መስከረም 1 ቀን 2008 ዓም
አዲስ አመት መባቱ ነው።
አገር ምድሩ በአውደ አመቱ ድባብ ተውቧል። ክረምት አልፎ በጋ መግባቱ ነውና የጸደዩ አየር በተራው እፎይታን ያጎናጽፍ ይዟል። ለበአሉ ድምቀት በአገር ልብስ የተዋቡ ሰዎች የዕለቱን ምንነት በግልጽ ይመሰክራሉ። ከዋዜማው መዳረሻ አንስተው በገበያ ውሎ ሲመላለሱ የከረሙትም ከበግ ዶሮው ግዢ መለስ ብለው ለጓዳቸው የሚበጀውን ሊያሟሉ ተፍ ተፍ ማለት ጀምረዋል።
በአዲስ ልብስ የተዋቡ ሴት ህጻናት ከበሯቸውን እያደመቁ ‹‹አበባአየሽ ሆይ›› ሲሉ አርፍደዋል። አቻ ወንድሞቻቸውም በቀለም የተሽቆጠቆጠ የወረቀት ስዕል ይዘው ለወዳጅ ዘመዱ ሲያድሉና ሲመረቁ ውለዋል።
የአዲስ አመቷ ፀሀይ ለሁሉም ድምቀቷን መርጨት ቀጥላለች። በዚህ ቀን የአዲስ አመትን አዲስ ተስፋ የተቀበሉ በርካቶች ዕለቱን ከሌሎች ጋር ዋጅተው በደስታ ለማክበር በቡና ጠጡ ጥሪ እየተሰባሰቡ ነው።
በመልካም መንፈስ አመቱን ለመቀበል የሻቱ ጥቂቶች አይደሉም። በቅያሜ ተኮራርፈው የቆዩ ጠበኞች ችግራቸውን በሰላም ፈተው በአንድ እንደታደሙ ቀኑን ማጣጣም ጀምረዋል። አሁንም የአውደ ዓመቱ ድባብ ገና አልደበዘዘም። በየቤቱ ደስታና ሁካታው ጨዋታና ግብዣው ቀጥሏል።
ዕለቱን በሌላ መንደር
ልደታ ልዩ ስሙ አርባ ሶስት ቀበሌ እየተባለ በሚጠራው ስፍራ በርከት ያሉ ወጣቶች በሹክሹክታ እየመከሩ ነው። ወጣቶቹ አብዛኛውን ጊዜ አብረው የሚያሳልፉ አብሮ አደጎች ናቸው። ሰሞኑን በሰፈራቸው አካባቢ ሆነ በተባለው እውነት ላይ እየመከሩ የራሳቸውን ሀሳብ ይሰነዝራሉ።
አብዛኞቹ ቀኑን ምክንያት አድርገው ሲዝናኑ የቆዩ ናቸው። በገጽታቸው የሚነበበው የተለየ ስሜት በመጠጥ ሀይል ሞቅ እንዳለቸው ያመላክታል። ከነዚህ መሀል ጥቂቶቹ በንዴት እየተበሳጩ ውሳኔ ለማሳለፍ ይጣደፋሉ። እየተነሳ ያለውን ጉዳይ ‹‹ጉዳያችን›› ያሉት ይመስላል። በ‹‹ተደፈርን›› አይነት ወኔ እግራቸውን ከመሬቱ እያማቱ በእጃቸው የዛቻ ምልክት ያሳያሉ።
ወጣቶቹ ዛሬን በተለየ አገናኝቶ በሚያነጋግራቸው ጉዳይ ላይ እየተስማሙ መልሰው ይቃረናሉ። የሁሉም አስተያየት ለየቅል ሆኗል። መጨረሻ ማድረግ ባሰቡት ዕቅድ ላይ ግን ሀሳባቸውን በአንድ አዋቅረው ጨርሰዋል። ለውሳኔውም የጋራ አቋም ይዘው መንገዳቸውን ለይተዋል። በእጃቸው መኖር ስለሚገባው፣ መፈጸም ስለሚኖርባቸው ግዴታና የስራ ክፍፍል ሁሉ ተደላድለው ጨርሰዋል። አሁን ማድረግ የሚገባቸው ኦፕሬሽኑን ለመፈጸም ሰፈራቸውን ለቆ መሄድ ብቻ ነው።
