ኦሮምኛንና አማርኛ ቋንቋዎችን አቀላጥፈው ይናገራሉ። የእናትነት ስሜት ባለው የእንግዳ አቀባበላቸው ይታወቃሉ። ከግል ተቀጣሪነት ተነስተው በሚሊዮኖች ኃብት ያለው ስራ እያንቀሳቀሱ የሚገኙ ሴት ናቸው።
ከሰራተኞቻቸው ጋር ያላቸው ቀረቤታ መልካም መሆኑን አብረዋቸው የሰሩ ባለሙያዎች የሚመሰክሩት ጉዳይ ነው። በከተማዋ የሰፈር ስም መጠሪያ እስከመሆን የደረሰ የሆቴል ስራ ላይ ተሰማርተው ለበርካቶች የስራ እድል ፈጥረዋል።
ልጅነት በድሬዳዋ
ወይዘሮ መሰረት በሪሁን ይባላሉ የዛሬዋ እንግዳችን። ወይዘሮ መሰረት ተወልደው ያደጉት በምስራቋ የንግድ ከተማ ድሬዳዋ ነው። ብዙ የቤተሰብ አባላት ባለበት ቤት ውስጥ አድገዋል። የመጀመሪያ ልጅ ሲሆኑ ከእርሳቸው በታች 10 ልጆች አሉ። አባታቸው ነጋዴ በመሆናቸው ከልጅነታቸው ጀምሮ የንግዱን ዓለም ሂደት እየተመለከቱ እንዲያድጉ ረድቷቸዋል።
ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ደግሞ እዛው ድሬዳዋ ሚካኤል የተሰኘው ትምህርት ቤት ገቡ። ከዚያም ልኡል መኮንን ትምህርት ቤትን ተቀላቅለው እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ተምረዋል። ቤተሰባቸው ወደ ንግዱ ዓለም በማተኮሩ ምክንያት እርሳቸውም በልጅነታቸው ገንዘብን በስራ ላይ አውሎ ወደተሻለ ደረጃ ስለማድረስ ነበር የሚያስቡት።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ግን ለአካውንቲንግ ትምህርት ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ ቤተሰቡ ወሰነ። እናም አዲስ አበባ ቦሌ አካባቢ የሚገኙት አክስታቸው ጋር እየኖሩ የአካውንቲንግ ትምህርታቸውን ተከታተሉ።
ስራ በአዲስ አበባ
የሁለት ዓመት ቆይታ የነበረው ትምህርታቸው ሲጠናቀቅም አራት ኪሎ አካባቢ በሚገኘው ተስፋ ገብረስላሴ ማተሚያ ቤት በሪከርድ ክፍል ስራ አግኝተው አዲስ አበባ የመቆየታቸው ጉዳይ እውን ሆነ። ይሁንና በየጊዜው ወደ ድሬዳዋ እየተመላለሱ ቤተሰባቸውን መጠየቃቸውን ግን አላቋረጡም ነበር።
በማተሚያ ቤቱ ለአራት አመታት እንደሰሩ ደግሞ የ1977 ዓመተ ምህረቱ የኢትዮጵያ ድርቅ ተከሰተ። በወቅቱ ድርቁን አስመልክቶ የእርዳታ ስራ ሲያከናውን በነበረው የስዊድሸ ተራድኦ ድርጅት ውስጥ በሒሳብ ሙያ ስራ በማግኘታቸው ድርጅቱን ተቀላቀሉ። በእርዳታ ድርጅቱ ውስጥ ለሁለት አመታት እንደሰሩ ግን ከልጅነታቸው ይመለከቱት የነበረው የቤተሰባቸው ንግድ ስራ ተጽእኖው እያየለ በመምጣቱ ሃሳባቸው ሁሉ የግል ስራ ስለመጀመር ሆነ።
