በግማሽ የሰውነት ክፍል ላይ በድንገት የሚወጣ ሽፍታ ሲሆን በአገራችን አባባሉ ሳይንሳዊ መሰረት ባይኖረውም አልማዝ ባለጭራ እየተባለ ይጠራል፤ ሽፍታው ውኃ ቋጥሮ በጣም የሚያም ነው፤ አብዛኛውን ጊዜ በጀርባ፣ በማጅራት፣ በደረት ወይም በፊት ላይ ይወጣል።ሽፍታው ለ2 ወይም 3 ሳምንታት ከቆየ በኋላ በራሱ ይጠፋል፤ አንዳንድ ጊዜ ሽፍታው ከጠፋ በኋላ ሕመሙ ሊቆይ ወይም መልሶ ሊያገረሽ ይችላል።የአልማዝ ባለጭራ በሽታ ዋና መንስኤ ጉድፍን( Herpes Zoster) (Chickenpox or Shingles) የሚያስከትለው ቫይረስ ነው።በሽታው ከዚህ በፊት ጉድፍ የነበረባቸውን ሰዎች ያጠቃል፤ ሆኖም አደገኛ የሚባል አይደለም።ነገር ግን ሁኔታው ምናልባት ሌሎች እንደ ካንሰር ወይም ኤድስ የመሳሰሉ አደገኛ በሽታዎች የማስጠንቀቂያ ምልክት ሊሆንም ይችላል።ቁስለቱ እንዳያመረቅዝ በማፅዳትና በመንከባከብ ማዳን ይገባል፤ በሽታው የሚከሰተው በቫይረስ አማካኝነት በመሆኑ የፀረ ተዋሲያን መድኃኒቶች ብንወስድ ምንም አይጠቅምም።ሁኔታውን ለመቆጣጠር ግን የፀረ ቫይረስ መድኃኒቶች ሊታዘዙና ሊወሰዱ ይችላሉ።
ኸርጲስ በሽታ ምንድነው?
ኸርጲስ እየተባለ የሚጠራው በሽታ በዓለማችን በስፋት የሚከሰት ሲሆን መንስኤው የቫይረስ ልክፍት ነው።በኸርጲስ ስር ሰዎችን የሚያጠቁ ስምንት የሚሆኑ የቫይረስ ዓይነቶች ያሉ ሲሆን በአጠቃላይ ኸርጲስ ይባላሉ ወይም ኸርጲስ ሂዩማን ቫይረስ (Herpes Human Viruses (HHV)) ይባላሉ።ከነዚህ ውስጥ አንዱ በአገራችን አልማዝ ባለጭራ (Herpes Zoster) የሚባለው ነው፤ ከስምንቱ ውስጥ በሰዎች ላይ በስፋት የሚታዩት ሁለት ሲሆኑ ኸርጲስ ሲምፕሌክስ ቫይረስ(herpes simplex virus) ይባላሉ፤ ወይም በአጭሩ( HSV) በመባል ይጠራሉ።እነኝህ የኸርጲስ ቫይረሶች ቁጥር 1 (HSV-1) እና ቁጥር 2 (HSV-2) ተብለው ይለያሉ።እነኝህ ቫይረሶች ተመሳሳይነት ያላቸው ቢሆንም የሚለዩት በአካል ላይ በሚወጡበት ቦታና በሚስፋፉበት መንገድ መሰረት ነው።የ(HSV-1) በአፍ አካባቢ የሚከሰተው ሲሆን ወደ ሌሎች፣ አፍ-ለ-አፍ በሚኖር የምራቅ ንክኪ ሊተላለፍ ይችላል። የ(HSV-2) ያለበት ሰው ደግሞ ከሌሎች ጋር በሚኖረው የግብረስጋ ግንኙነት ወደሌሎች ሊያስተላልፍ ይችላል።ባጠቃላይ ቁጥር 1 አብዛኛውን ጊዜ በአፍ አካባቢ የሚከሰት ሲሆን ቁጥር 2 ግን የብልት አካባቢዎች ላይ የሚታይ ነው፤ ይሁን እንጂ ሁለቱም በሌሎች የሰውነት አካባቢዎችም ላይ እንዲሁም አንዱ በሌላኛው ቦታ ላይ ሊከሰት ይችላል።