሲ ውስጥ የሚሰራ ዲፕሎማት ልባሹን የሚሰጣቸው ሆነዋል። ከዚያ ለወገኖች የማድረሱን ሥራ ይሰራሉ። በዚህም ምርቃት ብቻ ሳይሆን እውቅና አግኝተዋል። በእርግጥ አንዳንድ ያልተረዷቸው አካላት ብዙ ችግር ደርሶባቸው እንደነበር አይረሱትም። አንተ ማነህ፤ ከየት መጣህ በማለት ሰላዮች ይይዟቸውም እንደነበር ይናገራሉ። ታስረውና በርካታ ስቃዮችን አሳልፈው እንደነበርም ያስታውሳሉ። ግን ‹‹በጎነት ያድናል እንጂ አይገልም›› የሚል እምነት አላቸውና በስራቸው ፈተናውን ድል ነስተዋል።
ዶክተር ገዛኸኝ በመጨረሻ ጥንካሬያቸው የታየላቸውና ለበጎነታቸው ሽልማት የተበረከተላቸው ድንቅ ኢትዮጵያዊ ናቸው። የራሽያ መንግስትም እውቅና ሰጥቷቸው እስከ ዳይሬክተርነት ድረስ በመሾም በጉዳዩ ዙሪያ እንዲሰሩ ያደረጋቸው ጥቁር ሆነዋል። ከዚያም አልፎ በሥራቸው የተገረመው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባልደረባው አድርጓቸዋል።
ማህበራዊ ኃላፊነት
‹‹ስለሌሎች ሰዎች ሳስብ 14ቱ ወንድምና እህቶቼን እንዳነሳ እሆናለሁ። ምክንያቱም 15 ሆኖ በአንድ ገበታ ላይ በተለይ ድሃ ቤት ጠግቦ መነሳት የሚታሰብ አይደለም። ከዚያም አልፎ ለመብላት የማይደረስበት ጊዜም ይፈጥራል። እናም እኔም በዚህ ቤተሰብ ውስጥ እያለሁ ብዙ ጊዜ አንዳንድ ጉርሻ ሲያነሱ ታጥቤ የማልበላበት ጊዜ ብዙ እንደነበር አስታውሳለሁ። እንደውም መቼ ይሆን የምጠግበው እል ነበር። ይህ ጠግቤ ያልበላሁበት ጊዜ ሌሎች ላይ ሲፈጸም ማየትን አልሻምና ለሌሎች በመድረሴ እደሰታለሁ›› ይላሉ።
‹‹ስለተደረገልን ነገር አመስግነን ፤ ያልተደረገላቸውን ማሰብ ግዴታችን ነው። ዛሬ ጠግቤ እበላለሁ። ብዙዎች ደግሞ ሳይበሉ ያድራሉ። እናም ግዴታዬ እንደሆነ በማሰብ ነው ዛሬ የማደርገውን ሁሉ የማደርገው›› ሲሉ አሁን ባላቸው አቅም ማህበራዊ ሀላፊነታቸውን እየተወጡ መሆኑን አጫውተውናል። በእርግጥ ለዶክተር ገዛኸኝ በጎነታቸው የልጅነት ስጦታ ነው። ከልጅነታቸው ጀምሮ በአእምሯቸው ብሎም በተግባር ሲያድግ ሲጎለብት ዛሬ ለደረሱበት ደረጃ ደርሷል።
የአገር አበርክቶ
በ”ድረገታ” በጭቃ ምክንያትና በትራንስፖርት ችግር ይሰቃይ የነበረውን የአገሬውን ሰው ለመታደግ ኮሮኮንች መንገድን በማሰራት ስራ ጀመሩ። ቀጥለውም ለትምህርት ብለው ሰዓታትን በእግራቸው እየተጓዙ ያሳለፉትን ችግር ተተኪው ትውልድ እንዳይቀምሰው ከውጪ ባመጡት ገንዘብና ህብረተሰቡን በማስተባበር ‹‹ኦዳ ነቤ›› የተሰኘውን ትምህርት ቤት አሰርተዋል። በዚህም ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ክፍል ለሚማሩ ተማሪዎች ደርሰዋል። ከዚያ ቀጠሉና ደግሞ አዋላጅ ነርሶች በትልልቅ ሆስፒታሎች ውስጥ ሄደው ስልጠና እንዲያገኙና ልምድ እንዲቀስሙ አድርገዋል። አሁንም በቃኝ ሳይሉ በትምህርት ቤቱና ብዙ ህዝብ በሚገኝባቸው አካባቢዎች የውሃ ማቆሪያ ጉድጓዶችን በማዘጋጀት የውሃ ችግር በተለይ ለከብቶች እንዳይኖር አድርገዋል።
ከባልቻ ሆስፒታል ጋር በመስማማት ታማሚዎችን በባስ በመጫን አምጥተው ሙሉ ህክምና እንዲያገኙም ያደርጋሉ። በጣም ለመታከም አቅሙ የሌላቸውን ከአርባ በላይ ሰዎች እየወሰዱም ህክምና እንዲያገኙ እንደሚያስችሉ አጫውተውናል። ሌላው ያደረጉት ነገር አቧሬ አካባቢ ከሚገኘው የጀርመን የዓይን ሆስፒታል ጋር በመተባበር እንዲሁ አይናቸው በሞራና መሰል ነገር የተጋረደ ሰዎችን ህክምና የሚያገኙበትን መንገድ ፈጥረዋል።