በስራ ላይ እያሉ ትዳር መስርተው ነበር፤ መኖሪያ ቤታቸው ደግሞ ከዋናው መንገድ ዳር ይገኛል። እናም ቤት ውስጥ ምግብ ሲሰሩ ዘመድ አዝማዱ በተደጋጋሚ በጣም ይጣፍጣል ይላቸው ነበርና፤ ይህን ተወዳጅነት መንገድ ዳር ከሚገኘው ቤታቸው ጋር አገናኝተው ማሰላሰለ ያዙ። ተወዳጅ የቤት ውስጥ ሙያቸውን መንገድ ዳር በምትገኘው ቤታቸው አማካኝነት ወደውጭ አውጥተው ለመነገድ ይወጥናሉ። ስራቸውንም በመልቀቅ ስለምግብ ቤቱ እውን መሆን የሚረዱ ዝግጅቶችን በአጭር ጊዜ ማከናወን ጀመሩ።
ውሎ በሬስቶራንት
ከመኖሪያቸው ጀርባ ያለውን ቤት ጭምር በመከራየት መኖሪያቸውን ወደኋለኛው ግቢ አድርገው አነስተኛ ምግብ ቤት ከፈቱ። ቤታቸው ውስጥ የነበሩ ዕቃዎችን ሰባስበው ለአገልግሎት አዋሏቸው። በመጀመሪያው ቀን ውላቸውም የሰሯቸውን ምግቦች ለሚያውቋቸው ሰዎች ቅመሱ እያሉ የምግብ ቤታቸውን ትሩፋቶች አስተዋወቁ።
ድሬዳዋ የነበሩት እህታቸው ወደ አዲስ አበባ መጥተው አብረዋቸው ነበሩና እርሳቸውን ይዘው ምግብ ማዘጋጀቱን ተያያዙት። እንዲህ እንዲህ እያለ በመጀመሪያዋ ቀን ተጋብዘው የመጡ ሰዎች ከአድናቆት ጋር ተጨማሪ ደንበኞችን ይዘውላቸው መምጣት ጀመሩ።
አምስት አስር እያለ በየቀኑ በመቶዎች የሚስተናገዱበት ቤት ሆነ። ምግባቸው ታዋቂነቱ በመጨመሩ ከየአቅጣጫው ደንበኛ የጎበኛቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። በተለይ በምሳ ሰዓት ከየመስሪያ ቤቱ የሚመጡ በርካታ ደንበኞችን ያስተናግዱ ነበር። በዚህ ምክንያት ስራው እየተስፋፋ ሲመጣ አምባ ራስ ብለው የጀመሩት ምግብ ቤት ወደሬስቶራንትነት አደገ።
ከዓመታት በኋላ የወይዘሮ መሰረት ሬስቶራንት ደንበኞች በማየላቸው የተነሳ ከእርሳቸው አልፎ ስድስት ሰራተኞችም ተቀጥረው ምግብ ከመስራት እስከማስተናገድ ያለውን ስራ መከወን ጀመሩ። በዚህ ስኬት መሃል ግን ወይዘሮዋን የሚፈትን ነገር አጋጠመ። ለስድስት ዓመታት ከሰሩበት የሬስቶራንት ኪራይ ቤት እንዲለቁ በአከራያቸው አማካኝነት ይጠየቃሉ።
የሰው ቤት የሰው ነው ብለው በየጊዜው እየገዙ እና በባለሙያ እያሰሩ ያደራጇቸውን የሬስቶራንት እቃዎቻቸውን ሸክፈውም ሌላ ቤት ኪራይ ፍለጋ ሄዱ። ከብዙ ፍለጋ በኋላም አንድ ጥሩ ግቢ በመገኘቱ ተከራይተው ስራቸውን በአዲስ ስም ኦሜጋ ብለው አስቀጠሉት።
አዲሱ ሬስቶራንታቸው ሰፋ ያለ ነበርና በ10 ሺህ ብር ነበር የተከራዩት። በዚያም የተለመዱ የጾም እና የፍስክ ምግቦቻቸውን ማቅረቡን ተያያዙት። በወቅቱ አንድ በስጋ የተሰራ ምግብ በ10 እና በ15 ብር የሚቀርብ ቢሆንም ገንዘቡ ዋጋ ነበረውና በጥቂቱ ትርፋቸው ደግሞ በሌላኛው ቀን ግብዓቶችን ገዛዝተው ስራቸውን ያስፋፉ እንደነበር አይረሱትም።