አንድ ሰው በነኝህ ቫይረሶች ተለክፎ ምንም ምልክት ሳያሳይ እድሜልኩን ሊኖር ይችላል፤ አንዳንዶች ላይ ደግሞ ደጋግሞ በመመላለስ የግርሻ ሁኔታ ሊታይ ይችላል፤ አንድ ጊዜ ቫይረሱ ሲይዘን በነርቭ ስርዓት ውስጥ በመባዛትና በመውረር ዕድሜ ልኩን በዛው መሽጎ ይቆያል።በቆይታውም ምንም ምልክቶችን ሳያሳይ ለዓመታት ሊቆይ ይችላል፤ ነገር ግን አካላችን በተለያዩ ምክንያቶች በሚደክምበት ወቅት (ማለትም በሌላ በሽታ ምክንያት፣ በጭንቀትና ውጥረት ሰዓት፣ በሴቶች ላይ የወር አበባ በሚታይ ወቅት እንዲሁም የበረታ ፀሐይ በሚያገኘን ሰዓት) ራሱን በማንቃት መታየት ይጀምራል። በነኝህ ጊዜያት ቫይረሱ በመራባት ወረራ ያደርጋል፤ ተደጋግሞ እንዲከሰትብንም በር ይከፍታል።በዚህ ወቅትም ወደሌሎች የማስተላለፍ ሁኔታችን ከፍተኛ ይሆናል።አብዛኛውን ጊዜ ጤናማ የሚባል ሰው ቫይረሱ በአንዳች አካል ክፍል ላይ ሲለክፈው የሚወጣው ሽፍታና ውኃ መቋጠር የከፋ መስሎ ቢታይም የማገገም ሁኔታ ይኖራል፤ ነገር ግን እንደ ኤች አይ ቪ(HIV) ያለ ቫይረስ የያዛቸው የመድኀን ስርዓታቸው(immune systems)የተዳከመባቸው ሰዎች ቫይረሱ ሊነግስባቸው ይችላል፤ ለሌሎች አደገኛ በሽታዎችም ሊዳርጋቸው ይችላል።ምንም እንኳን በሽታው የቫይረስ ልክፍት ሆኖ የሚድን ባይሆንም፣ ሁኔታውን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ፀረ ቫይረስ መድኃኒቶች ግን አሉ።ቁጥር 1 ኸርጲስ ወይም በአፍ አካባቢ(Oral Herpes) የሚከሰት
ይህ በሽታ አብዛኛውን ጊዜ በአገራችን ምች መታኝ ወይም ገረፈኝ የሚባለው ነው፤ ቁጥር 1(HSV-1) ኸርጲስ በቫይረሱ በተበከለ ምራቅ አማካኝነት መተላለፍ የሚችል ሲሆን በሕፃናትና በአዋቂዎች ላይ ሊከሰት ይችላል፤ በሕፃናት ላይ ሲከሰት ድንገተኛ ትኩሳት፣ ያበጠና የቀላ ድድ እንዲሁም በአፍ፣ በምላስና በከንፈር ላይ ውኃ የቋጠሩ ሽፍታዎች ይፈጠራሉ።እነኝህ ሽፍታዎች በመፈነዳዳት አንድ ትልቅ ቁስል እንዲፈጠር ያደርጋሉ፤ የንፍፊት ስሜትም ይኖራል።ይህ የበሽታው የመጀመሪያ ክፍል ሲሆን ከ5-7 ቀናት ይቆያል፤ በመቀጠል ምልክቶች እየታዩ እስከ ሁለት ሳምንታት ይዘልቃል፤ በሦሥትና ከዛ በላይ ሳምንታት ምንም እንኳን ቫይረሱ በምራቅ ውስጥ ያለ ቢሆንም ሁኔታው ጠገግ ብሎ ይድናል።በአዋቂዎች ላይ ደግሞ ከአፍና ከከንፈር ይልቅ ሰርንና አንቃር ላይ ይከሰታል፤ በነኝህ አካባቢዎች የሚፈጠረው ውኃ የሚቋጥር ሽፍታ ሊፈጠር ይችላል፤ በተለይ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያዝ ሰው ላይ ሽፍታ፣ ራስምታት፣ ድካምና የአንቃር ቁስለት ሊከተል ይችላል።