ከሁሉም ግን ሰራሁት የሚሉት በቅርብ ቀን በመጡበት ወቅት ለምረቃ የበቃውን 500 ሰዎች የሚያስተናግደውን ቤተመጽሐፍ ነው።ቤተመጽሀፉ ወደ 200 የሚሆን መጽሐፍና 10 ኮምፒውተሮች ተሟልቶለት ለአካባቢው አስተዳዳሪና ትምህርት ጽህፈት ቤት አስረክበዋል።
በተጨማሪም ከአምስት ሺህ ብር በላይ በሆነ ወጪ የተለያዩ የቤተሙከራ ቁሳቁሶች እና አንድ ባለ 55 ኢንች ቴሌቪዥንም ለትምህርት ቤቱ አስረክበዋል። ሌሎች ስራዎችና ድጋፍ ቢያደርጉም አሁንም ብዙ የጎደለ ነገር ስላለ ጉድለቱን ለማሟላት እንደሚተጉ ነግረውናል።
ዶክተር ገዛኸኝ ለተወለዱበትና ላደጉበት አካባቢ ብቻ አይደለም የሚያስቡት። ከዚያም አልፈው ዱከም ላይ የተማሩበትን ትምህርት ቤት 10 ኮፒውተር ደጉመዋል። በቅርቡም የእሳት አደጋ መኪና፣ አምቡላንስና ሌሎች እቃዎች ለዱከም ከተማ ለማምጣት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን አጫውተውናል። ምክንያቱም ሁሉም አካባቢ እሳት አደጋ ሲፈጠር ከአዲስ አበባ እየመጣ ነው አገልግሎት የሚሰጠው። ይህም አደጋው ብዙ ካጠፋ በኋላ ስለሚሆን ማገዝ እንዳለብኝ በማሰብ ነው። በደሪገታ አሁን ዋነኛ ችግር የህክምና ተቋም አለመኖር ነው።በመሆኑም ቀጣዮ እቅዳቸው ህዝቡ የሚገለገልበትን ክሊኒክ ማቋቋም መሆኑን ገልጸዋል።
ሽልማት
ሩያል ባንክ ኦፍ ካናዳ በየዓመቱ ምርጥ አዲስ ወደ ካናዳ የገቡ ስደተኞች ይሸልማል። እናም በካናዳ ዙሪያ ከተጠቆሙ 3000 አዲስ ስደተኞች መካከል 25ቱ ነጥረው የወጡ ናቸው። እናም ዶክተር ገዛኸኝም ከእነዚህ መካከል ለአዲስ ወደ ካናዳ ለሚገቡ ስደተኞች ባበረከቱት አስተዋዕጾ ተሸላሚ ሆነዋል። እንዲሁም የካናዳ ገቨርነር አዋርድንም አሸንፈዋል። በተጨማሪ ደግሞ ከአለም የሚመጡ ስደተኞችን በመንከባከብና ምክረ ሀሳብ በመስጠት የተሻሉና አንደኛ በመባል ከንግስቲቱ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። እአአ 2016 ደግሞ ዓለም አቀፍ የሰላም ፌዴሬሽን የአለምአቀፍ የሰላም አምባሳደር ሲል ሸልሟቸዋል።
አርሶአደሮችን በተለያየ መስክ በማሰልጠናቸውና የስልጠናው ለውጥ የተሻለ ውጤት በማምጣቱ ከአርሶአደሮች ማህበርም ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። ‹‹ከእነዚህ ሁሉ የሚልቀው ሽልማት ግን አሁን በአገሬ ሰዎች የተሸለምኩት ነው። ምክንያቱም በወረወርኩት ጥቂት ጠጠር ይህንን ያህል ክብርና ሞገስ ካገኘሁ ከዚህ የበለጠ ለአገሬ ብሰራማ ምን እንደማገኝ መገመት አያዳግተኝም። ለሰው አገር ሙሉ ሰዓቴን ገብሬ እሰራለሁ፤ ግን ማን እንደአገር ሆነና ልዩነቱ የየቅል ሆነ። ግን ለሽልማት ተብሎ ሳይሆን ለአገር ለውጥ ሲባል የተቻለን ያህል ማድረግ ብዙ ክብር አለውና ሁሉም ይትጋ››ይላሉ።
ውሃ አጣጭ ሲሰጥ