ከአንድ ቀን በፊት
የአዲስ አመት ዋዜማ ነው። በዚህ ቀን አብዛኞቹ ለበአሉ ድምቀት በተለየ ሁኔታ ይዘጋጃሉ። በግና ዶሮ የሚገዙ፣ ሽንኩርት፣ ኮባና ኩበት ገበያ የሚመላለሱ፣ ለቤት ማስዋቢያ ያማራቸውን ለመግዛት የሚጠይቁ ሸማቾች መንገዱን አጨናንቅውታል። ምሽቱን በችቦ ማብራት ለማሳለፍ ያሰቡ ደግሞ የረጃጅም ጭራሮ እስሮችን በትከቸው ይዘው መንገዱን ያቋርጣሉ።
ከነዚህ ትዕይንቶች በአንዱም የሌሉበት ጥቂት ወጣቶች ደግሞ ቀስ በቀስ እየተጠራሩ በአንድ ስፍራ መሰባሰብ ጀምረዋል። ከወጣቶቹ ባሻገር በሌላ ስፍራ ያሉ ሌሎች ወጣቶችም በራሳቸው ምክክር ተጠምደዋል።
ሁሌም በፍቅር አሳልፈው ከማያውቁት የ40 ቀበሌ ወጣቶች ጋር በዕለቱ ያለመስማማታቸው ጉዳይ ሌላ ችግርን አስከትሏል። ከቡድናቸው መሀል አንደኛው መፈንከቱና ክፉኛ መጎዳቱ ህመሙን የጋራ እያደረገው ነው። ይህን ያወቁት የአንድ ሰፈር ወጣቶች ምሽቱን ወደ ጠበኞቻቸው መንደር ተጉዘው ባላንጣዎቻቸውን አሳር ለማብላት እያቀዱ ቆይተዋል።
የአዲስ አመት ዋዜማ ለአይን መያዝ ሲጀመር ተጠራርተው የተገናኙት ወጣቶች ወደ አርባ ቀበሌ ገስግሰው አደጋ ለመጣል ሞከሩ። በስፍራው ያገኙትንና ለመብራት የተዘጋጀውን ችቦ ሰባብረውም ያጋጠሟቸውን ሁሉ አውከው ከስፍራው አመለጡ።
አዲስ አመት ብቶ መስከረም አንድ ብሎ ሲጀምር መንደርተኛው ከአውደዓመቱ ቡና ጋር የትናንትናውን ምሽት ሲያወጋው አረፈደ። የወጣቶቹን ቡድን ለይቶ የመደባደብ ልማድን በስጋት እያነሳም በጉዳዩ ተመካከረበት።
የጠቡን መነሻ ‹‹እናውቃለን›› ያሉ አንዳንዶች ደግሞ ለወጣቶቹ ድብድብ ምክንያት ሆናለች የተባለችውን ወጣት እያነሱ ሲራገሙና ግምታቸውን ሲያሳልፉ ቆዩ። የሁለቱ መንደር ወጣቶች ቁርሾና አለመግባባት ሁሌም ‹‹ያስገርመናል›› ባዮችም የህጉን መላላትና የወጣቶቹን ተደጋጋሚ ድርጊት አውስተው፣ የሚወቀሰውን ሁሉ ወቀሱ።
ከነዚህ መሀል የሰፈሩን ጩሀትና ግርግር የለመዱ ጥቂቶች በሚባለው ሁሉ ግድ ሳይሰጣቸው የበአሉን ድባብ በሰላም ማጣጣም ይዘዋል። አልፎ አልፎ በነዚህ ወጣቶች መሀል የሚፈጠረውን ጠብና አለመግባባት የልምድ ያህል የተቀበሉት ሆኗልና የሌሎችን ስጋትና ፍራቻ ከምንም የቆጠሩ አይመስልም።