ይህ በሽታ አንዴ ከዳነ በኋላ ተመልሶ ሊመጣ ይችላል፤ ግርሻው በአብዛኛው ሰዎች ላይ በዓመት ሁለት ጊዜ ሊያጋጥም ይችላል፤ አንዳንዶች ላይ ደግሞ በመጥናት በየወሩ ሊመላለስባቸው ይችላል።እንዲህ ሲሆን በአካላችን ላይ እንደወረራ (Outbreaks) ሊቆጠር ይችላል።ወረራው ሲጀምር የመቆጥቆጥ፣ የመለብለብና የሕመም ስሜት በአካባቢው ላይ ይሰማናል፤ በመቀጠልም ቀይ ሽፍታ ይወረናል፤ እነኝህ ሽፍታዎች በመፈንዳት ከ24 ሰዓት እስከ 5 ቀን ባለው ጊዜ ውስጥ ቫይረሶቹ ተጋልጠው በመውጣት ሌሎች ሰዎችን ሊበክሉ ይችላሉ።
ቁጥር 2 ኸርጲስ ወይም በፆታ ብልቶች(Genital Herpes) አካባቢ የሚከሰት
ምንም እንኳን በብልት አካባቢ የሚከሰተው ቁስለት በቁጥር 2 ኸርጲስ (HSV-2) ቢሆንም ሁኔታው በቁጥር 1 ቫይረስ አማካኝነትም ሊከሰት ይችላል(ለምሳሌ በአፍ በሚፈፀሙ ግንኙነቶች (oral sex) ሊያጋጥም ይችላል)።ቫይረሱ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያገኘን ከ3-7 ቀን ባለው ጊዜ ውስጥ ምልክቶች መታየት ሊጀምሩ ይችላሉ።በመቀጠል ትኩሳት፣ ራስምታት፣ የድካም ስሜትና የጡንቻ ሕመም ሊሰማን ይችላል።የቫይረስ ልክፍቱ ባጋጠመው የብልት አካባቢም የሕመምና የማሳከክ ሁኔታ ይኖራል፤ በተጨማሪም ለመሽናት መቸገር፣ ፈሳሽ ከብልት መውጣት(በተለይ ሴቶች ላይ) ይኖራል፤ እንዲሁም ንፍፊት ያጋጥማል።ልክ በአፍ አካባቢ እንደሚያጋጥመው ቁጥር 1 ኸርጲስ፣ በብልት አካባቢ የሚያጋጥመውም ሽፍታ በመፈነዳዳት የቁስለት ሁኔታ ሊፈጥር ይችላል፤ በመሆኑም በሴቶች ላይ በብልትና በብልት ከንፈሮች ላይ፣ በቂጥና አልፎ ተርፎ እስከ አንገት ማህፀን ድረስ ሊዘልቅ ይችላል።በወንዶች ላይ ደግሞ በብልትና ቆለጥ ከረጢት ላይ፣ በቂጥና በጭን እንዲሁም እስከ ሽንት ትቦ ሊያዳርስ ይችላል።በፊንጢጣም አካባቢ ግንኙነት ከተደረገ ሊያጋጥም ይችላል።በብልት አካባቢ የሚከሰተው የዚህ ቫይረስ ልክፍት አስቸጋሪነቱ ተመላልሶ ማገርሸቱ ነው፤ ግርሻው ከሰው ሰው የሚለይ ቢሆንም አብዛኞች ላይ ግን በያዛቸው በዛው ዓመት ደግሞ የመከሰት ሁኔታው ያጋጥማል።
ምርመራ እንዴት ነው የምናደርገው?
ኸርጲስ ለክፎኛል የሚል ጥርጣሬ ከገባን ወደ ቆዳና አባለዘር ሐኪም መሄድ አለብን፤ ሐኪሞች የቫይራል ካልቸር እንድናሰራ ሊያዙ ይችላሉ፤ ይህ ሂደት ከጥቂት ቀናት እስከ ሳምንት ሊወስድ የሚችል ነው(የምርመራ ውጤት)፤ በተጨማሪም ከቆዳ ላይ በሚወሰድ ቅንጣትና በደም ምርመራ ሊታወቅ ይችላል።
ሕክምናው ምንድነው?