ከአትክል ተራ እና ከተለያዩ አካባቢዎች የሚያመጧቸው እና ለምግብ ዝግጅት ግብዓቶቻቸውን የሚሆኑ ጥሬ ዕቃዎችን እራሳቸው እየገዙ ያቀርቡ ነበር። ባለቤት ነኝ ብለው ከመቀመጥ ይልቅ በየስራዎቹ ላይ ሁሉ ተፍ ተፍ በማለት ሰርቶ በማሰራት ጥንካሬያቸውን ያሳዩ እንደነበር ያስታውሳሉ።
በቤት ኪራይ ውስጥ ብቻ ተወስነው መስራታቸው የኋላ ኋላ ጉዳት ላይ ሊጥላቸው እንደሚችል የታዘቡት ወይዘሮ መሰረት ደርግ ወደመውደቂያው አካባቢ ቅይጥ ኢኮኖሚን ተግባራዊ ሲያደርግ የመስሪያ ቦታ ጠይቀው ለመስራት ይወስናሉ። እናም ለሆቴል ቤት መስሪያ የሚሆን ቦታ እንዲሰጣቸው ጠየቁ።
የሆቴል ጅማሮ
ከብዙ ጥረት በኋላ በአዲስ አበባ ቤለር የተሰኘው አካባቢ መሬት ተፈቅዶላቸው ለግንባታው የሚሆን ብድር ያፈላልጉ ገቡ። ከልማት ባንክ አራት ሚሊዮን ብር ብድር እና ከእራሳቸው ተጨማሪ ገንዘብ አድርገው ያለሙለትን ሆቴል ግንባታ ጀመሩ። የሬስቶራንት ንግዳቸውን ሳይለቁ የሆቴል ግንባታው ቀስ በቀስ ማሰራቱን ቀጠሉ። በ1988 ዓ.ም ሆቴሉ ግንባታው እና ሙሉ እቃዎች ተሰናድተው በመጠናቀቃቸው የአሁኑ ራስ አምባ ሆቴልን ስራ በይፋ አስጀመሩ።
ሆቴሉ ከመሬት በላይ ባለ ሶስት ወለል የያዘ ነው። ወይዘሮ መሰረት የራስ አምባ ሆቴልን ሲያስጀምሩ በጊዜው 70 ሰራተኞችን ቀጥረው ነበር። ሆቴሉም የተዋቡ መኝታ ክፍሎች እና የመሰብሰቢያ አዳራሾችን በመያዙ ተመራጭ መዝናኛ ቦታ ነበር። በወቅቱ በአካባቢው ምንም አይነት ሆቴል ባለመኖሩ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና የተለያዩ ኤምባሲዎች ዋነኛ ደንበኞቻቸው እንደነበሩ ያስታውሳሉ።
አሁንም ድረስ የሆቴሉ ቋሚ ደንበኛ የሆኑ ሰዎችም በርካታ ናቸው። ሆቴሉን ስራው እያደገ እና ታዋቂነቱ ሲጨምር ደግሞ የቀድሞውን የልማት ባንክ ብድራቸውን ከፍለው ጨረሱ። ከዚያም በ1996 ዓ.ም የማስፋፊያ ግንባታ በሆቴሉ ግቢ ለማከናወን ተነሱ።
ከማስፋፊያው በኋላ
የማስፋፊያው ግንባታ ከመሬት በላይ ባለ አምስት ወለል ህንጻ የያዘ ነው። እራሳቸው እየተከታተሉ ያስገነቡት ህንጻ በውስጡ የመኝታ ክፍሎች እና ለሰርግ የሚሆኑ አዳራሾችን ይዟል። አሁን ላይ የወይዘሮ መሰረት ሁለት ህንጻዎች ያሉት ራስ አምባ ሆቴል በአጠቃላይ 52 መኝታ ክፍሎች አሉት። እያንዳንዳቸው ከ700 ብር በላይ እንደየደረጃቸው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛል።
ሰፊው የህንጻው አዳራሽ ደግሞ በሰው ልክ በሚታሰብ አሰራር ለሰርግ አገልግሎት ከመዋሉ ባለፈ የተለያዩ ስብሰባዎች ይስተናገዱበታል።
የካፌ እና የምሳ መመገቢያ ክፍሎች ደግሞ ከተማዋን ከላይ ሆነው እያዩ ለሚስተናገዱ ሰዎች ምቹ በሆነው ስፍራ ላይ በመገኘቱ ብዙዎች ይታደሙበታል። በንጽጽር ከከተማዋ የሆቴሎች ዋጋ ጋር ሲወዳደር በዝቅተኛ ወጪ መዝናናት የሚቻልበት ሆቴል መሆኑን የሚናገሩት ወይዘሮ መሰረት፤ በባለሙያዎች በጥራት የሚዘጋጁ ምግቦች አሁንም ድረስ ተወዳጅ መሆናቸውን ይገልጻሉ።
አብዛኛውን የሆቴሉን ስራ በመቆጣጠር የሚያሳልፉት እንስት፤ ከልጆቻቸው ጋር አብረው የሚሰሩበት ጊዜም አለ። ከሁለቱ ልጆቻቸው በተለይ አንደኛዋ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉ ትምህርቷን የተከታተለች በመሆኑ ወደፊት እርሳቸውን ተክታ ስራውን የምታስቀጥል እንደሆነች ተስፋ አድርገዋል።
አሁን የሆቴሉ ስራ ላይ በአጠቃላይ 110 ሰራተኞች ተቀጥረው የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ። በዚህ ደስተኛ መሆናቸውን እና ማንኛውም ሰው ከእራሱ አልፎ ለሌሎች ስራ መፍጠር ከቻለ በርካታ ያልተነኩ ዘርፎች በኢትዮጵያ መኖራቸውን ይናገራሉ።
ቀጣይ ውጥን
በቀጣይ ወይዘሮ መሰረት በቱሪስት መዳረሻ ከተማዎች ላይ ሰፋፊ የሆቴል እና የሎጅ አገልግሎቶች ላይ ለመሰማራት አቅደዋል። በተለይ በቢሾፍቱ ከተማ ሆቴል ለመገንባት የኢንቨስትመንት ፈቃድ አውጥተው እንቅስቃሴ ጀምረው ነበር። ይሁንና የቢሮክራሲው ችግር ፈተና ሆኖባቸዋል። ይሁን እንጂ ፈተናዎችን ተቋቁመው በሆቴል ዘርፉ ተጨማሪ ስራዎችን እንደሚያከናውኑ ተስፋ ሰንቀዋል።
ተስፋ መቁረጥ የማያውቁት ወይዘሮ መሰረት፤ ማንኛውንም ተግባር ለማከናወን በተለይ ደግሞ ሰርቶ ለማትረፍ የአላማ ጽናት ያስፈልጋል ይላሉ። ንግድ ከመጀመር በፊት አደርገዋለሁ ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል የሚል እምነት አላቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም ከተረጋገጠ እና ምቹ አሰራር ከተፈጠረ በርካታ ያልተነኩ የስራ መስኮች አሉ። በመሆኑም በተለይ ወጣቱ አዳዲስ የስራ መስኮችን ከፍቶ ለእራስም ለአገርም የሚጠቅም ስራ ስለማከናወን ማሰብ አለበት የሚለው ደግሞ ምክራቸው ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 18/2012
ጌትነት ተስፋማርያም