ተስፋዬ መኮንን አዲሱን ዓመት የተቀበለው በተለየ ተስፋና መልካም በሚባል ስሜት ነው። ለበአሉ ቤቱን አሟልቶ ልጆቹን ለማስደሰት ሲያስብበት ከርሟል። ከትዳር አጋሩ ጋር ያቆመው ጎጆ ለአውደ አመት ቢጎድልበት አይወድም። እንደ ሌሎች የአቅሙን ገዛዝቶ ከጎረቤቶቹ ጋር አዲስ አመትን በደስታ ተቀብሏል።
ተስፋዬ በአካባቢው ነዋሪዎች የሚከበር ጎልማሳ ነው። በብዙዎች ዘንድም የተጣላን በማስታረቅ ባህሪው ይታወቃል። እስከዛሬ በነበሩ አጋጣሚዎች ከጠብ መሀል ዘሎ እየገባ በርካቶችን ሲያገላግል ቆይቷል። ይህ ልማዱን በዙዎቹ ባይወዱለትም በእሱ ዘንድ ግን እንደ ግዴታው ተቀብሎታል። ሁሌም ቢሆን ሰዎች ሲደባደቡ አይቶ ማለፍ አይሆንለትም። ሲጨቃጨቁ ከተመለከተም ጉዳዩን ያለጠብ እንዲፈቱ ለማስማማት ይሞክራል። ከቻለ ደግሞ በእርቅ እንዲፈታ የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል።
የበአል ዋዜማ ምሽት በወጣቶቹ መሀል ጠቡ ሲፈጠር ተስፋዬ በስፍራው ነበር። የድብድቡን ሁኔታ አይተው ብዙዎች በሸሹ ጊዜም እሱ እንደለመደው ጉዳዩን በሰላም ለመፍታት ሲሞክር ታይቷል። ጠቡ ተጋግሎ ወደ ድብድብ ሲያመራም እጁን ዘርግቶ ወጣቶችን በልመና ሲማጸን ነበር።
የዋዜማው ምሽትና ግርግር አልፎ ሁሉም ከተበታተነ በኋላ ሁኔታውን ያዩ ብዘዎች ድርጊቱን እየኮነኑ ሊወቅሱት ሞክረዋል። የተስፋዬን በጠብ መሀል የመግባት ልምድን ያልወደዱለት አንዳንዶችም ‹‹ገላጋይ ይሞታል›› ይሉትን አባባል እየደጋገሙ አስፈራርተውታል። ከሁሉም ግን ከአርባ ቀበሌ የመጡ ተደባዳቢዎች ሁኔታ ለየት ይላል። ወጣቶቹ ሰፈር አቋርጠው የመጡ ባላንጣዎቻቸውን እንዳሰቡት ላለመመከታቸው ሰበብ ያደረጉት ግልግሉን ነበር። ለዚህም ጥርስ መንከሳቸው አልቀረም።
የአውደ አመቱ ከሰአት
በመንደራቸው ዕለቱን ሲመክሩ ያረፈዱት ወጣቶች የአካባቢያቸውን የትናንትና ጥቃት ፈጽሞ መርሳት አልሆነላቸውም። አውደአመቱን አሳልፈው በአርባ ቀበሌ ወጣቶች ላይ የሚሰነዝሩትን የበቀል ጥቃት እየነደፉ ዕቅዳቸውን መወጠን ይዘዋል። አብዛኞቹ ለበአሉ የቀማመሱት መጠጥ በሞቅታ እየነዳቸው ነው። የሚናገሩትን አያውቁም። ከነዚህ መሀል ጥቂት የማይባሉት ዛሬም ጠብ ተነስቶ የደንቡን ቢያደርጉ እንደሚወዱ በእርግጠኝነት ይናገራሉ።
ይህ እየሆነ ባለበት አጋጣሚ ከሰፈሩ ማዶ ከሚገኝ መኖሪያ ጥቂቶች ሰብሰብ ብለዋል። ዕለቱን በቴሌቪዢን የሚተላለፈውን የበአል ልዩ ዝግጅት በአትኩሮት እያዩ ይዝናናሉ። በዚህኛው ቤትም እንደወጉ የአውደዓመቱ ድባብ አልጠፋም። ማለዳውን ቄጤማ ተጉዝጉዞ ቡና ተፈልቷል። ዳቦ ተቆርሶና ጎረቤት ተጠርቶ ሲጨዋወት አርፍዷል።
አሁን እንግዶች ሁሉ ተሸኝተዋል። በቤቱ የቀሩት እኩያ የሚባሉ የመንደሩ ወጣቶች ናቸው። ከነዚህ መሀል አንዱ አዲሱ ይባላል። የቤቱ ባለቤት ልጅ ነው። አዲሱ የአርባ ቀበሌ ልጅ እንደመሆኑ በትናንትናው ምሽት ሁኔታ ሲያስብበት አርፍዷል። እሱም እንደሌሎች ባልንጀሮቹ የድብድቡ ቆይታ የበቃው አይመስልም።
በድንገት በሩ ተንኳኳ። ይህኔ ትኩረቱን በቴሌቪዢኑ ጨዋታ ላይ አድርጎ የቆየው አዲሱ መኮንን ፈጠን ብሎ ተነሳ። የበሩን እጀታ አዙሮ በሩን እንደከፈተም ደጅ ላይ ቆሞ ባገኘው ወጣት ፊት ላይ አፈጠጠ። ወጣቱ ከግንባሩ በሚወርደው ደም ተሸፍኖ በእልህ እየተንቀጠቀጠ ነው። አዲሱ ሁኔታውን እያስተዋለ የሆነውን ሁሉ ያስረዳው ዘንድ አፋጠጠው።
የመጣው ወጣት በሰፈሩ ችግር መኖሩን መናገር እንደጀመረ አዲሱ ጠቡ ከማን ጋር እንደሆነ ደጋግሞ ጠየቀው። ተጎጂው ደብዳቢዎቹ የሌላ ሰፈር ወጣቶች መሆናቸውንና እነሱም የአርባ ሶስት ቀበሌ ልጆች እንደሆኑ አረጋገጠለት።
አዲሱ ይህን በሰማ ጊዜ በንዴት ተንጨረጨረ። እንደ ትናንቱ ዛሬም ለጠብና ድብድብ መጋበዛቸው ከልብ አበሳጨው። ይህን እያሰበ አይኖቹን ከወዲያ ወዲህ አንከራተተ። ወዲያው ያሰበውን ፈልጎ በእጆቹ አስገባ። አንድ ትልቅ ገጀራ በጎኑ ሸጉጦ በሩን የኋሊት ሲደረግመው መልዕክት አድራሹ ተጎጂ የበር መቀርቀሪያ ይዞ ተከተለው።
ግጥሚያ
እነ አዲሱ በመጡበት ፍጥነት ተሯሩጠው የሰፈሩን መሀል ሲያጋምሱ የአርባሶስት ቀበሌ ልጆች ላይ ደረሱባቸው። አብዛኞቹ ጠርሙስና ድንጋይ ይዘዋል። አመጣጣቸው ስለትናንቱ የሰፈራቸው ጥቃት የመልስ ምት ለመስጠት ይመስላል። አዲሱ ገጀራውን እያወዛወዘ ከኋላቸው ሲከተል ሁኔታውን ያስተዋሉ ቡድነኞች ወደ ኋላ እያፈገፈጉ ወደመንደራቸው ገሰገሱ።
አዲሱን የተመለከቱ ሌሎች የሰፈሩ ልጆች እገዛ ለመስጠት የያዙትን ገጀራና ዱላ አጥብቀው የፊተኞቹን መከተል ያዙ። አዲሱ የባልንጀሮቹን መበራከት ሲመለከት ውስጡ በወኔ ተመላ። ቆሞ ብሎ ትዕዛዝ እየሰጠም እንዲከተሉት ምልክት አሳያቸው። ወጣቶቹ ትዕዛዙን ተከትለው በሆታ ወደፊት ገሰገሱ። ወደ ጠበኞቻቸው ክልል ሲደርሱም ያገኙትን ሁሉ እየጨረገዱ ሁከቱን አባባሱ። በመንገድ የቆሙ እናቶችንና ወጣት ሴቶችን እየደበደቡ፣ በርና መስኮቶችን በገጀራ እየሰነጠቁ ሌሎች የሚሰበሩና የሚቀጠቀጡ ንብረቶችን ፍለጋ ባዘኑ።
የሁለቱ ጎራዎች ድብድብ አይሎ ሰፈሩ በታላቅ ጩሀት ሲደባለቅ በርካቶች ይደበቁበት ጥግ አጥተው በሽብር ታወኩ። የአርባ ሶስት ቀበሌ ነዋሪዎች በአዲሱ አመት መግበያ የመጀመሪያው ዕለት የመጣባቸውን ክፉ አጋጣሚ መቋቋም አልቻሉም። ከሌላ ሰፈር በመጡ ወጣቶች እየተሳደዱ ጥቃትን መቀበል ከአቅማቸው በላይ ሆነ።
በእንዲህ አይነቱ ክፉ ቀን ለሰፈሩ ቀድሞ የሚደርሰው ተስፋዬ እየሆነ ያለውን ጉዳይ እንደዋዛ ሊያልፍ አልተቻለውም። የሚወረወረውን ድንጋይ እያነሳ ከአካባቢው ለማራቅ ሲሞክር ቆየ። ጠቡ ጥቂት ጋብ ሲል ደግሞ እንደትናንቱ ምሽት እጆቹን ዘርግቶ የሰፈሩን ልጆች መማመጸን ጀመረ። ማንም ትልቅ ሰው መሆኑን አይቶ ድብድቡን ለመተው የፈቀደ አልነበረም።
ጠቡ በቀላል አልበረደም። ተስፋዬም አምባጓሮውን ሸሽቶ ወደቤቱ አልገባም። ከሚወረወረው ድንጋይ፣ ከሚወነጨፈው ዱላ መሀል ገብቶ ፊት ለፊት ተማገደ። ይህን ያዩ ተፋላሚዎች የተስፋዬን ድንጋይ ማንሳት ሲያውቁ ጥርጣሬ ገባቸው። ወዲያውም በአይኖቻቸው ተናበው እጃቸውን አነሱበት። በያዙት ዱላና ድንጋይ አፈራርቀውም በእርግጫና ጡጫ ቀጠቀጡት። አዲሱ ተስፋዬን ሲመለከት ገጀራውን አንስቶ አንገቱ ላይ አሳረፈ። ተስፋዬ ከዚህ በኋላ ዳግም ማንሰራራት አልቻለም። በደም ተለውሶ በቁሙ ከመሬት ተዘረረ።
ቡድነኞቹ ያሰቡትን ፈጽመው ስፍራውን ለቀው ሲሄዱ የተስፋዬን ጉዳት ያስተዋሉ ሰፈርተኞች ተሯሩጠው ደረሱ። ጎልማሳው ገላጋይ በትንሹም ቢሆን ይተነፍሳል። ተረዳድተው ከሆስፒታል አደረሱት። ተስፋዬ በዕለቱ እርዳታ አግኝቶ አልጋ እንዲይዝ ተደረገ። ሶስት ቀናትን በከባድ ጉዳት ውስጥ ሆኖም በበዛ ስቃይ አሳለፈ። አራተኛው ቀን መሻገር አልቻለም። የህይወት ፍጻሜው ሆኖ የሞት መርዶው ተሰማ።
የፖሊስ ምርመራ
በደረሰው ጥቆማ መሰረት ፖሊስ በሰፈሩ ደርሶ መረጃዎችን ማሰባሰብ ጀምሯል። የጠቡን መነሻ መርምሮ የጉዳቱን ስፋት ሲያጣራም በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች መደብደባቸውን አረጋገጠ። በመርማሪ ፖሊስ ዋና ሳጂን መንግስቱ ታደሰ የሚመራው ቡድን በተለይ ለተስፋዬ ህይወት መጥፋት ተጠያቂ ይሆናሉ የተባሉ ተጠርጣሪዎችን ለይቶ በመዝገቡ አሰፈረ።
አዲሱን ጨምሮ ቀንደኞቹ አምባጓሮ ፈጣሪዎች ሰድስት መሆናቸው እንደታወቀ ፖሊስ የፍርድ ቤት ማዘዣ አውጥቶ አሰሳውን ቀጠለ። በፖሊስ መዝገብ ቁጥር 301/05 የተከፈተው ዶሴም የየዕለቱ መረጃዎቸ በጥንቃቄ ሲመዘገቡበት ቆየ።
ከቀናት በኋላ ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ በሱዳን በኩል ከሀገር ለመውጣት መንቀሳቀሳቸው መረጃ ደረሰው። መረጃውን ይዞም ከጎንደር ከተማ ጀምሮ ፍለጋውን ቀጠለ። ይህ በሆነበት አጋጣሚ ከተፈላጊዎቹ መሀል አንደኛው በከተማዋ ሲዘዋወር ታይቶ በፖሊሶች ጥርጣሬ ተያዘ። ቃሉን እንዲሰጥ ሲጠየቅም ተፈላጊዎቹ ድንበር ለማቋረጥ መዘጋጀታቸውን ጠቆመ።
ፖሊስ ወደ መተማ ገሰገሰ። በስፍራው ያገኘውን ሌላ ተጠርጣሪን ይዞም ፍለጋውን ቀጠለ። ሌሎቹ ግን ቡድኑ ከመድረሱ ጥቂት ቀናት አስቀድሞ ድንበር በማቋረጣቸው ርቀው ነበር። በሌላ ክስ ማረሚያ ቤት ያለውን አንድ ተከሳሽ ጨምሮ ሁለቱን ወጣቶች በመያዝም ክሱን አደራጅቶ ለዓቃቤ ህግ አስተላለፈ።
ውሳኔ
በፖሊስ ምርመራው ተጣርቶ በዓቃቤ ህግ ከሳሽነነት መዝገቡ የደረሰው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሶስት ተከሳሾች ላይ የመጨረሻውን የፍርድ ውሳኔ ለመስጠት በችሎቱ ተሰይሟል። ዳኛው የክስ መዝገቡን አንብበው እንደጨረሱ በቁጥጥር ስር የዋሉት ሶስቱ ተከሳሾች ጥፋተኛ ስለመሆናቸው ጠቅሰው ‹‹ይገባቸዋል›› ያሉትን ውሳኔ አነበቡ።
በዚህም መሰረት አንደኛ ተከሳሽ አዲሱ መኮንን በአስራ ሁለት አመት ጽኑ አስራት፣ ሁለተኛው ተከሳሽ ደምሰው ወርዶፋ በዘጠኝ አመት ጽኑ አስራት፣ እንዲሁም ሶስተኛው ተከሻሽ ይታየው አበበ በሰባት አመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ የተወሰነባቸው መሆኑ ታውቆ መዝገቡ ተዘጋ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 18/2012
መልካምስራ አፈወርቅ