ሕክምናው ከሐኪም ጋር በመነጋገር የሚካሄድ ሲሆን የተለያዩ አማራጮች ያሉት ነው፤ ኸርጲስ በቫይረስ አማካኝነት የሚከሰት እንደመሆኑ ጨርሶ የሚድን በሽታ ባይሆንም አንዳንድ ሁኔታውን ለማቅለል የሚታዘዙ መድኃኒቶች አሉ፤ እነኝህ የፀረ ቫይረስ መድኃኒቶች ደጋግሞ ለሚጠናባቸው ሰዎች ይታዘዛሉ።ከሚታዘዙ መድኃኒቶች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙባቸዋል፤ (Acyclovir (Zovirax) አሳይክሎቪር፤ Famciclovir (Famvir) ፋምሳይክሎቪር፤ Valacyclovir (Valtrex) ቫልትሪክስ) ከነዚህ በተጨማሪም በቅባት መልክ የሚዘጋጁ ቁስሉ ላይ የሚደረጉ ያለሐኪም ትዕዛዝ የሚሸጡ መድኃኒቶች አሉ።እነዚህ በአፍም ሆነ በቅባት መልክ የሚወሰዱ መድኃኒቶች ቁስሉ ወዲያው እንደጀመረ ቶሎ መወሰድ አለባቸው፤ በፍጥነት ለማገገም ይረዳሉ።
ራሳችንን እንዴት ከበሽታው ወይም ከቫይረሱ መከላከል እንችላለን?
ኸርጲስ በሽታን የሚያስከትሉት ቫይረሶች በዓለማችን ላይ ሰፍነው የሚገኙና የተለመዱ የሚባሉ ናቸው፤ አብዛኛውን ጊዜ ከአንዱ ወደ ሌላው የሚተላለፈው በግብረ ስጋ ግንኙነቶች ውስጥ ነው።ይህም በመሆኑ የመከላከል ሂደቱን ከባድ ያደርገዋል፤ ነገር ግን የማይቻል አይደለም።ቫይረሱን ለመከላከል፣ በተለይ ገና ከያዛቸው ሰዎች ጋር ያለንን ንክኪ ያለው ግንኙነት ማቆም፤ ግድ ከሆነ በግብረ ስጋ ግንኙነቶች ወቅት ኮንዶም መጠቀም፣ በብልት አካባቢ የሚከሰተውን ኸርጲስ ሊከላከል ይችላል፤ ይህም ቢሆን በጥንቃቄ መከወን አለበት።ምክንያቱም ከብልት አካባቢ ውጪ ባሉ ቦታዎችም ቫይረሱን ሊያስተላልፉ የሚችሉ ክፍተት ያላቸው ቁስሎች ሊኖሩ ይችላሉና።
ኸርጲስ በማኀበረሰቡ ውስጥ
ብዙ ሰዎች በነዚህ ቫይረሶች በሚለከፉበት ጊዜ ምንም ምልክትና ስሜት ላይኖራቸው ይችላል፤ ምልክቱ ካለ ደግም በጣም ቀላል ስለሚሆን ሳይታወቅ ለረዥም ጊዜ ሊቆይ ይችላል።በዚህ ምክንያት ሰዎች በቫይረሱ መቼ እንደተያዙ ለማወቅ አስቸጋሪ ነው።በማኀበረሰብ ውስጥ እንደሚታየው በሽታው ገና በቁስል መልክ ብቅ ሲል በሁለት ጓደኛሞች መካከል አንተ ነህ/አንቺ ነሽ ያመጣኸው/ ሽው የሚል ንትርክ እንዲኖር ምክንያት ይሆናል።
ማጠቃለያ
ምልክቶች በሚታዩበት ጊዜ በአፍ፣ በከንፈር ወይም በብልት አካባቢዎች ላይ መጀመሪያ ቀላ ያሉ፣ በመቀጠል ውኃ የቋጠሩ አንድ ወይም ከዛ በላይ የሆኑ ሽፍታች በአንድ ላይ እጅብ ብለው ይወጣሉ።የቋጠረው ፈሳሽ በራሱ ይፈርጥና ክፍት ቁስል ይፈጠራል።ይህ በራሱ ከ2 – 4 ሳምንታት ባለው ጊዜ ውስጥ ይድናል። ለመጀመሪያ ጊዜ ብቅ በሚሉበት ጊዜ አብሮ የሚከሰት ብርድ ብርድ ማለት፣ ራስ ምታት፣ ቁርጥማት እና የንፊፊት የዕጢዎች እብጠት ሊታይ ይችላል።እነዚህ ክፍት ቁስሎች የህመም ስሜት እንዳላቸውም ማወቅ ተገቢ ነው፡፡
ምንጭ – ሐኪም በሌለበት (በጠና አበረ)፣ www.goshhealth.org
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 18/2012