ከባለቤታቸው ጋር የተገናኙት ራሽያ ውስጥ የሚገቡ አዲስ ስደተኞችን ለማገዝ የሚያስችል መርሃግብር ላይ ነው። እርሷ ተጋባዥ እንግዳ ሆና ካስተናጋጆቹ እኩል ስትሳተፍና ስታግዝ ነበር። እናም ከሁሉም በላይ በእርሷ ተደንቀው ሲመለከቷት ቆዩ። ‹‹እነዚህን ስደተኞች በመመገብና ሌሎች የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማሟላት የተለያዩ ነገሮችን መስራት የሚፈልግ ከመካከላችሁ ፈቃደኛ አለ›› ብለው ሲጠይቁም ቅድሚያ ፈቃደኝነቷን የገለጸችው እርሷ ነበረች። ይበልጥ በሁኔታዋ ተገረሙ። አሁንም ቢሆን አብሮ የበጎ ፈቃድ ስራውን ለመስራት እንጂ ለፍቅር አልተመኟትም ነበር። ምክንያቱም የውጪ ዜጋ አገባለሁ ብለው አስበው አያውቁምና ነው።
ቅንና ደግ የሆነችው የዛሬዋ ሚስታቸው ግን በሁሉ ነገሯ ልባቸውን እየረታች መጣች። ያም ሆኖም ግን ለትዳር ሊጠይቋት አልደፈሩም ። ምክንያቱም ገና ቀረቤታቸው አልጠነከረም። ይሁንና በተለያዩ የድጋፍ ስራቸው ከራሽያ ጀምረው እስከ ካናዳ የሚያስተሳስራቸው መስመር በመዘርጋቱ ለሌላ መሆን እንደሌለባት አሳመናቸው። በዚህም አንድ ቀን ድፍረታቸውን አሰባሰቡና ጥያቄ አቀረቡ። የእርሷም ምላሽ ቤተሰብ ይጠየቅ ሆነ። እጅ ነስተው ቤተሰቡን ተዋወቁ። ፈቃድ ተሰጣቸውና ትዳር ተመሰረተ።
‹‹እኛን ያቀራረበን በበጎ ተግባር መሳተፋችን ብቻ አይደለም›› የሚሉት እንግዳችን፤ ባለቤቴ አገሬን ወዳድ መሆኗና ለኢትዮጵያ ያላት ምልከታ የሚያስደስት ስለነበር ነው። አገሬን በጣም ትወዳታለች። ዜጎቿንም በጣም ታከብራለች። ስለዚህም እርሷን የሚመስል ከእኔ ባህሪ ጋር በሚገባ የሚግባባ ከየትም አላገኝም ብዬ አገባኋት ። ከዚያም የአንድ ወንድ ልጅ አባት አደረገችኝ›› ይላሉ። የእንግዳችን ባለቤት ኒኮል ትባላለች። ካናዳዊት ብትሆንም የአማርኛ ቋንቋ ለመቻል ብዙ ትጥራለች። በዚህም ትንሽትንሽ እንደምትናገር አጫውተውናል።
የሜዲካል ኢንጅነሪንግ ምሩቅ የሆነችው ኒኮል፤ ሰዎችን መርዳት እና ማስደሰት ተፈጥሮዋ ነው። ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ችላለች።በዚህም በጣም እንደተደሰተችና በተለይም በአገሪቱ እንግዳ አቀባበል እንደተገረመች ተናግራለች።”ኢትዮጵያ ተወዳጅና ሁሌ ልኖርባት የምፈልጋት አገር ነች” ብላለች።
መልዕክት
‹‹ሁሉም ነገር በሁሉም ቦታ ቢሰራ ለውጥ እንደሚያመጣ ግልጽ ነው። ሰው በስደት ሌላ ቦታ ሄዶ ሰርቶ መለወጡም መልካም ነው። ግን አገርን መርሳት ተገቢ አይደለም። የትም ቢኬድ ስደተኛ ከመባል ውጪ የአገር ዜግነት ተሰጥቶ እንኳን ክብሩ የአገርን ያህል አይሆንም። እናም ሁሉም ነገር በአገር ያምራልና በተቻለን መጠን አገራችንን ማስታወስ ይገባናል። ›› ይላሉ የመጀመሪያ ምክረሀሳባቸውን ሲያነሱ።
ቀጥለው ደግሞ፤ ደግነት ከሰፈር ይጀምራል። የትውልድ ቀያችንን እየረዳን ከመጣን በአገሪቱ ውስጥ ያለው ክልል ሁሉ ያላንዳች ልዩነት ያድጋል። እናም ዲያስፖራዎች ቢያንስ ለቀያቸው መደጎም ይልመዱ ብለዋል። በተለይ በችግር የወጣንባትን ምድር ልንረሳ አይገባም ይላሉ።
‹‹አስከሬናችን ሳይሆን ማንነታችንና እገዛችን ለአገር ያስፈልጋል። በቁም ሆነን መደጎምን የነገ ልናደርገው አይገባም። በእግራችን መጥተን አሻራችንን ማሳረፍ እንልመድ›› በማለትም ማሳረጊያ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። እኛም ያሉትን በተግባር እናውል በማለት ለዛሬ አበቃን። ሰላም!
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 19/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው